ለበለጠ ለውጥ መትጋት

          ኢህአዴግ አዲስ ለውጥ ለማምጣት በገባው ቃል መሰረት እነሆ በአይነቱ አዲስና ያልተለመደን ከዚህ በፊትም ያልነበረ መንግስታዊ አወቃቅር ይፋ አድርጎአል፡፡ በርካታ የሚኒስትርነት መንግስታዊ ሹመቶችን ለሀገሪቱ አንጋፋ ምሁራን ሰጥቶአል፡፡ ሹም ሽሩ በየደረጃው ከላይ እንደጀመረ ሁሉ እስከ ታችኛው አካል ድረስ እንደሚወርድ ይጠበቃል፡፡ ይሄ በጎና ቀና ጅምር በሀገሪቱ የተጀመረውን ግዙፍ ልማትና የእድገት ለውጥ ለማስቀጠል ወሳኝ ድርሻ ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡

ምሁራኑ በየሰሩበት የስራ ዘርፍ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ጉልህና የሚጨበጥ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በሙያቸውም አንቱ የተባሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ህዝቡ የሚታይ ተጨባጭ ለውጦችን ማየት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም መነሻ ምክንያቱ በየደረጃው ከላይ እስከ ታች ህዝብና መንግስት ይሰራሉ ብሎ አምኖ  በሃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው ሰዎች በመልካም አስተዳደር፣ በሙስናና ምዝበራ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በመሬት ቅርምት ችግር ውስጥ መውደቃቸው ብልሹ አሰራር በመስፈኑ ይህም ህዝብን ያስከፋና ያስመረረ ሁኔታ በመፍጠሩ ነው፡፡ ይህ በህዝቡ ውስጥ ምሬትና መከፋት ያስከተለውን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት ኢህአዴግ በውስጡ ጥልቀታዊ ተሀድሶ እንደሚያደርግ ቀደም ብሎ ባስታወቀው መሰረት አሁን በሚታይ ደረጃ የለውጡ እንቅስቃሴ ተጀምሮአል፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ ፈርጀ ብዙ ሲሆን የማይዳስሰውና የማይሸፍነው መስክ የለምም ተብሏል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉና የህዝብን ይሁንታ በሚያረጋግጥበት ደረጃ ቀጣይ ስራዎችን ይሰራል፡፡

የሚኒስትርነት ቦታዎች ቀድሞ በድርጅት አባላት በተለይም የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ ወዲያው የሚሰጥ ሹመት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ስርነቀል የአሰራር ለውጥ በማድረግ ይህ ከፍተኛ የመንግስታዊ ሀላፊነት ቦታ የፓርቲ አባል ባይሆኑም ብቃቱና ክሂሎቱ ላላቸው በትምህርት ደረጃቸውም የላቀ ደረጃ ለደረሱት የበለጠም ሀገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን ለውጥ ወደፊት እንዲራመድ የማድረግ ብቃቱ ላላቸው ዜጎች እንዲሰጥ መደረጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡

ሹመቱ በዚህ መመዘኛና መስፈርት መሰረት በበቂ ጥናትና ፍተሻ የተደረገ ሲሆን ይሄው ከፍተኛ መንግስታዊ ሀላፊነት የተሰጣቸው ተሿሚዎች በየተመደቡበት ቦታ ስርነቀል ለውጥ በማምጣት የላቀ ስራ እንደሚሰሩ ታምኖበታል፡፡ ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ ያለች እንደመሆንዋ መጠን በብዙ መስክ ተጨማሪ ሀገራዊ ስኬቶች የያዙ የድል ለውጦች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል፡፡ እንደተለመደው ሁሉንም ነገር በመቃወምና በማጥላላት የሚታወቁት አክራሪ ተቃዋሚዎች ሹመቱን ለመንቀፍ ሰከንድ አልወሰደባቸውም፡፡

በሀገር ውስጥ ያሉት ተቀዋሚዎች ድጋፋቸውን በመስጠት ከተሾሙት ምሁራን የሚጨበጥ ለውጥ እንደሚመጣ ሲገልጹ የዳያስፖራውና በሀገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ሲነቅፉ ተደምጠዋል፡፡ እስቲ ግዜ ሰጥተን ስራቸውንና የሚያመጡትን ለውጥ እንመልከት ለማለት እንኩዋን አልደፈሩም፡፡ የአብዛኛው ህዝብ እምነት ለውጥና መሻሻል ያመጣሉ የሚል ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት ሁከትና ብጥብጥ ነግሶ ከነበረበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ የበለጠና አስተማማኝ ሰለምና መረጋጋት ሰፍኖአል፡፡ በየትኛውም ክልል አዲስ አበባን ጨምሮ የመማር ማስተማሩ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተራመደ ነው፡፡ ሁከት፣ ግርግር፣ ረብሻ የለም፡፡ ተማሪዎች በሁሉም ደረጃ  ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በሰላም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

