ስለሃገራችን ሰላምና ልማት ጎልተው የወጡ ነጥቦች

     

ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ሙሉ ቀን ተሰይሞ በዋለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከቀትር በኋላ የነበረው ፕሮግራም በምክር ቤቱ የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት በፕሬዚዳንቱ የቀረበውን የመክፈቻ ንግግር አስመልክተው ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት ማብራሪያና በዚያ ላይ በመመሥረት ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት መልስ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሰጧቸው ማብራሪያዎች መካከል ከሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ከሃገራችን ሰላምና ልማት ጋር የተያያዙትን እና ወሳኝ የሆኑትን ነጥቦች መመልከትና ማስታወስ ስለህዝብ ተሳትፎ ጠቃሚ ይሆናል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ውሏቸውም ከሰጡት ማብራሪያ መካከል ስለሃገሪቱ የመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ የሆነውና የምርጫ ስርአትን የተመለከተው ነው። 
የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት የሚባለው በዓለም ላይ ካሉት ሦስት የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ አገራችን በመረጠችው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይህን የምርጫ ሥርዓት ላለፉት አምስት ምርጫዎች ስንጠቀም ቆይተናል፡፡ በዚህ ሥርዓት የአብዛኛው መራጭ ሕዝብ ውክልና ሲኖረው አነስተኛ ድርሻ ያለው ሕዝብ በምክር ቤት ውክልና የለውም ማለት ነው። 
በማለት ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ይህንን ሥርዓት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በጥናት ሲመረምረው መቆየቱን ጭምር ለምክር ቤቱ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
“ይህንን ከግምት በማስገባት የአገራችንን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ውክልና በማረጋገጥ፣ እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴን በተሻለ ለማሳደግ የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን በመተግበር የምክር ቤት ውክልናን ማሳደግ አለብን” ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም አሳውቀዋል፡፡ በዚህ አግባብ ደግሞ እንደአሸን በፈሉ ፓርቲዎቻችን ተበጣጥሰው ሜዳ ይቀሩ የነበሩ ድምጾች ዋጋ ስለሚኖራቸው ምክር ቤቱ ጥሩና ለሃገር ጠቃሚ የመሟገቻ መድረክ ይሆናል ማለት ነው።
ሌሎች ሥርዓቶች በማለት ከጠቀሷቸው የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓትና የአብላጫ ድምፅ ውክልናን ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን ዕውን ማድረግ ነው። ይህም የገዢው ፓርቲ የቤት ስራ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎችንም የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅና ለድርድር ልባቸውን እና ቤታቸውን ክፍት እንዲያደርጉ የሚያጠይቅ ነው።    
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በአገሪቱ ማጎልበት የመንግሥት አቅጣጫ መሆኑን፣ በተጨማሪም በሕጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር ሕጎችን የማሻሻልና ካስፈለገም የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት እንደሚሠራ ሲያረጋግጡ በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርአት ላይ ያገባናል የሚሉ ተቃዋሚዎችም እንደተለመደው በጭፍን ከመቃወምና ስልጣን ከመጋራት አባዜ ተላቀው በዚህ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ ስለሚያስችላቸው ፖሊሲ ቢያስቡ ጠቃሚም ተገቢም ይሆናል፡፡
ሌላውና በዚህ ፅሁፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚል ሚዛን ደፍቶ የተገኘው የጠቅላይ ሚንስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከተው ማብራሪያ  ነው። አዋጁን በተመለከተ አንዳንዶች ለማነወር ቢሞክሩም በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ የነበረውን አደጋ ሙሉ በሙሉ መቀነስ መቻሉን እያየን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም ለምክር ቤት አባላቱ ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። በአዋጁ ምክንያት ተሽሽለዋል ያሏቸውን የፀጥታ ጉዳዮች ከጠቀሱ በኋላም፣ የአዋጁን አንዳንድ ድንጋጌዎች ማላላት፤ ከተቻለም የበለጠ መቀነስ እንደሚቻልም ፍንጭ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለይም የውጭ ዲፕሎማቶች ሳይፈቀድላቸው ከ40 ኪሎ ሜትር ራድየስ ውጪ እንዳይጓዙ ገደብ የተጣለው ድንጋጌ በቅርቡ ሊነሳ እንደሚችልም መጠቆማቸው የአዋጁን ትክክል የነበረ መሆንና ሃገሪቱን ማረጋጋት የቻለበትን ደረጃ የሚያመላክት ነው፡፡
በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ቀውስ ውስጥ ዓብይ ክስተት ከነበረውና በምክር ቤት አባላት ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮንና ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች ላይ የተቃጣው ጥቃትን የተመለከተውም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይም በዋሽንግተን ያለውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጨምሮ በአውሮፓና በአውስትራሊያ የሚገኙ ሚሲዮን ጽሕፈት ቤቶች በትውልደ ኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ስለመወረራቸውና ጥቃት ስለማስተናገዳቸው፣ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ስላለው ዕርምጃ አቶ ኃይለ ማርያም ማብራሪያ መጠየቃቸውም ሆነ መስጠታቸው ተገቢና ወቅታዊ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ሚሲዮኖች ከሚገኙባቸው አገሮች መንግሥታትና በአዲስ አበባ መቀመጫቸው ከሆኑ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር መንግሥት መወያየቱንና ግልጽ አቋሙን ማሳወቁ ትክክለኛና ወቅቱ የሚጠይቀው ውሳኔና የሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በሚሲዮኖችና በቆንስላዎች ላይ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦችን ባሉባቸው አገሮች ሕጎች መሠረት በመክሰስ ተጠያቂ ለማድረግ መንግሥት ጠበቃ መቅጠሩ ለሉአላዊነታችን መንግስት ያለውን ቦታና ይልቁንም በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያለንን ቦታ የሚያመላክት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ሲያረጋግጡም ‹‹ከሁሉም አገሮች ጋር ከመነጋገራችንም በላይ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥበቃ እንዲያጠናክሩ በግልጽ አሳስበናቸዋል፡፡ እኛ የእነሱን ኤምባሲዎች ለራሳችን ተቋማት ከምናደርገው በላይ ጥበቃ እያደረግንላቸው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እነሱ የእኛን ተቋማት በአግባቡ የማይጠብቁ ከሆነ እኛም የእነሱን እንደማንጠብቅላቸው ጨምረን ገልጸንላቸዋል፤›› በማለት የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ግብጽንና ዴያስፖራውንም የተመለከተው ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ከነበሩት ውስጥ ሊመደብ የሚገባው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የግብፅ ጣልቃ ገብነትን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብፅ መንግሥት ግልጽ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በጣልቃ ገብነት የተጠቀሱት ተቋማት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት በአገሩ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን እንዲቆጣጠር የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያም የሰከነ ኃላፊነት የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን በማከናወን፣ ተገቢውን ሥራ ለመቀጠል መወሰኗ ስለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የተሳካ አፈጻጸም ተገቢነት የሚኖረው መሆኑ አያከራክርም፡፡
በውጭ የሚኖሩ ጽንፈኛ የዳያስፖራ አካላትም ኢትዮጵያን ለመበታተን ያላቸውን ሴራ በግልጽ ሳያፍሩ በማንፀባረቅ ላይ መሆናቸውንና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት መጋለጣቸውን  አስረድተው፣ የጽንፈኛ ኃይሎች መጥፊያ ቅርብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ መተንበያቸውም በምክንያትና መጥፊያቸው ቅርብ መሆኑን የሚያጠይቁ ተጨባጭ ማሳያዎች ስላሉ ነው።
የአገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ግብርናውን ማዘመን ዋናው ጉዳይ መሆኑ ሌላውና ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመስኖ ግብርናን ማስፋፋትና ግብርናን መሠረት ያደረጉ የግብርና ግብዓት የሚጠቀሙ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ትኩረት የሚሰጠው መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት ማፋጠን፣ የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብና የመጠጥ፣ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪውን ማስፋፋትና ማዘመንም የሁለተኛ ዕቅድ ዘመን ልዩ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም በምክር ቤቱ ላይ ከተወሱት እና ሃገራችን ከምትገኝበት ደረጃ አኳያ ተገቢነት ካላቸው ቁም ነገሮች ውስጥ የሚካተቱት ናቸው፡፡ ክልሎች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ድርሻ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጻቸው ይታወሳል፤ ለዚህ እንዲረዳም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተዘረጋው የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንሲንግ ሥርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠልም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑም በጠቅላይ ሚንስትሩ ተመልክቷል፡፡      

ባጭሩ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ተኩረት ተሰጥቷቸው ውይይት የተደረገባቸው አንኳር ነጥቦች ስለሃገራችን ቀጣይ ሰላምና ልማት፣ አጠቃላይ እድገት አመላካችና ወሳኝ መሆናቸውን ልብ ልንልና ለተግባራዊነታቸውም ከመንግስት ጎን በመሆን ልንተጋ ይገባል።