የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም በመላው አገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ካደረገ በኋላ አዋጁን ለማስፈፀም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ የኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል።
የኮማንድ ፖስቱ ተደራጅቶ የአገሪቷ የፀጥታ ሃይሎች በአንድ ኮማንድ ስር እንዲሆኑ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፈፃሚ አካላት ዘንድ በየደረጃው ተገቢውን ግንዛቤ እንዲፈጠር ከተደረገ በኋላ የአፈፃፀም መመሪያ በማፅደቅና ዕቅድ በማዘጋጀት በፍጥነት ወደ ስራ ገብቷል።
በዚሁ መሰረት ከማዕከል ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የተቋቋሙት የኮማንድ ፖስቶች በሰላም ወዳዱ ህዝባችን የላቀ ድጋፍና ትብብር እየታገዙ እስካሁን ድረስ ባካሄዱት እንቅስቃሴ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፤-
በአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 31 መሰረት
o በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ከጎንደር ከተማና አካባቢው ሸፍተው ጫካ የገቡና ከአሸባሪ ሃይሎችና ታጣቂዎች ጋር ሲገናኙ ከነበሩት ውስጥ በአካባቢው ህዝብ ድጋፍና ትብብር 93 ሰዎች በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ሃይል እጃቸውን ሰጥተው የገቡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 45 ከነሙሉ ትጥቃቸው 48 ደግሞ ያለ ትጥቅ የገቡ ናቸው።
o በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን በደምቢ ዶሎ ከተማና ሶዶ ወረዳ ዙሪያ ከተለያዩ ቦታዎች ተዘርፈው የተወሰዱ በቁጥር 70 የሚደርስ የጦር መሳሪያ በራሳቸው በዘራፊዎቹና በህብረተሰቡ ጥቆማ ለፀጥታ ሃይሎች አስረክበዋል።
o በዚሁ በቄለም ወለጋ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል በአካባቢው ህዝብ የማያቋርጥ የማጋለጥና የጥቆማ ስራ እስካሁን 110 ሁከተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ለጊዜው ተደብቀው የቀሩትን ሁከተኞች ለመያዝ የክትትል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
o በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን በተፈጠረው ሁከትና በህዝብ ንብረትና የልማት ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በሕዝቡ ትብብርና ጥቆማ በሻሸመኔ ከተማ 450 እና በምእራብ አርሲ የተለያዩ ወረዳዎች 670 በድምሩ 1120 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ይገኛል
o በዚሁ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሻመኔ ከተማን ጨምሮ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በሁከተኞች ከተዘረፈው 162 የጦር መሳሪያ ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች ጥረትና በራሳቸው በሁከተኞቹ በጎ ፈቃድ ከተዘረፈው የጦር መሳሪያ ውስጥ እስከአሁን ድረስ 88 ያሕሉ የተመለሰ ሲሆን የቀረውን ለማስመለስ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለጊዜው መጠኑና አይነቱ ያልታወቀ ከተለያየ የመንግስት፣ የግልና የልማት ተቋማት የተዘረፈ ብዛት ያለው ንብረትም የማስመለስ ስራ አየተሰራ ይገኛል።
o በምእራብ ጉጂ ዞን ከተዘረፉት የጦር መሳሪያዎች መካከል በሕዝብ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ 32 ክላሽ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ከተለያዩ የሕዝብ ተቋማት በሁከተኞች ተዘርፈው የነበሩት ኮምፒተሮች፣ የሞተር ሳይክሎች፣ የብሮ ቁሳቁሶች ወዘተ የማስመለስ ስራ የተካሄደ ሲሆን፤ የሁከቱ አስተባባሪና ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በአካባቢው ሕዝብ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ እስከ አሁን 302 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ፤ ሌሎች 20 የሚሆኑ የሁከቱ አስተባባሪዎች ደግሞ በአዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ የጊዜ ገደብ መሰረት በፈቃዳቸው እጃቸውን ለመስጠት ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ።
o በምዕራብ ሸዋ ዞን በአዳማ፣ ቦራ፣ ሎሜ ሊበን ጭቋላ፣ አደአ፣ ቦስትና አዳሚ ቱሉ በተባሉ ሰባት ወረዳዎች በተፈጠረው ሁከት ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ግለሰቦችና ተቋማት የተዘረፉ የጦር መሳሪያዎች ውሰጥ በሕዝቡ ጥቆማና ፍተሻ እስከ አሁን 92 ዘመናዊና ኋላቀር የጦር መሳሪያዎችና ስምንት ሽጉጦች የተሰበሰበ ሲሆን፤ የሁከቱ ቀንደኛ መሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
o በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት ከተዘረፈው በድምሩ 513 የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በተደረገው እንቅስቃሴ 384 ያህሉ ተመልሷል፡፡
- በአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ አንቀጽ 4 ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍ
o በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 13 የሚሆኑ ጥቂት ነጋዴዎች የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ውስጥ ውስጡን ሲቀሰቅሱ የነበሩ ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከትምህርት ገበታ ሆን ብለው በመቅረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሞከሩ ሦስት አስተማሪዎች ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል፡፡
o በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱና ህዝቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 35 ነጋዴዎች መካከል ስደስቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ ሲለቀቁ፤ የቀሩት 29 የንግድ ተቋማቱ ባለቤቶች ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ወራት ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የህዝብን ሰላም በማወክና የግልና የህዝብ የልማት ድርጅቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ የተሳተፉ ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በአዋጁ አፈፃፀም መመሪያ መሰረት በራሳቸው ፈቃድና በህብረተሰቡ ጥቆማና የማጋለጥ ሥራ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ጉዳያቸው እየተጣራ ሲሆን፤ በየደረጃው በተቋቋሙት የኮማንድ ፓስቶች ከህዝቡ በሚያገኙት ጥቆማና ድጋፍ የጦር መሳሪያን ጨምሮ የተዘረፉ በርካታ የግልና የህዝብ ንብረቶች የማስመለሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የሰላሙና የልማቱ ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነው ህዝባችን የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት ከማክሸፍ አልፎ በየደረጃው ለተቋቋሙ የኮማንድ ፖስት አካላት መረጃ በማቅረብና ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በማጋለጥና አሳልፎ በመስጠት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚነት ባሳየው ቁርጠኝነት በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ሰላም ለማስፈን ማስቻሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት በከፍተኛ አድናቆት እየገለጸ፤ ለሰላም ወዳዱ ህዝባችን ያለውን የላቀ ክብርና ምስጋና በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ይወዳል፡፡
ህዝቡ ያነሳሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በቅድሚያ በመላው አገራችን አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ አንፃር ህብረተሰቡ ሰው የገደሉ፣ ማንኛውም ንብረት ያቃጠሉና የዘረፉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና የአፈፃፀም መመሪያው ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ጥፋት የፈፀሙ ሰዎችን በየደረጃው ለተቋቋሙ የኮማንድ ፖስቶች መረጃ በማቅረብ የጀመረውን ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአንዳንድ የሃገራችን አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ሁከት እንቅስቃሴ ላይ በቡድን ወይም በግል የተሳተፈ፣ የጦር መሳሪያ ወይም ማንኛውንም የግልም ሆነ የመንግሥት ንብረት የዘረፈ፣ ለህገ ወጥ ተግባራት የገንዘብ የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ፣ ወረቀት በመበተን አድማ በማድረግ የተሳተፈና ያነሳሳ፣ እንዲሁም ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠላና ወንጀል የፈፀመ በአስቿካይ ጊዜ አዋጅ የእርምጃ አፈፀፃም መመሪያው አንቀጽ 31 መሰረት የተሰጠው የጊዜ ገደብ ከማለቁ በፊት በቀሩት አምስት ቀናት ውስጥ በአቅራራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እጁን እንዲሰጥና የዘረፈውንም ንብረት እንዲመልስ በጥብቅ የሳስባል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት
ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