የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ስናስብ…

በመጪው ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለ11ኛ ጊዜ ይከበራል። ታዲያ ዕለቱን ስናስብ የማንዘነጋቸው በርካታ ቁም ነገሮች ቢኖሩም፣ ሀገራችን ውስጥ ህገ መንግስቱ ያስገኛቸውን እንደ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነትን፣ ልማታዊ ተጠቃሚነትን የመሳሰሉ ትሩፋቶችን ለኢዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን ትርጉም ከትላንት ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም አንዳንድ ወገኖች ከሚያነሱት የተሳሳተ እሳቤ ጋር በማያያዝ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህን ጉዳዩች በማንሳት ዕለቱን ስናስብ፤ የሀገራችን ህዝቦች በህገመንግስቱ አማካኝነት የተጎናፀፈችውን ድሎች ለማመላከትና ድሎቹን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት እንድንገነዘብ ያደርገናል ብዬ ስለማምን ነው።  
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቷን አስጠብቃ፣ ህዝቦቿም ለማንም ወራሪ ኃይል ሳይንበረከኩ የኖሩባት ሀገር ትሁን እንጂ፣ ከገዥዎቻቸው የአፈና እና የጭቆና ቀንበር ነፃ አልነበሩም። ይህ ሁኔታም መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ያነሷቸው የነበሩትን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቻቸውን በረጅምና መራር ትግል እንዲመልሱ ምክንያት ሆኗቸዋል። ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ዕውን ባደረጉት ህገ-መንግስት አማካኝነትም ጥያቄዎቻቸውን በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ምላሽ ሊሰጡ ችለዋል። በዚህም ብዝሃነታቸውን እንደ ውበት በመቁጠር አንድነታቸውን አጠናክረው ዛሬ የደረሱበት የዕድገት ማማ ላይ ለመውጣት ችለዋል። 
እርግጥ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያዊያን በቀደምት አበውና እመው ዘመን አንድነት ያላቸው በመሆኑ፣ ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም ሊሉ ይችላሉ። በእኔ እምነት ይህ አስተሳሰብ ፈፅሞ የተሳሳተ ነስው። ምክንያቱም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል ባካሄዷቸው ትግሎች ወቅት የነበራቸውን አንድነት፤ ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና ይሁንታ ለተመሰረተው አንድነት መገለጫ አድርጎ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። 
በእኔ እምነት ባለፉት ስርዓቶች የተፈጠረው አንድነት፤ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃ ፍላጎትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ይልቁንም ገዥ መደቦች ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቃድ ውጭ የመሰረቱት የኃይል አንድነት ነበር በመላ ሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየው። አዎ! በያኔዋ ኢትዮጵያ የነበረው አንድነት በዥዎች የጠብ-መንጃ አፈሙዝ እንጂ፤ በእውነተኛ ህዝቦች ፍላጎትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። እርግጥም አንድነት እውነተኛ ሊሆን የሚችለው የትኛውም ህዝብ የራሱን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብቱን ተጠቅሞ የሚመሰርተውና ሊመሰርት የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲኖር ነው። ባለፉት ስርዓቶች ይህ ባለመኖሩ ነው—የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ሁሉንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ያረጋገጠና በተግባር ላይ ውሎ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን ህገ-መንግስት ያፀደቁት። 
በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት 22 ዓመታት በህገ-መንግስቱ መሰረት ገቢራዊ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንጂ፣ በኃይል ወይም ለይስሙላ ሲባል የተደረገ አንድነት አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተመሰረተው አንድነት ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃነታቸውንና እኩልነታቸውን በማወጅ፤ አንዱ የሌላው የበላይ ሳይሆን በጋራ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁኔታም አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔርና ህዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ትውፊቶችን የማክበር፣ የመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ተግባሮችን ሊፈጥር ችሏል። 
ዳሩ ግን አንዳንድ ወገኖች ይህን ጉዳይ ሲቀበሉት አይስተዋልም። ለዚህም ‘የሀገራችን ህዝቦች ባህልና ታሪክ ብሎም ህብረ-ብሔራዊነት ትናንት የነበረ እንጂ በገዥው ፓርቲ የተፈጠረ አይደለም’ የሚል ሙግትን ያቀርባሉ። ልክ እንደ ቀደም ሲል እንዳነደሳሁት የአንድነቱ ጉዳይ ሁሉ፣ ይህም እሳቤ ትክክል አይመስለኝም። ለዚህም በአስረጅነት ባለፉት ስርዓቶች ይፈፀሙ የነበሩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አፈናን መመልከት የሚቻል ይመስለኛል። 
ሁላችንም እንደምናውቀው መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ተነፍገዋል። እርግጥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች ዓለም አቀፍ  ዶኩመንቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (Self- determination) ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም፤ ያለፉት የኢትዮጵያ ገዥ መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል።  በተለይም በስርዓቶቹ ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በእኩልነት የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም። 
እንዲያውም በአካባቢያቸው አስተዳደር ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ የሚሾሙ አስተዳደሮችና ዳኞች ከማዕከላዊ መንግስት የሚላኩ የኋላ ታሪካቸው ያስረዳል። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ የነበረውን የመንግስት ሠራተኞችን ሁኔታ ብንመለከት እንኳን፤ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ነበሩ። የአካባቢው ተወላጆች እንኳንስ መሾም ይቅርና በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ የመካተት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ግመል በመርፌ ቀዳዳ እንደ መሽሎክ ያህል እጅግ አስቸጋሪ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት ተነፍጓቸው በሌሎች እየተተዳደሩ እንዲሁም ሀብታቸውም እተየመዘበረ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል።  
የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለፅጉበት ዕድል አልነበራቸውም። አዎ! በእነዚያ ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር…ወዘተ. መብት ስላልነበራቸውም፣ አብዛኛዎቹን ቋንቋዎች እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም እጅግ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም የሚዘነጋ አይመስለኝም። ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት መብታቸው የተነፈገ እንደነበርም እንዲሁ።
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች ሰብዓዊ መብታቸውንም ተገፈፈው ኖረዋል። የአካል ደህንነት፣ በህይወት የመኖር መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ… ወዘተን. ከመሳሰሉ መብቶች ጋር አይተዋወቁም ነበር። ከዚህም አልፎ በህግ ባልተደነገገ ሁኔታ ኢ-ሰብዓዊ ለሆነ እስር የመዳረግ፣ በስውር የመታገት…ወዘተ. ወንጀሎች እየተፈፀመባቸው ለከፋ ስቃይና እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸው የታሪክ ድርሳናቸው ያስረዳል። ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ዓይን የማይታዩ መሆናቸውም ጭምር። 
እርግጥ እነዚህን ዋነኛ የመብት ጥሰቶችን በዚህ አጭር ፅሑፍ ላይ በአስረጅነት አነሳኋቸው እንጂ፤ ስርዓቶቹ በዜጎች ላይ ሲፈፅሟቸው የነበሩትን ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ‘ቤቱ ይቁጠራቸው’ ብሎ ማለፍ ተገቢ ይመስለኛል—እንግልቶቹንና አፈናዎቹን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልምና። ዳሩ ግን እነዚህ ሲከማቹ የቆዩ ብሶቶች በስተመጨረሻ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ዳግም ላይመለስ ስርዓተ-ቀብሩ እንዲፈፀም አድርጓል። ከደርግ ግብዓተ-መሬት በኋላም በሽግግሩ ወቅት የተረቀቀው ቻርተር ቀደም ሲል የገለፅኳቸውንና ሌሎች ተነፍገው የነበሩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ዕውን ማድረግ ችለዋል። 
እነዚህ መብቶችም እስከ ታች ድረስ በዘለቀ ህዝባዊ ውይይት ታጅበውና ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ መክረውና ዘክረው የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ባፀደቁት ህገ- መንግስት አማካኝነት፤ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት፣ በራስ ቋንቋ የመጠቀምና የማሳደግ፣ ባህልን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪክን የመጠበቅ እና ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፍ እንዲረጋገጥ ተደርጓል። 
እንግዲህ ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ይህን የመሰለን በህዝቦች ፍላጎትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተን በቋንቋ የመጠቀምን፣ ባህልንና ታሪክን የማሳደግንና ሌሎች ህብረ-ብሔራዊ ጉዳዩችን “ከዚህ በፊትም የነበሩ ናቸው” የሚለውን የአንዳንድ ወገኖች የተንጋደደ ዕይታን ትክክል አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ የሀገራችን ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ዕውን ያደረጉት ህገ-መንግስት ምን ያህል ትሩፋቶችን እንዳስገኘላቸው እንደሚገነዘብ ተስፋ አደርጋለሁ።  
እርግጥ በህገ-መንግስቱ የተለያዩ አንቀፆች ላይ የተቀመጡት ሁሉም መብቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በትግላቸው የተጎናፀፏቸው ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህን ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብቶች ተጠቅመውም የበርካታ ትሩፋቶች ባለቤቶች ሆነዋል። ዛሬ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል። 
ታዲያ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀንን ስናስታውስ ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፍ ጉዳይ ቢኖር፤ በፀረ-ሰላም ኃይሎች አማካኝነት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የተሞከረው ወቅታዊ ክስተት ነው። ክስተቱ “በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አበው፤ ባለፉት 22 ዓመታት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዟቸው ውስጥ በህገ-መንግስቱ አማካኝነት ያገኙትን መብቶችን እንዲሁም ልማታዊ ተጠቃሚነታቸውን አንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተቀናጅተው በሁከትና በብጥብጥ ሊነጥቋቸው መሞከራቸው አይዘነጋም። 
ዳሩ ግን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህ የሁከት ፈጣሪዎች ሴራ በትግላቸው ላመጡት ህገ-መንገስታዊ ስርዓት አደጋ መሆኑን ስለሚገነዘቡ የችግሩን ፈጣሪዎች የማይታገሷቸው መሆኑን በተግባር እያረጋገጡ ነው። ለዚህም ነው—መንግስት ‘ሁከትን ከዚህ በላይ መታገስ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው’ በማለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት ላወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊነት በሚያስገርም ሁኔታ በውስጣቸው የተሰገሰጉ ዘራፊዎችንና ንብረት አጋዩችን እያጋለጡ ለኮማንድ ፖስቱ እያቀረቡ ያሉት። 
ይህም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስቱ የተቀዳጇቸውን ትሩፋቶች ለማንም አሳልፈው እንደማይሰጡ ሁነኛ መገለጫ ይመስለኛል። እናም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ቀን ስናስታውስ የተለያዩ ወገኖች በህገ መንግስቱ ዙሪያ ለሚያነሱት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊ ቁርጠኝነትም በቂ ምላሽ መሆኑ ሊጠቀስ የሚገባው ይመስለኛል። ይህ ‘ሁከት ፈጣሪዎችን አልሸከምም’ ባይነት ህዝቡ ህገ-መንግስታዊ ትሩፋቶቹ እንዳይነኩበት ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነውና።