የአዲስ ምዕራፍ ስኬታማ ጅማሮ

 

 

ኢትዮጵያ ዕምቅ የአረቢካ ቡና ባለፀጋ አገር ናት። ሆኖም በዚህ ሀብቷ በሚገባት ደረጃ ገና አልተጠቀመችበትም። በዓለም ገበያ በዓመት በቢሊዮን ዶላር  የቡና ግብይት ይካሄዳል። ታዲያ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ቡና ከአምስት በመቶ አይበልጥም። ከዚህ የገበያ ዕድል የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች አይደለችም። በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ባለሃብቶችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ከሰሩ አገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ልታገኝ ትችላለች። ለዚህም እንዲረዳ የዓለም ወቅታዊ መረጃን በመጠቀም ምርትን በስፋትና በጥራት ለመላክ መረባረብ ያስፈልጋል። ቡና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛልና ትኩረት ማድረጌ ላያስገርም ይችላል።   

የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚል ሃሳብ በተስተጋባበት ወቅት እቅዱ የተለያዩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ያቀፈ ነበር። መንግሥት ህዝብን አስተባብሮ በ2003 ዓ.ም  እጅግ የተለጠጠውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  ትግበራ ሲጀምር በበርካታ ሰዎች ዘንድ መጠራጠርን ፈጥሮ ነበር። “ይህ እቅድ ከፍተኛ የፋይናንስና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቅ በመሆኑ የቀን ቅዥት ካልሆነ በስተቀር ይተገበራል ተብሎ አይታሰብም።” በሚል የደመደሙ ወገኖችም አልጠፉም።

መንግሥት በበኩሉ “እቅዱ የተለጠጠ ግን ደግሞ የሚቻል ነው” የሚለውን ሃሳብ ለማስረጽ ተንቀሳቅሶ ነበር። በአገሪቱ ያለውን የግብርና መር ኢኮኖሚ በኢንዱስትሪ ለመተካት የሚያስችል መሠረት ለመጣል እቅዱን መተግበር አማራጭ የሌለው የዕድገት ጉዞ እንደሆነም ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የማስገንዘብ ሥራ ተከናውኗል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የኃይል ማመንጫዎች፣ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የማኑፋክቸሪንግ ማስፋፊያ፣ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት፣ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ሌሎች በዚህ እቅድ ውስጥ ተካተዋል። በእቅዱ የታያዙት ሜጋ ፕሮጀክቶች ባለፉት ዓመታት የነበራቸውን አፈጻፀም መነሻ ላይ ከነበረው ድባብ በንጽጽር ሲታይ የልማት አቅጣጫው ትክክለኛነቱን ያሳያል።

ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ ፋይናንስና ጠንካራ የመፈፀም አቅም የሚጠይቁ ስለነበሩ አንዳንዶቹ ላይ ሥጋት ማጫራቸው የማያስገርም ቢሆንም አሁን ላይ ቆመን ወደኋላ መለስ ብለን ስናይ ግን ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች አፈጻፀማቸው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት  መከናወኑን እንገነዘባለን።  

አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለማፈላለግና ሌሎች ዝግጅቶችን ለማድረግ ሰፊ ጊዜን የጠየቁ ነበሩ። ከዚህ አንጻር ዘግይተው መጀመራቸው የግድ ነበር። እነዚህ ዓመታት ቀላል የማይባል የአቅም ግንባታ ሥራ የተከናወነባቸው፣  ቅድመ ዝግጅት የተካሄደባቸው፣ አቅም የተገነባባቸውና በቀጣይ ዓመታት ሥራውን በፍጥነት ለማከናወን የሚያስችል ስንቅ የተሰነቀባቸው ጊዜያት ነበሩ ማለት ይቻላል።

በአንዳንድ ሜጋ ፕሮጀክቶች መዘግየት ቢታይም የባከነ ጊዜ አልነበረም – ቀጣዩን  ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችል ቁመና ፈጥረዋልና። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት በርካታ ልምዶች ተቀምረዋል። አገር በቀል አቅምን  በማሳደግ ረገድም ቀላል የማይባል  ልምድና ተሞክሮ ተገኝቷል። ማንኛውም እቅድ በሚፈፀምበት ወቅት የተለያዩ ተግዳራቶች ማጋጠማቸው ነባራዊ በመሆኑ መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን በሚተገብርበት ጊዜ ያጋጠሙትን የተለያዩ ተግዳራቶች እንደየሁኔታው እየፈታና ጥሩ አፈጻፀም ያሳዩትን እያጠናከረ ተጉዟል።

በእነዚህ ዓመታት የሚያበረታታ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተከናወነ በመምጣቱ አገሪቱ በቀጣይ ለሚኖራት የልማት ጉዞ ከፍተኛ ግብዓት ሆኖ አገልግሏል። በአገሪቱ የሰፈነው አስተማማኝ ሠላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተነሳ የተለያዩ የልማት  አጋሮች በመንግሥት አፈጻፀም ላይ እምነት በማሳደራቸው የሚሰጡትን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ መጥተዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ሃብትም ሆነ ከውጭ የምታገኘውን የልማት ድጋፍ በባለቤትነት ስሜት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መርህ በመከተል በድጋፍ አጠቃቀም ተዓማኒነት መፍጠሯን የልማት አጋሮቿ ያረጋግጣሉ። አገሪቱ ለልማት ያላትን ቁርጠኝነትና እያስመዘገበች ያለችውን ስኬት ግምት ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ ለእርሻ ልማት፣ ለመንገድ ግንባታና ለኃይል ማመንጫ የሚውል ከፍተኛ በጀት ትይዛለች።  

በአገሪቱ የተፈጠረው የልማት ስኬት አሁን ላይ የአይቻልም መንፈስን በመስበር የሥራ ባህልን ማሳደግ ችሏል። በተለይ በአባይ ወንዝ ማንኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማካሄድ የማይታሰብ ተደርጎ ለዘመናት ሲታሰብ የነበረው አስተሳሰብ ዛሬ ላይ ተሰብሯል። አገሪቱ ማንኛውንም ዓይነት ነገር መፈፀም የሚያስችል አቅም እንዳላት በተግባር አሳይታለች። ኢትዮጵያ በየትኛውም የታዳጊ አገር የውስጥ አቅም ብቻ የማይተገበር ፕሮጀክቶችን መተግበር ችላለች።

ያለፉት ዓመታት የልማት ጉዞ ስኬት የሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን አንድ ከሆኑ የአገራቸውን ህዳሴ ማረጋገጥ እንደሚችሉ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ እና የጊቤ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የባቡር ሃዲድ ግንባታና የሌሎች ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻፀም ተስፋን የሚሰንቁ ሆነዋል። ይህ ሲባል አንዳንድ ፕሮጀክች ላይ የአፈጻጸም ችግር የለም ማለት አይደለም። የአፈጻጸም ብቃት ማነስ የሚስተዋልባቸው ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።  

ዛሬ በአገራችን የይቻላል መንፈስ ተፈጥሯል፣ አጠቃላይ መነሳሳትና ቁርጠኝነት በመጎልበት ላይ ይገኛል፣ በተግባር ውስጥ በመግባት እውነትም ይቻላል የሚለውን ማስመስከር ተችሏል። ያሉንን ሜጋ ፕሮጀክቶች በአንድ ማዕቀፍ ደምረን ስናይ አገሪቱ የያዘችውን የልማትና የለውጥ መስመር ትክክለኛነት መገንዘብ ያስችላል። አገሪቱንም ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል በተጨባጭ አሳይቷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብና  ከዚሁ ጋር የተያየዙ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥሩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ያሉና በአገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ትልቁን ቦታ የሚይዙ ናቸው፡፡  ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊያኖች ችለው አይተገብሩትም የተባለው ፕሮጀክት አፈጻጸም 54 በመቶ ደርሷል። በቀጣይም ህዝብና መንግስት ግንባታውን ለማጠናቀቅ  በቅርበት በመስራት  ላይ ናቸው።  የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት በአስተማማኝ ደረጃ በማረጋገጥ ለሌሎች አገራት ኃይልን በመሸጥ እየተደረገ ያለው ጥረትና የተጀመረው ጉዞም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የጥንካሬ መገለጫ  ነው ማለት ይቻላል።  

በዚህ ረገድ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን በማሳደግ የዜጎቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደምትገኝ ያለፉት ቅርብ ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ አረጋግጧል። ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን በይቻላል መንፈስ በጥሩ አፈፃፀምና አቋም ላይ ይገኛሉ። የአገሪቱ የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ በማልማት መሠረተ ሰፊ ርብርብ በማድረግ የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ለመጣል አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ይህ ጅማሮ  በቀጣይ ሁለንተናዊ ለውጥን በማረጋገጥ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ያላት አገር እንደምትሆን አያጠራጥርም።

ከተቀመጠው የአፈጻፀም መርሀ ግብር በላቀ ደረጃ የተከናወኑና ቀድሞ የተሳኩም አሉ። በተለይም በጤናው ዘርፍ የሚሊኒዬም የልማት ግቡን ዳር ለማድረስ ከተቀመጡ ግቦች የህፃናት ሞት ቅነሳ ቀድሞ የተሳካው ነው።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ እያስመዘገበች ያለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት በበርካቶች ዘንድ እማኝነትን አግኝቷል። ከእውቅናም አልፎ ኢትዮጵያ በየዘርፉ ባሳየቻቸው ስኬት ለሌሎች አገራትም አብነት ልትሆን ይገባል በሚል በአርአያነት እየተጠቀሰች ነው። ይህ እውነታ አገሪቱ በትክክለኛ የለውጥ ጎዳና ውስጥ እንዳለች ያመላክታል። ሌላው ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራም እና በጥቃቅንና አነስተኛ ልማትም ተስፋ ሰጪ ውጤት  ማስመዝገብ ተችሏል። ሁሉም ዜጋ በመረባረብ ችግሮቹን ማስወገድና ስኬትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ ይገባል።

በግብርናው ዛርፍ እየመጣ ያለው ዕድገት ለኢንዱስትሪው ዕድገት የሚኖረውን ሚና በማሳደግ የማኑፋክቸሪንግ ቁመናን ማጠናከር ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ይሆናል።  ባለፉት  ዓመታት ለኢንዱስትሪው መሪነት መሠረት ሊጥሉ የሚችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። ይህ የበለጠ ተጠናክሮና ጎልብቶ መሄድ ይችል ዘንድ ገና ሰፊ ጥረት ይጠይቃል። ዛሬ "አይቻልም" የሚለው መንፈስ የተሰበረ ቢሆንም እስካሁን የተገኘውን ስኬት የበለጠ ሙሉ ለማድረግ አሁንም ወሣኝ ሥራዎች መኖራቸውን ተገንዝበን መረባረብ እንጂ የሚያዝናና ደረጃ ላይ አይደለንም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት  የጉዞዋን መሠረት ለማረጋገጥ በሚያስችል ሂደት ላይ ነች። በተለይ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በሌሎችም ዘርፎች እያጋጠሙ ያሉ ተግዳራቶችን በማስወገድ እሴት ፈጣሪ የኢንዱስትሪ መስኮች ላይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ላይ ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ሥራ ይጠብቀናል፤ በስኬት ውስጥ ሆኖ ብዙ ተግዳሮች ያሉበት የልማት ጉዞ በመሆኑ ስኬቱን ሙሉ ለማድረግ አሁንም በይቻላል መንፈስ ርብርብ  ልናደርግ ይገባል።

በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ መሠረት ያደረገና በሂደት ወደ ኢንዱስትሪ መር እየተሸጋገረ ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን ለመወጣት የሚያስችለውን አቋም እየተላበሰ ግብርናውም በተሻለ ዘይቤ ዕድገቱን እያረጋገጠ እንዲሄድ በሚደረገው ማዕቀፍ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጡ እውን እየሆነ ይሄዳል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ የሜጋ ፕሮክቶቹ ትርጉም ከፍተኛ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብና እያንዳንዱ አካል እንደ በኩር ልጅ ሊያያቸው ይገባል። ስኳርን አንድ ቦታ፣ ባቡርን ሌላ ቦታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሌላ መልክ፣  የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በተለየ ደረጃ በማስቀመጥና በተበታተነ መልክ በማሰብ ሳይሆን ሁሉም ፕሮጀክቶች ተያይዘው የአገራችን ትራንስፎርሜሽን ከማረጋገጥ አኳያ የሚኖራቸውን መሠረታዊ ፋይዳና አጠቃላይ መስተጋብሩን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች በጠቅላላ አገራዊ ዕድገታችን ውስጥ ወደ ብልጽግና ለመምራት ትልቅ መሠረቶቻችን  ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ እየተገነቡ ባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች አማካይነት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተፈጠረ ይገኛል። ለአርሶ አደሩ የግብርና ትራንስፎርሜሸን የሚያመጣ ትልቅ የቴክኖሎጂ  አቅርቦትና ትውውቅ ፈጥሮለታል። የግብርና ምርታማነትና ዕድገት በራሱ እሴት እየጨመረ ለኢንዱስትሪው ግብዓት በመሆን ላይ ይገኛል። ኢንዱስትሪው በግብርናው ላይ ተመስርቶ የአገሪቱ  ምጣኔ ሀብት በኢንዱስትሪው መሪነት እንዲረጋገጥ ግብርና ትልቅ ሚና ይጫወታል። ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ለመዋቅራዊ ለውጡ ለኢንዱስትሪ መሪነት ትርጉማቸው የላቀ በመሆኑ በህዳሴ ጉዞ  ውስጥ ቦታቸውን መመዘንና ለስኬታቸውም  የድርሻችንን መወጣት የግድ ይላል።

ይህ የስኬት ጉዞ የሚሊዮኖችን ሕይወት የለወጠ የመሆኑን ያህል የጠላቶቻችንን ቅስም የሰበረ ጭምር ነው። ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቅማ ልማቷን እንዳታፋጥን በተለያየ መልክ ለማደናቀፍ ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አገራትም ሆኑ ቡድኖች እሬት…እሬት እያላቸውም ቢሆን ይህን ሐቅ ለመቀበል ተገደዋል። እንደ ግብጽ የመሳሰሉ አገራት የአባይ የውኃ ሃብታችንን ተጠቅመን እንዳንለማ ለዘመናት የዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳናገኝ ሲቀሰቅሱብን ኖረዋል። እኛም አይቻልም በሚል አስተሳሰብ በመሸበብ ተጠቃሚነታችን ሳይረጋገጥ ዓመታት ገፍተናል።

ይህ ዕርዳታን የማከላከል ዘዴ አሁን ላይ የማይሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይ ባለፉት 14 ዓመታት ወዲህ የተገኘው የምጣኔ ሀብት ዕድገት በራስ አቅም ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን መገንባት ከሚያስችል ቁመና ላይ አድርሷታል። የውጭ ድጋፍ ባይገኝ ለሕዝባችን የሚጠቅም ልማት በሕዝብና መንግሥት  አቅም መገንባት የሚቻልበት ደረጃም ላይ ተደርሷል። የሜጋ ፕሮጀክቶች በስኬት መጠናቀቅ ደግሞ በአገሪቱ ሌላ አስተማማኝ መሠረት ያለው ምዕራፍ እንደሚፈጥር ይታመናል። በመሆኑም የጀመርናቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ከዳር ለማድረስና የአገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ያደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል።