ተስፋና ስጋት

የተጀመረው ጥልቀታዊው የተሀድሶ ለውጥ በጎና መልካም ጅምሮችን ይዟል፡፡ አዲሱ ሹመት ለሀገሪቱም ለህብረተሰቡም የሚጠበቀውን ታላቅና መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ዘንድ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ቆሞ ጸንቶም ሊያግዛቸው ሊተባበራቸው ይገባል፡፡ ሀገር የሚለወጠውና የሚያድገው እያንዳንዱ ሰው በተናጠልም ሆነ በወል በከፍተኛ ሀገራዊና ብሄራዊ ፍቅር መስራት ሲችል ብቻ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ትልቁ ሀብቷ ዜጎችዋ ናቸው፡፡ አንድን ሀገር የሚለውጣት፣ የሚያሳድጋት፣ ከጥቃት የሚጠብቃት፣ ታላቅ ሀገርም የሚያደርጋት ህዝብ ነው፡፡ ሀገራችን ታላቅ ተስፋ የሰነቀች ሀገር ስትሆን የዛኑም ያህል ልንመክታቸው የሚገቡ ስጋቶች አሉ፡፡

ብሄራዊ ፍቅር ያለው ህዝብ ሀገሩን ያስቀድማል፡፡ ለሀገሩ ክብር ማንኛውንም መስዋእትነት ይከፍላል፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱ ሀገር አፍራሽ ሴራዎችን ደባዎችን ያመክናል፡፡ የትኛውንም በሀገሩ ላይ የሚነሱ ትንኮሳዎችን ጥቃቶችን ወረራዎችን በግንባር ይመክታል፡፡ የህይወት መስዋእትነት እየከፈለ፤ ለተተኪው ትውልድም ሰላምና መረጋጋት ያላት ብሄራዊ ክብርና ነጻነትዋ የተከበረችና የማትደፈር ሀገር ያስረክባል፡፡

የእኛ አባቶች፣ አያቶች፣ ቅድመ አያቶች በአንድነታቸው ጸንተው ምንም አይነት የውጭ ሀይሎች ከፋፋይ ሴራ ሳይበግራቸው መንፈሳቸው ሳይላላ ችግሩን ሁሉ ተጋፍጠው  በአጥንታቸው ክስካሽና በደማቸው ፍሳሽ ሳትደፈር ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያ ነው ያስረከቡን፡፡ ዛሬ ላይ ያለውም ትውልድ ለነገ ልጆቹ ሊያስረክባቸው የሚገባው በሁሉም መስክ ያደገች፣ የበለጸገች፣ የተከበረች ኢትዮጵያን ነው መሆን ያለበት፡፡

ተረት ሳይሆን ጥንት በአክሱም ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ ሀያልና ገናና፣ ቀደምት ስልጣኔ የነበራት፣ ቀይ ባህርን ተሻግራ እስከ የመንና ሳኡዲ አረቢያ ድረስ ትገዛ፣ ታስተዳድር፣ ትመራ የነበረች ሀገር እንደነበረች ተጽፈው የሚገኙ ድርሳናት ይዘክራሉ፡፡ ከሁሉም ቀድማ የባህር ሀይል፣ መደበኛና ተከፋይ ሰራዊት፣ መገበያያ ገንዘብ፣ የራስዋ ፊደልና የስነ-ጽኁፍ ሀብት ሁሉ ያላየ ነች፤ የሮማው ባይዛንታይን ኢምፓየር በገነነበት ዘመን የእኛም ሀገር ታላቅና ገናና ነበረች፡፡

ጥንታዊ መንግስትነት ከነበራቸው የአለም ሀገራት አንዱዋም በመሆን ትታወቃለች፡፡ በኋላም በሀገር ውስጥ በሚካሄድ ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት እየተዳከመች የውጭ ሀይሎችም ጫናና የመከፋፍል ሴራ እየበዛ በሂደት ታላቅነትዋና የነበራት ክብር እያዘቀዘቀ ሄደ፡፡ በታሪክ ውስጥ የቁልቁለቱን መንገድ ተያያዘችው፡፡ ድህነት፣ ድርቅና ተረጂነት መለያዋ እስከመሆን ዘለቀ፡፡

