የሰላምና መረጋጋቱ ፋይዳ

                                                                                 
በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚታወጀው ለህዝብና ለሀገር ሰላም አሳሳቢ የሆነ ድርስ አደጋ መኖሩ በተጨባጭ ሲረጋገጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሀገር ውስጥ ህዝቡ ለመብቱ መከበር ያነሳውን ህጋዊ ጥያቄ በመጥለፍ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማሳካት በማቀድ በህዝቡ ውስጥ ሰርገው የገቡት የውጭ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው የሆኑት የውስጥ ሀይሎች በጋራ በመቀናጀት በሀገሪቱ ልማትና እድገት በህዝቡም ሰላማዊ ኑሮ ላይ ከፍተኛ አደጋዎችን ደቅነው እንደነበር አስተውለናል፡፡ አሁን ሰላምና መረጋጋቱ ወደነበረበት ተመልሶአል፤ የመረጋጋቱም ፋይዳ በጉልህ መታየት ችሎአል፡፡
ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቓረጥ ወዘተ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡  ከዚሁ ጋር ተያይዞ  ብዙ ሺህ ዜጎች ሰርተው የሚያድሩበትን ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማቶች፣ የመንግስት ቢሮዎች፣ የግለሰብ ድርጅቶች፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች፣ የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች ጭምር እሳት እየለኮሱ አጋይተዋል፡፡ አውድመዋል፡፡
እቅዳቸው ያተኮረው ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ማሰናከል፣ ማጥፋት በተለይም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችንም ማስቆም ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ለዚህ ድርጊት በግንባር የተሰለፉት ኦነግና አክራሪው ኢስላም ጀዋር መሀመድ በፋይናንስ፣ በስልጠና፣ በስምሪትና በአማካሪነት በቅርብ የምትረዳቸውና የምታግዛቸው ግብጽና የኤርትራው የሻእቢያ መንግሰት መሆናቸው ቀደም ብሎ ቢታወቅም በተለይ  በአሁኑ ሰአት በተጨባጭ ማስረጃ ተረጋግጦአል፡፡
የኦነግ ዋና ጸሀፊ ግብጽ/ካይሮ የሚኖር ሲሆን በቅርቡም ጽንፈኛና አክራሪ የኦሮሞ ምሁራን ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ወደ ለንደን በመሄድ ባደረጉት ስብሰባ በኦሮሚያ ግዜያዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም መክረው በማጽደቅ ለእኛ ያልሆነች ኢትዮጵያ ሲያሻት ትበታተን፣ ትበጣጠስ እስከማለት ደርሰዋል፡፡
በሌላም ወገን ሀገሪቱን የሁከትና የትርምስ ማእከል ለማድረግ ስርአተአልበኛነት እንዲነግስ፤ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ፤ መንግስት መምራት/ማስተዳደር የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፤ በዚህም ሀገሪቱ የከፋ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ፣ እንድትፈርስ፣ እንድትበታተን፤ የእርስ በእርስ ጦርነት በጎሳዎች መካከል እንዲቀሰቀስ፤ በዘረኝነት ላይ የተመረኮዘ ቅስቀሳ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በማድረግ ይህ ቀረው የማይባል ተጨባጭ አደጋ በሀገሪቱ ላይ እንዲጋረጥ አድርገዋል፡፡ 
ይህን ሙሉ በሙሉ በመቀልበስ በጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች የተጠነሰሰውን ሀገር የማጥፋትና ንብረት የማውደም፣ ህዝብንም ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ የማድረግ አደጋን ለማስወገድ ብቸኛው መፍትሄ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በስራ ላይ ማዋልና ሁኔታዎችን መቆጣጠር ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ሀገርን ከተጋረጠ ጥፋት የታደገ፣ ህዝብንም ከስጋትና ከመጨነቅ ከሽብር ስጋትም ያወጣና ያላቀቀ፣ የተናጋውን ሰላምና መረጋጋት ወደ ነበረበት የመለሰ፣ የንግድ ልውውጡና ግብይቱ በሰላም እንዲቀጥል፣ የትምህርት ሂደቱም በሁሉም ቦታዎች በሰላም እንዲካሄድ ያስቻለ ስራ ተሰርቶአል፡፡
