መቻላችንን የምናሳይባቸው ጅማሮዎች

በመንግስት የልማት ስራ አፈፃፀሞች ውስጥ የተወሰኑ ጉድለቶች ቢኖሩም፤ ጠንካራ ሊባሉ የሚችሉ ክንዋኔዎች መኖራቸው ግልፅ ነው። እነዚህ ጠንካራ አፈፃፀሞች አንዳንዶቹ ‘አይቻሉም’ የተባሉ ጉዳዮችን “በመቻል’ የቀየሩ ጅማሮዎች ናቸው ቢባሉ የሚበዛባቸው አይመስለኝም። ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው የሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት አንዱ ነው። ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ውስጥ ተርታ እንድትሰለፍ መንግስት ከተለማቸው የልማት አውታር ዕቅዶች ውስጥ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት በቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ቦታ እንድንይዝ የሚያደርግ ነው።
ታዲያ ይህን ዕቅድ ገቢራዊ ለማድረግ በመንግስት በኩል ሁሉን አቀፍ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ሆኖም በፓርኮች ልማት ስራዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መቅረብ ያለባቸው ተጨባጭ ሃቆች መኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም። እናም በዚህ ፅሑፌ እነዚህን የፓርኮቹን ልማት ተግባራትን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በመሆኑም በዋነኛነት ‘የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለዜጎች ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?፣ ፓርኩ ሰፊ መሬት የሚጠይቅ በመሆኑ ከቦታቸው ለሚነሱ ሰዎች የሚደረገው የካሳና የክፍያ ሁኔታ ምን ይመስላል?፣ ተግዳሮቶቹስ ምንድናቸው’ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መረጃዎችን ተንተርሼ እንደሚከተለው ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ። 
የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱን በበላይነት ከሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማለት በአንድ በተከለለ አካባቢ ወይም ቦታ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚቋቁሙበት ሆኖ ልማቱን ለማፋጠን ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች በሕግ አግባብ የሚሰጡበት ማዕከል ነው። 
በዚህ አግባብ የሚገነባ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይለዋል። በዘመናዊ አሰራር ውስጥ የሚታወቀውን የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ አሰራርንም ይከተላል። በፓርኩ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። 
እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለማግኘትም በመንግስት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ከሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት በተጨማሪ የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ማስጀመር መቻሉን መረጃዎች ያስረዳሉ። የቦሌ ለሚ ሁለትና ቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የዲዛይን ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውም እንዲሁ። ከዚህ ጎን ለጎንም የድሬዳዋ፣ የአዳማ፣ የባህርዳርና የጅማ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች አብዛኛው የቅድመ ዝግጅት ስራዎቻቸው የተጠናቀቁ ሲሆን፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም የደብረብርሃን፣ የአረርቲና አይሻ/ደወሌ ግንባታዎችም የመጀመሪያ ዙር ስራቸው ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ታዲያ ይህ በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል። ለዚህም በምሳሌነት በቅርቡ ለተገነባው የሃዋሳ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ባለውና በፓርኩ የማሽነሪ ተከላ እያካሄደ በሚገኘው “ታል-ግሩፕ” የተሰኘው የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያ 125 ኢትዮጵያውያንን በኢንዶኔዥያ ማሰልጠን መጀመሩን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። 
በፓርኮቹ ልማት ሳቢያ ከይዞታቸው ለሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው። በመሆኑም ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በመልሶ ማስፈር የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ተገቢውን ካሳና ምትክ ቦታ የመስጠትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች በተገቢው ወቅት እንዲፈፀሙላቸው ተደርጓል።  ከዚህ አኳያ ሁለት ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን። አንደኛው በአዲስ አበባ የቦሌ ለሚ አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በየፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያው ሳይክል በ130 ሄክታር መሬት ላይ የተመሰረተውና የስራ ዝግጁ የሆነው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። 
ከመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስንነሳ፤ ፓርኮቹን ለማልማት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 346 አባዎራዎች የተማላ መሰረተ-ልማት ያለው ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ተደርጓል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን በማህበር አደራጅተው እንዲያቋቁሙ ለማድረግም በእንስሳትና በእንስሳት ተዋፅኦ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠረላቸው መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ። 
የሃዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክም በልማቱ የተነሱ 186 አባዎራዎች ከክልሉ መንግስትና ሃዋሳ ከተማ መስተዳድር ጋር በመሆን ምትክ የመስጠት ስራ ተከናውኗል። በልማቱ ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተማ አስተዳደሩ ወደ 200 የሚጠጉ ቤቶችን ገንብቶ ሰጥቷል። በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ ሰፊ ቦታ ያላቸውና ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦችም መንግስት ባቀረበው የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ ሆነው ቤት የመገንባት ስራውን እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ከመቀሌ፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማና ሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች በልማት የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እስካሁን በተገኙት ተሞክሮዎችን በመቀመርና በተሻለ ውጤት በማስፋት የመልሶ ማስፈሩ ስራ ይከናወናል። 
እንግዲህ እነዚህ ተግባራት የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር ለልማት የሚነሱ ዜጎች ተመጣጣኝና ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ተገቢው ምትክና ካሳ በመንግስት በኩል ተፈፃሚ እየሆነላቸው መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታም ዜጎች ለልማት ተነሺ ቢሆኑም፣ ከሚካሄደው ልማት በየደረጃው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የሚያሳይ ይመስለኛል።
ያም ሆኖ ግን ከሀገራችን የልማቱ ጀማሪነትና ስራው ከሚጠይቀው በጀት አኳያ ዘርፉ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሊኖሩት ይችላሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከዘርፉ ተግዳሮቶች ውስጥ፤ ልማቱን ለማረጋገጥ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና ግንባር ቀደም ባለሃብቶች በስፋት መሳብ የሚያስችል አቅም አለመኖሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና እነዚህን ችግሮች የተሻለ አቅም በመፍጠር፣ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግና ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እገዛ በማድረግ በሂደት ዘላቂነት ባለው ሁኔታ መፍታት የሚቻል ይመስለኛል። 
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሀገራችንና ህዝቦቿ መቻላቸውን የሚያሳዩበት ጅማሮች ስለሆኑ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ለውጦች እንዲመዘገቡ የበኩላቸውን እገዛ የሚያደርጉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን መደገፍ ያለበት ይመስለኛል—ይህን ስንከውን ሀገራችን በመጪዎቹ አስር ዓመታት በቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ ለመሆን የነደፈችውን ዕቅድ እንድታሳካ የዜግነት ድርሻችንን እንወጣለንና።