“በጥልቀት መታደስ” የሚለው ጉዳይ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና የመንግስት የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ነው። ይህን በጥልቀት መታደስ የተሰኘ እሳቤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና አባል ድርጅቶቹ፤ ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦሀዴድና ደኢህዴን በስራ አስፈፃሚና በምክር ቤት ደረጃ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ የወሰኑት ነው። ይህን ተከትሎ አባል ድርጅቶቹ የሚያስተዳድሯቸው የትግራይ፣ አማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት አመራራቸውን በጥልቀት ለማደስ ወስነው የመንግስት አሰፈጻሚውን አወቃቀር የማሻሻል እርምጃ ወስደዋል። እየወሰዱም ነው። በተለይ የኦሮሚያና የአማራ ክልላዊ መንግስታት፤ የፌደራል መንግስቱም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። አሁን በየደረጃው ያሉ የክልል አመራሮች፣ መካከለኛና የመጀመሪያ አመራሮች በጥልቀት የመታደስ ዓላማ ያለው ውይይት እያካሄዱ ነው። በጥልቀት የመታደሱ እርምጃ ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የመጀመሪያ ደረጃ አመራሮች ጋር መድረሱ ወደሕዝቡ እየቀረበ መሆኑን ያመለክታል።
ይህ ከባለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ በተለይ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንን ያጨናናቀ ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ያለው ግንዛቤ ግን እጅግ አነስተኛ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ግንዛቤ ባለፈው ዓመት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልልች አጋጥሞ የነበረውን ችግር ተከትሎ እንደመፍትሄ የተቀመጠ ከመሆን ያለፈ አይደለም። ዝርዝር ጉዳዩን የሚያውቁት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። በየደረጃው ያሉ አመራሮችን አንስቶ በአዳዲስ መተካት ብቻ አድርገው የወሰዱትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። አብዛኛው ሕዝብ ግን ከመስማት ያለፈ የሚያውቀው ነገር የለም። እናም ይህን በጥልቀት መታደስ የሚል ጉዳይ የግንዛቤ ጫፍ ለመጨበጥ በሚስችል መጠን መመልከቱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በጥልቀት የመታደስ ጉዳይ ሲነሳ ብዙዎች መታደስ ወይም ተሃድሶ የሚለው እሳቤ አይበቃም ወይ? በጥልቀት የሚለው ገላጭ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣል። እናም በጉዳዩ ላይ የምሰጠውን አስተያየት ከዚህ ልጀምር፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ተሃድሶ ሲያካሂዱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ኢህአዴግ ወደመንግስት ስልጣን ከመጣ በኋላ በ1993 ተሃድሶ አካሂዷል። የአሁኑ ተሃድሶ በጥልቀት መታደስ የተባለው የበፊቱ ተሃድሶ የፈጠረው ለውጥ ስለቀነጨረ እንደገና በማደስ ህይወት እንዲዘራና እንዲፋፋ የማድረግ ስራ ስለሆነ ነው።
ይህን ዘርዘር አድርገን እንመልከተው። የ1993 ተሃድሶ መነሻ ምክንያት ልክ እንደአሁኑ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ብልሽት ነበር። ኢህአዴግ ከሽግግር መንግስቱ ጀምሮ እስከ 1993 ለአስር ዓመታት አገሪቱን በመራበት ወቅት፣ የመንግስት ስልጣን ላይ የሾማቸው አመራሮቹ ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምሮ የድርጅቱ ዋነኛ ባህሪና መገለጫ የነበረውን ለሕዝብ መኖርና ማገልገልን ወደጎን ገፈተው ስልጣናቸውን ራሳቸውንና የእኛ የሚሏቸውን ጥገኞች መጥቀሚያ መሳሪያ የማድረግ አዝማማያ ጎልቶ ወጣ። ይህ ሁኔታ ጥቂት በመንግስት አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦችና ወዳጆቻቸው ያለአግባብ ያለልክ እንዲበለጽጉ አድርጎ ነበር። ሁኔታው በቁጥጥር ስር ካልዋለ የአገሪቱን መሪዎች በብዙ ታዳጊ አገራት እንደታየው ወደ አምባገንን ዘራፊነት በማሸጋገር ድርጅቱ ይዞ ከተነሳው የልማታዊ ዴሞክራሲ ሃዲድ ውጭ በማድረግ ስርአቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ስለታመነበት ተሃድሶ ማድረግ አስፈላጊ ሆነ።
