በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታዩ ለውጦች

መቼም ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤዋን ገና አላጣጣምነውም ፡፡አስከፊው ድህነታችን ቢንገዳገድም አልሞተምና ፡፡አዎ ድህነት ሳይጠፋ ምንም ቢሆን ሰላማዊ እንቅልፍ አይኖርም ፡፡አዎ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሰላም የናፈቀን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በመጥፎ አብነት የምንነሳ ህዝቦች ነበርን ፡፡ አሁን  እፎይታን ያገኘነው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ነው ፡፡ሰላማችንን አግኝተንም በጀመርነው ልማት ተስፋችን ብሩህ ሆኗል ፡፡ግን ምን ዋጋ አለው በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል እንዲሉ ከዓምና ጀምሮ ሰላማችንን ታወከ ፤ተናወጠ ፡፡ የበርካታ ዜጎቻችን ህይወት እንደዋዛ ተበላ ፡፡ንብረት ወደመ ፡፡ይህም ኪራይ ሰብሳቢዎች ያመጡብን ጦስ ነበር ፡፡ የውስጥና የውጭ ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ኃይሎችም በእጅጉ ነበር የተረባረቡት ፡፡የአንዳንድ የዋህ ሰው በውሸትም በማጋነንም ለማደናገር የተቻላቸውን ሁሉ ፈጸመዋል ፡፡እነዚህ እኩያን ግን ዓቅም አልነበራቸውም እንጂ ፡፡ይሁንና መንግስት ችግሩን ለማቆም የነበረውን ህጋዊ  አካሄድ በሙሉ ስለተሟጠጠበት ከአንድ ወር በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማውጣቱ ይታወቃል ፡፡በዚሁም የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታን አግኝቷል ፡፡የተቃጠሉት ቤቶች በህዝቡ ትብብር እየተገነቡ ናቸው ፡፡ፋብሪካዎችም እንደዚሁ መለስተኛ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ስራ ገብቷል በብዙ ሺዎች ያለ ስራ ተበትነው የነበሩት ወገኖችም ስራቸውን ቀጥሏል ፡፡ ከጥቂት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ፋብሪካዎች በስተቀር ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ 3 በመመሪያ ቁጥር 1 አንቀጽ 12 አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ከአሁን ቀደም በወጣው መመሪያ ላይ ተጥሎ ከነበሩ ክልከላዎች ውስጥ አንዱ ሙሉ በሙሉ ሁለተኛው ደግሞ በከፊል አንስቷል ፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ 3 በመመሪያ ቁጥር 1 አንቀጽ 12 ያልተፈቀዱ አልባሳትን ይዞ መገኘት ወይም በቤት ውስጥ ማስቀመጥ በአዋጁ ተከልክሎ ነበር ። ይህ ግን ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ህዝባዊ ባህሪ ያለው ነውና ክልከላው እንዲነሳ ነው ያደረገው ፡፡

አዎ አሁን የህግ አስከባሪዎችን የደምብ ልብስ ይዞ መገኘት ወይም በቤት ውስጥ ማስቀመጥን አስመልክቶ የተደረገው ክልክላ በመመሪያ ቁጥር ሁለት ተነስቷል ።

ይህም የሆነው ከዚህ ቀደም በሻዕቢያ ወረራ የተሳተፈው ህዝብ በርካታ ነው ፤ይዞት የመጣ ልብስ አለ ፡፡ከመከላከያ በክብር የተቀነሰ ፣በጥሮታና በሌላም ምክንያት ከሰራዊቱ የተገለለ ሊኖር ይችላል ፡፡ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበረ ለወንድሙ ወይም ለዘመዱ አበርክቶ ሊሆን ይችላል ፡፡ለዚህም ነው  ኮማንድ ፖስቱ ከህዝብ ጋር በተለያዩ ክልሎች  በተፈጠሩ መድረኮች የተወያየው ፡፡ በዚሁም የህዝቡን ቅሬታዎች አዳመጠ ፡፡ሁሌም በገበያ ፣በስራ ፣በማንኛው ስፍራ ላይ ተላብሶ ይታይ ነበር ፡፡እናም አዋጁ ከከለከለው በኋላ ህዝቡን አስጨንቆታል ፡፡በቤቱ ያስቀመጠ ወታደራዊ ደንብ ልብስ የት ያስቀምጠው ፡፡ያቃጥለው? ታዲያ የት ይጣለው ? ይህ ደግሞ ነውር ነው  አይደረግም ፡፡ስንት ጀግንነት የተፈጸመበት ደንብ ልብስ ፍቅር አለው ፡፡ለዚህም ነበር ኮማንድ ፖስቱ በደስታ የተቀበለው ፡፡

የኮማንዱ ፖስቱ ሴክሬታሪያት እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ “ ይህ ሊሆን የቻለው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ የህብረተሰብ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት የደንብ ልብሱን በየቤታቸው አስቀምጠው የሚገኙ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት እንደ መደበኛ ልብስ የሚጠቀሙበት መሆኑን በማንሳታቸው ነው” ብለዋል።

ከአሁን ቀደም በወጣው እና ባለፉት ሶስት ሳምንታት በተተገበረው መመሪያ ላይ ማንኛውም ሰው የጸጥታ ሀይል አስከባሪ የደምብ ልብስን ይዞ ቢገኝ፣ ቢለብስ፣ ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ቢሰጥ ወይም ደግሞ ቢሸጥ በህግ እንደሚቀጣ ነበር የሚደነግገው ፡፡

በዚሁ ስር ግን ማንም ሰው ሊያስተውል የሚገባው የመከላያ ልብስን ጨምሮ የህግ አስከባሪዎች ደንብ ልብስ መልበስ፣ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠትና መሸጥ አሁንም ክልክል መሆኑ ነው ፡፡

 ሁለተኛው ክልከላ የተነሳበት ያለ ፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ነው።

ከአዲስ አበባ ከተማ በ40 ኪሎሜትር ዙሪያ ያለፍቃድ የሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ለደህንነታቸው ሲባል የተደረገው ክልከላን ሙሉ በሙሉ  ተሰርዟል ። ይህም በሀገራችን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው ፡፡ምክንያቱም አሁን በሀገራችን የቱሪስቶች ፍሰት እየጨመረ ይገኛል ፡፡የውጭ ኢንቨትሮችም እንደዚሁ ፡፡በተለያዩ የመሰረተ ልማቶች ግንባታ የሚንቀሳቀሱ ነጮችም አያሌ ናቸው ፡፡ ይህ ደግሞ አገራችን በውጭው ዓለም የነበራት መልካም ገጽታ ወደ ነበረበት የሚመልስ መልካም ዜና ነው ፡፡የኮማንዱ ፖስቱ ሰክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ አዲስ የምስራች ይዘው የመጡትም ይህ ብቻ አልነበረም ፡፡

 

ካሁን በፊት በአንቀጽ 4 ያለፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ተደንግጎ ነበር ፡፡ይህም በመመሪያው ቁጥር 1 አንቀጽ 18 ላይ  “የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለራሱ ደህንነት ሲባል ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅ አለባቸው” የሚል ነበር ፡፡ አሁን ይህ ክልከላ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል።

ምክንያቱ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ በሀገሪቱ የነበረው የሰላም እና የደህንነት ስጋት እና አሁን ያለው የተለያየ መሆኑን መሆኑን ነው የተመለከተው ፡፡ ሀገሪቱ በአንፃራዊነት ወደ ሰላም እና መረጋጋት በመመለሷ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል ቢንቀሳቀስ የሰላም እና የደህንነት ስጋት ስለሌለ ክልከላውን ማንሳት አስፈላጊ ሆኗል ነው የተባለው ።

ሀገራችን እንደሚታወቀው በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ ናት ፡፡በሰፋፊ ኢንቨስትመንትና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚዘዋወሩ የውጭ ዜጎች አያሌ ናቸው ፡፡ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ እና በርካታ ድንቅ የሆኑ ታሪካዊ ፣ባህላዊ ፣ሃይማታዊና ጥንታዊ የቅርስ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል ፡፡ የዓለማችን ህዝብ ትኩረት እየሳበ በመምጣት ላይ መሆኑም እንደዚሁ  ፡፡ ሁሉም ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነው ፡፡ይህም ተከትሎ የቱሪስቶች ፍሰትም እየጨመረ ይገኛል ፡፡የውጭ ኢንቨስተሮችም እንደዚሁ ፡፡ለዚህም ነበር የመከላከያ ሚኒስትሩ ዲፕሎማቶች ለደህንነታቸው ሲባል ከአዲስ አበባ ከተማ 40 ኪሎሜትር ዙሪያ ያለፍቃድ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግደውን ድንጋጌ መነሳቱን ያሳወቁት ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመመሪያ ቁጥር ሁለት በተለያዩ እርምጃዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ነው የተገለጸው ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የጸጥታ አስከባሪው ኃይል ራሱን ለመከላከል ስለሚወስደው እርምጃ የሚመለከተው ነው።

ከዚህ ቀደም በወጣው መመሪያ ላይ “የድርጅት ጥበቃ እና ጸጥታ የማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በጦር መሳሪያና በስለት ሊፈጸምባቸው ከተቃጣ ራሳቸውን ለመከላከል እርምጃ ይወስዳሉ “ይላል።

አሁን በተሻሻለው መመሪያ ቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ የህግ አስከባሪዎች እና የድርጅት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ራሳቸውንና የራሳቸውን ንብረት ብቻ  አይደለም ከጥቃት የሚጠብቁት ፡፡ “የሚጠብቁትን ህብረተሰብና ድርጅት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ድርጊት በጦር መሳሪያ፣ በስለት፣ በኃይል ወይም በሌላ ማንኛውም ዘዴ አማካኝነት በህይወት፣ በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳይ የሚያደርስ ከሆነ ያን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ” በሚል ተሻሽሏል።

ከአሁን በፊት በነበረው መመሪያ ላይ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የህግ አስከባሪ አካላት ብርበራ ማከናወን ይችላሉ” የሚል ነው።

በመመሪያ ቁጥር ሁለት ላይ በብርበራ ዙሪያ ዝርዝር ሁኔታዎች ተካቶ ማሻሻያ ነው የተደረገው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ “ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካል ብርበራ በሚያደርግበት ጊዜ መታወቂያ የማሳየት እና ብርበራውን የሚያደርግበትን ምክንያት የማሳወቅ ግዴታ አለበት” የሚለው ተካቷል።

ይህ ብቻ አይደለም ፤ “ብርበራው የሚካሄድባቸው ሰዎች የብርበራ ሂደቱን እንዲከታተሉ መፍቀድ እና በርባሪው አካል ብርበራውን በሚደረግበት ወቅት የአካባቢው ፖሊሶችና የማህበረሰቡ ተወካዮች በታዛቢነት እንዲከታተሉ የማድረግ ግዴታ አለበት ”የሚለውም በማሻሻያው ተካቷል። ይህም የሆነው አንዳንድ አስመሳይና አጭበርባሪ ግለሰቦች ህብረተሰቡን ሲያታልሉ በመገኘታቸው ነው የኮማንድ ፖስቱ ሰክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ያስገነዘቡት ፡፡

አዲስ በወጣው መመሪያ ቁጥር ሁለት አንቀጽ 7 ላይ “ሚስጥር መጠበቅ” የሚል አዲስ ድንጋጌም ተካቷል ።

በዚህም “ማንኛውም በብርበራ እና በፍተሻ ላይ የተሳተፈ የህግ አስከባሪ አካል ብርበራ እና ፍተሻውን ከማካሄዱ በፊትም ይሁን በኋላ ያገኛቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው አካል ከማሳወቅ ውጭ መረጃዎቹን በሚስጥር የመያዝ ግዴታ አለበት” ተብሏል። ይህም የተገኘው መረጃ ሚስጢር ለቤተሰብ ይሁን ለታማኝ ለጓደኛ በፍጹም አሳልፎ መስጠት በፍጹም አይፈቀድምና  ነው ፡፡

በተረፈ በአንቀጽ 8 የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ላይ በሁለተኛው መመሪያ ከተነሱት ክልከላዎችና ከተሻሻሉት እርምጃዎች በስተቀር ከዚህ በፊት የወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2009 ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ህዝቡ አሁን በጀመረው ትብብር ሰላሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ካስጠበቀ አዋጁ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊያበቃ ይችላል ፡፡ካልሆነ ግን ተመልሶ ችግሩ የሚያገረሽበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሊራዘምም ይችላል ፡፡ ለምን ቢሉ እንደሚኒስትሩ አባባል ገና አሁን ላይ ሆኖ የሚሆነውን መገመት ስለማይቻል ፡፡ ዘላለማዊ ሰላም ለእናት ሀገራችን !