ከመጋረጃው ጀርባ 

                                                                   
ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ሀገሪቱን ለማዳከምና የጥፋት ማእከል እንድትሆን በማቀድ በተለያዩ ስሞችና ሽፋኖች ወደሀገራችን በመግባት የቤት ስራቸውን ለመስራት ከመሞከር ቦዝነው አያውቁም፡፡ ምንም እንኳን ያሰቡትን ማሳካት ባይችሉም፤ ከመጋረጃው ጀርባ በመሆን፣ የራሳችንን  ዜጎች በመሳሪያነት በመጠቀም ለአላማቸው መሳካት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሁከትና ነውጥ ብጥብጥ የህዝብ አመጽ እንዲነሳ ልማትና እድገትዋ እንዲሰናከል ከሚደረገው ዘመን የማይሽረው የመጋረጃው  ጀርባ ሴራም ሁሌም መሪ ተዋናይዋ ግብጽና ሌሎች አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች አሉ፡፡ 
በኢትዮጵያ ከ1997 በፊት ባገኘው አጋጣሚ በመጠቀም አክራሪው እስላማዊ ሀይል ወደ ሀገር ውስጥ በሽፋን ሰርጎ በመግባት ገዝፎ ነበር፡፡ የውጭ መንግስታዊ ያልሆኑ የእስልምና አለም አቀፍ ድርጅቶች ከመንግስት ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው ቢሮ ከፍተው ሲንቀሳቀሱ በሽፋን የሚሰሩት ስራ አክራሪ እስላማዊ እምነትን ወደሀገራችን የማስገባት ሰዎችን የመመልመል፣ ለመመሳሰል እንዲያመቻቸውም ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በማግባት ከአዲስ አበባም አልፈው በክልሎች በእርዳታ ስም ቢሮዎችን በመክፈት የመስክ ጉብኝት እያሉ በመውጣት ከፍተኛ ገንዘብ የሚረጩበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡
እነዚሁ ከውጭ በእርዳታ ድጋፍ ስም ወደሀገራችን የገቡ አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች መስጊዶችን ከነባሩ የኢትዮጵያ ሱፊ ሙስሊም እምነትና የቆየ ባህል ውጪ ከመስራትም አልፈው ተርፈውም የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤትን አመራር ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሲሉ በገፍ በረጩት ገንዘብ በሙስሊሙ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ ረብሻ እንዲፈጠር ማድረግ ችለውም ነበር፡፡
ሁኔታውን ከስረ መሰረቱ የተከታተለው መንግስት የሁኔታውን አደገኛነት በማስረጃ ይዞ በተለያየ ስም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እስላማዊ የእርዳታ ድርጅቶች ፈቃዳቸው ተሰርዞ ቢሮአቸውን ዘግተው በአስቸኳይ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አድርጎአል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በአፍጋኒስታን ጦርነት የታሊባን ተዋጊ የነበሩ አክራሪና አሸባሪ ሙስሊሞች የእርዳታ ድርጅቶቹ የበላይ ሀላፊ በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በሽፋን የገቡበት ሁኔታም ተደርሶበታል፡፡ መንግስት በወሰደው ወሳኝ እርምጃ በሀገሪቱ ላይ ሲጠነስሱት የነበረውን ታላቅ አደጋ ማምከን ችሎአል፡፡ በወቅቱ ተቃዋሚዎች ሲያጣጥሉት የነበረው የአክራሪ እስልምና እምነት  በኢትዮጵያ ውስጥ የለም የሚለው ርካሽ የፖለቲካ ድጋፍ ፍለጋ ሀገራዊና ህዝባዊ ሀላፊነት የጎደለው ጩሀት ነበር፡፡  አደጋው ይህንን ያህል ገዝፎ የነበረ ሲሆን ከተባረሩ በኋላም በስውር እንቅስቃሴአቸውን ማድረግ አላቆሙም፡፡
የግብጹ አክራሪና አሸባሪው እስላማዊ ድርጅት ሙስሊም ብራዘር ሁድ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ የገባው በንጉሱ ዘመን ግብጽ በመሄድ የእስልምና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ይማሩ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ውስጥ በመመልመል ነበር፡፡ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላም ውስጥ ለውስጥ በምስጢር መዋቅራቸውን በመዘርጋት ሲሰሩ መኖራቸውና በተለይም ወጣቱን ሙስሊም በአክራሪነት ለመቅረጽ መቻላቸው ይታወቃል፡፡
ይሀው ሁኔታ ገፍቶ ሄዶ ንጉሱ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በደርግ የመጀመሪያዎቹ ዘመን እንቅስቃሴው ጎልብቶ በሀረር፣ በጅማ፣ በባሌ፣ በኢሊባቡርና በሰሜን ሸዋ አካባቢ ንቅናቄው በመግፋቱ ከፍተኛ እርምጃ በመውሰድ እንደገታው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚህም ጀርባ ግብጽ ነበረች፡፡
ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ 700 ኪ/ሜ ግዛታችንን ጥሳ ግዙፍ ወረራ ስታደርግ ጀነራል ዚያድ ባሬ በገንዘብ በጦር መሳሪያ፣ በሎጅስቲክ፣ በአማካሪነት የወረራውን እቅድ ከመንደፍ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ሙሉ በሙሉ ይደገፍ የነበረው በግብጽ ነበር፡፡ ኤርትራ በባድመ በኩል ኢትዮጵያን ለመውረር ስትዘጋጅ የጦር መሳሪያ፣ ትጥቅና ድርጅት ገንዘብ በመስጠት እንዲሁም የጦር አማካሪ የነበሩት ግብጾች ነበሩ፡፡
ሶማሊያ እንደ ሀገር ከተበተነችም በኋላ የተለያዩ የጦር አበጋዞችን በአክራሪ እስላማዊ እምነት ያጠመቀው የግብጹ አክራሪና አሸባሪ ድርጅት ሙስሊም ብራዘርሁድ ሲሆን እነዳሂር አዌይስ ይመሩት የነበረው እስላማዊ ምክር ቤት በኋላ ላይ ወደ አልሻባብነት የተለወጠው አክራሪና አሸባሪ ድርጅት  ይረዳና ይታገዝ የነበረው በግብጽ ነበር፡፡
ግብጽ ሶማሊያን ለመቆጣጠርና በእስዋ አማካኝነት ከጀርባ የሚመራ ሳተላይት መንግስት ለመመስረት ስትታግል የነበረው በቅርብ ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ ለማዳከምና ለመውጋት በማቀድ ነበር፡፡ በቅርቡም በሶማሊያ ቋሚ የጦር ሰፈር ለመመስረት ጠይቃ ጥያቄዋ ውድቅ ሆኖአል፡፡
በሶማሊ ላንድም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት አላገኘችም፡፡ በደቡብ ሱዳንም በኩል የደቡብ ሱዳንን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ በገንዘብ በስልጠና በጦር መሳሪያ ወዘተ ልርዳ በሚል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ወደፊት ተለዋዋጭ ከሆነው ሁኔታ አንጻር እነዚህ አጎራባች ሀገራት የሚኖራቸውን አቋም ለመገመት ቢያስቸግርም ቁልፉና ወሳኙ ነጥብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የመከላከያና የደህንነት አቅም አሁን ካለውም በላይ የጎለበተ እንዲሆን አድርጎ መገንባት  ነው፡፡ የነግብጽ የእስከአሁኑም ተደጋጋሚ ፈርጀ ብዙ ሙከራቸው የከሸፈው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ተሰሚ፣ ተደማጭና ልእለ ሀያል ሀገር ለመሆን በመብቃትዋ ነው፡፡ በአንድ በኩል እነጀዋር መሀመድንና ኦነግን፣ ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉ በግብጽና በሌሎችም አክራሪ ሙስሊም ሀገራት የሚረዱ ቅጥረኞች የተለያየ አጀንዳ ይዘው በሀገራቸው ላይ ሲዘምቱ በሌላም በኩል የቀለም አብዮት አራማጆች በውጭ ሀይሎች ስምሪት ተሰጥቶአቸው ሀገሪቱን የሁከትና የብጥብጥ የእርስ በእርስ ግጭት ማእከል ለማድረግ በወኪሎቻቸው አማካኝነት ዘምተዋል፤ ጥፋትም አድርሰዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያቸውን በመጠቀም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተው የስነልቦና ጦርነት በህዝቡ ላይ አካሂደዋል፡፡ ከፍተኛ ውዥንብርና አለመረጋጋት በህዝቡ ውስጥ እንዲፈጠር የሀሰት ወሬ የሚያሰራጩት ኢሳትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በቀጥታ የሚረዱት በግብጽ ነው፡፡ በሌላም አቅጣጫ አልሻባብ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ሰራዊት ተደምስሶ፣ ይዞታውን ተነጥቆ አፈግፍጎ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ሰራዊት ለቆ በመውጣቱ ሶስት ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችሎአል፡፡ ኢላማው ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡
የመን ላይ የዘመተው የገልፍ ሀገራት የዋሀቢና የሰለፊያ አክራሪ ሙስሊም መንግስታት የባህር ሀይል ተዋጊ መርከቦቻቸውን፣ የእግረኛ ሰራዊትና ተዋጊ ጀቶቻቸውን የሚያርፉበት ጦር ሰፈርና ማዘዣ ጣቢያ እንዲሆን  የኤርትራ መንግስት አሰብን በሊዝ እንዲይዙት አድርጎአል፡፡ ይህ አሰብ ላይ የመስፈራቸው ጉዳይ ሲታይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነትና ሉአላዊነት ምን ያህል አደገኛ ሁኔታ በዙሪያዋ አንዣቦ እንደሚገኝ በግልጽ ያሳያል፡፡
በሀገር ውሰጥ በህዝቡ የተነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ መከበርና የሙስና ጥያቄዎችና ተቃውሞዎችን መንግስት በጥልቀታዊ ተሀድሶ ለመፍታት ሰፊ እንቅስቀሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ቀዳዳ በመጠቀም የህዝቡ ህጋዊ ጥያቄ መንገድ ስቶ እንዲሄድ፣ ስርአት አልበኝነት እንዲሰፍን በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችም ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ፣ ሀገሪቱ የጀመረቸው የልማትና የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ እንዲገታ ለማድረግ ግብጽ ኦነግንና ጀዋር መሀመድን በማሰለፍ የእጅ አዙር የውክልና ጦርነት ከፍታለች፡፡
ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ በማቀድ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ኦነግ በግብጽ በመረዳት እነጀዋር መሀመድ እስላማዊ ኦሮሚያን ገንጥለው ለመመስረት በማለም በሻእቢያና በግብጽ አሽከርነት ወኪሎቻቸውን በማሰማራት አውዳሚ በሆነ ተግባር ላይ ተሰማርተው ከፍተኛ ሀገራዊና ህዝባዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ንብረቶች አውድመዋል፡፡
ሀገሬን ወገኔን እወዳለሁ ለሚል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ የወቅቱ ወሳኝ ጉዳይ ሀገሪትዋን በየአቅጣጫው ሊያጠፉዋትና ሊበታትኑዋት ከተነሱ የጠላት ሀይሎች ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ነው፡፡ ስለፖለቲካ ስልጣን ከማውራት በፊት መጀመሪያ የተከበረች፣ የታፈረች ሀገር መኖር መቻል አለባት፡፡
ኢትዮጵያን ዙሪያዋን በከበባትና ባሰፈሰፈ ጠላት መሀል ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ኢህአዴግ ስልጣኑን ይልቀቅ ማለት ምን ያህል የከፋ አደጋ በሀገሪትዋ ላይ እንደሚፈጥር ሁሉም ዜጋ አርቆ ማስተዋል አለበት፡፡ ስልጣኑን ቢለቅስ ክፍተቱን ሊሞላ፣ ሀገሪቱን ሊያስተዳደር፣ ደህንነትዋን፣ ሉአላዊነትዋን ጠብቆ የህዝቡንም ሰላምና መረጋጋት ሊያስጠብቅ የሚችል የተደራጀ ተቃዋሚ የትኛው ነው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ የለም፡፡ አማራጭና ተስፋ የሚሆን ፓርቲ እስካሁን አልታየም፡፡
ባሀር ማዶ ሁኖ ማውራትና ሀገር መምራት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ለውጥ ቢመጣም ኢህአዴግ አንዱ ግዙፍ የፖለቲካ ድርጀት በመሆኑ እሱን ማግለል አይቻልም፡፡ ሰባት ሚሊዮን አባላት ያሉትን ድርጀት በማግለል የሚመጣ ሀገራዊ መፍትሄም ለውጥም አይኖርም፡፡ ለዚህ ነው ስለትልቅዋ ሀገራችን ስናስብ ከጥላቻ፣ ከመናቆር፣ ከመጠፋፋት፣ ከመባላት አስተሳሰብ በመውጣት እንዴት ሀገራችንንና ሰላምዋን እንጠብቅ የተጀመረውን ሀገራዊ ልማት እንዴት እናስቀጥል የተከሰቱትን የውስጥ ችግሮች እንዴት እንፍታ፣ የተሻለ አሰራር እንፍጠር፣ ብሎ ማሰብ ተገቢ የሚሆነው፡፡ ለውጭ ጠላቶች በር መክፈትም አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ለተቃዋሚው ብቻ ሳይሆን  ለኢህአዴግም ሀገሩ ነች፡፡ ተቀራርቦ በመነጋገር፣ በመወያየት፣ ጥላቻን በማስወገድ ችግሮቻችንን ሁሉ ፈተን ሀገራችንን ሊያጠፉ ከዘመቱብን የውጭ ሀይሎች መከላከልና መጠበቅ አለብን፡፡ ግብጾች ያን ያህል ርቀት በመሄድ ከጥንት እስከ ዛሬ የሚዘምቱብን ለሀገራቸው ብሄራዊ ጥቅም መከበር ሲሉ ነው፡፡ እርስ በእርስ እየተባላን ሀገራችንን ለከፋ አደጋ አሳልፈን መስጠት አይገባንም፡፡ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን ይሄንን አላስተማሩንም፡፡ የአባቶቻችን ልጆች መሆን ነው ያለብን፡፡ ሀገራችንን ነቅተን እንጠብቅ!!