የግብፅ ተቋማትና የሀገራችን አሸባሪዎች ትስስር

 

“የኦነግና የግንቦት ሰባት አመራሮች ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጋር በመሆን የሀገራችንን ልማት ለማደናቀፍ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ”

                                      -የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ

ይህ የፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ንግግር ትናንት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት ከተናገሩት ቀንጭቤ የወሰድኩት ነው። እርግጥ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ሀገራችን ታላቁን የህዳሴ ግድብ በራሷ አቅም መገንባት መጀመሯን ያልስደሰታቸው አንዳንድ ሀገራት የሀገራችንን አሸባሪዎችንና ፅንፈኛ ዲያስፖራዎችን በማሰማራት  ዕድገታችንን ለማስተጓጎል ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

አዎ! ግብፆች በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን “እናንተ ሁሌም እንደተራባችሁ ኑሩ፣ እኛ ግን እንብላ” የሚል የቅኝ ግዛት ዘመን ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብን ዛሬም አልተውም። ከዘመነ ኦሪት እስከ ዘመነ ዘፀዓት፣ ከዘመነ ጋማል አብዱልናስር እስከ ሆስኒ ሙባረክ ብሎም እስከ ዘመነ መሐመድ ሙርሲ አገዛዞች ድረስ የነበሩት የግብፅ ገዥ መደቦች በዓባይ ወንዝ ላይ ያራመዷቸው የነበሩት አቋሞች ተመሳሳይ ናቸው። ሁሉም ዓላማቸው የስራ ባህል የሌላት፣ በድህነት የማቀቀች፣ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትዳክር ኢትዮጵያን ማየት ነበር። የራዕያቸው ማጠንጠኛ ነጥብም ሀገሪቱ ሁሌም ተመፅዋች ሆና በድህነት አዙሪት ቀለበት ውስጥ እንድትሽከረከር ማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በጦርነት ከማስፈራራት እንዲሁም በኤርትራ መንግስት ሳንባ የሚተነፍሱ የሀገራችንን ተቃዋሚዎች ከመርዳት ጀምሮ ብድርና እርዳታ እስከ ማስከልከል ድረስ በሀገራችን ላይ ደባ ሲፈፅሙ ነበር። ለዚህም ባለፉት ጊዜያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት የነበራችውን እንደ ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ ዓይነት ዜጎቻቸውን በማሰማራት ሀገራችን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ምንም ዓይነት ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ የማድረግ ሴራን ከውነዋል። ሌላ…ሌላም ሴራ ላለመጎንጎናቸው ማንም እርግጠኛ መሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያ ሁሉ ሴራና ደባ አለፈና የኢፌዴሪ መንግስት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከህዝቡ ጋር በመሆን ድህነት ድል ለመንሳት ዘመቻ አወጀ። ዘመቻውም ውጤታማ ሆኖ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፈጣን ዕድገት ውስጥ እንዲገባ አደረገው። የውስጥ አቅማችንንም ማጎልበት ቻለ። ያኔም ‘የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በተፈጥሮ ሃብታችን በመጠቀም ድህነትን እንቀርፋለን’ የሚል አቋም በመያዝ የታላቁን ህዳሴ ግድብን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተጣለ። ግንባታውም ተጀመረ። ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው መረባረብ ጀመሩ።…

በወቅቱ ግብፅ ውስጥም ፓርላማውን ሰብስቦ የህዳሴውን ግድብ ለማፍረስ የኢትዮጵያን ፀረ-ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን ከመጠቀም እስከ ‘ቀጥተኛ ጦርነት እናደርጋለን’ የሚል የማስፈራሪያ ዲስኩር ሲያሰማ የነበረው የመሐመድ ሙርሲ መንግስት፤ በፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ በሚመራው የሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ-መንግስት ተደረገበት። እናም የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ስልጣን ላይ ወጡ።

