የአዲስ አበባና የዙርያው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን መነሻ አድርጎ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ምላሽ ቢሰጠውም መልኩን ወደሁከት ቀይሮ እና በውጭ ተላላኪ ሃይሎች ተጠልፎ በተለይ እስከመስከረም ወር 2009 መጨረሻ ለብዙ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ስፍር ቁጥር ለሌለው ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ የሚታወቅና ብዙዎችን አሳዝኖ ያለፈ ክስተት ነው፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በወልቃይት የማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞም ከ2008 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በተመሳሳይ የተጠለፈና የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ መልኩን ቀይሮ፣ የተለያዩ የአማራ ከተሞችና አካባቢዎች በመዝለቅም ለተመሳሳይ ጥፋት ያበቃ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተለይ ባለፈው እሑድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት የኢሬቻ በዓል ላይ የተገኙ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የታደሙ ነዋሪዎች የተገኙበትን ሃይማኖታዊ መድረክ ለመጥለፍ የሞከሩ ሃይሎች ባስነሱት ግርግር የደረሰው አሳዛኝ የወጣቶች ሕይወት ሕልፈት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የንብረት ውድመትን ማድረሱና መዛመቱም ሃገሪቱን ከብሄራዊ የሃዘን ቀን እስከ ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አብቅቷታል፡፡
እነዚህ ጥፋቶች በህዝባዊ ተቃውሞ ሽፋን ከተቀሰቀሱ ከዓመት በላይ ያስቆጠሩ ከመሆኑ ባሻገርም ስፋታቸው በመግዘፉ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በነሐሴ ወር ላይ ተሰብስቦ የችግሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን መለየቱም ይታወሳል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ባወጣው መግለጫም፣ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥትን ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጐ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅምን ማስቀደም ይታያል፤›› የሚለው ዋነኛ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ፍላጎትና የሥራ አጥነት ችግርን በፍጥነት አለመፍታት፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለተንሰራፋው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያቶች መሆናቸውን የገመገመ ስለመሆኑና፤ ከሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ የትምክህተኝነትና የጠባብነት አስተሳሰብና ጥገኝነት መኖራቸውን፣ እነዚህንም በጥብቅ በመታገል እንዲተጉ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችን ማዘጋጀቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ ታዲያ ትናንት አመታዊ ስራውን የጀመረው ፓርላማ ዋና ስራ በመንግሥት መዋቅር አስፈጻሚዎች ላይ ሹም ሽርና የሽግሽግ ለውጥ ማድረግ እንደሆነ የሚያስቡ በርካታ ድምጾችና ጉምጉምታዎች እየተሰሙ ነውና ይህን የተመለከተው ጉዳይ የጥልቅ ተሃድሶው ዋና አካል እንዳልሆነ እና የማይሆንበትን ምክንያት ጨምሮ የፓርላማው ልዩ ትኩረትና አሳሳቢው ጉዳይ የቱ እንደሆነ ግምገማውን እና የፕሬዘዳንቱን የመክፈቻ ንግግር መነሻ በማድረግ ይህ ጽሁፍ ለማሄስ ይሞክራል፡፡ በእርግጥ ሂሳችን ጉዳዩ መሰረታዊ አለመሆኑን ያጠይቃል እንጂ አጠቃላይ ለውጡና የተሃድሶው ውጤት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብቃት ላይ መሠረት ያደረገ ምደባ ማድረግን፣ ለዚህም የፓርቲ አባልነት ቦታ እንደማይኖረው ማረጋገጡን የዘነጋ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ደካማ የሕዝብ አገልግሎት፣ መልስ የማይሰጥ የተኛ ቢሮክራሲ፣ በአግባቡ የማይሠሩ ፍርድ ቤቶች፣ የባለሥልጣናት ሙሰኛ መሆን፣ ያልተመጣጠነ የካሳ ክፍያና በመናር ላይ የሚገኝ የኑሮ ዋጋ (ግሽበት) ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ያማረሩት ከመሆኑ እውነታ ስንነሳ እንኳ ሹም ሽረት ቁልፍ ጉዳይ እንደማይሆን ለመገመት አይከብድም፡፡
ባለሥልጣናትን ማንሳት የአገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ላይ ያሉትን ችግሮች ለማሻሻል ምክንያት ቢሆንም ህዝቡ ያማረረባቸውን ጉዳዮች ከመመለስ አንጻር መንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሙስናን መታገልና በነዚህም ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጥልቀት ያለው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ቁልፉ ጉዳይ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ከተነሺው እና ከተሿሚው ይልቅ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ጤነኛ ፓርላማ፣ በቅጡ የሚሠሩ ኮሚሽኖች ተፈጥረው ሥራ አስፈጻሚውን ሥርዓት ማስያዝ የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋትና የመንግስትን እና የፓርቲን ሚና ለይቶ መንቀሳቀስ ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን የሚገባ መሆኑ ላይ ስለሃገሪቱ መጻኢ እድል ከሚብሰለሰሉ ሁሉ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።
ይህ የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት ገዥው ፓርቲና መንግሥት ቃል ከገቡት መሠረታዊ ከሚባሉት መፍትሔዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ሹም ሽርና ሽግሽግ፣ እንዲሁም በብቃት ላይ የተመሠረተ እንጂ የኢሕአዴግ አባልነት ላይ ያላተኮረ የካቢኔ ምሥረታ ፋይዳው በራሱ በኢህአዴግ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
የህግና የፖለቲካ ጠበብቶች መሠረታዊ የፖለቲካና የሕግ ማሻሻያዎች አብረው ካልተደረጉ፣ ‹‹የዓለም ምርጥ ብሩህ አዕምሮዎች ካቢኔውን ቢሞሉትም ለውጥ አይመጣም፡፡ አስቀድሞ ለቴክኖክራቶች አስቻይ ሁኔታዎች ሊዘጋጁ ይገባል፤›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸውም ከሹም ሽረት በላይ የህግና የአሰራር ስርአት ማሻሻያዎች የላቀ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ስላረጋገጡ ነው፡፡ በፓርላማው የመክፈቻ ስነስርአት ላይ ንግግራቸውን ያደረጉት የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር ትኩረትም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ መፍጠርን የተመለከተ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚረጋገጥበትን እና ከወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና ስነምግባር ግንባታ ጋር መያያዙ፣ ሕግና አቅምም ከፓርቲ አሠራር በላይ የሚሆንበትን አሰራር የተመለከተ መሆኑ፣ በጥቅሉ ከፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን የተመለከቱ መሆኑ ከሹም ሽረት በላይ የችግሩ መፍትሄ የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት የአሰራር ስርአት መዘርጋት ላይ ማነጣጠር ግድ የሚል እወነታ ስላለ ነው።
ዋናው ጉዳይና የችግሩ ምንጭ ህገ መንግሥቱን የሚመስል ፖለቲካዊ ሥርዓት ካለመፍጠር ጋር የተያያዘ እስከሆነ ድረስ የሚያስፈልገን የታይታ እና ዘላቂ የማይሆን ሹም ሽረት ሳይሆን ህገ መንግስቱን የሚመስል ፖለቲካዊ ስርአት መፍጠርና መገንባት ነው። ሹም ሽርና ሽግሽግ እንዲሁም ብቃት ላይ የተመሠረተ የካቢኔ አወቃቀር መፍጠር መፍትሄ ቢሆንም የሚሆነው ግን ቁንፅል መፍትሔ ነው፡፡
ዋነኛው መፍትሄና ተሳትፎው የማያጠያይቀ የሚሆነው ህዝብ ከላይ ከተመለከቱት እና ለንብረትና የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ከነበሩት ችግሮች አኳያ ከመንግስት መጠበቅ የሚገባው ሹም ሽረትን ሳይሆን የዜጐችን ተቋማዊ አቅም መገንባትን፣ የፖለቲካ መብታቸውን ያለ ገደብ እንዲተገብሩ ማድረግን፣ እንዲሁም የተጠያቂነት አሰራርን እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን የተመለከቱ ማሻሻያ እና አሰራሮችን ነው።
እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በፍጥነት እየተመለሱ መሄድ የሚችሉት ደግሞ በሹም ሽረት ሳይሆን በዋናነት በህግ ማሻሻያ እና በዳበረ የአሰራር ስርአት ሲሆን ሹም ሽረት ቀጥሎ የሚመጣ እና የአሰራር ስርአቱን እና ማሻሻያዎቹን ታሳቢ አድርጎ ነው።
ስለ ሚኒስትሮች ሹመት፣ ህገ መንግሥቱ የሚለውን ስናይ ሁለት መሥፈርቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው፣ አንቀጽ 74(2) ላይ የተቀመጠው ‹‹ብቃት›› ነው፡፡ ሁለተኛው በቀጥታ ሚኒስትርነትን የሚመለከት ባይሆንም እንኳን፣ አንቀጽ 39(3) የተገለጸው የብሔሮች በፌዴራል ተቋማት ‹‹በሚዛናዊነት የመወከል መብት›› የሚለው ነው፡፡ የሴቶች ፖለቲካዊ ውክልናም ሳይዘነጋ ፡፡
ሚኒስትሮች በተናጠልም ይሁን በጋራ በርካታ ኃላፊነትና ግዴታዎች ያሉባቸው ሲሆን በዋናነት ሕግ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ፣ ፓርላማው የሚያወጣቸውን ህጎች ሥራ ላይ ማዋል፣ ረቂቅ ህጎች ማዘጋጀት፣ ፖሊሲዎች መንደፍ፣ ደንብና መመሪያ ማውጣት፣ የእያንዳንዱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መምራትና በዚያ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማማከርና ሌሎች በርካታ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ሁሉ የሚኒስትሮች ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመወጣት አቅምና ብቃት ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ወይንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሆኑ፣ ወይንም ደግሞ ሌላ ማንኛውም ሰው ሚኒስትር ሊሆን የሚችልበት እድል መኖሩንም መዘንጋት አይጋም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም የምልመላ መሥፈርት በዋናነት ይሄው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ጥበቃችን ደግሞ ከአሰራር ስርአቱ ማሻሻያ በኋላ ነው፡፡
ህገ መንግሥቱ ላይ ቢቀመጥም ባይቀመጥም ከላይ የተገለጹትን ኃላፊነቶች ለመወጣት በትምህርትና በልምድ የታገዘ አቅምና ብቃት መታየቱና እንደዋንኛ መስፈርት መወሰዱ ግን የሹም ሽሩ ጊዜ መቸም ይሁን መች ግድ ነው፡፡