ስለ ሠላም ሲባል …

 

 

ሠላም የሁሉም መሠረት ነው። ሠላም ከሌለ ብርሃኑ ጨለማ ይሆናል። ወጥቶ መግባት የሰማይ ያህልን ይርቃል። ልጅ ወልዶ፣ አስተምሮና ለወግ ማዕረግ ማብቃት የቅንጦት ያህል ይቆጠራል። በሥጋትና በሰቆቃ ህይወትን መምራት ግድ ይሆናል። ለሠላም ዋስትናው ደግሞ የተረጋጋ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሆነ በበርካቶች ዘንድ ይታመናል። ይሁን እንጂ  የሠላምን ዋጋ በመገንዘብም ይሁን ባለመገንዘብ ሁከትን የመፍጠር አባዜ የተፀናወታቸው አንዳንድ ጽንፈኛ ቡድኖችና አገራት የውስጥ ሠላማቸውንንም ሆነ የከባቢ ሠላም የሚያውኩ እንደ ሻዕቢያ የመሳሰሉ ቡድኖች በሚፈጥሩት ችግር በርካታ ዜጎች ለጉዳት ተዳርገዋል።

የሻዕቢያ መንግሥት ውስጡ ታምሶ ቀጠናውን ለማመስና ለማተራመስ የማይበጥሰው ቅጠል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የኤርትራ ህዝብ ለከፍተኛ የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ቀውስ ተዳርጎ ባለበት በዚህ ወቅት ሻዕቢያ የተለያዩ የሽብር ተግባራት እየፈፀመ ይገኛል።

የሻዕቢያ መንግሥት እጅግ በጣም እየተባባሰ በመጣው የዚያች ምስኪን አገር ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ምክንያት ማጣፊያው ስላጠረው ብቻ ጎረቤት ኤርትራን የሣዑዲ ዐረቢያ መራሹ «ኢስላማዊ የፀረ – ሽብር ህብረት» አባል እንድትሆን ያደረገበትን አግባብ ፌዝ የሚያስመስሉት ምፀታዊ ገፅታዎች አሉት ፡፡

እንደ ታዛቢዎቹ የትችት ትንታኔ ከሆነ በተለይም ደግሞ ከጠቅላላ ህዝቧ ምናልባትም ከሃምሣ በመቶ በላይ ያህሉን ቁጥር የሚይዘው የክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆነ ራሳቸው የሻዕቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩላት እንደነበር ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ጎረቤታችን ኤርትራ ድንገት ዛሬ ላይ ብድግ ብላ ያውም ከነሣዑዲ ዐረቢያ  እኩል «ኢስላማዊ አገር ነኝ» ለማለት ሲቃጣት ማየት በራሱ የአቶ ኢሣያስን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝና ይሉኝታ ቢስነት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አጉልቶ የሚያሳብቅ ነው፡፡

ሌላው ይህን ሰሞነኛ ኤርትራ ነክ ርዕሰ – ጉዳይን አነጋጋሪ እንዲሆን ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ «የሶማሊያውን አልሸባብ ጨምሮ ሌሎች ፅንፈኛ ቡድኖች ለሚያደርጉት የሽብርተኝነት እቅስቃሴ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚሰጥ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዓለም አቀፍ የጥናት ቡድኑ አማካይነት ሳይቀር  ያረጋገጠበት እውነታ መኖሩ ነው።

የሻዕቢያ  መራሹ  ሥርዓት  አሁን የፀረ ሽብርተኝነት ትግሉን ስለመቀላቀሉ ሊነግረን የደፈረው ምን የሚሉት መልዓክ ቀርቦት ይሆን ጃል!? የሚል ምፀታዊ ጥያቄን ለማንሳት የሚጋዝ ሆኖ መገኘቱ ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ጎረቤት ኤርትራ ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ያወጣችው መግለጫ «ሣዑዲ ዐረቢያ መራሹን የእስላማዊ አገራት ፀረ ሽብር ጥምረት ስለመቀላቀሏ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ይወቅልኝ» የሚል አንድምታ እንደነበረው አይዘነጋም፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጉዳዩ ዙሪያ የራሳቸውን ሃሳብ ለመሰንዘር ሲሞክሩ የተደመጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ሻዕቢያ መራሹ የአሥመራ መንግሥት ሣዑዲ ዐረቢያና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንደተካተቱበት የተነገለትን «የፀረ ሽብርተኝት ኢስላማዊ ጥምረት» ስለመቀላቀሉ ማሳወቁን ተከትሎ፤ የጥምረቱን ወታደራዊ የጦር ሠፈር ቀይ ባህርን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር በሚያዋስነው የአሰብ ወደብ አቅራቢያ እንዲቋቋም ስለተፈለገ ኤርትራ ያሻቸውን የሚያደርጉበት መሬት «ለዐረብ ወንድሞቿ አበርክታለች» የሚል ነበር።

ኢትዮጵያ እንደ አንድ የምሥራቃዊ አፍሪካ ትልቅ አገር ለመላ የቀጠናው ህዝቦች የጋራ ልማት መንገድ የሚጠርግ ዘለቄታዊ ሠላምና መረጋጋትን በማስፈን እየተጫወተች ያለችውን ታሪካዊ ሚና ለማደናቀፍ ያለመ ጂኦ – ፓለቲካዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚመስል ሁኔታ ለመውተርተር ያደረገችው ሙከራ እንደሆነ አስተያየት ሰጪ ወገኖች ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ስለሆነም የኢፌዴሪ መንግሥት ከሻዕቢያ መራሹ የጎረቤት ኤርትራ ጠንቀኛ ሥርዓት አኳያ እስከ ዛሬ ድረስ ያሳየውን የሆደ  ሰፊነት አዝማሚያን ለማጤን ብሎም ለመፈተሸ እንዲገደደድ ከሚያደርጉ መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል አንዱ ይህ አካባቢውን ለውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ወደሚዳርግ ጂኦ – ፓለቲካዊ ሴራ የሚያመራ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

በእርግጥም ደግሞ የአቶ ኢሣያስ አፈወርቂን እጅግ ሥር የሰደደ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ለምንገነዘብ የዚህች አገር ዜጎች የሻዕቢያ ጉዳይን በንቃት ብንከታተል እምብዛም ሊያስገርም አይገባም፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ የዜጎች ጤናማ ሥጋት የመነጨን ምክንያታዊ አስተያየት ልብ ብሎ ለመስማት የሚፈቅድ መንግሥት ያተርፍ እንደሁ እንጂ አይከስርምና ነው ለጉዳዩ አፅንኦት መስጠታችን፡፡

እንግዲህ የኢትዮ – ኤርትራን አሳሳቢ ገፅታዎች የበዙበት ጉርብትና በተመለከተ ዛሬ ላይ ሆነን እንነጋገር ከተባለ ከሞላ ጎደል ይህን የሚመስል ነባራዊ እውነታ ነው የሚስተዋለው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ የፀጥታ ሥጋቶችን የሚደቅኑ ጂኦ – ፖለቲካዊ ክስተቶች እየተባባሱ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከአሳፋሪው የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪኳ ለመውጣት ስትል የተያያዘችው ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ በዓለም አቀፍ ማኅረሰብም ጭምር እማኝነት ይሰጠው ከጀመረ ወዲህ፣ ለመላው የአገራችን ህዝቦች በጎ አስበው የማያውቁ ኃይሎች ሁሉ ከቅርብም ከሩቅም እየተጠራሩ አሥመራ ውስጥ ሲዶልቱ የሚስተዋሉበት አግባብ ሲታይ ምን እየተደገሰልን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሻዕቢያ መራሹ የኤርትራ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ያለ የሌለ የማጭበርበር አቋሙን ተጠቅሞ ያቺን አገር ወደለየለት የፀረ – ኢትዮጵያ ኃይሎች መፈንጫነት የቀየረ ሁኔታ ስለ መፍጠሩ በዚያው ልክም ዳጎስ ያለ ኪራይ ሳይሰበስብ እንዳልቀረ የሚናገሩ ታዛቢዎች ጥቂት አለመሆናቸው ሲታሰብ ጉዳዩ «ሳይቃጠል በቅጠል» ነው  የሚያሰኝ ዓይነት አደጋ አዝሎ ይታየን ዘንድ የሚጠቁም ነው፡፡ 

እናም ከዚሁ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነጨ የግል ምልከታዬ ላይ ተነስቼ ጉዳዩ ስለ ሠላም ሲባል ለሚመለከታቸው የኢፌዴሪ መንግሥት አካላት የሚሰማኝን ለመግለፅ የሞከርኩባትን መጣጥፍ ሳጠቃልል ላሰምርበት የምሻው ቁልፍ ነጥብ አለ።

አገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ አሳክታ ድህነትን ተረት ማድረግ ካለባት ከጎረቤት ኤርትራ በኩል የሚቃጣብንን የመንግሥታዊ ሽብርተኝነት ጥቃት ሁሉ በማያዳግም መልኩ የሚያስወግድ ዘለቄታዊ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም የሚለው ይሆናል፡፡

በተረፈ ግን መጪው ጊዜ ለኢትዮ – ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች የጋራ ዕድገትና ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚረባረቡበት የሠላም ዘመን ይሆንላቸው ዘንድ ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ።