ግብጽ አልተኛችም!!

የግብጽ ማንነት ከጥንት ጀምሮ በውል ስለሚታወቅ ብዙም አይደንቅም፡፡አስገራሚው ጉዳይ የግብጽ አላማ አስፈጻሚ ሁነው የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም የሸጡት በመሳሪያነትም በማገልገል ያሉት ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ግብጽ ከአንገት በላይ ወዳጅ በመምሰል ውስጥ ውስጡን ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ለማዳከም በዚህም በአባይ ውሀ ላይ በነጻነት የመጠቀም መብት አገኛለሁ ብላ የምታምን ሀገር ነች፡፡ግብጽ በአባይ ወንዝ ውሀ የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ ከማሴር መቼም ተኝታ አታውቅም፡፡ግብጽ ዛሬም  አልተኛችም፡፡

የግብጽ  ህዝብ  በአባይ ውሀ እንደልቡ ይጠቀም ባለቤቱ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ሲያሻው ይራብ በድህነትን ውስጥ ይኑር የሚል ስግብግብ እና ለእኔ ብቻ የሚል አቋም የምታራምድ ሀገር ናት፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች በጀት መድባ ለአክራሪ ተቃዋሚዎች በማደል የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቓረጥ እንዲቆም በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ኦነግን እነ ጀዋር መሀመድን የመሰሉ ወኪሎችዋን አሰልጥና በማሰማራት በእነሱም ግንባር ቀደም አስተባባሪነትና መሪነት በሀገር ውስጥ  ጥፋትና ውድመት እንዲያደርሱ አድርጋለች፡፡

የቱንም ያህል በውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳያችን ልዩነትና አለመግባባት ቢኖር በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው አቋም አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ለድርድርም ለሽምግልናም አይቀርብም፡፡ የተጀመረውም የተገነባውም በህዝቡ ገንዘብ ስለሆነ የአባይን ግድብ ስራ ግንባታውን የደረሰበትን ደረጃና አፈጻጸሙን የሚከታተለው  ዳር የሚያደርሰውም ሆነ የሚጠብቀው ህዝብ ነው፡፡የሀገሩም የሰላሙም ባለቤት ህዝብ ነው፡፡

በአባይ ውሀ ጉዳይ ግብጽ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚለው ዘመናት ያስቆጠረ መሰሪ ባህርይዋ መቼም የማትቆጠብ ከኢትዮጵያ ላይም እጅዋን የማታነሳ ሀገር መሆንዋ ይታወቃል፡፡ በመልካም ወዳጅነት ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀም የሰጠንን በጋራም ያቆራኘና ያስተሳሰረንን የአባይ ውሀ በሰላም መጠቀም ሲቻል ዛሬም በጸረ ኢትዮጵያ አቋማ ገፍታበታለች፡፡ኢትዮጵያ ላይ በምትፈጽመው ስውር ተንኮልና ወንጀል በራስዋ ላይ ሊመለስ የማይችል ጥፋትና ውድመት ለህልውናዋም የሚያሰጋ ችግር ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል በውል አላጤነችውም፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ ለሁላችንም ይበቃል የግብጽ ሕዝብ እንዲጠማ አልፈልግም በጋራና በትብብር በሰላም ውሀውን መጠቀም እንችላለን የሚለውን አቋሟን ዛሬም በጽናት ቀጥላበታለች፡፡የሚበጀውም መንገድ ይሀው ነበር ፡፡

ግብጽ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር መንግስት መምራት እንዲሳነው በአመጽና በሁከት በውድመት ትልቅ ትርምስና አደጋ እንዲፈጠር በማቀድ ለአላማዋ ስኬት የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ሰርታለች፡፡ ደካማ የተበታተነች አቅመቢስ ከድህነት የማትወጣ በተረጂነት ስር የምትኖር ኢትዮጵያን መፍጠር ነው የግብጽ ምኞትና ፍላጎት፡፡ይሄ ደግሞ መቼም አይሆንም፡፡

አለምን ባስገረመና በምሳሌነት በሚጠቀስ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ግንባታና እድገት ውስጥ እየተራመደች የምትገኘውን ኢትዮጵያን ለማዳከም ብሎም ለማፈራረስ ወጥና የምትሰራው ግብጽ ዛሬ ላይ ኦነግንና ጀዋር መሀመድን እነግንቦት ሰባትን በመደገፍ በሀገር ውስጥ የከፋ ውድመትና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር የእልቂት አውድማ እንድትሆን  እየሰራች ትገኛለች፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄንን የግብጽ መሰሪ ሴራ በማምከን ሀገሩን ይጠብቃል፡፡

አይሲስ ባዘጋጀው የእስላማዊ መንግስት ካርታ ኢትዮጵያን አካቶአል፡፡አልሻባብ የእርሱው አጋር አልሆንለት ብሎ እንጂ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያልወጠነው ያላቀደው መንገድ የለም፡፡የዋሀቢና ሰለፊያ አክራሪ እስለማዊ መንግስታትና ቡድኖች አሰብ ላይ ሰፍረው እያማተሩ ያሉት በኢትዮጵያ ላይ መሆኑ ይተወቃል፡፡

ግብጽ  ደግሞ ኦነግንና ጀዋር መሀመድን በመጠቀም ሌሎችንም በማሰማራት የመንግስትና የህዝብን የግለሰቦችን ንብረት የልማት ተቋማትን የማውደሙን ስራ በወኪሎችዋ አማካኝነት ሰርታለች፡፡አንዱ ግባቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሽመድመድ  ኢንቨስተሮች ወደሀገሪቱ እንዳይገቡ የገቡትም በፍርሀት ተውጠው እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡

ይሄንን በተጠና መንገድ አቅደው ለመፈጸም ሞክረዋል፡፡አሁን ህዝቡ እውነታውን ተረድቶአል፡፡ከጀርባ እነማን እንዳሉ አላማቸው ምን እንደሆነም ጠንቅቆ አውቆአል፡፡

በኢትዮጵያ በአራቱም ማእዘናት ጠላቶችዋ አሰፍስፈው ሊቀራመቱዋት ተዘጋጅተው  በሚገኙበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን ስም የተሸከሙ አክራሪና ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች በግብጽና በሻእብያ ተላላኪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት በራሳቸው ሀገርና ህዝብ ላይ በጠላትነት መሰለፋቸው ህዝብን አስቆጥቶአል፡፡

በሀገር ውስጥ የተከሰተው የመልካም አስተዳደር የፍትህ የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ስር የሰደደ ችግር የሚፈታው በህዝቡና በመንግስት የጋራ ተሳትፎና ርብርብ እንጂ አጋጣሚውን ተጠቅመን አላማችንን እናሳካለን በሚሉ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡

ከጥቂት አመታት በፊት የአረቡን አለም አብዮት ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲሰሩ  የነበሩት አክራሪ ተቃዋሚዎች ያልተረዱት እውነት የአረቡ አለም አብዮት የተመራው በግብጹ ጽንፈኛ አክራሪ እስላማዊ ድርጅት ሙስሊም ብራዘር ሁድ የበላይነት ሲሆን ግቡም በተለያዩ አረብ ሀገራት በነበሩት ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ አማካኝነት ተንቀሳቅሶ በሸሪአ የሚመራ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እንደነበር በኃላ ላይ ይፋ የወጡት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ያስገኘውም ሆነ የአመጣው ለህዝብ የሚጠቅም የሚበጅ ለውጥ የለም፡፡ ጭርሱንም መመለስ በማይችሉበት ደረጃ አጥፍቶአቸው ነው ያለፈው፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮች ሀገራቱ በነበራቸው የቀደመ ሰላምና መረጋጋት በአረቡ አለም ኢንቨስት ያደረጉትን ሀብት ወደ ሌሎች ሰላም ወዳለባቸው ሀገራት አሻግረውታል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ አዲስ የውጭ ኢንቨስትመንት አይታሰብም፡፡ሰላምና መረጋጋት ከጠፋ ሀብቱን የሚያፈስ የውጭም የሀገር ውስጥም ባለሀብት አይኖርም፡፡ዋናው ሰላም ነው፡፡ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ሰላም እንዲደፈርስ የተጀመረው ልማትና የእድገት ጉዞ እንዲታወክ ግብጽና ከጀርባ ያሉት ሀይሎች ተቀናጅተው እየሰሩ ያሉት፡፡

በጭፍን ጥላቻና እብደት የናወዘው አክራሪ ተቃዋሚ ሀይል ሊቆሰቁስ በሞከረው አቅጣጫ የሌለው የህዝብ  ነውጥና አመጽ ቀጣዩ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ወደየት ያመራል ብሎ ለማሰብ አልቻለም፡፡የውድመትና የእብደት አብዮት ትርፉ የሀገር መጥፋት የዜጎች እልቂትና ስደት ብቻ ነው፡፡ተጠቃሚም አትራፊም የለም፡፡

