አንድነትን ያጸና ሕገ መንግሥት!

 

 

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከጸደቀ ህዳር 29 2009 ዓም 22 ዓመቱን ይደፍናል። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በዘውዳዊው መንግስት እንደነበረው በንጉሠ ነገሥቱ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ የተሰጠ አይደለም። እንደወታደራዊው ደርግ ህገመንግስትም ለአንድ ዓመለካከት የበላይነት የቆሙ የጥቂቶች አምባገነናዊ ቡድን (oligarchy) ፍላጎት መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚህች ኢትዮጵያ በተባለችው ምድር ማንነታቸውን እንደጠበቁ ለዘመናት የኖሩ ብሄሮችን፤ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን መብትና ነጻነት፤ ጥቅምና ፍላጎት መሰረት በማድረግ በራሳቸው የተዘጋጀ፤ የዳበረና የጸደቀ፤ የሉዓላዊት ኢትዮጵያን የባለቤትነት ስልጣን ያጎናጸፋቸው፤ በመከባበርና በእኩልነት አብረው ለመኖር የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነዳቸው ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብቶችና ነጻነቶች የሕገ መንግሥቱ አምዶች ናቸው። ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበት ዕለት ህዳር 29 በየዓመቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሆኖ እንዲከበር ያደረገው መሰረታዊ ምክንያትም ይኸው ነው። ዘንድሮ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለ12ኛ ጊዜ በሀረሪ ክልላዊ መንግስት ሐረር ከተማ ይከበራል።

ከ80 በላይ እንደሚሆኑ የሚገመቱት የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው መልክዓ ምድራዊ ወሰን ውስጥ ለብዙ ክፍለ ዘመን ኖረዋል። በቋንቋቸው እየተናገሩ፣ ተፈጥሯዊ የመኖሪያ አካባቢያቸውና ታሪካዊ አጋጣሚዎችን መሰረት በማድረግ በተቀረጹና የኑሮ ዘይቤያቸውን በወሰኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህላቸው እየተመሩ ነው ለዘመናት የኖሩት፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንደማንኛውም በዓለማችን ላይ የሚኖር ሰብአዊ ፍጡራን ተፈጥሯዊ አካባቢያቸውን ለመኖር አመቺ በሆነ መንገድ አቅንተው ከመኖር የመነጨ መሬትን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ ስጦታዎች ላይ የባለቤትነት መብት ነበራቸው። የባለአገርነት መብት ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸው የማንነት መለዮ ኖሯቸው እንደ አንድ ግዙፍ ማህበረሰብ በዚህች አሁን ኢትዮጵያ በምንላት ምድር ላይ መኖራቸው ለድርድር የማይቀርብ ሀቅ ቢሆንም፤ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ በኋላ ብሄራዊ ማንነታቻው እና የማንነታቸው መገለጫ የሆኑት ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ወጋቸው፣ ታሪካቸው . . . የህግ እውቅና ተነፍጎታል። ይህም የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አካል የሆነ እውነት ነው። ይህን ያደረጉት “ሕዝቡን ለመግዛት ከፈጣሪ የወረደ ስልጣን አለን” በሚሉ የፊዉዳላዊ ዘውዳዊ ሥርዓት ነገሥታት ናቸው። እነዚህ ነገሥታት በአበዛኛው በኃይል፤ አልፎ አልፎም ከየአካባቢው ፊውዳላዊ ነገሥታትና የጎበዝ አለቆች ጋር የሕዝቡን ፍላጎት ባላገናዘበ የገዢነት ስልጣን ክፍፍል ስምምነት በመዋዋል የኢትዮጵያን ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዘውዳዊ ሥርዓት ስር እንዲወድቁ በማድረግ ነበር ማንነታቸውን ሕጋዊ እውቅና የነፈጉት፤ በዘወዳዊው ሥርዓት ቋንቋቸው ህጋዊ እውቅና ተነፈጎታል።  ፍትህን ጨምሮ የመንግስት ማንኛውንም የመንግስት አገልግሎት በቋንቋቸው ማግኘት እንዳይችሉ ተደርገዋል። ፍርድ ቤት ቀርበው በጉዳያቸው ላይ ምንም በማይግባቡበት፤  በማይሰሙትና በማይናገሩት ቋንቋ እንዲሟገቱ የሚያስገድድ ሁኔታ ነበር። ሕፃናት አፍ ከፈቱበት፤ በብቸኝነት ከሚናገሩትና ከሚሰሙት ውጭ በሆነ ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲከታተሉ ይገደዱ ነበር። ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህላቸው እንዲዋረድና የኋላቀርነት መገለጫ እንዲሆን ተደርጓል። እውነተኛ ታሪካቸው ተሸሽጓል። በዚህ አኳኋን  ማንነታቸው በተቀረፀበት ባህልና ቋንቋ መኖር ያሳፍራቸው ያዘ፤

ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ዘውዳዊው ሥርዓት ‘የእኔ ማንነት’ ነው በሚለው ብሄራዊ ማንነት፤ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ፤ ሃይማኖት . . . ራሳቸውን እንዲቃኙ የሚያስገድድ ስትራቴጂ ስራ ላይ ውሎ ነበር። ይህ ስትራቴጂ ሁሉንም ብሄራዊ ማንነቶች አቅልጦ አንድ ተመሳሳይ ማንነት ያለው አገር ለመፍጠር የተነደፈ  ነበር። የሕዝብን ብሄራዊ ማንነት ሆን ብሎ ማጥፋት በራሱ ተገቢ ያለሆነና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ስትራቴጂው የተተገበረበት ሂደት በተለያዩ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ላይ አሸማቃቂ የስነ ልቦናና ቁሳዊ ጉዳት ያስከተለ ነበር።

ይህ የሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ጨፍለቆ የማጥፋት ስትራቴጂ የተወሰኑት ዋና፤ ሌሎች ደግሞ ተከታይ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጓል። የተወሰኑቱ ከሌሎች የላቀ ታሪክ ያላቸው፤ ስልጡን፤ አገር መስራች፤ አቅኚ፤ ታማኝ . . .  እንደሆኑ ተደርገው ሲወሰዱ፤ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ያልተገሩና ያልሰለጠኑ፤ ለአገር ያላቸው ውዴታ አጠራጣሪ፤ አገራቸውን አሳለፈው ሊሰጡ የሚችሉ፣ . . . ተደርገው ይወሰዱ ነበር። እዚህ ላይ ሥርዓቱ ሊቀርጸው ያለመው ብሄራዊ  ማንነት ያላቸው ዜጎች “ከሥርዓቱ ልዩ ጥቅም አግኝተዋል” እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። በብሄራዊ ማንነታቸው የማፈር አስከፊ ጭቆናን ባይጋሩም እንደተቀሩት ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቻቸው ያልተሟሉ በአስከፊ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነጭ ድሀዎች ነበሩ።

 በፊውዳላዊው የነገሥታት ሥርዓት በኢትዮጰያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ላይ የተጫነው ጭቆና ይህ ብቻ አልነበረም። ሕዝቦች ማንነታቸውን እንደጠበቁ ለዘመናት አቅንተው በኖሩበት መሬታቸው ላይ የባለቤትነት መብት እንዳይኖራቸው ተደርጓል። በመሬታቸው ላይ ለረጅም ዘመናት ከመኖርና ከመጠቀም የመነጨ የባለቤትነት መብታቸው የማይገሰስ ሆኖ ሳለ፤ ይህ መብታቸው ተገፎ  አርሰው የሚኖሩበት የእኔ የሚሉት መሬት የሌላቸው የመሳፍንቱ፤ የመኳንነቱና የሥርዓቱ ቢሮክራቶች፤ እንዲሁም ወኪል ባላባቶች ገባርና ጢሰኞች እንዲሆኑ ተደርጓል። በገዛ አገራቸው በጢሰኝነት ከመኖር ውጭ አማራጭ ስላልነበራቸው የተጫነባቸውን ጭቆና ተሸከመው በገባርነት ለመኖር ተገደዱ። በመሬታቸውና በጉልበታቸው ላይ የሚያዝዙት ባለርስትና ባለጉልት መሳፍንት፤ መኳንንትና ተሿሚዎች ነበሩ።

ታዲያ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ይህን ሥርዓቱ የጫነባቸውን አስከፊ  ጭቆናና በዚህ ጭቆና ላይ የተመሰረተውን ለገባርነት የዳረጋቸውን ኢኮኖሚያዊ ጭቆና በፀጋ አልተቀበሉም። የጭቆናውን አስከፊነት ያህል ተቃውመውታል። ብረት አንስተው ተዋግተውታልም። መጀመሪያ ያካሄዱት ተቃውሞና ትግል ያልተደራጀ፤ ስትራቴጂና ታክቲክ የሌለው ግብታዊ የየአካባቢው ባላባቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር። ይህ በየአካባቢው የተካሄደ ትግል ግን ከባላገር አድማነት ያለፈ ውጤት ማስገኘት አልቻለም።

እየከራረመ ግን በኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ላይ የተጫነው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና የወለደው የአርሶ አደር ምሬት፤ ተቃውሞና ትግል በተለይ ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ አገራዊ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ቅርጽ ወደመያዝ ተሸጋጋረ። ይህም የጭቆናውን አስከፊነትና ምንጭ በተረዱ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን ነበር።

ይህ በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ያነጣጣረ ተቃውሞና ትግል ዋናዎቹ የጭቆናው ገፈት ቀማሽ አርሶ አደሮችን ያማከለ ሳይሆን ከተሞች አካባቢ ባልተደራጀ ሁኔታ የሚካሄድ የልሂቃንና የተማሪዎች ትግል ነበር። የዚህ ትግል ዋነኛ ማጠንጠኛ ከ85 በመቶ በላይ  የነበረውን ገባር አርሶ አደር ከጭሰኘነት፤ እንዲሁም ከብሄራዊ ጭቆና ነፃ ማውጣት ነበር። የትግሉ መሪ ሃሳብ አገሩን ለባለቤቱ አርሶ አደር እንዲመለስ የማድረግ “የመሬት ለአራሹ” ጥያቄ ነበር። በልሂቃን የሚመራው የተማሪዎች ንቅናቄ ሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ከፈጠሯቸው አቀጣጣይ ቀውሶች ጋር ተዳምሮ፤ በስራ አጥነት፤ በስራ ዋስትና እጦትና በመኖሪያ ቤት እጦት ሲነገላታ የኖረውን ጭቁን ከተሜ አሰልፎ ተቀጣጠለ። በተለይ በአዲስ አበባ ትግሉ ዘውዳዊውን ሥርዓት አሰጨንቆ ያዘው።

ይህ በልሂቃን የተመራና በዋናነት በተማሪዎች የተካሄደ፤ በጭቁን ከተሜዎች የታጀበ ትግል ዘውዳዊውን ሥርዓት አናጋው። ይሁን እንጂ፤ ትግሉ በተደራጀ መልክ ሲካሄድ ስላልነበረ ስልጣን ወደሕዝቡ ማምጣት የሚቻልበት እድል አልነበረም። እናም የመጨቆኛ መሳሪያ ሆኖ ዘውዳዊውን ስርአት ሲያገለግል የነበረው መለዮ ለባሽ (የጦር ሰራዊትና ፖሊስ) የተነቃነቀውን ሥርዓት ጠግኖ በአዲስ መልክ የማስቀጠል ዓላማ ይዞ “ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ” በሚል ስያሜ ተደራጀቶ ወደስልጣን መድረክ መጣ። በኋላም ወታደራዊ ደርግ ሆኖ፤ በመጀመሪያ በጊዚያዊ ወታደራዊ መንግስት፤ ቀጥሎም ራሱን ወደ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲነት (ኢሰፓ) ቀይሮ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢህዲሪ) መንግስት የመሰረተው ይህ 120 ያህል ወታደራዊ መኮንኖች ተመራርጠው ያደራጁት ቡድን ነው። ይህ ወታደራዊ ቡድን በ1967 ዓ.ም መስከረም 2 በተማሪዎች እና በጭቁን የከተማ ኗሪዎች ትግል ስሩ የተነቀለውን ሥርዓት መውደቅ አብስሮ አገሪቱን መግዛት ጀመረ።

ከላይ እንደተገለጸው በከተሞች አካባቢ ባልተደራጀ ሁኔታ የተቀጣጠለው የልሂቃንና የተማሪዎች ትግል በወቅቱ አጠቃላይ አአገሪቱ ሕዝብ 85 በመቶ ያህሉን ይወክል የነበረውን አርሶ አደር ከገባር ጢሰኝነት ነፃ ለማውጣት የ“መሬት ለአራሹ”ን መሪ ሃሳብ ያደረገ ነበር። እናም ወታደራዊው ቡድን በአርሶ አደሩና በልሂቃኑ ተቀባይነት ለማግኘት “መሬት ለአራሹ” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነበረበት። ይህንንም የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም ላይ ባወጀው የገጠር መሬት አዋጅ አደረገው። የጭቁን ከተሜዎች ዋነኛ ችግር ለነበረው የስራ ዋስትና እጦትና የመኖሪያ ቤት ችግርም ለጊዜውም ቢሆን ምላሽ የሰጡ የሚመስሉ አዋጆችን አውጥቶ ስራ ላይ አዋለ።

ይሁን እንጂ፤  አርሶ አደሩ በአዋጅ የተሰጠውን መሬት አልምቶ ባገኘው ምርት ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት እንዲኖረው አልተደረገም። በከተማዎች አካባቢም የመኖሪያ ቤት እጥረትን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አልተቻለም። ስራ አጥነትን በተጨባጭ ማቃለል የሚያስችል የልማት ስትራቴጂና ፖሊሲም አለነበረውም። በመሆኑም የአርሶ አደሩም ሆነ የከተሜው የኑሮ ሁኔታ መሻሻል አልቻለም። ነገሩ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ።

ከሁሉም በላይ ወታደራዊው ደርግ የዘውዳዊ ስርአት ጭቆናዎች ሁሉ መሰረት ለነበረው ብሄራዊ ጭቆና ምላሽ መስጠት አልፈለገም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለአንድ ክፍለ ዘመን በቆዩበት ብሄራዊ ጭቆና ስር እንዲቀጥሉ ነበር ያደረገው፤ ወታደራዊው ሥርዓት ልክ እንደዘውዳዊ ስርአት የወሰን አንድነት እንጂ የሕዝቦች አንድነት ያላት አገር ለመመስረት አልፈለገም። የወታደራዊው ሥርዓት የኢትዮጵያ አተያይ፤ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ አገር እንደሆነች ሳይሆን፤ ከአጎራባች አገራት ጋር በውል የታሰረ ወሰን እንዳለው መሬት ብቻ እንደሆነች ነበር። እናም ለብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት መከበር ዋጋ ሳይሰጥ የወሰን አንድነትን ማስከበር ዋነኛ ተግባሩ አደረገ። በመሆኑም ለረጅም ጊዜ ውስጥ ውስጡን ሲቀጣጠል የቆየው የብሄራዊ መብትና ነፃነት ጥያቄ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ተግል ገጽታ ይዞ ወጣ። በወታደራዊ ደርግ ሥርዓት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ብሄራዊ የነፃነት ንቅናቄዎች ሃያ ገደማ ነበሩ። በመጨረሻም ግንቦት 20 1983 ዓ.ም ወታደራዊውን ደርግ ያስወገደው ይህ ትግል ነው።

እርግጥ፤ አሁንም በዘውዳዊውና በወታደራዊ ሥርዓቶች  ብሄራዊ ጭቆና የነበረ መሆኑን የማይቀበሉ፤  በየአቅጣጫው ለብሄራዊ ነፃነት የተደረገውን ትግል ተገቢነት መቀበል የማይፈልጉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን አሉ። እነዚህ ወገኖች ብሄራዊ የነፃነት ትግል የመጨረሻውን አሃዳዊ የመንግስት ሥርዓት፤ ወታደራዊ ደርግ ፈንቅሎ ዳግም ላይመለስ አስወግዶ የብሄሮች፤ ብሄሮችና ሕዝቦች ብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና የሌለባትን፤ የሕዝቦች አንድነት ያላትን ፌደራላዊት አገር ለመመስረት ሲነሱ እነዚህ ወገኖች “አገር ተቆረሰ፤ ተበታተነ . . .” የሚል ጩኸት አሰምተዋል። አሁንም በተዘጋ ድምጽ ሲያላዝኑ ይደመጣሉ።

ያም ሆነ ይህ፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ በኋላ ለአንድ መቶ ያህል ዓመታት በኢትዮጰያ ሰፈኖ የነበረው ለኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ነፃነት እውቅና የነፈገ ጨቋኝ ሥርዓት ተወግዶ በምትኩ ፍፁም አዲስ የመንግስት ሥርዓት ተገንብቷል። በኢፌዴሪ ሕገመንግስት፤

የመጨረሻው የኢትዮጵያ አምባ ገነን የመንግስት ሥርአት የነበረው ወታደራዊው ደርግ በተገረሰሰ ማግስት፤ ከዚያ ቀደም ተንሰራፍቶ የነበረውን በኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ላይ የተጫነውን ጭቆና በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን የተዛባ ግንኙነት የሚሽር አዲስ የመንግሥት ሥርዐት የመገንባት እንቅስቃሴ ተጀመረ። በቅድሚያ የደርግን መንግስት በትጥቅና በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የነበሩ ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች የአገሪቱን ዘላቂ እድል ለመወሰን በአንድ አዳራሽ ታደሙ።

የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ከታደሙት መካከል አብዛኞቹ ለብሄራዊ ነፃነት የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ናቸው። እነዚህ ብሄራዊ የነጻነት ድርጅቶች ባካሄዱት መራራ ትግል ወታደራዊው የደርግ መንግስት ከተወገደ በኋላ፤ የየራሳቸውን ነፃ መንግስት የመመስረት ዕድል ነበራቸው። ይህን ከማድረግ ይልቅ አብረው በኖሩባቸው ዓመታት ባፈሯቸው በጎ የጋራ እሴቶች ላይ በመመስረት አብረው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ ይኖር እንደሆነ ይህን በቅንነት መመካከርን ነበር የመረጡት፤ እናም የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካና የነፃነት ትግል ዋነኛ መነሻ የሆነው ብሄራዊ ጭቆና የሌለበትንና በእኩልነት መኖር የሚችሉበትን ሥርዓት ለመመስረት ተስማሙ። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ተሰባስበው በሚወከሉት ሕዝብ ቁጥርና ወታደራዊውን ሥርዓት ለማስወገድ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ልክ ሥልጣን የተጋሩበትን የሽግግር መንግስት መሰረቱ። የዚህ የሽግግር መንግስት ቀዳሚ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመቻቻልና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበትን የመንግስት ሥርዓት መመሥረት ነበር። ይህ መንግስት የሚመራበትን ሕገ መንግሥት መቅረፅ የዚህ የሽግግር መንግሥት ቀዳሚ ተልዕኮ ነበር።

በዚህም መሰረት በሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች፤ እንዲሁም በሌሎች አመለካከቶች የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉበት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ተቋቋመ። ይህ ኮሚሽን የመጀመሪያውን የሕገ መንግሥት ረቂቅ አዘጋጀ።

በቅድሚያ በኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚወከሉ ሁሉም ለአካለ መጠን የበቁ 16 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ እንዲወያዩ ተደረገ። መቀነስ አለበት ያሉትን ቀንሰው፤ መጨመር አለበት ያሉትን አክለው አዳብረው መልሰው ላኩት። ኮሚሽኑ ረቂቁን በሕዝብ በቀረበው አስተያየት መሰረት አሻሽሎ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሕዝብ መራው። ረቂቁ የተመራለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ አንቀፅ በአንቀፅ አድቅቆ ተወያይቶ፤ ማሻሻያ ሃሳቦችን አካትቶ መልሶ ላከው። ከዚህ በኋላ ይህ ሁለት ጊዜ በሕዝብ ውይይት የዳበረ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ሕዝብ በዴሞከራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት ባዋቀረው የሕገ መንግሥት አጽዳቂ ጉባኤ ጸደቀ። ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት የተመረጡ አባላትን የያዘው የሕገ መንግሥት አፅዳቂ ጉባኤ በሕዝብ ውይይት የዳበረውን ረቂቅ ሕገ መንግሥት እያንዳንዷን አንቀፅ በድምፅ ብልጫ አያሳለፈ በመጨረሻ ሙሉውን ሕገ መንግሥት አፀደቀው።

የዚህ ሕገ መንግሥት ባለቤቶች፤ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፤ እርስ በእርስ በመከባበርና በመቻቻል በእኩልነት የሚኖሩበትን የመንግስት ሥርዓት መመስረት የቻሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሰረታዊ መርሆዎች በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሁለት ሰፍረዋል። በዚህ ምዕራፍ ከአንቀፅ 8 እሰከ 12 የሰፈሩት ድንጋጌዎች የሕዝብን ሉዓላዊነት፤ የሕገ መንግሥትን የበላይነት፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን፤ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን፤ የመንግሥት አሰራርና ተጠያቂነት መርሆዎችን የሚመለከቱ ናቸው። ከእነዚህ የሕገ መንግሥቱ መርሆዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሄሮችን፤ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት የሚመለከተውን ድንጋጌ በዚህ ጽሁፍ ልመለከተው ወድጃለሁ። የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 8 “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው ርዕሥ ሥር፤

  • የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።
  • ይህ ሕገመንግሥት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው።
  • ሉዓላዊነታቸውም የሚገለፀው በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሚመረጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳተፎ አማካይነት ይሆናል።

በሚል ተደንግጓል።

በአንቀፅ 39 “የብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብት” በሚል ርዕሥ ሥር ደግሞ የሚከተለውን ተደንግጓል፤

  • ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰብ፤ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እሰከመገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ የተጠበቀ ነው።
  • ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰብ፤ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፤ የመፃፍ፤ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ የማዳብርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው።
  • ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰብ፤ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው። ይህ መብት ብሄሩ፤ ብሄረሰቡ፤ ሕዝቡ በሰፈረበት መልከዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በውክልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል።

እንግዲህ ይህ በሕዝብ ተዘጋጅቶ በሕዝብ የፀደቀ የኢትዮጵያ ብሄሮችን፤ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን መብትና ነፃነት፤ የህግ የበላይነትን ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ እነሆ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ዕለት የብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሚል በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን ይከበራል። ዘንድሮም ለ11ኛ ጊዜ በሐረሪ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት ይከበራል።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት በስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ድንጋጌዎቹ ተግባራዊ ተደርገዋል። ከእነዚሀ ድንጋጌዎች የሚፈለጉት የመብትና ነፃነት መከበር፤ የዴሞክራሲ መሰፈን፤  በልማት የተሻለ ህይወት መኖር . . . ዕውን ሆነዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ስልጣን በውክልና በሰጧቸው ሰዎቸ ብቻ የመተዳደር፤ ፍትህን ጨምሮ የመንግስት አገልግሎት በቋንቋቸው የማግኘት፤ በቋንቃቸው የመተዳደር፤ ልጆቻቸውን በቋንቋቸው የማስተማር መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋቸውንና  ባህላቸውን እያጎለበቱ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ የኦሮሚኛ፤ የሲዳምኛ፤ የሶማሊኛ፤ የትግሪኛ ቋንቋዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እየተሰጡ ይገኛል። በተለይ ኦሮሚኛ እሰከ ፒ ኤች ዲ ዲግሪ ድረሰ እየተሰጠ ነው። ይህም በቋንቋው ላይ ጥናቶችን በማካሄድ፤ ቋንቋውን የስነፅሁፍ፤ የፍልስፍናና የሳይንስ ቋንቋ ወደመሆን ደረጃ ያሸጋግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በየክልላቸው የባህል ማዕከላት በመገንባት ነባር ባህላቸው በቅርስነት እንዲጠበቅ፤ አንዳንዶቹንም በዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ቅርስነት እንዲመዘገቡ እያደረጉ ይገኛሉ። ከአንድ ዓመት በፊት በዩኔስኮ የተመዘገበው የሲዳማዎች የዘመን መለወጫ – ፊቼ ጨንበላላ፤ ሰሞኑን የዩኔስኮን እውቅና ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን የኦሮሞዎች የገዳ ሥርዓት ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውን አንዱ ለሌላው እያስተዋወቁ እየተደናነቁና

አሁን የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሕገ መንግሥቱ መሰረት በፈቃዳቸው በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሕዝቦች አንድነት ለመመሰረት በገቡት ቃለ ኪዳን መሰረት ሁሉም እኩል ኢትዮጵያዊ ናቸው።

እርግጥ አሁንም ሕገ መንግሥቱን፤ በተለይ በአንቀጽ 39 ላይ የሰፈረውን ድንጋጌ እየጠቀሱ አገር ይበታትናል በሚል የሚጮሁና አሃዳዊ ሥርዓት ለመመስረት የሚመኙ ጥቂት ትምክህተኞች አሁንም አሉ። በሕገ መንግሥ’ቱ ላይ የተደነገገው እስከመገንጠል የዘለቀ መብት ግን፤ አዲሲቱን ኢትዮጵያ በፈቃዳቸው የገነቡት ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ነፃነታቸው ሳይሸራረፍ የሚከበር ለመሆኑ የተሰጠ ዋስትና እንጂ፤ መገንጠልን የሚያነሳሳ አይደለም። ተገንጥሎ ነፃ መንግስት መመስረት በራሱ መድረሻ አለመሆኑን፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ያውቃሉ። በመሆኑም መብትና ነፃነቶቻቸው ከተከበሩ ከሌሎች ጋር በአኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ኖሯቸው መኖርን ይመርጣሉ። እሰከመገንጠል የሚዘልቀው መብት መብትና ነፃነታቸው ለመከበሩ ዋስትና ነው። ይህ ትምክህተኞችን ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የመገንጠል አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ጠባቦችንም መቆሚያ ያሳጣ ድንጋጌ ነው። በየዓመቱ የጸደቀበትን ዕለት መነሻ በማድረግ ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሚል የምንዘክረው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ትምክህተኞችንና ጠባቦችን ቦታ አሳጥቶ የሕዝቦችን አንድነት ያጸና ሕገ መንግሥት ነው።