በላ ልበልሀ!!

                                                                       
ያሳለፍነው ሳምንት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጣቢያ በአንገብጋቢ፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የገዢውን ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችን፣ ምሁራንን እንዲሁም የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችን በመጋበዝ ያዘጋጀው ልዩ ፖለቲካዊ ውይይት ለመደመጥ የበቃበት፣ የበርካታ ታዳሚዎችን ትኩረት የሳበበት ሳምንት ሆኖ አልፏል። ፋና የውይይቱን ተሳታፊዎችን ሲጋብዝ የምርጫ መስፈርቱ ምን እንደሆነ ለጊዜው ባይታወቅም ካወያያቸው ውጭ ለችግሩ መፍትሄ ሊያመነጩ፣ መንገዱንም ሊያመላክቱ፣ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና መረጋጋት ገንቢ እሳቤዎችን ሊያበረክቱ ይችሉ የነበሩ በርካታ፣ ገለልተኛ ዜጎችን፣ አዛውንቶችን ወዘተ መጋበዝ ነበረበት፡፡ በላ ልበልሀውን ይበልጥ ያሳልጠው ነበርና፡፡
በልምድና በእውቀት የዳበሩና የተለያየ ሙያ ያላቸውን ዜጎች በማሳተፍ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እንዲመክሩ፣ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ፣ አገራዊ አስተያየታቸውን እንዲለግሱ ማድረግ ይገባውም ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ ይህን ልል የቻልኩበት አቢይ ምክንያት ችግሩ የሚመለከተው መላውን ዜጋ እንጂ ጥቂቶችን ብቻ ባለመሆኑ ነው፡፡ ልድገመውና፣ ለማለት የፈለኩት ፋና በሰራው ስራ እጅግ ይደነቃል፤ ለወደፊቱ የተሻለ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ ግን አንዳንድ አስተያየቶች ያስፈልጉታል። የዚህ ምጥን ፅሁፍ አቢይ አላማም የሄው ነው።
መድረኩ ለውይይቱ የበለጠ ድምቀትና አሳታፊነት በምሁራን፣ በታዋቂ ሰዎች ወይንም በሲቪክ ማህበራት ወዘተ ቢመራ የተሻለ ድባብ መፍጠር በቻለ ነበር፡፡ ውይይቱን ከፓናሉ ጭብጥ(ጦች) አኳያ ገዢውን ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚውን ወክለው ከተገኙት ግለሰቦች አቢይ የመከራከሪያ ጭብጦች አንጻር ሲመዘን፤ ልክ እንደ በላ ልበልሀ የምንለው እድሜ-ጠገብ፣ ባህላዊና ጥንታዊው ቃለምልልስ (የዳኝነት ሂደት)፣ ጆሮና ቀልብን የገዙ፣ የአድማጭን ስሜት ከልብ የማረኩ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበታል፡፡ ይበል ይበል እንዲሉ መሪጌታ፣ እኔም እንዲያ እላለሁ – ይበል!!
በአበው ህመሙን የደበቀ መድሀኒቱ አይገኝለትም እንዲሉ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የገጠመውን የውስጥ ህመምና መሰረታዊ ችግር ሳይደብቅ፣ በራሱ ግምገማ አበጥሮ የፈተሻቸውን፣ አንጥሮም ያወጣቸውን መሰረታዊ ችግሮች በመለየት በውስጡ ያለው ችግር ውሎ አድሮ በሀገራዊ ደረጃ የሚያስከትለውን ከባድ ፈተና አስቀድሞ በመገንዘብ ለማስቀመጥ ችሎ ነበር፡፡ ይሄ ትልቅና ጠንካራ ጎኑ ሲሆን ፈጥኖ እርምጃ ለመውሰድ ያልቻለውም እጅና እግሩ በኪራይ ሰብሳቢው የውስጥ ሀይል ተጠፍንጎ (እራሱ ፓርቲው እንደገለፀው) በመያዙ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
የመንግስት አመራሮች ሀላፊነታቸውን በህግና በተጠያቂነት መንፈስ ያለመስራት፣ መንግስታዊ ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ችግሮች በሂደት ለስርአቱ ከባድ አደጋ ከመደቀናቸውም በላይ የህዝብ አመኔታ እንዲሸረሸር አቢይ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን የውስጥ ችግሮች ለመፍታትም ጥልቀታዊ ተሀድሶ የማድረግ እርምጃ ውስጥ መግባቱን ደግሞ ደጋግሞ ገልጾአል፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሰፊው በመዳሰስ በሀሳብ ክርክሩ ነጥብ የማስቆጠር ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ህልውና የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ሀገሪቱን እንዴት ከገባችበት ቀውስ እንታደጋት የሚል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ክርክሩና በላ ልበልሀው ችግሩን ከመፍታት አንጻር ግማሽ  መንገድ የመሄድ ወይም የመቃረብ ያህል ነበር፡፡ እንደነዚህ አይነት በተለያየ ደረጃ የሚዘጋጁ ውይይቶች በስፋት ቢካሄዱና ህብረተሰቡን ቢያሳትፉ ለበርካታ ችግሮቻችን አፋጣኝ መፍትሄዎችን ማግኘት  በተቻለ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት፣ በፀና የታመመው መንግስት ሲሆን ዶክተሩና መድሀኒቱ ደግሞ ህዝቡ መሆኑ ነው፡፡ ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ዋናውና ወሳኙ ሀይል ነው፡፡ መንግስት ይሁንታ አግኝቶ የሚመረጠውም የሚሻረውም በህዝብ ነው፡፡ የህዝብን ይሁንታ ድጋፍና አመኔታ ካላገኘ መንግስት መንግስት ሁኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ መንግስት ህዝብ የሚለውን የማዳመጥ፣ የመስማት፣ መልስ የመስጠት ግዴታም ሀላፊነትም አለበት፡፡ ሀላፊነቱን በአግባቡና በስርአቱ ለመወጣት ሳይችል ሲቀር ደግሞ በህዝብ ይጠየቃል፤ ይወቀሳል፤ ከፍተኛ ተቃውሞም ይቀርብበታል፡፡ አልገዛማ፤ አሻፈረኝ ባይነትም ይነግሳል፤ አመጽና ሁከትም ይቀሰቀሳል፡፡ ህዝብ በቃኝ ካለ መንግስት እንደመንግስት ሊቀጥል አይችልም፡፡ በየትኛውም መስፈርት የመንግስት አለቃው ህዝብ ነው፡፡
ሕዝብን የሚሰማና የሚያዳምጥ መንግስት በህዝብም ይከበራል፡፡ ይወደዳል፡፡ መንግስት በሰዎች ስብስብ የሚመሰረት በመሆኑ ከስህተት የጸዳና ፍጹማዊ አይደለም፡፡ ትልቁ ነጥብ ስህተቶቹን የሚያርምና የሚያስተካክል ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጥኖ መልስ ሊሰጥ የሚችል ሁኖ ሲገኝ ህዝባዊ ድጋፍና አመኔታውን ያሳድጋል፡፡ በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚው በኩል ያሉ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በሚዲያውም በኩል ያሉት ሰፊ ችግሮች በውይይቱ ላይ በሰፊው ተፈትሸዋል፡፡ የመፍትሄ ሀሳቦችም ቀርበዋል፤ ይበል ይበል እንዲሉ አበው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
በመንግስት ሹሞችና ሀላፊዎች ህዝብን ያስመረሩ ያንገፈገፉ ብሶቱን ያናሩ መጠነ ሰፊ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መዛባት፣ አድልዎና መድልዎ፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፍትህ እጦት ወዘተ ስር የሰደዱ ችግሮች ሞልተው ፈሰዋል፡፡ ህዝብ እንዲመሩና እንዲያገለግሉ በህዝብ የተመረጡ ሰዎች የመንግስትንና የህዝብን ሀብት ለግል ጥቅማቸውና ለመክበሪያነት ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ በህዝቡ ውስጥ ለአመታት የተጠራቀመ ብሶትና ችግር ገንፍሎ ወጥቶ በአደባባይ የታየውን የህዝብ ተቃውሞ አስከተለ፤ የሀገር ሰላምና የህዝብን ህይወት ያናጋ ሁኔታ ተከሰተ፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ እንዴት ከዚህ አዘቅት እንውጣ? እንዴትስ ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ እንታደጋት? የሚለው ነው፡፡ በህዝቡ ውስጥ የተከሰተውን የመረረ ተቃውሞ በመጠቀም የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች በበኩላቸው አጋጣሚውን ለራሳቸው ድል አድርገው በመቁጠር የምንፈልገውን ማድረግ እንችላለን በሚል ስሌት አቅማቸውን አሟጠው ለመጠቀም እየሞከሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ኢህአዴግ ለሀገርና ለህዝብ አልሰራም፤ ለውጥ አላመጣም የሚል ክርክር የሚገጥም የለም፤ በታሪክና በትውልድ ፊት የሚዘከሩ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን አከናውኖአል፡፡ ተቆጥረው በማያልቁ መስኮች ታላላቅ ሀገራዊ ልማትና እድገትን ያስገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
የመንገዶች በዘመናዊ መልኩ መስፋፋት፣ የቀለበት መንገዱ የድልድዮች ስራና ግንባታ አዳዲስ ግድቦች ግቤና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሀገሪቱ ደረጃ አራትና አምስት የነበሩት ዩኒቨርስቲዎች ዛሬ ላይ ከ35 በላይ መድረሳቸው በሀገሪቱ የሚሰጠው የትምህር ሽፋንና በትምህርት ገበታ ላይ ያለው ወጣት ትውልድ ከ75 በመቶ በላይ መድረሱ በጤና ረገድ በርካታ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና ጤና ጣቢያዎች ተገንብተው ስራ ላይ መዋላቸው ሁሉ የኢህአዴግ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ችግሩ ያለው በዚህ ሁሉ መሀል በኢህአዴግ ውስጥ የተቀፈቀፈውና ተንዘራጦ የተቀመጠው ሙሰኛነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ መፍትሄ የሚሻውም አቢይ ጉዳይ ይሀው ነው፡፡
የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ከፍተኛ ክሊኒኮችና የህክምና ኮሌጆች፣  የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ድርጅቶች ቁጥር መበራከት በሀገሪቱ ውስጥ አዲስና እንግዳ የሆኑ የታላቅ እርምጃና እድገት ለውጦች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀድሞ ከነበረው ውስን አቅም በላይ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ደረጃ አየር ማረፊያውን ጨምሮ መስፋፋቱ፣ ዘመናዊና አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ምርጥ የተባለ ለመሆን መብቃቱ፣ የንግድ መርከቦቻችን ቀድሞ ከነበራቸው አቅም በላይ በእጥፍ አድገው በአለም ገበያ ላይ መሰማራታቸው በኢህአዴግ ዘመን የተመዘገቡ ሀገራዊ ድሎችና አመርቂ ውጤቶች ናቸው፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የግዜውን እድገት በሚመጥን መልኩ መስፋፋታቸውና በዘመናዊ ግንባታ እንደ አዲስ መወለዳቸው፣ አዲስ አበባ በአለም አቀፍ ደረጃ ከኒውዮርክና ከቤልጂየም በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ መሆንዋ፣ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ሰላም የማስከበር ግዳጅ ተመራጭ ሀገር ለመሆን መብቃትዋ ሁሉ በኢህአዴግ የአመራር ዘመን የተገኙ ታላላቅ ውጤቶች ናቸው፡፡ 
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ 50 ሚሊዮን የነበረው ህዝብ ዛሬ 103 ሚሊዮን ደርሶአል፡፡ 70 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ወጣት ነው፡፡ የተማረ፣ በእውቀት የተገነባ ጠያቂና ምክንያታዊ ትውልድ ተፈጥሮአል፡፡ ይህ ደግሞ ለወጣቱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የሚጠይቅ አመራርን ይሻል፡፡ ኢህአዴግ ይሄንን ክፍተት በመሙላት ረገድ ራሱን ብቁ ካላደረገ ሂደቶቹ ፈታኝ ሊሆኑበት እንደሚችሉ ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባል፡፡
ዲሞክራሲን በተመለከተ አሳታፊና የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያስተናግድ ፓርላማ መገንባት፣ የግሉን ፕሬስ በማስፋፋት የተለያዩ አመለካከቶች በነጻነት የሚንሸራሸሩበትን ምህዳር ማስፋት፣ በመደማመጥ የጋራ መግባባትን መያዝ፣ ለጋራ ሀገር በጋራ መቆም ሰላም የተመላበትን ህብረተሰብ ለመፍጠር፣ ያደገች ሀገር ለመገንባትም መሰረት ይጥላል፡፡ ሁከት ብጥብጥና ትርምስን ያስቀራል፤ ለውጭ ሀይሎችም ቀዳዳ ባለመክፈትም የሰላም ዋስትናችንን ያረጋግጣል፡፡
በሀገራዊ ጉዳይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ የውጭ ሀይሎችና ተላላኪዎቻቸው በመጡበት አቅጣጫ በጸና አንድነት ቆሞ ለመመከት አሳፍሮም ለመመለስ ይረዳል፡፡ አለመደማመጥና አለመግባባት ተግባብቶም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከልዩነት ባሻገር በአንድነት  ቆሞ ለመስራት አለመቻል እዳው ብዙ ነው፡፡ ለትውልድ ሊያልፍና ሊተርፍም ይችላል፡፡ እንዲህ እንዳይሆን የሰለጠነ ፖለቲካዊ አካሄድን መከተል፣ ብዝሀነትን ማስፋት፣ ሙስናን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ችግርን ጸንቶ በመታገል ተጠያቂነት ያለው አሰራር መገንባት፣ የህዝብን አደራ የበሉትንም ተጠያቂ ማድረግ የበለጠ ተአማኒነትን ይገነባል፡፡
የህዝብን ብሶት ተረድቶ ለጥያቄዎቹ በፍጥነት መልስ መስጠት ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች በቅጡ ተለይተው ተለያይተው መሰራት ሲኖርባቸው ሊደበላለቁ ሊተረማመሱ በጭራሽ አይገባቸውም፡፡ አንዱና ዋናው የህዝብ ቅሬታ ምንጭና ሊፈታ የሚገባው ችግርም ይሀው ነው፡፡ በመንግስት ስልጣን ተጠቅመው ለግል ሀብትና ንብረት የሰሩ፣ የዘረፉ አካላት የህግ ተጠያቂነት ከፊታቸው እንዳለ አያውቁም አይባልም፤ ያውቃሉ።
ባጠቃላይ፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ህዝባዊ መድረክ የማደራጀት አቅሙን አስፍቶና አጎልብቶ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ የተለያዩ አስተያየቶችና አመለካከቶችን ማስተናገድ ጠቀሜታው ለሀገርና ለህዝብ ብቻ ሳይሆን  ለመንግስትም ነው፡፡ ይበል ይበል እንዲሉ፤ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ይበል ብለናል፤ በላ ልበልሀ!!