በውጭ ሀይሎች ከጀርባ መሪነት ኦነግና ጀዋር መሀመድን በመሰሉ አክራሪ ጽንፈኛ ሀይሎች አስተባባሪነት እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያው ጽንፍ የወጣ ሁከት፣ ግጭት ቀስቃሽነት፣ ዘረኝነት ላይ የተመረኮዘ፣ ለአብሮነት ጠንቅ የሆነ አስከፊ ቅስቀሳቸው ምክንያት አደፍርሰውትና አናግተውት የነበረው  ሰላም ዛሬ እንደቀድሞው በነበረበት ቦታ ተመልሶአል፡፡ ያደረሱት ጥፋትና ውድመት የሚታይ ጠባሳ ትቶ አልፎአል፡፡ የመንግስትና የህዝብ የግለሰቦችም ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰበት ንብረት ወድሞአል፡፡ ፋብሪካዎች  እርሻዎች ቀላልና ከባድ መኪኖች ህዝቡ የሚገለገልበት አምቡላንስ ጨምሮ ውድመዋል፡፡

ይህ አይነቱ ጸረ ልማት፣ ጸረ እድገትና ጸረ ህዝብ ድርጊት ተመልሶ እንዳይደገም የተጠናከረ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ በድሀ ሀገር አቅም ይሄ ሁሉ ንብረት እንዲወድም ሆን ተብሎ የተደረገው በግብጾች፣ በኦነግና ሌሎችም ተባባሪዎች ሴራ መሆኑን ህዝቡ በግልጽ አውቆታል፡፡ ሀገራችን ከድህነት ለመላቀቅ በምታደርገው ወሳኝ ትግል የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት እድገትና ልማት ለማጨናገፍ ህዝቡንም ወደስራአጥነት ለመለወጥ የተፈጸመው የንብረት ማውደም ወንጀል እንዲስፋፋ እንዲዛመት እነኦነግና ግብጽ ያደረጉት ጥረት ብዙም ሳይራመድ ሊገታ የቻለው በህዝቡ ርብርብ ነው፡፡

ድርጊቱን የፈጸሙትም በአደባባይ በመውጣት ለመንግስት እጃቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሀገር እያወደሙ ሀገሬ  ማለት ህዝብ ሰርቶ የሚኖርባቸውን ቤተሰቡን የሚያስተዳድርባቸውን ድርጅቶችና ተቋማት በእሳት እያጋዩና እያነደዱ ወገኔን ህዝቤን እወዳለሁ ማለት ከቶውንም አይቻልም፡፡ ሀገርንም ህዝብንም በመካድ ከጠላቶችዋ ጋር ተገዝቶ በመሰለፍ የሚፈጸም  በህግ በታላቅ የሀገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት ነው፡፡

በህዝቡ በኩል በየአካባቢው በየክልሉ ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከፍትህ ጉድለት፣ ከመሬት ቅርምት፣ ከሙስናና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙትን ችግሮች  አስቀድሞ በራሱ ጉባኤ የገመገመው ኢህአዴግ ችግሮቹን ለመቅረፍ በጉዳዩ ላይም የሞት የሽረት ትግል ለማድረግ የወሰነው በአስረኛው ጉባኤው ነው፡፡ ከጉባኤው መልስ ችግሩን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር የውይይት መድረኮች በመፍጠር በግልጽ በመነጋገር ጎልተው ባይታዩም  በየደረጃው እርምጃዎችን ወስዶአል፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር የትግራይ ክልል የአማራው ክልል የኦሮሚያም ክልል ህገወጦችና ሙሰኞች እንዲሁም በህዝቡ ላይ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግር አድርሰዋል ባላቸው ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል መራመድና መቅደም አልቻለም፡፡ ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው በራሱ በኢህአዴግ ብብት ውስጥ መሽጎ የሚገኘው ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል ቢሮክራሲውን በመጠለል አላነቃንቅ ማለቱን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ተደጋጋሚ ግምገማዎች ላይ ተቀምጠው በኋላም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የህዝቡን የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ በአክብሮት እንደሚመለከተው በመግለጽ በጥልቀታዊው ተሀድሶ አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥ፣ መንግስታዊ አወቃቀርና አደረጃጀቱን እንደሚፈትሽ፣ አዳዲስ ለውጦችን ይዞ እንደሚመጣ በመግለጽ ወደ ተግባራዊ ምላሽ ገብቶአል፡፡ በህብረተሰቡ የተነሳውን ጥያቄ በአቓራጭ በመጠቀም አጀንዳቸውን ለማሳካት ሲራወጡ የታዩት እነኦነግና ግብጽ የተቃውሞውን አድማስ ለማስፋትና ከመንገድ እንዲወጣ ለማድረግ በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ የሚመለስ ሁኖ እያለ መልኩን ለማስለወጥ የተኬደበት ሀገር አውዳሚ የጥፋት መንገድ ከህዝቡ ጥያቄ ጋር የሚያገናኘው ምንም አይነት ሁኔታ የሌለ መሆኑን ህዝቡ ራሱ ገልጾአል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ መብቴ ይከበርልኝ እንጂ ሀገር ለመበታተን ንብረት ለማውደም አይደለምና፡፡ ድርጊታቸውም ሆነ ጥረታቸው በራሱ በህዝቡ ተጋልጦ መክኖአል፡፡ በአሁኑ ሰአት በሁሉም ቦታዎች የተረጋጋ ሰላም ሰፍኖአል፡፡

ከላይ የተጀመረው የሹም ሽረት ለውጥ የህዝቡን ቅሬታና ብሶት በተገቢው መንገድ መመለስ በሚያስችልበት መልኩ በየደረጃው ይቀጥላል፡፡ ወደታችኛው የአመራር አካልም ይወርዳል፡፡ በመንግስት መስሪያቤቶች በተቓማት በመስተዳድሮች በክልሎች በዞን ክፍለከተማና በተለይም ዋናው የህዝብ ቅሬታና ብሶት መነሻ በሆኑት ከህዝቡም ጋር እለት በእለት በሚገናኙት ቀበሌዎች ውስጥም ስር ነቀል የሆነ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራርና አመራር እንዲኖር የሚደረግ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ጉዳዩን በቅርብ የመፈተሸ፣ ያሉትን ለውጦችና መሻሻሎች እንዲሁም ችግሮች ከስር ከስር እየተከታተለ እርምት እንዲወሰድ ሙሰኞችንና ጉቦ አፍቃሪዎችን የማጋለጡ ወሳኝ ሀላፊነት የህዝብና የህዝብ ብቻ ይሆናል፡፡ ህዝቡ ካጋለጣቸው የሚደበቁበት ዋሻ አይኖርም፡፡ አንደኛው የመቆጣጠሪያ መንገድ ህዝቡ ጉዳዩን ጉዳዬ ነው ብሎ በንቃት እንዲሳተፍ ማደረግ ነው፡፡ ኢፍትሀዊ አሰራርን አድልዎን መድልዎን ሙሰኝነትን ኪራ ስሳቢነትን ሳይፈራ ከታገለ የተሻለ አሰራርና አመራር እንዲፈጠር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ተኪ የሌለው ወሳኙ ሚናም የህዝብ ነው፡፡

የህዝቡን ቅሬታ ለመቅረፍ ችግርና ብሶቱንም ፈጥኖ ለማሰማት እንዲችል ለአሰራሩ ቀልጣፋነት እንዲያግዝ በየቀበሌው በየክፍለከተማው በየመስተዳድሩ የህዝብ ቅሬታ ተጨባጭ ቅሬታዎች የሚገለጹባቸው በሌላ የመንግስት ቅሬታ ሰሚ አካል ብቻ የሚከፈቱ አስተያየት መስጫ ሳጥኖች እንዲኖሩ ቢደረግ የበለጠ ውጤታማ የሆነ አሰራር ይፈጠራል፡፡ ችግሮቹንም በእንጭጩ ለመቅጨት ይረዳል፡፡ እንዲህ አይነቱን አካል ከህዝቡ ውስጥ በተውጣጡ ጨዋ፣ ታማኝ፣ መልካም ስነምግባር ባላቸው፣ በህብረተሰቡ የተከበሩና የተወደዱ ሰዎችን ከመንግስት አካል ጋር አቀናጅቶ ቢሰራበት ውጤቱ አመርቂ ይሆናል፤ ችግሮችን በፍጥነት  ለመፍታትም ያግዛል፡፡