ዋናው ለሀገሪቱ ውድቀት አስተዋጽኦ ያደረጉት በውጭ ሀይሎች ሴራና ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ እየተደለሉ፣ ሀገራቸውንም አሳልፈው እየሰጡ፣ እርስ በእርስም እየተፋጁ በር የከፈቱት የራስዋ ልጆች ናቸው፡፡ ዛሬም የውጭ ሀይሎች በተለይም የዘመናት ጠላትነትዋ የማያባራው ግብጽ በሀገር ውስጥ መከፈፈል፣ ብጥብጥ፣ ሁከትና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲነሳ የተለያዩ አክራሪ ተቃዋሚዎችን (ኦነግን ኦብነግን ግንቦት ሰባትና የመሳሰሉትን) ከሻእቢያ ጋር ሁና በመርዳት ገፍታበታለች፡፡

እኛ ስንባላ እስዋ የአባይን ወንዝ የውሀ ፍሰት ባለቤትነት በብቸኝነት ተቆጣጥራ በእኛው ውሀ ታላላቅ ልማቶችን እያካሄደች እየለማች እየበለጸገች ኢትዮጵያ ደግሞ በገዛ ሀብትዋ ተጠቃሚ ሳትሆን በድህነት ውስጥ እየማቀቀች እንደትኖር ህዝብዋ ተከፋፍሎ እየተፋጀ ሰላም አልባ ሁኖ ለዝንተ አለም እንዲኖር ከጥንት እሰከ ዛሬ እየወጋችን እያደማችን ዛሬም በዚሁ ድርጊትዋ ገፍታበት ትገኛለች፡፡

ብዙዎቹ ከኢትዮጵያ የመገንጠል አላማ ይዘው የተነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያየ ስያሜ ይዘው የተመረቱት በግብጽ ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬም እየረዳቻቸው ትገኛለች፡፡ ምንም ሆነ ምን ግብጽ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትኖር አትፈልግም፡፡ የአባይ ወንዝ ውሀ ምንጩ ኢትዮጵያ ስለሆነች፡፡ ይሄንን ያህል ርቀት የሄደ የከፋ ጠላትነት ያላት ሀገር ነች ግብጽ፡፡ ስለ ግብፅ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

ወደዋናው ነጥብ ስንመለስ በውስጣችን የሚነሱ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ መያዝና መፍታት ከቻልን እርስ በእርስ መናቆሩን ካስወገድን ህብረታችን ከብረት የጠነከረና የጸና ከሆነ የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙት ጠላቶችዋ ያሰቡትን ማሳካት አይችሉም፡፡ አባቶቻችን የኢጣሊያ ፋሽስት ወራሪን መክተው የመለሱት ከመላው የሀገሪትዋ ክፍሎች በመውጣጣት ዘምተውና ተዋግተው ነው፡፡

ብሄር በሄረሰብ፣ ሀይማኖትና ጾታ ሳይለዩ በአንድነት ዘምተው፣ ተዋግተው፣ አብረው ወድቀው መስዋእትነት ከፍለው በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የአውሮፓ ነጭ ወራሪ ሰራዊት በጥቁሮች ምድር እንዲሸነፍና እንዲማረክ በማድረግ አለምን ጉድ ያሰኙት በነበራቸው ጠንካራ አንድነት ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም መቀጠል ያለብን ይሄንኑ የእነሱን ፈለግና አርማ ይዘን ነው፡፡ መለያየቱ፣ እርስ በእርስ በጠላትነት ስሜት መተያየቱ፣ በዘረኝነት ስሜት መለከፉ፣ በጥላቻ መዘፈቁ ሀገርን ከማጥፋትና ለጠላቶችዋ ሲሳይ እንድትሆን አሳልፎ ከመስጠት ውጪ ለማንም አይጠቅምም፡፡

ለምን ግብጾች እርስ በእርስ አይናቆሩም፤ ለምን የመገንጠል ወዘተ ጥያቄ እነሱ ጋ የለም? ብለን መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ ታላላቅ የአለማችን ሀገራት በውስጣቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ብሄር ብሄረሰቦች አሉዋቸው፡፡ ለአንድ ሀገራቸው ጸንተው ይቆማሉ እንጂ በዘረኝነት በጎጠኝነት ተዘፍቀው እርስ በእርስ አይባሉም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የሰው ልጅ ማንም ከማንም አይበልጥም፡፡ የዘርና የጎሳ ልዩነት የበላይና የበታች ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ የለም፡፡

ሰው ከየትኛውም ብሄረሰብ ይፈጠር፣ የፈለገውን ሀይማኖት ይከተል፣ የቆዳው ከለር ምንም አይነት ይሁን በህግ ፊት አንድና እኩል ነው፡፡ በስራው፣ በብቃቱ፣ በችሎታው ይመዘናል፡፡ ለሀገሩ ማድረግ የሚገባውን የዜግነት ግዴታውን ይወጣል፡፡ አሜሪካ የአለም ህዝብ በሙሉ ማለት በሚቻልበት መልኩ በስደት ከያለበት ሄዶ የሰፈረባት፣ የኖረባት፣ ተጋብቶ የተዋለደባት፣ ሰርቶም ያገኘባት፣ ህይወቱን የለወጠባት ሀገር ናት፡፡

በአሜሪካ በምድር ላይ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሀይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ የተለያዩ የቆዳ ቀለሞች ያሉባት ሲሆን ሁሉም አንድ ሀገሬ አሜሪካ ናት ብሎ የሚያምንባት፣ የጎሳ የብሄር ግጭት የሌለባት ሀገር ነች፤ የሀያልነትዋ ምስጢርም ይኸው ነው፡፡

በአሜሪካ ሁሉም ሀገሬ ብሎ ይሰራል፡፡ ለልዩነት ቦታ የለም፡፡ ካጠፋም በህጉ ይዳኛል፡፡ አበቃ፡፡ በእኛ ሀገር ስንወስደው ህዝቡን በጎሳና በብሄረሰብ እንዲጋጭ፣ እንዲናከስ የሚያደርጉት፣ የሚከፋፍሉት አንድም ገና አልሰለጠነም፣ በእውቀት አልገፋም፣ ባሳየነው መንገድ ይሄዳል፤ ይበጣበጣል እኛ በዚህ መሀል ብሄራዊ ጥቅማችንን እናስከብራለን፣ የፈለግነውን እናገኛለን ብለው ይሄንን የጥፋት ደባና መሰሪ ተንኮል የሚያደሩት የውጭ ሀይሎች የራሳችንን ዜጎች በመጠቀም በገንዘብ በመግዛትና በመደለል ነው፡፡ ምንም የሚያባላን፣ የሚያበጣብጠን ነገር የለም፡፡ ሀገሪትዋ ገና ብዙ አልተሰራባትም፡፡ እጅግ በጣም ሰፊ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ያልተነካ ብዙ ሀብት ያላት፣ የብዙ ወንዞች ባለቤት፣ ከርሰ ምድርዋ ገና ተመርምሮ ያልተደረሰበት፣ ከእኛም አልፎ ለሌላው አለም የሚተርፍ ሀብትና ምስጢር ያላት ነች፡፡

ይሄንን የሚያውቁት የውጭ ሀይሎች ህዝቡን እርስ በእርስ አባልተው ሲያበቁ ሲተረማመስ  ህግና ስርአት ሲጣስ ለሀገሪቱ የሚቆረቆር መንግስት ሲጠፋ በዚህ መሀል ገብተው ሊዘርፉአት ሀብትዋን ሊያግዙ እነሱ ሊከብሩበት እኛ ደግሞ በድህነትና በጦርነት ውስጥ እየተባላን እንድንኖር፣ እንድንተላለቅ ነው የሚፈልጉት፡፡ ኢራቅን፣ ሊቢያን፣ ሶርያን፣ የመንንና ሌሎችንም በዚህ መልኩ ነው ያጠፉአቸው፡፡ ሊቢያ በነዳጅ፣ በወርቅ ሀብትዋ ታዋቂ ሀገር ስትሆን አጠቃላይ ህዝብዋ 7 ሚሊዮን ነው፡፡ ጋዳፊ ልክ እንደ ሳዳም ሁሴን ሁሉ የሀገሬን ሀብት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ነው በርካታ የስም ማጥፋት ውንጀላዎች በራሳቸው ግዙፍ አለምአቀፍ ሚዲያዎች (ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ፎክስ ኒውስ፣ አልጀዚራ ወዘተ) ነው የተካሄደበት፡፡ ሰፊ ዘመቻ ከፍተውበት የራሳቸውን ቅጥረኞች በተቃዋሚነት ስም አሰማርተው ሲያበቁ በመጨረሻ ሰራዊታቸውን ልከው ወረሩት፡፡ ከሞተም በኋላ ዘለው በጥድፊያ የገቡት የሀገሪቱን ሀብት ለመቀራመት ብቻ ነበር፡፡

ለዛውም የተለያዩ ሀገራት የነዳጅ አምራችና አከፋፋይ፣ የወርቅና የጋዝ አለም አቀፍ ካምፓኒዎች ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው ሰተት ብለው ገብተው ከልካይና ሀገሬን ብሎ ተሟጋች መንግስት በሌለበት የሚበቃቸውን ያህል ዘረፉ፡፡ አጋዙ፡፡ ሀገሪቱም ሰላም አጥታ የጦርነት ቀጠና ሆነች፡፡ በየጎጡም ተከፋፍለው ጭራሹንም የአለም አቀፍ አሸባሪዎች መናሀሪያና መቀፍቀፊያ ሆኑ፡፡ ዛሬም ሰላምና መረጋጋት የላቸውም፡፡ ተከፋፍለው እየተዋጉ ይገኛሉ፡፡ እርቅ ቢባልም አልሰመረም፡፡

ልብ ያለው ልብ ይበል እንዲሉ ከዚህ የሀገራት ውድቀትና መጥፋት ምን እንማራለን ብሎ ማለት ብልህነት ነው፡፡ አይሳካለቸውም እንጂ ለእኛም የደገሱት ጥፋት ተመሳሳይ ነው፡፡ እነሱ እንዲዘርፉ እንዲከብሩ ሌሎች ሀገራት መጥፋት፣ መውደም፣ መፈራረስ አለባቸው፡፡ መንግስት አልባ ሲሆኑ በተለመደው ሁኔታ ሰላም ለማስከበር ለማረጋጋት ወዘተ በሚል ሽፋን ሰተት ብለው ይገቡና የሀገራቱን ሀብት ከልካይና ተቆርቋሪ ተከላካይ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በገፍ ለሊት ከቀን ያግዙታል፤ ይዘርፉታል፡፡ ቆይታቸውን የተለያየ ምክንያት በመስጠት ያራዝሙታል፡፡

በአመታት ውስጥ ስንትና ስንት የሀገር ሀብት እየተጫነ ወደ ውጭ ሀገር እንደሚጋዝ መገመት አይከብድም፡፡ እንዲያውም የጦር መሳሪያ ስለሚሸጡም በዛ ሀገር ውስጥ የተነሳው ጦርነት እንዲቆም አይፈልጉም፡፡ የሀገሬው ተወላጆች በየጎራው ተከፋፍለው እነሱም ሞተው ሀገራቸውንም ህዝባቸውንም እየገደሉ ለሚያደርጉት ጦርነት የሰለጠኑት ሀገራት ሰብአዊ ነን የሚሉት ሰባኪዎች የጦርመሳሪያ በአውሮፕላንና በመርከብ እያመላለሱ ይቸበችባሉ፡፡

በዚህ ሁሉ የሁከትና ሽብር ሂደት ህዝቡና ሀገሪትዋ በእጅጉ ይጎዳሉ፡፡ ለእነሱ የጦፈ የደራ ገበያ ነው፡፡ እንዲህ እያደረጉ ነው ሀገራትን የሚያፈራርሱት፡፡ መጠንቀቅ የሚገባንም ለዚህ ነው፡፡ አንዴ ሁኔታው ከእጅ ከወጣ ዳግም ሀገርን ቀድሞ በነበረችበት ሁኔታ ሰላምዋን መልሶ ለማግኘት “አይቻልም” ባየባል እንኳ እጅግ ከባድ ነው፡፡ የአክራሪው ተቃዋሚ ግብታዊነት፣ ስሜታዊነት፣ ጀብደኝነት ለውጭ ሀይሎች ቅጥረኛ ሁኖ በራሱ ሀገር ላይ መዝመቱ ነው ሀገራትን ያፈራረሰው፡፡

አክራሪና ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች አይናቸው እያየ ሀገራቸው ስትፈርስ ስትበታተን፣ ህዝቡ ሲሞትና ሲሰደድ፣ ከተሞቻቸው በመድፍ ሲፈራርሱ፣ ልማቶቻቸው፣ ድልድዮቻቸው፣ ተቓማት፣ መንገዶች፣ ታሪካዊ ቅርሶች እንዳልነበረ ሁነው ሲወድሙ ወደ አመድነት ሲለወጡ ጸጸታቸው እንደሚበረታ ለማሰብ አይከብድም፡፡ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮሀ በመሆኑ ትርጉም የለውም፡፡ በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ . . . አሁን ምን ያደርጋል ምጣድ ጥዶ ማልቀስ እንዳለው የሀገሬ ሰው፡፡ የሀገር የማደግና የመልማት ተስፋን መጠበቅ ሊያጠፉዋት ከሚያልሙ ሀይሎች መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው፡፡