ሕዝቡም ይነዛ ከነበረው የተሳሳተ የፈጠራ፣ የሀሰትና የሽብር ወሬና አሉባልታ ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ከነበረበት ሁኔታ ተላቆአል፡፡ ሁኔታውን በግልጽ ለይቶ ባለማወቅና ባለመገንዝብ ግብጽ፣ ኦነግና እነጀዋር መሀመድ ተቀናጅተው በሰሩት ሀገር አውዳሚና አጥፊ ተግባር ተሳታፊ የነበሩ በተለያየ አካባቢ ውድመትና ጥፋት ያስከተሉ ወጣቶችም በድርጊታቸው በመጸጸት በይፋ ህዝብና መንግስትን ይቅርታ የጠየቁበት ሁኔታም ተፈጥሮአል፡፡ ተከስቶ የነበረው የሰው ህይወትና ንብረት መውደም ቆሞአል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖአል፡፡
ሌላው በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ቀውስ ውስጥ የጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎቹ ሴራ ያነጣጠረው ወደሀገር ውስጥ የገቡ ኢንቨስተሮች ሰላምና መረጋጋት የለም ብለው ጓዛቸውን ሸክፈው እንዲወጡ፣ ወደኢትዮጵያ ለመምጣት ያሰቡትም እንዳይመጡ፣ የቱሪስቶች ፍሰት እንዲቀንስ የተደገረው መሰሪ ሴራ ሲሆን ይሄንንም እኩይ አላማቸውን ህዝብና መንግስት በጋራ ርብርብ እንዲከሽፍ ማድረግ ችለዋል፡፡
የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር፣ በመንግስትና ህዝብ ስልጣን ያለአግባብ የመገልገልን ብልሹ አሰራር በተመለከተ የህዝቡን ጥያቄ መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ለመመለስ ሰፊና ጥልቀታዊ ተሀድሶ የተጀመረ በመሆኑ ምንም ለሁከትና ለብጥብጥ ቀዳዳ የሚከፈትበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
ይሄንን ክፍተት በመጠቀም አመች ግዜና ወቅት ነው አሁን ኢትዮጵያን ማተረማመስና መበታተን እንችላለን በሚል የተሳሳተ ስሌት ያለ የሌለ የፕሮፓጋንዳ ሀይላቸውን በሶሻል ሚዲያና በሌሎችም በመጠቀም አመጹ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲቀጣጠል ያደረጉትን ጥረት ህዝብና መንግስት አምክኖታል፡፡ የውስጥ ችግር የሚፈታው ህግና ስርአት ባለው መልኩ ህዝብና መንግስት በጋራ በየደረጃው በሚያደርጉት ውይይትና ምክክር እንጂ  ሀገር እንድትጠፋ በመፍቀድ አይደለም፡፡
ለዚህ ነው ህዝቡ የኦነግና የጀዋር መሀመድ፣ የግብጽና የሻእቢያ የተቀናጀ ሴራን በሚገባ በመረዳቱ እንቅስቃሴአቸውን በአጭር ግዜ ውስጥ እንዲገታ ያደረገው፡፡ ከየቦታው እያወጣም ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ ላይ የሚገኘው፡፡ በውስጥ ባሉ ቅሬታዎች ብሶቶች ተከስተዋል፡፡ ይሄ በውስጥ የሚፈታ ነው፡፡ መቼም ቢሆን በሀገር ህልውናና ደህንነት ላይ ድርድርና ንግግር የማያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደተለመደው ዳር ከዳር የውጭ ጠላቶችን ሴራ ለማምከን በአንድነት ጸንቶ ቆሞአል፡፡
ከእንግዲህ ለግብጽ፣ ለኦነግና ለኦብነግ፣ ለሻእቢያና ለግንቦት ሰባት ሴራና ደባ የሚንበረከክ ሀገሩን፣ ሰላሙን፣ ልማትና እድገቱንም አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚሉት የኦነግና የጀዋር መሀመድ ተላላኪዎች የፈጠሩትን ሁከት  በመንተራስ ግብጽ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስቆማለሁ ብላ ማሰብዋ አስቂኝ ነው የሚሆነው፡፡
የግድቡ ግንባታ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን እየገነባ ያለውም በራሱ ገንዝብ ነው፡፡ የግብጽን ዘመናት ያሳለፈ ምናልባትም ሺህ አመታቶችን ያስቆጠረ ጸረ ኢትዮጵያ ተንኮል የነበረውንም ትግልና ተጋድሎ መቼም የማትተኛ ሀገር መሆንዋን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመሆኑም ሁልግዜም ዝግጁ ሁኖ ይጠብቃል፡፡
ቢሆንና ቢልላት ኖሮ ለግብጽ የሚጠቅማት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ መሆንዋ ነበር፡፡  ኢትዮጵያ – የአባይ ውሀ ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀምበት የሰጠችን ጸጋ እንደመሆኑ መጠን የግብጽን ድርሻ በማይነካ መልኩ በጋራ ልንጠቀምበት እንችላለን – የሚል ጠንካራ እምነት ይዛ  በጋራ መድረኩ እየሰራች ያለች ሀገር ብትሆንም ግብጽ ኢትዮጵያን በአራቱም ማእዘናት የተለያዩ ሀይሎችን በማደራጀት ከጀርባ እየወጋች ያለች ሀገር ስለመሆንዋ በተደጋጋሚ በማስረጃ ታላላቅ የምእራቡ አለም ሀገራትና መንግስታት በተጨባጭ ማስረጃ ደርሰውበታል፡፡ የኢትዮጵያንም ሰላማዊና ወዳጃዊ አካሄድም የበለጠ ተረድተውታል፡፡ 
ግብጽ እየፈጸመች ባለችው ጸረ ሰላም ወንጀለኛ ድርጊት ወኪሎችዋን እያሰማራች የአንድን ሉአላዊ ሀገር ሰላምና መረጋጋት ለማወክ በምትፈጽመው አደገኛ ድርጊት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ ተቃውሞ ሊያጋጥማት እንደሚችል ይታመናል፡፡ ግብጽ አለም አቀፍ ህጎችንና የድርደር ውሎችንም በመተላለፍ ግለኛና ስግብግብ፣ ሁሉም የአባይ ውሀ ለእኔ ብቻ ይሁን በሚለው አቋሟ ባለቤትዋን ኢትዮጵያን ለመበቀልና ለማጥፋት የሄደችበት ርቀት እጅግ አደገኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላት የተረዳች አይመስልም፡፡
ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም በምታደርገው ያላሰለሰ ሴራ በሌላ ወገን አክራሪና አሸባሪ እስላማዊ ሀይሎች በአፍሪካ ቀንድ እንዲስፋፉ፣ አቅምና ጉልበት እንዲያገኙ ሰፊ መሰረትም እንዲኖራቸው በስውር እያደረገች መሆኑን አለም እየተመለከተ ነው፡፡ ግብጽ በአሁኑ ሰአት ከቢን ላደን ሞት በኋላ አልቃይዳን የሚመራው የአይመን አልዘዋሀሪ ሀገር መሆንዋ ይታወቃል፡፡ ይሀው ግለሰብ አልተሳካለትም እንጂ ከአልሻባብ ጋር ባላቸው ጥብቅ ትስስርና አጋርነት የተነሳ ለበርካታ ግዜያት በኢትዮጵያ ላይ የጅሀድ ጦርነት ማወጁ አይዘነጋም፡፡ 
የግብጹ ሙስሊም ብራዘርሁድ አክራሪ እስላማዊ ፓርቲ አሸባሪና አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች ከሆኑት በአለም አቀፍ አሸባሪነትም ከተመዘገቡት ከነአልሻባብ፤ አልቃይዳ፤ አይሲስ፤ ቦኮ ሀራምና ከአፍጋኒስታን ታሊባኖች ጋር የጠነከረ ግንኙነት እንዳለው ይታመናል፡፡ ስማቸው ቢለያይም አላማቸው አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ ፊልድ ማርሻል ሲሲ በሀገራቸው ላይ አደጋ ጋርጦአል በሚል በሙስሊም ብራዘር ሁድ ፓርቲ ላይ ጠንካራ እርምጃ ወስደው ቢመቱትም ድርጅቱ በውጭ በሚያደርገው አክራሪ እስላማዊ እምነትን ለማስፋፋትና በሸሪአ የሚመራ መንግስት በየሀገሩ ለመመስረት የሚያደርገውን እንስቃሴ ይቃወማሉ ለማለት አይቻልም፡፡
ውሎ አድሮ የሚገለጽ ምስጢር ቢሆንም ሲሲ በአሜሪካ የጦር ኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ባቀረቡት የመመረቂያ ቴሲሳቸው ላይ እስላማዊነትንና ወታደራዊነትን አዋህደው መምራት የሚፈልጉ ሰው መሆናቸውን የሚያመላክቱ ፍንጮች መኖራቸውን ለሳቸው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀው ለመውጋት ከሚታገሉ አሸባሪና አክራሪ እስላማዊ ድርጅቶች ጀርባ በስውር ሙሉ ድጋፍ በማድረግ በመተባበር ረገድ የግብጽ ደህንነት የለበትም ብሎ ማመን ፍጹም የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡
ሲሲ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ለከፍተኛው ሀላፊነት ያጫቸው በሌተና ጀነራልነት ማእረግ መከላከያ ሚኒስትር አድርጎ የሾማቸው በኋላም የፊልድ ማርሻልነት ማእረግ የተሰጣቸው በሙስሊም ብራዘርሁድ መሪዎች መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
ወደተነሳንበት እንመለስ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚታወጀው ለህዝብና ለሀገር ሰላም አሳሳቢ የሆነ አደጋ መኖሩ በተጨባጭ ሲረጋገጥ መሆኑን በመግቢያችን ጠቅሰናል።  በመሆኑም አዋጁ በማስፈለጉ ታውጇል። በመታወጁም ከፍተኛ ሰላምና መረጋጋትን ፈጥሯል። ይህ ይቀጥል ዘንድም አጠቃላይ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የዜግነት ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል