ነግቶልናል ስንል እንዳይመሽብን!

ባላገሩ ወገኔ የቆየ ስጋቱን ከዕለታት አንድ ቀን እውን ሆኖ ሲያገኘው፤ ‹‹…የፈራሁት ነገር መጣ ድሆድሆ››ይላል። እንግዲያውስ እኔም አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምትገኝበትን አጠቃላይ እውነታ ሳስብ ይህ ስነ ቃል ያዘለውን መልዕክት እንዳስታውስ የሚያደርግ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፤ ምክንያቱ ደግሞ ይህቺን አገር የአሰቸዃይ ጊዜ አዋጅ እስከ መደንገግ ያደረሷት እጅግ በጣም አሳሳቢ የሰላምና የመረጋጋት ችግሮች ድንገት ዛሬ የተፈጠሩ አለመሆናቸውን ስለምገነዘብ ነው፡፡

ስለዚህ ለዓመታት በስጋት ስሜት እየተመለከትን ከዛሬ ነገ ትርጉም ያለው የመፍትሔ እርምጃ ይወሰድባቸው ይሆናል ብለን  ስንጠብቅ ከመፍትሔ እርምጃው ይልቅ የችግሮቹ ስፋትና ጥልቀት ሚዛን  እየደፉ መጥቶ አሁን ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ ያስገደደን የአገራዊ ደህንንት አደጋ ሊጋረጥብን መቻሉ የፈራሁት ነገር መጣ ድሆ ድሆ የሚያሰኝ ጉዳይ ሆኖብናል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት ቀዳሚ የመወያያ አጀንዳችን አገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ይበልጥ አጠናክሮ ስለማስቀጠልና የፀረ ድህነት ትግሉን ዳር ስለማድረስ የሚያወሳ ርዕስ ጉዳይ እንዳልነበር፤ በዚህን ያህል ፍጥነት ነገሮች እየተለዋወጡ ሄደው አሁን ላይ የአብዛኛው ህብረተሰባችን አሳሳቢ ስጋት በሰላም ውሎ የማደር ደህንነትን የሚመለከት ጥያቄ ወደ መሆን መለወጡ የሚያስቆጭ ገፅታ ያለው ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው፡፡

ለማንኛውም ግን ‹‹መቼስ ምን ይደረጋል›› ከሚል ዓይነት ቁጭት በመነጨ ስሜትም ቢሆን ስለወቅታዊው የአገራችን ጉዳይ አንስተን መወያየት ይጠበቅብናልና እነሆ አሁን በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፋለሁ፡፡

የኢትዮጵያና የመላ ሕዝቦቿ ክፉ አይነጥላ ሊባል የሚችለውን ነጋ ስንል መሽቶ የመገኘትን አደጋ የሚጋብዙ ክስተቶች አሁንም ድረስ ይህቺን አገር ከፉኛ ሲፈታተናት እየታዘብን ያለንበት አስጊ እውነታ ቀልብሰን ዳግም ወደ ትናንቱ የጨለማው ዘመን አሳፋሪ ገፅታችን የምንመለስበት ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት ሊኖር እንደማይችል እርግጠኞች ሆነን የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል እንተጋ ዘንድ፤ ታስቦ ስለተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተያየት ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡

በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኋላ ታሪክ አዲስ ነገር ስላልሆነው ነጋ ስንል መሽቶ የመገኘት አደጋ ጉዳይ የሚያስታውሱንን አንዳንድ ነጥቦች በማውሳት እጀምራለሁ፡፡ ስለሆነም ከዚህ መሰረተ ሃሳብ አኳያ ያለውን  የኋላ ታሪካችንን አሳዛኝ ገጽታ በማስታወስ ረገድ የተሻለ ሚዛን የመድፋት አቅም ይኖራቸዋል ተብለው ከሚገመቱ የድህረ ዘመነ መሳፍንቷ ኢትዮጵያና የመላው ሕዝቦቿ ፈተናዎች  መካከል አንዱለሆነው፣ የ196619619999199 የሆነው የ1966 ዓ.ም. አብዮታዊ የሥርዓት ለውጥ ንቅናቄና ለዚች አገር ስላተረፈላት  መከራ ማውሳት ብቻ የእኔ ስጋት ምክንያታዊ መሆኑን ለማስረገጥ በቂ ይመስለኛል፡፡

እንዴት ቢባል ደግሞ፤ ወቅቱ በተለይም ከዘመነ መሳፍንቱ  የመውደቅ አሳዛኝ ታሪካችን ጀምሮ ተያይዞ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የጨፍልቀህ ግዛ አሀዳዊ የመንግስት ሥርዓት አወቃቀር ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ስር እየሰደደ የሄደውን ድህነትና በኋላ ቀርነት መቋቋም ያቃታቸው መላ የአገራችን ሕዝቦች እንደ አንድ ህብረተሰብ በጋራ ህልውናቸው ላይ የተጋረጠ አደጋ መኖሩን ተገንዝበው አደጋውን ለመቀልበስ ያለመ የለውጥ ፍለጋ ንቅናቄ ያሳዩበት ታሪካዊ አጋጣሚ እንደነበር መካድ የሚቻል ጉዳይ አይደለምና ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን፤ ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከመሻት በመነጨ  ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤ የተቃኘውን የዚያን ወቅቱን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፀረ ብሔራዊና መደባዊ  ጭቆና ትግል በቅጡ ለመምራት የሚያስችል አገር አቀፍ ቁመና መሰረት አድርጎ የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል ስላልነበረ፣ ደርግ የተሰኘው ወታደራዊ ጁንታ ክፍተቱን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ በትረ ስልጣን ጨብጦ የአብዮታዊ  ንቅናቄ ዋነኛ ግቦች ከሽፉ። ከቶውንም አንድን ቀለም ቀመስ ትውልድ እርስ በርስ ያገዳደለ አሳዛኝ ድምር ውጤትም አመጣ ፡፡

እንግዲያውስ የ1966ቱን የ ኢትዮጵያ አብዮት፤ መላው የዚች አገር ሕዝቦች ሊነጋልን ነው የሚል ብሩህ ተስፋ ሰንቀው ሲጠብቁ ታሪካዊ ሂደቱ መልኩን ቀይሮ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በማምራት ምክንያት፣ የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለመግባት የተገደዱበትን ትራጀዲ ያስከተለበት አሳዛኝ ወቅት ነበር የሚያሰኘውም ይሄው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያው ያልተጠበቀ ክስተት ያመጣብን መዘዝ ሲታወስ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው መጥፎ ትዝታ ደግሞ፣ በተለይ እነኢ.ህ.አ.ፓ ና መ.ኢ.ሶ.ንን የመሳሰሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጼ ኃይለ ሥላሴን መንበረ ስልጣን የመቆናጠጥ ዕድል ከገጠመው የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ጋር በእሳት እንደመጫወት ያህል ግብግብ የገጠሙበት የ‹‹ነጭ ሽብር፤ ቀይ ሽብር›› አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ መንኮታኮት ምክንያ ት የሆነው የ1966ቱ የኢትዮጵያ  ሕዝቦች አገር አቀፋዊ የሥር ነቀል ለውጥ ፍለጋ ንቅናቄ ወይም ደግሞ አብዮት የታለመለትን ግብ ሳይመታ መቅረቱን ተከትሎ፤ እንደ ህብረተሰብ የሃዘን ማቅ አጥልቀን   የታየንበት የ‹‹ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር›› ዘግናኝ ታሪካችን ያመጣብን መዘዝ ብቻ ግን አልነበረም ወደ ባሰ ድቅድቅ ጨለማ ያስገባን፤ ይልቁንስ  ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ  መራሹን የኢትዮጵያ  ሕዝቦች ፀረ መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና የትጥቅ ትግል ጨምሮ፤ ሌሎችም ተመሳሳይ የመብትና የነፃነት መሻት ጥያቄን ያነገቡ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በሁሉም የአገራችን ክፍል መበራከት የጀመሩበትን ሁኔታ ከማስከተሉ የተነሳ፤ በዚሁ ምክንያ ት ምናልባትም   የ‹‹ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር››  ፓለቲካዊ የድብብቆሽ ጨዋታ ለህልፈተ ህይ ወት ከዳረጋቸው ወገኖቻችን በቁጥር የማይተናነስ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ዕርስ በርሱ ጐራ ለይቶ ሲገዳደል የተስተዋለባቸው እጅግ ዘግናኝ ጦርነቶችና አካባቢያዊ ግጭቶች እንዲከሰቱ አድርጓል፡፡ ጉዳዩን በተሻለ መልኩ ለመረዳትም  ደርግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው 17 ዓመታት ውስጥ ጦርነትን ልክ እንደ የሙሉ ጊዜ ስራው አድርጐ የሚወስድ መንግስት የሆነው  ያለምክንያት እንዳልነበር ማስታወስ  ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡  በአጠቃላይ እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ መሰል የቅርብ ጊዜው  የጋራ ታሪካችን  ያስተናገዳቸው አሳዛኝ እውነታዎች ሁሉ፤ ምናልባትም የሚያጋጥሙንን መልካም ዕድሎች ተጠቅመን ወደ ስኬታማ ውጤት ልንቀይራቸው ስንችል፤ ግን ደግሞ አያያዙን ሳናውቅበት ቀርተን ያኮረፉና ‹‹አብረን ከምንቀዳጀው ትንሳኤ የኔ ድርሻ ያነሰ ሆኖ ስለሚሰማኝ ተያይዘን የምንወድቅበትን የጥፋት መንገድ ለመከተል ወስኛለሁ›› እንደ ማለት የሚቆጠር አፍራሽ እንቅስቃሴ ላይ መሰማራትን የሚመርጡ ወገኖች በሚጋርጡብን የቅልበሳ አደጋ ምክንያት ሊነጋ ነው ብለን ስንጠብቅ እየመሸብን ተቃራኒውን ድምር ውጤት ለመጋፈጥ የተገደድንባቸው እንደነበሩ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡     

እንደዚህ ዓይነቱ ፖለቲካዊ ስልጣን የመጨበጥ አለመጨበጥ ጥያቄ፤ የመላው ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ ከተመሰረተበት አገራዊ ህልውናችን በላይ አድርጐ የመቁጠር ክፉ አባዜ የተጠናወታቸው ልሂቃን አሁንም ድረስ መኖራቸውን ልብ ስንል ደግሞ፤ ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ነግቶልናል  ያልነው ቀን ድንገት ይመሽብን ይሆን እንዴ ? የሚል ስጋት በውስጣችን ማጫሩ አይቀርም፡፡ በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ስልጣን የመጨበጥ አስፈላጊነትን በተመለከተ የጠራ ግንዛቤ ኖሮት ፤ ፓርቲዎችን ለምን  መደግፍ  ወይም መቃወም እንዳለበት እንዲረዳ አለመደረጉ ሲታይ  ጉዳዩ  በእርግጥም  ሊያሳስበን እንደሚገባ ነው የሚሰማኝ፡፡

 

ምንም እንኳን ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ገዥውን ፓርቲ በምርጫ አሸንፈው አገር ለመምራት የሚያስችላቸውን መንግስታዊ ስልጣን ለመጨበጥ መፈለጋቸውና ፍላጐታቸውን እውን ለማድረግ ያለመ ትግል ማካሄዳቸው በራሱ የሚበረታታ እንጂ የሚወገዝ ተግባር እንዳልሆነ ብገነዘብም፤ ግን ደግሞ ወደ ስልጣን መምጣት ያለባቸው አሁን የሚስተዋሉትን የጋራ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ረገድ ከኢህአዴግ ተሽለው እንደሚገኙ የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስታዊ ቁመና ላይ የተመሰረተ ጥረት በማሳየት ብቻ መሆን ይኖርበታል ማለቴ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን እነርሱ በተለመደው የዘመነ “ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር” ፖለቲካዊ የድብብቆሽ ጨዋታቸው አማካኝነት ይህቺን አገር አተረማምሰው በአቋራጭ መንበረ ስልጣኑን ለመቆናጠጥ ሲሉ የኢትዮጵያን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ህልውና  አደጋ ላይ እንዲጥሉት መፍቀድ ማለት ታሪክ ይቅር ሊለው የማይችል ስህተት እንደመፈፀም ይቆጠር እንደሆነ እንጂ ለየትኛውም ወገን የሚበጅ ድምር ውጤት ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እናም እንደኔ እምነት ከሆነ ለምወዳት አገሬና ለመላው ሕዝቦቿ የተሻለ ዓለም ተፈጥሮላቸው ማየት እንሻለን የምንል እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ማድረግ የሚጠበቅብን ጉዳይ ቢኖር ዛሬ እንኳን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተፈፀሙ ታሪካዊ ስህተቶቻችንን ላለመድገም ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ካለፈው ጊዜ ስህተቶቻችን እየተማርን ወደፊት መቀጠል እየተገባን ጭራሽ ወደ ትላንቱ  ተያይዞ የመውደቅ አደጋ ሊመልሱን  ሲሞክሩ የሚስተዋሉትን የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ አስተሳሰብ  አቀንቃኝ ቡድኖች በምንም መልኩ የሚያበረታታ ድጋፍ ከመስጠት መቆጠብ እንደሚጠ በቅብን ነው የሚሰማኝ፤

የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደ የአንድ አገር ህብረተሰብ ካለፈው ዘመን ታሪካችን የወረስናቸውን አሉታዊ ልምዶች ልናወግዛቸውና ልናስቀራቸው እንጂ ፈፅሞ ዛሬም እንዲደገሙ ልንፈቅድ አይገባም ከሚል የኃላፊነት ስሜት የሚመነጭ አቋም ላይ የተመሰረተ ጤናማ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴን በማድርግ ለሚታወቁ ፓርቲዎችም ሆነ መሪዎቻቸው ተገቢ ክብር መስጠት እንደሚኖርብን፤ እንዲሁም ከትናንት እስከዛሬ ሲፈታተናቸው የሚስተዋሉ የአቅም ማነስ ተግዳሮቶቻቸውን ቀርፈው ሰላማዊ ትግሉን በተሻለ ጥንካሬ ለማካሄድ የሚያስችል ድርጅታዊ ቁመና እንዲይዙ ልናግዛቸውም ጭምር እንደሚገባ ነው እኔ በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ የምፈልገው፤ ምክንያቱም ነግቶልናል ያልነው ብሩህ ቀን ያልታሰበ የመምሸት አደጋ እንዲያጋጥመውና አሁንም አብሮ ከማደግ ይልቅ አብሮ መውደቅን በሚያስከትል የድህነት ጨለማ ውስጥ መዳከራችንን እንድንቀጥል የሚሹት የጥፋት ኃይሎች እንደፈሊጥ በያዙት አገር አውዳሚ የሁከትና የግርግር ተግባር የማምረቻ ኢንዱስትሪዎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃት እጅጉን የሚጎዳን  የመሆኑን ያህል፤ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አክብረው ጤናማ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ በማካሄድ የሚታወቁትን ሰላማዊ ፓርቲዎች ተገቢ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ የሚያተርፈን እንጂ የሚያጎድልብን ነገር አይኖርምና ነው፡፡ ስለዚህም የተጋረጠብንን ወቅታዊ አደጋ ቀልብሰን ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ዘለቄታው የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት የሚበጅ ፅኑ መሰረት የተጣለበትን የኢትዮጲያ ህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል እንችል ዘንድ እንደህብረተሰብ በእኩል የኃላፊነት ስሜት ተንቀሳቅሰን  ወጣት ዜጎቻችንን ለጥፋት ኃይሎች መሳሪያ እንዳይሆኑ ማድረግ የሚያስችል አግባብ ለመፍጠር መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡  

በግልጽ አነጋገር፤ ነግቶልናል ስንል ዳግም ወደ ድቅድቅ ጨለማ የመመለስ አደጋ ላይ እንድንወድቅ ከሚሹ የኢትዮጵያና የመላው ሕዝቦቿ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ወግነው በሚዶሉቱት የጥፋት ሴራ የህዳሴ ጉዟችንን ለመቀልበስ ሲንቀሳቀሱ የሚስተዋሉት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ አሁን በያዙት የአመፃ መንገድ ስልጣን እንዲጨብጡ የሚፈቅድላቸው አንድም የህብረተሰብ  ክፍል እንደሌለ፤ ወይም ደግሞ ሊኖር እንደማይገባ እርግጠኞች መሆን ይጠበቅብናል ማለቴ ነው፡፡ በተረፈ ግን ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ ፡፡ መዓሰላማት!