ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚነት

የሕገ-መንግስታችንን አንቀጽ 93 መሰረት አድርጎ በሚኒስተሮች ምክር ቤት የተደነገገውና ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ስራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ ከሆነ እነሆ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዛል፡፡ ስለዚህ አዋጁ ስራ ላይ የመዋሉ ዜና ከተስማበት ቅደሜ በመስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ምን ምን ተጨባጭ ቁም ነገሮች ተከናውኑ? መላው ሰላም ወዳድ ህብረተሰባችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት ጉዳይ እውን በቅጡ እየተገነዘበውነውን? ወይስ አሁንም የሕግ የበላይነት እንዳሰፍን የሚሹት የጥፋት ሃይሎች ህዝቡ ውስጥ ስነልቦናዊ ሽብር ከመገዛት አልታቀቡ ይሆን? ወዘተ በሚሉ ወቅታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳትና የግል ምልከታዬን መሰረት ያደረገ አስተያየት መስዘር ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡

ስለሆነም ከዚህ አኳያ ሲታይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደንገግ የሰማንበት ዜና ከተደመጠ ጀምሮ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተከናወኑ ተጨባጭ ቁም ነገሮች መኖራቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ በተለይም ደግሞ ለአዋጁ መደንገግ እንደዋነኛ ምክንያት የሚወሰደውን የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሀገር አውዳሚ የሁከትና ግርግር ፈጣሪ ቡድኖች እኩይ ተግባር እንዳይቀጥል የማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ የተጀመረው አደጋውን የመቀልበስ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በሚመሩትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማዎች የማስፈፀም ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነት የተጣለበት ኮማንድ ፖስት አማካኝነት የሚከወን ተግባር እንደሆነም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡  

ሆኖም እኔ እንደአንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት አበክሮ የሚገነዘብ ሰላም ወዳድ ዜጋ፣ አዋጁ መተግበር ከጀመረበት ቀን አንስቶ፣ እየተደረገ ያለው ጅምር እንቅስቃሴና እንዲሁም ደግሞ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የመሻሻል ድባብ የሚንፀባረቅበት እንፃራዊ መረጋጋት ግምት ውስጥ አስገብቼ ስገመግም፤ በእርግጥም የተጋረጠብንን የሀገራዊ ደህንነት አሳሳቢ አደጋ ከመቀለበስ የሚያግደን ሃይል ሊኖር እንደማይችል ከወዲሁ የሚያመለክት አዝማሚያ ነው የሚታየኝ፡፡ በዚህ ረግድ የሚስማኝን ተስፋ እንዳሳድር ካደረጉኝ መስረታዊ ምክንያቶች ዋነኛው ደግሞ፣ ህብረተሰባችን ራሱ ወቅታዊውን የፀጥታ መደፍረስ ችግር ለመፍታት ሲል ከሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ የመንግስት አካላት ጎን ተሰልፎ የጥፋት ሃይሎችን እያጋለጠ መስጠትና ለፍርድ ቀርበው የስራቸውን እንዲያገኙ የበኩሉን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ስለመጀመሩ መረዳቴ ነው፡፡

ለአብነት ያህልም፤ ባለፈው መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም የተከበረውን የኢሬቻ በዓል ተከትሎ በአንዳንድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ከተሞችና እንዲሁም የገጠር ወረዳዎች ጭምር የተከሰተውን የሁከት ተግባር ከመቀስቀስ፣ የተለያዩ የልማት ተቋማትን እስከማውደም በደረሰ የጥፋት ድርጊት የሳተፉትን ግለሰቦች ማንነት እንዲያጋልጡ እድል የተሰጣቸው የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች፣ ያለ አንዳች ማቅማማት ወንጀለኞቹን እየጠቆሙ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ መወጣት እንደ ጀመሩ ነው በተለይ  ፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት ሰሞኑን ከሚያቀርባቸው ወቅታዊ ዘገባዎች ለመገንዘብ የቻልኩት፡፡

እንደ ፋናው ዜና የመረጃ ግብዓቶች ከሆነም፣ ከዘንድሮው የኢሬቻ ክብረ በዓል ጋር  በተያያዘ መልኩ የተከሰተውን የሁከትና ግርግር እንቅስቃሴ ተከትሎ፤ የኦ.ነ.ግን የሽብር ፈጠራ ተልዕኮ ለማስፈፀም በተሞከረባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መስተዳደር አካባቢዎች በተደራጀ ጥቃት የወደመውን መጠን ብዙ ሀብት ንብረት አስመልክቶ የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ህብረተሰብ ራሱ ሲናገር የተደመጠውን በመስማት ብቻ የቡድኖቹ እኩይ ተግባር ምንኛ አሳፋሪም፣ አስደንጋጭም ገፅታ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ እንደምሳሌ ማስታወስ ተገቢ መስሎ የሚሰማኝም ደግሞ፣ በተለይ የሰበታ ከተማ ነዋሪዎችና እንዲሁም የምዕራብ አርሲ ህዝብ በነውጠኞ ሃይሎች የጥፋት ተግባር ስለተቃጠለው ሀብት ንብረት ምስክርነት ሲሰጥ የተደመጠበትን ጥልቅ ቁችት ነው፡፡

እንግዲያውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመጭዎቹ ስድስት ወራት የሚፀና ሕግሆኖ መደንገጉን ያለአንዳች ማመንታት ተቀብለው ለተፈፃሚነቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ የማድግ ጥረት ስለመጀመራቸው የተነገረላቸውም የለምክንያት አይደለም፡፡ ይለቁንስ ለእነርሱ ፍፅሞ ሊገባቸው እንኳን በማይችል ፖለቲካዊ የአመፅ ሴራ ምክንያት፣ የሚቀሰቀሰው የሁከትና ግርግር ተግባር ምንኛ ሀገር አውዳሚ ጥፋትን ሊያስከትል እንደሚችል፣ ከአምና እስከ ዘንድሮ በዓይናቸው በብረቱ ደጋግመው ያዩት አስደንጋጭ እውነታ ስለሆነ እንጂ፡፡

ዓመታትን በፈጄ የህዝብና የመንግስት ፈርጄ ብዙ ጥረት ተገንብተው ገና በቅጡ አገልግት መስጠት ሳይጀምሩ እንደተራ ነገር የጥፋት ቡድኖቹ ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት እየለኮሱባቸው ከመቅፅበት ሲጋዩና ወደ ዶጋአመድነት ሲቀየሩ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ተቋማቶቻችን ጉዳይ፣ እንኳንስ አንዲህ እንደ ኢትዮጵያ ባለሀገር ነባራዊ እውነታ ውስጥ፤ ለበለፀጉት ሀገራትም የሚያንገበግብ ቁጭት መፍጠሩ እንደማይቀር መገመት አይከብድም፡፡ ይህ መራር ጥሬ ሀቅ እነደተጠበቀ ሆኖ፤ ግን ደግሞ የትፋት ሃይሎችን ዕኩይ ተግባር ሰሞኑን ፋና ብሮድ ካስትንግ ኮርፖሬት ባስደመጠን ዓይነት የሰበታ ከተማና የምዕራብ አርሲ ህዝብ ጥልቅ  የቁጭት ስሜት ማውገዝ ያለብን የግድ ሀብት ንብረታችንን በተመሳሳይ መልኩ እስኪያወድሙት ጠብቀን መሆን አይኖበትም የሚለው ነጥብላይ አስምርበት ዘንድ እወዳለሁ፡፡

አለበለዚያ ግን፣ ሀገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመደንገግ ያስገደዱንን ወቅታዊ የጋራ ችግሮቻችንን በሚጠበቀው ፍጥነት ቀርፈን አሁን ላይ የመናጋት አደጋ ያጋጠመውን ስላምና መረጋጋታችንን ወደ ቅድመ 2008 ዓ.ም አስተማማኝ ይዞታው የመመለሱ ጥረት ፈታኝ ገፅታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ፣ በተለይም ግብፅን የመሳሰሉ መላው የሀገራችን ህዝቦች እንደ አንድ ህብረተሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚያካሂዱትን ፀረ ድህነት ትግል በበጎ መንፈስ መመልከት ያቃታቸው የውጭ ሃይሎች በሚሰፈሩላቸው ቀለብ እየተደለሉ እኛን እንደ ሀገር ለማተራመስ ያለለመ የሁከትና የግገርግር ተግባ መፈፀምን እንደ ”አዋጭ የትግል ስልት” የቆጠሩት ፅንፈኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ተልዕኳቸውን ያሳኩ እየመሰላቸው የሚያወድሙት የመሰረተ ልማት ተቋምሁሉ፣ በአሮሚያም ሆነ በአማራ፣ ወይም በሌላ ክልል የሚያስከትለው ኪሳራ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚነካ ድምር ውጤት ይኖረዋል ብለን ማመን ይጠበቅብናል ማለቲ ነው፡፡

ጉዳዩ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ እጣ ፈንታ መተቃት ፅኑ መሰረት እንደጣለ የተመሰከረለትን የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጥያቄን የሚመለከት ጉዳይ እንጂ፣ ለኦሮሚያ ወይም ደግሞ ለአማራ ክልል መንግስት የሚተው ስላልሆነ በዚህ ረገድ ምንም አይነት ብሻብታና የ “እኔን አይመለከተኝም” ክፍተት መፈጠር የለበትም የሚል እምነት ነው ያለኝ”፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመደንገግ ያስገደዱን ወቅታዊ ችግሮች፣ የትኛውንም ክልል በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚነካ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ገጽታዎች ስላሉትም ነው ሀገር አቀፋዊ ማድረግ ያስፈልገው፡፡

ስለዚህም በኔ እምነት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አላማዎች ተፈፃሚነት መላውን የዚች አገር ሰላም ወዳድ ህዝቦች በንቃትና በስፋት የሚያሳትፍ የጋራ መድረክ መፍጠር ግድ የሚል ጉዳይ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስገኝልንን ጠቀሜታ በተመለከተም፣ የጥፋት ተግባር ላይ ከተሰማሩት ቡድኖች ጋር ተሰልፈው ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች፣ ምናልባትም ማንነታቸውን ላለማሳወቅና በሕግ ከመጠየቅ ለማምለጥ ሲሉ ለወትሮው የሚኖሩበትን ክልል ወይም አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ የክልል መስተዳደር አካባቢ እየተዘዋወሩ እግረመንገዳቸውን የትምክህት፣ አልያም ደግሞ የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አስተሳሰባቸውን እንደወረርሽኝ የማዛመት እድል እንዳያገኙም ጭምር የሚረዳ ሀገር አቀፋዊ ዕርስ በርስ የመናበብ አግባብ መፍጠር ያስችለናል የሚለው ነጥብ እንደአብነት መጠቀስ ያለበት ሆኖ ይሰማኛል፡፡

እንደዚህ አይነቱን ለጋራ ሰላምና መረጋጋታችን መደልደል እንደ ህብረተሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘብ እንድንቆም የሚመክር የሚዘክር የጋራ መድረክ በመፍጠር ረገድ ቀዳሚ ሚና መጫወት የሚጠበቅባቸውም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሚዲያዎቻችን በአብዛኛው የሚገለፁበችተ ተጨባጭ እውነታ ሲታይ፤ ከዚህ አኳያ ሊፈጠር ይገባዋል የምንለውን ሀገር አቀፍ ለጋራ ስላምና መረጋጋት ዘብ የመቆሚያ ህዝባዊ መድረክ በመሪተዋናይነት አንቀሳቅሰው ለማናበብ የሚያስችል አጠቃላይ  ቁመና ያላቸው ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ያስቸግራል፡፡

ስለሆነም፣ ሚዲያው ከእስከዛሬው ውስንነቶቹ ተላቆ ምልዓተ ህዝቡን ለአንድ ወሳኝ ሀገር አቀፍ የጋራ አጀንዳ ከማሰለፍ አኳያ፣ ትርጉም ያለው አወንታዊ ተፅእኖ መፍጠር የሚያስችል አጠቃላይ ቁመና እንዲኖረው የማድረጉ ስራ መቅደም ያበት አንገብጋቢ ተግባር ነው ቢባል የተሸለ ይመስለኛል፡፡ ወቅቱ ለሚዲያ ጦርነት የተጋለጠ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ የሚስተዋልበት የመሆኑ ጉዳይ ሳይዘነጋ፣ ይልቁንም ሀገራችንን አሁን ላይ ስለገጠማት አሳሳቢ ችግር መንስኤና መፍትሔ ስናነሳ የመገናኛ ብዙሃን የሙያ ዘርፍን ሚና በቅጡ መፍተሸ  ግድ እንደሚል ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚነትም ቢሆን  ሚዲያው ዋሳኝ ድርሻ እንዳለው መዘጋት አይኖርበትም ፡፡  መዓ ሰላማት!