ለዚህ ፅሑፍ መነሻ የሆነኝ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ በተናጠል በድምቀት የተከበረውን የሰንደቅ ዓላማ በዓል ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሀገራችን ህዝቦች ያደረጉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው። ፕሬዚዳንቱ በዕለቱ “ህዝቡ ድህነትን ለማሸነፍ በእልህና በቁጭት በመነሳቱ በዓለም ላይ የሀገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ከፍታ እየጨመረ መጥቷል” በማለት ተናግረዋል።
እርግጥም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ…ከፍ በማለት ላይ የሚገኘው፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ለመቅረፍና በአዲስ የህዳሴ ጉዞ ለመጓዝ እያደረጉት ባለው ብርቱ ጥረት ነው። በዚህም የሀገራችን ህዝቦች ላለፉት 14 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በየመስኩ ተሰልፈዋል። ይህ የሆነውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲያዊ አንድነቱ መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰባስቦ ልማቱንና ዕድገቱን ማፋጠን ስለቻለ ነው።
የሰንደቅ ዓላማ ምንነት ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ጥልቅ ትርጉሞች አሉት። አንድም ከታሪካችን ጋር የሚያይዘው ዕውነታ ስላለ፣ ሁለትም ከብዝሃነታችን ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ስለሆነ ነው። ከታሪክ አኳያ ስንነሳ፤ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የሀገራችንን የግዛት አንድነት ለማስከበርና ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመታደግ እንደ አንድ ሰው በመሆን በዱር በገደሉ ያካሄዱትን ተጋድሎ ዕውን ያደረጉት በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው ነው። የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከብዝሃነታችን አኳያም ስንመለከት፤ በሰለጠነው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት የዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው መገለጫ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም። በልዩነታችው ውስጥ ያለው አንድነታቸው ሁነኛ ማሳያም መሆኑ እንዲሁ።
እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው አንዱ የሌላውን ማነነት እንዲያውቅ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩ ስራዎችን አከናውነዋል። በተለይም ያለፉት ፊውዳላዊና ጨቋኝ ስርዓቶች በህዝቦች መካከል ጥለዋቸው ያለፉት ቁርሾዎችና ጠባሳዎች እንዲሽሩ፣ የመፈቀቃቀድና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲጎለብት፣ ልዩነታቸው ተጠብቆ በሚያስተሰስሯቸው እጅግ የበዙ ታሪካዊና ነባራዊ ጉዳዩች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጉ ስራዎችን ገቢራዊ አድርገዋል።
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም የገዘፈ ነው። በቡድንም ይሁን በግል አሊያም በሀገር ደረጃ የሚሰራ ማናቸውም ጉዳይ ያለ አንድነት ዕውን ሊሆን አይችልም። አዎ! በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖር ነው። የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፅኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅና የብዝሃነታችን ጥላና ከለላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።
ይህ ሃቅ አንዳንድ ወገኖች ይህን በልዩነት ውስጥ ያለን የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለብተና እንደሚዳርግ በማስመሰል ያስሙ የነበሩትን ልፈፋ መና ያስቀረ ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት (ዛሬም ቢሆን)፤ ሀገራችን ተበታትና ማየት የሚሹ ሃይሎች በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈረውንና በአንቀፅ 39 ላይ የሚገኘውን “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስመገንጠል” የሚለውን ፍፁም ዴሞክራሲያዊ አንቀፅ ገልብጦ በማየት “ኢትየሎጵያ አበቃላት፤ መበታተኗ የሚቀር አይደለም” ሲሉ የጥንቆላ ትንበያን ሲያሰሙ ነበር። ግና ይህ ሟርታቸው ሊሰምር አልቻለም። በተግባር የታየው የዚህ ተቃራኒ ነውና። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሀገራችን የምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት መሆኑ አይካድም።
ይሁንና በቅርቡ ይህን በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት ያጠናከረውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመቀልበስ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር ሞክረዋል። ፕሬዚዳንቱም በንግግራቸው ላይ “የሀገሪቱን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የመቀልበስ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በሀገራችን ጥቅም ላይ አፍራሽ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው” በማለት ሃቁን ገልፀዋል። እርግጥ እነዚህ ኃይሎች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ከሚያደርጓቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ሰንደቅ ዓላማውን ያለመቀበል ነው።ህ ፍላጎታቸው በተለያዩ ወቅቶች ተረጋግጧል። አንዳንዶቹ ሰንደቅ ዓላማውን ሲቀዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ለሰንደቅ ዓላማው ምንም ዓይነት ዕውቅና ሳይሰጡ ቀደምት ስርዓቶች ይጠቀሙበት የነበረውንና መሐሉ ላይ ኮከብና ጨረር የሌለውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሌጣ ሰንደቅ ዓላማን ብቻ ይዘው ሲወጡ ተስተውሏል።
እነዚህ ኃይሎች የፌዴራሉን ሰንደቅ ዓላማ ያለመቀበላቸው ምክንያት ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም ልዩነትን የሚፈታ ስርዓት እያለ፣ ልዩነትን በኃይል በማስፈፀም እነርሱ ወደሚፈጉት የቀደምት ስርዓቶች እንድንመለስ ስለሚፈልጉ ነው። ይህ ፍላጎታቸው ግን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው። ባለንበት የሰለጠነ ዘመን ልዩነትን በመቻቻልና በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መሞከር እንጂ በአስገዳጅ ኃይል ለመፍታት መሞከር ስለማይቻል ነው።
በተለይም የሀገራችን ታዳጊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላለፉት 25 ዓመታት የመጣባቸው መንገዶች የሚያሳየን ነገር ቢኖር፣ ማናቸውንም ችግሮች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ነው። ይህ ዕውነታም ስርዓቱ በውስጡ ሊከሰቱ የሚችል የትኛውንም ዓይነት ውስብስብ ችግር የመፍታት ብቃት እንዳለው ነው። እናም ሰንደቅ ዓላማውን ባለማክበር ስርዓቱ የተጎናፀፋቸውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ድሎችን ወደ ኋላ ለመቀልበስ ማሰብ፤ ላለፉት ዓመታት ሲገነቡ የመጡትን በጎ እሴቶች ለማፍረስ መሞከር መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። ለዚህም ነው—ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ “…ህዝቡ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እኩይ ዓላማ በውል ተገንዝቦ ሊታገላቸውና ሊያጋልጣቸው ይገባል” በማለት ያሳሰቡት። አዎ! ህዝቡ የሀገራችንን ሰላም በመጠበቅ ረገድ የራሱን ሚና ሊወጣ የግድ ነው።
እርግጥ መንግስት ሰላምን ዕውን ለማድረግ የመሪነት ሚናውን የሚወጣ ቢሆንም፤ የህዝቡ የነቃና የእኔነት መንፈስ የታከለበት ብርቱ ተሳትፎ ከሌለበት በአንድ እጅ የማጨብጨብ ያህል ይሆናል—ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ግቡን ሊመታ አይችልምና። እናም ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የመላው የሀገራችን ህዝቦች ሚና የማይተካ መሆኑ ግልፅ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ በብዝሃነት ውስጥ ልዩነታቸውን እያስተናገዱ መጥተው ዛሬ ላይ የደረሱት የሀገራችን ህዝቦች፤ ‘ጥያቄዎቻችን ናቸው’ በማለት ያነሷቸውና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩችን ተጠልለው እኩይ ምግባር እየከወኑ ባሉ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አማካኝነት ሲነጠቁ ዝም ብለው ይመለከታሉ ማለት አይቻልም። እናም በአሁኑ ወቅት እያደረጉ እንዳሉት እነዚህን የእኩይ ሴራ አራማጆችን በመታገልና አጋልጦ በመስጠት ሰላማቸውን ራሳቸው መጠበቃቸው የሚቀር አይመስለኝም—ባለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው ያገኙትን ትሩፋቶች በሚገባ ይገነዘባሉና።
ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ እንዳሉት የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የጠለቀና የረቀቀ ስሜት ያለው በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ስፍራ ይሰጡታል። እናም በሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ ያለውና የሀገራችንን ብሔረሰቦች በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን የሚያንፀባርቀውን አርማን መንካት ማለት የእነርሱን ህልውና መካድ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እናም ይህን መሰሉን ህልውናን የሚክድ ተግባር ሊቀበሉት አይችሉም። ተግባሩም ከእነርሱ ፍላጎት ውጪ በፀረ-ሰላም ኃይሎች አማካኝነት የግል ፍላጎትንና ጥቅምን ማዕከል በማድረግ ስለሚከናወን እነዚህን ኃይሎች በማጋለጥ ህዝቦች በራሳቸው ፈቃድ እውን ያደረጉት ስርዓት ላይ የተጋረጠውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ አደጋ መታደጋቸው የግድ ይሆናል።
ለነገሩ ሰንደቅ ዓላማውን ዕውን ያደረጉት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። የስርዓቱ መገለጫ የሆነው ይህ ሰንደቅ ዓላማ ያለ እነርሱ ፍላጎትና ፈቃድ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊደረግበት አይችልም። ያለ ህዝቦች ይሁንታ ማንኛውንም ነገር ለመፈፀም መሞከር የእነርሱን ሉዓላዊ ስልጣን መጋፋት ነው። ይህ ደግሞ ጥቂቶች በፍፁም “እኔ አውቅልሃለው” የሚል ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተመሩ እጅግ የሚበዛውን ህዝብ መብት በማን አለብኝነት በኃይል ለመንጠቅ መሞከር ነው። ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ የለየለት የጉልበተኞች መንገድ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሰራ አይችልም—የሀገራችን ህዝቦች እስካሉ ድረስ።
በአጠቃላይ በእኔ እምነት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከፊውዳሎችና ከአምባገነኖች ጋር የታገሉት ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በመሆኑ፤ በጥቂት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሳቢያ የታገሉላቸውን መብቶቻቸውን አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉበት ምክንያት የለም። እናም በመብቶቻቸው ላይ የመጡባቸውን ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በህግ አግባብ ሊታገሏቸውና ከህግ በላይ ሆነው ሲንቀሳቀሱም አሳልፈው ሊሰጧቸው ይገባል።