እርግጥ የፕሬዚዳንት አል-ሲሲ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ፤ የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት ‘የተሻለ የመተማመን መንፈስን የሚያጎለብትና በዓባይ ጉዳይም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመረኮዘ ይሆናል’ የሚል ተስፋን የሰነቁ ወገኖች በርካታ ናቸው። በፕሬዚዳንት አል-ሲሲ የሚመራው መንግስት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን ሰጥቶ መቀበልና የጋራ ተጠቃሚነት መገለጫው በሆነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚመራ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ሆነ። ምንም እንኳን የግብፅ መንግስት ተቋማት ከሀገራችን አሸባሪዎችና ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በማድረግ ላይ ያሉት የጥፋት ጋብቻ ምክንያት ይህ የአል-ሲሲ መንግስት አቋም ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም፤ እነዚህ ወገኖች ይህን እምነት የሰነቁት ግን ያለ ምክንያት አልነበረም—አዲሱ የካይሮ መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ከሀገራችን ጋር ለመተባበርና የልማቷም ደጋፊ እንደሚሆን በመግለፁ እንጂ።

ዳሩ ግን በግብፅ መንግስት ውስጥ የሚገኙትና ፕሬዚዳንት ሙላቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ በስም ያልጠቀሷቸው ተቋማት ዛሬም ራሳቸውን “ኦነግ” እና “ግንቦት ሰባት” እያሉ ከሚጠሩ እንዲሁም ከአንዳንድ ፅንፈኛ የዲያስፖራዎች ጋር የጥፋት ቁርኝት መፈፀማቸው ግብፆች ዛሬም በሚንገታገተው አሮጌ አስተሳሰብ እየተመሩ መሆናቸውን አመላካች ሆኗል። እናም ዛሬም “ታሪካዊ የውሃ ድርሻችንን እንዳናጣ” የሚል የላሸቀና ኋላ ቀር አስተሳሰብ እንደ “ኦነግ” እና “ግንቦት ሰባት” እንዲሁም እንደ ጃዋር መሐመድ ዓይነት ፅንፈኛ ዲያስፖራዎችን በሀገራችን ላይ በማሰማራት የህዝብ እልቂት እንዲፈጠርና ብጥብጥ እንዲነግስ እንዲሁም የተጀመረው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገታችን እንዲቀጭጭና ወደ ነበርንበት የድህነት ታሪክ እንድንመለስ የልማት አውታሮችን የማቃጠልና የማውደም ተግባር እንዲካሄድ አድርገዋል። 

እርግጥ የግብፅ መንግስት ተቋማት ፍላጎት በትርምስ ውስጥ ሆነን የጀመርነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንዳንገነባ ማድረግ ቢሆንም፤ የሀገራችን ተቃዋሚ ነን የሚሉ አሸባሪዎች ከካይሮ ተቋማት መመሪያ በመቀበል የፈፀሙትና በመፈፀም ላይ ያሉት ተግባር ግን ሀገርን የመሸጥ አሳፋሪ ባንዳዊ ተግባር መሆኑ ከማንኛውም የሀገራችን ህዝብ የሚሰወር አይመስለኝም።

አዎ! አስመራ ውስጥ አቶ ኢሳያስ ሲያስነጥሳቸው መሃረብ ይዞ በቅረብ የሚሯሯጠውና በዳውድ ኢብሳ የሚመራው “ኦነግ” እያለ ራሱን የሚጠራው የሽብር ቡድ፤ን እጅግ አስነዋሪና አሳፋሪ ሀገርን የመሸጥ ባንዳዊ ተግባሩን የጀመረው ዛሬ አይደለም። ከተፈጠረ ከ40 ዓመት በላይ እንደሆነ የሚነገርለት ኦነግ ከግብፅ ጋር “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ” የሆነው ዛሬ አይደለም። በዘመነ-ሙባረክ የስልጣን አገዛዝ ወቅት የተለያዩ የሁከት ተልዕኮዎችን ተቀብሎ በንፁሃን ላይ ግድያ የፈፀመ፣ ትምህርት ቤቶችን ያቃጠለና ዘር በመለየት ጭፍጨፋ ሲያካሂድ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ በሀገራችን ላይ በሶማሊያው “እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” አማካኝነት ተደቅኖ የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ወደዚያች ሀገር ሲያመራ፣ ፅንፈኛውን ቡድን በመደገፍ በባዕድ ሀገር ውስጥ ተሰልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህም የባንዳዊ ተግባሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በመሐመድ ሙርሲ የስልጣን ዘመነም ይኸው ባንዳ ቡድን ተከፍሎት ካይሮ ጎዳናዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ መላው የሀገራችን ህዝብ ቁጭት የሆነውንና ከድህነት ለመውጣት ለሚያደርገው ትግል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ተቃውሟል። አሁን ደግሞ “ለስልጣን አብቁን እንጂ ኢትዮጵያ የምትገነባውን ግድብ ግብፅ በምትፈልገው መንገድ እናደርጋለን” በማለት ለካይሮ መንግስት ተቋማት ቃል በመግባት እየወሸከተ ነው—ሃሳቡ “ላም አለኝ በሰማይ…” ዓይነት የቀን ቅዠት ቢሆንም።

ለግብፅ መንግስት ተቋማት በመላላክ የሚሰራውና ፕሬዚዳንት ሙላቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የጠቀሱት ሌላኛው ባንዳ፤ በአሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው “ግንቦት ሰባት” እያለ ራሱን የሚጠራው የካይሮ ጀሌ ነው። ይህ “ለከፈለኝ ሁሉ እሰራለሁ” በሚል ዘይቤ የተሰባሰበው የግብረ-ሽበራ ቡድን በኤርትራ መንግስት አማካኝነት ተቋቁሞ ሀገሩን ለመሸጥ የተሰለፈ ሃይል ነው። እንደ “ኦነግ” ሁሉ ይህ የሽብር ቡድንም የራሱ ባንዳዊ መገለጫዎች አሉት። አንደኛው በመሐመድ ሙርሲ የስልጣን ዘመን ወቅት አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለመዶለት ከአሜሪካ ወደ ካይሮ እንደ ውሃ ቀጂ መመላለሱ ነው። በዚህም ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ሀገሩን ለመሸጥ የተዘጋጀ መሆኑን በይፋ ሲለፍፍ ነበር—‘በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል ከማንኛውም ኃይል ጋር እሰራለሁ’ የሚል የሞኝ ፈሊጥን አንግቦ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመቃወም።

ይህን ባንዳዊ ቃሉን ዕውን ለማድረግም በኤርትራ መንግስት አማካኝነት ኢሳትን ከፍቶ የግብፆችን የማተራመስ አጀንዳ እያራመደ ይገኛል። ከመሰንበቻውም የሽብር ቡድኑ መሪ የሆነው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ‘…በሀገር ቤት ውስጥ የሚካሄዱትን ማንኛውንም ተቋማት በማውደም በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እናሳድራለን።…’ በማለት ሲናገር አድምጠነዋል። ይህም ሰውዬው ከጥንስሱ ጀምሮ ለግብፅ መንግስታዊ ተቋማት እየሰሩ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል—አካሄዱ የተቀዳው ከካይሮዎቹ ፍላጎት ነውና። እርግጥ በአጭሩ አሸባሪው ቡድንና መሪው ጫንቃቸውን ለካይሮ ተቋማት በማከራየት ንፁሃንን እያስፈጁና ሀገሪቱ ያፈራቻቸውን ከድህነት መውጫ ንብረቶች እያስወደሙ የሚኖሩ ባንዳዎች ናቸው ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን የግብፅ መንግስት ተቋማት፤ መንግስታቸው በአንድ በኩል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከሀገራችንና ከሱዳን ጋር እየተደራደረ መሆኑን እያወቁ፣ በሌላ በኩል እነርሱ የሀገራችንን አሸባሪዎች በመደገፍ ሰለማችንን ለማወክ መጣራቸው በፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። እርግጥም የካይሮ መንግስት ተቋማት የሚያከናውኑትን ይህን በሌላው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አካሄድ ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ በመሆኑ በቸልታ ሊታይ የሚገባ አይመስለኝም። በመሆኑም የሀገራችን መንግስት ከግብፅ አቻው ጋር በሰለጠነ መንገድ በግልፅ ቋንቋ መነጋገር ያለበት ይመስለኛል—የኢትዮጵያ መንግስት ተገቋማት በግብፅ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡት ሁሉ፤ የግብፅ መንግስት ተቋማትም በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብተው የመፈትፈት ምንም ዓይነት መብት የላቸውምና። ህዝቡም የሽብር ቡድኖቹ ዓላማ ተላላኪ ሆኖ ገንዘብ መሰብሰብ እንጂ የህዝቡን ተጠቃሚነት በማገናዘብ አለመሆኑን ተረድቶ የእነዚህን ባንዳዎች እኩይ ሴራ ለማጨናገፍ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን የማይተካ ድጋፍ ማድረግ ያለበት ይመስለኛል።