በነውጥና በውድመት መነሻነት የሚካሄድ አመጽ ለህዝብ የሚጠቅም በህዝባዊ ምርጫና ውሳኔ ላይ የተመረኮዘ ሰላማዊና የሰለጠነ የሰልጣን ሽግግር አያመጣም፡፡ሀይልና ነውጥን መሰረት ያደረገ ሀገርና ህዝብን ለአደጋ አሳልፎ የሚሰጥ የፖለቲካ ስልጣን ቀጣዩ እድሉ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ዛሬም ግብጽ የመን ሶሪያ ሊቢያ ሰላም የላቸውም፡፡በቀውስ እየተናጡ እየራዱ ይገኛሉ፡፡

አመጽ ሁከትና ግርግሩን  ንብረት ማውደሙን መርተነዋል የሚሉት እነኦነግ በራሳቸውም በኩል ስምምነት የላቸውም፡፡በተለያየ ዓላማና አደረጃጀት ውስጥ የሚቀዝፉ ናቸው፡፡ በትርምሱ ውስጥ ተጠቃሚ ለመሆን ያሰፈሰፈው የስርዓት አልበኛው ሀይል የጎዳና ግርግሩንና ትርምሱን አጥብቆ ይፈልገዋል፡፡ለዘረፋ ለንጥቂያ ለውንብድና ተግባሩ አመቺ መሰረት አገኛለሁ ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ከአሁን በኃላ ለዚህ የጠላቶች ሴራ የሚሆን ክፍተት በኢትዮጵያ አይኖርም፡፡

ህዝቡ የተፈጠረውም ሆነ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስና ትርምስ ከማንም በላይ የሚጎዳው የችግሩም ቀጥተኛ ተጠቂና ሰለባ የሚያደርገው ራሱን መሆኑን በውል ተረድቶታል፡፡ ሰላሙን መረጋጋቱን የሚጠብቀውም ለዚህ ነው፡፡ታግሎ ያከሸፈውም ህዝብ ነው፡፡

ለሀገርና ለሕዝብ ካለማሰብ የሚመጣ መነሻውን ጎዳና ያደረገ በሂደትም ወደ ብሔራዊ ጥፋትና ውድመት የተረማመደ እርምጃ ለሀገር ሰላም ዲሞክራሲ ፍትሕና መልካም አስተዳደር አያመጣም፡፡ለህዝብ ከመቆርቆር የመጣ  ሊሆንም አይችልም፡፡

የአደጉና የበለጸጉ ሀገሮች በውስጥ ልዩነት ሲኖራቸው በሃሳብ ተፋጭተው በሕዝብ ምርጫ አሽናፊ የሆነው የፖለቲካ ስልጣኑን ተረክቦ ሀገሪቱን በሰላማዊ መንገድ ይመራል፡፡ሀገር አያወድሙም፡፡ችግሮች ሁሉ በሰከነና በሰለጠነ ሰላማዊ ውይይቶች ይፈታሉ፡፡ሀገሪቷ ሳትወድም ልጆቿም ሳያልቁ  ከተሰራውና ከቆመበት ደረጃ ተነስተው ለተከታዩ ሀገራዊ እድገት ይሰራሉ፡፡ቀድሞ የተገነባው ወድሞ ከባዶ ሜዳ እንነሳ የሚል በሀገርና በትውልድ የመቀለድ የጅል ጨዋታ የላቸውም፡፡

ስልጡን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ግትሮችና ጭፍኖች አይደሉም፡፡ በሀገራቸው ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት በህዝባቸውም ሰላም ላይ ከውጭ ሀይሎች ጋር ተደርበው አያሴሩም፡፡በቅጥረኛነትም አይሰለፉም፡፡ግብጽ ዛሬም ነገም በኢትዮጵያ ላይ ከማሴር አትቆጠብም፡፡አትተኛም፡፡ሴራዋን ማምከን የመንግስትም የዜጎችም የጋራ ሀላፊነት ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

ግብጽ ከጥንት እስከአሁነ ትውልድ ድረስ ለኢትዮጵያ ፈተናዎችን እየደቀነች  የውስጥ ተላላኪዎችን  በገንዝብ ሀይል እየገዛች ዘመን የማይሽረው ጠላትነትዋን ገፍታበታለች፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የዘረጋችላትን የሰላምና የወዳጅነት እጅ በመንከስ በውስጥ ጉዳያችንም በመግባት አክራሪና ጽንፈኛ ሀይሎችን በመደገፍ በሀገራችን ሰላም እንዲደፈርስ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲከሰት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ይህንን ጸረ ኢትዮጵያ  ሴራ ማምከን  የሁሉም ዜጋ  ሀላፊነትና ግዴታ  መሆኑ  መታወቅ  አለበት፡፡ግብጽ ዛሬም ነገም  አትተኛም፡፡ እኛም አንተኛም፡፡ ነቅተን ሴራዋን  እናመክናለን፡፡