የ1993 ተሃድሶ ዓላማ ዴሞክራሲንና ልማትን ማስፋትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነበር። ይህን የ1993ን ተሃድሶ ከአሁኑ በጥልቀት መታደስ አንድ ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ። ይህም ያኔ በኢህአዴግ አመራሮች መበላሸት ምክንያት ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ከድርጅቱ ውስጥ መሆኑ ነው። የአሁኑ ብልሽት ግን ሕዝባዊ ተቃውሞ ነው የገጠመው። ሁኔታው ድርጅቱን ማፍረሱና ስርአቱን ለአደጋ ማጋለጡ አይቀሬ መሆኑ ታመኖበት ነበር። ይህ ተሃድሶ ከ1993 በኋላ ባሉት ተከታታይ 15 ዓመታት በአገሪቱ ለተመዘገበው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት መሰረት መሆኑ ይታመንበታል።
በዚህ የመጀመሪያው ተሃድሶ ወቅት ድርጅቱ የሕዝቡ ትግል በተቀዛቀዘና ፋታ በተገኘበት በማንኛውም ወቅት የአመራር ብልሽት ሊያጋጥም እንደሚችል፣ በዚህም ምክንያት ተሃድሶው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አቋም ተይዞበት እንደነበረ የድርጅቱ የርእዮተ ዓለም ሰነዶች ያስረዳሉ። አገሪቱ በገለልተኛ ወገኖች ጭምር እውቅና የተሰጠውን ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ብትችልም፣ ከዚሁ ጋር በመንግስት ስልጣን ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ለራስ መጠቀሚያ የማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነትና ጥገኝነት አመለካከትና ድርጊት እየተንሰራፋና ስር እየሰደደ መጥቷል። ይህም በትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ወቅትና በተመደበላቸው በጀት ተጠናቅቀው ወደአገልግሎት አለመግባት፣ በፕሮጀክቶች ግንባታ አሰጣጥና ክትትል ላይ፣ በመንግስት ግዢና መሬት አስተዳደር እንዲሁም በመንግስት ገቢ አሰባሰብ ላይ በሚፈጸም ሙስና ማንም ሊያስተውለው በሚችል ደረጃ ይፋ ወጣ።
በዚህ ምክንያት የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆኑት የመልካም አስሰተዳደር መጓደል፣ ጥገኝነት፣ ትምክህትና ጠባብነት፣ የፍትህ እጦት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት አደባባይ ወጥተው የሕዝቡ መነጋገሪያ ጉዳይ ለመሆን በቁ። ድርሻን ይዞ ገሸሽ የማለት ጉዳይ በተለይ በየደረጃው ባሉ ባለስልጣናትና ባለሞያዎች ዘንድ የተለመደ ሆነ። ህግና ስርአትን አክብሮ ሕዝብን ማገልገል የሞኝነት መለያ ሆነ። ሁሉም ለዘረፋ አሰፈሰፈ። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ “ድርሻዬ” የሚሉትን መቦጨቅና ማስቦጨቅ የወቅቱ የኑሮ ዘይቤ ለመሆን በቃ። በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙና በፍጥነት ማደግ በጀመሩ የኦሮሚያ ከተሞች የነበረው የመሬት ዘረፋ የአመራሩንና የባለሞያውን ሽሚያ ጥንብ ላይ ያረፉ አሞሮች አስመስሎት ነበር። በአጠቃላይ ደላላው በአንድ በኩል፣ ከቀበሌ ጀምረው ያሉ አመራሮች በሌላ በኩል ምዝበራውን አጧጡፈውት ነበር።
ምስኪኑ ከተሜና አርሶ አደሩ መሬቱ ይነጠቃል። አስተዳደራዊ መፍትሄ ለማግኘት የሚያቀርው አቤቱታ የሚሰማው የለም። ፍርድ ቤት ቢሄድም ፍትህ የሚያገኙት እውነት ያላቸው ሳይሆኑ ገንዘብና ወገን ያላቸው በመሆኑ ይፈረድበታል እንጂ አይፈረድለትም። ኪራይ ሰብሳቢነቱና ሙስናው ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እስከተዘጋጀው የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት አደረጃጀትና ገንዘብ አሰጣጥ ድረስ የዘለቀ ነበር።
“በደንባሪ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሕዝቡ ቁጥር በ40 በመቶ ያህል በመጨመሩ፤ ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገቱ የወለደው ከፍተኛ ቁጥር ያለው በከፍተኛ ደረጃ የተማረ ወጣትና ተጨማሪ ፍላጎቶች እየተመዘገበ ባለው እድገት ማርካት የማይቻልበት ሁኔታ አስከተለ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተማረ መብትና ነጻነቶቹ ላይ የተሟላ ግንዛቤ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠሩ በየደረጃው ባሉ አመራሮችና የፍትህ ተቋማት የሚደርስበትን ጫና፣ የአገርና የሕዝብ ሃብት ምዝበራ፣ የአመለካከት ብዝሃነትን ማስተናገድ ላይ ጉድለት ያለበት ዴሞክራሲን በዝምታ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም።
እናም የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የአመለካከት ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የስራ እድል . . .ወዘተ. ጥያቄዎች እዚህም እዚያም የሕዝቡ መወያያ አጀንዳዎች ለመሆን በቁ። ቁም ነገሩም ቧልቱም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያተኩር ሆነ። በተለይ ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቃቸው የመሰረተ ልማቶች ተጀምረው ሳይጠናቀቁ መቅረት፣ በአገሪቱ ከተሞች ያለው የስራ አጦች ቁጥር እየጨመረ መሄድና ስራ የማግኘት እድል መጥበብ ተስፋ መቁረጥ አስከተሉ። ይህ ሁኔታ እያደረ ሕዝቡ በስርአቱ ላይ ያለውን እምነት እየሸረሸረው ቅሬታዎች መንገድ ሲያገኙ ገንፍለው ወደኃይል ተቃውም የሚቀየሩበትን ነባራዊ ሁኔታ ፈጠረ።
ይህ ነባራዊ ሁኔታ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ለተፈጠረውና በርካቶች የተሳተፉበትና በርካቶች ደግሞ ከኋላ ሆነው ይደግፉት የነበረውን ሁከት ቀመስ የመንግስት ተቃውሞ ቀሰቀሰ። እነዚህ ሁከት ቀመስ ተቃውሞዎች የፈነዱበት ሰበብ ቢኖራቸውም እስኪፈነዳ ያበጠ የሕዝብ ቅሬታ የፈጠሩት ግን ከላይ በመጠኑ የጠቀስናቸው በመንግስት በኩል ያሉ ችግሮች ናቸው። በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ ስርአቱን ለአደጋ ያጋለጠበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። አሁንም ይህ አደጋ አልተገፈፈም። እንዳንዣበበ ነው። መፍትሄው በጥልቀት መታደሱን እውን ማድረግ ብቻ ነው።
እንግዲህ ይህ ሁኔታ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትና ልማት፣ እየጨመረና እየሰፋ የመጣውን የሕዝብ ፍላጎት በሚያረካ መጠን ማስቀጠል የማያስችል ማነቆ ሆነ። በመሆኑም ለሕዝብ የፍትህና የመልካም አስተዳደር፣ የልማት ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ብቃትና ፍላጎት ያለው የአመራር መዋቅር መፍጠር የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የስርአቱ መቀጠል አለመቀጠል ጥያቄ ሆኖ ፊት ለፊት ወጣ። የ1993ቱ ተሃድሶ ግፊት ጉልህና ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረገ ውጤት ማስመዝገብ ቢያስችልም፣ ግፊቱና ፍጥነቱ እየቀነሰ መጥቶ አላላውስ ብሎ የተገተረበት ደረጃ ላይ ደረሰ ማለት ነው። አሁን የ1993ን መላወስ ያቃተው የቀነጨረውን አሮጌ ተሃድሶ እንደገና ማደስ አስፈልጓል። አዲሱ ተሃድሶ ያስፈለገው ለዚህ ነው። ተሃድሶውም በጥልቀት መታደስ የተባለው ባለፉት 15 ዓመታት በአገሪቱ እመርታዊ ሊባል የሚችል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስገኘውንና አሁን ላይ ቀንጭሮ አልፋፋ ያለውን ተሃድሶ ዳግም ገባ ብሎ የማደስ ተግባር በመሆኑ ነው።
ይህ በጥልቀት የመታደስ እርምጃ የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። ከእነዚህ መካከል ለሕዝብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ብቃት ያለው የመንግስት አመራር መሰየም፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በአመራር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በባለሞያውም ዘንድ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስና ባህሪን መፍጠር ወይም የአመለካከት ለውጥ ማምጣት፣ የመንግስትን መዋቅርና ስልጣንን ለራስ ጥቅም ካዋሉና የማዋል ዝንባሌ ያላቸውና ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ብቃት ከሌላቸው አመራሮችና ባለሞያዎች ማጽዳት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንዳነሳሁት፤ በተለይ የመንግስትን መዋቅር የሕዝብ አገልጋይነት ፍላጎት ከሌላቸውና ብቃት ከጎደላቸው አመራሮች የማጽዳቱ ስራ ተጀምሯል። እርግጥ ሕዝቡ አሁንም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አለው። በክልልም ይሁን በፌዴራል ደረጃ የተነሱት አመራሮች ሁሉም በትክክል ችግር ያለባቸው ናቸው ወይ? በደፈናው የሕዝብ አገልጋይነትና ብቃት ማነስ ያለባቸው ከማለት ያለፈ ምን ጉድለት እንዳለባቸው በይፋ ይገለጽ፣ የሚጠየቁም ካሉ በይፋ ተጠያቂ መሆን ይኖረባቸዋል እያለ ነው። በአጠቃላይ በመንግስት በኩል ሕዝብን ያስኮረፈና ተስፋ ያስቆረጠ፣ ለተቃውሞም ያነሳሳ ችግር መኖሩ ምንም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ በመሆኑ ይህን ለማስተካካል የተሃድሶ እርምጃ መወሰዱ አስፈላጊነት የሚያከራክር ባይሆንም ከአመራሮች መነሳት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ብዥታ መጥራት አለበት። የተጀመረው ተሃድሶ የሚጠበቅበትን ውጤት ማምጣት የሚችለው የተሸረሸረውን የሕዝብ አመኔታ መልሶ መጠገን ሲቻል ብቻ በመሆኑ ምንም ተደበስብሶ የሚታለፍ ነገር መኖር የለበትም። በጥልቀት የመታደሱ ዋነኛ መገለጫ የመንግስት ግልጽነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ቆስቋሽ አጋጣሚ አግኝቶ የፈነዳው የሕዝብ ተቃውሞ መንስኤ መንግስት እያደገ ለመጣው የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት የሕዝብ አገልጋይነት ፍላጎት እየነጠፈ ሄዶ መልካም አስተዳደር በመጓደሉ፣ ፍትህ በመዛነፉ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በመጥፋቱ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህም ስርአቱን አደጋ ላይ መጣሉም እንዲሁ የማያሻማ እውነት ነው። በመሆኑም፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሁሉም ደረጃ ያሉ አመራሮች እስከ ሲቪል ታች ያለው አስፈፃሚ በጥልቀት መታደስ ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ተሃድሶው ወደሕዝቡ ይወርዳል።ይህ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ቅሬታውን አስወግዶ ስርአቱን የማስቀጠል ያለማስቀጠል ጉዳይ ነው።
ለዚህ ተሃድሶ ሕዝብም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። በየደረጃው ያሉ አመራሮች እርስ በርስ ያደረጉትን ግምገማ ውጤት ይዘው ታች ወርደው በሕዝቡ ሊለቀለቁ ይገባል። ከዚያም የጸዳው ብቻ ነው ማለፍ ያለበት፤ በተለይ በሕዝብ አደራ ስልጣን የተረከበው ኢህአዴግ አመራሮቹንና አባላቱን በዚህ አኳኋን በሕዝብ እያስለቀለቀ ከላይ እስከታች በጥልቀት መታደስ ካልቻለ ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ይዞ ወደጥልቅ ጉድጓድ እንደሚገባ መገንዘብ አለበት። እናም አመራሮቹ በጥልቀት ለመታደስ በጥፍራቸው ቆመው ቀን ከሌት መስራት ይጠበቅባቸዋል። በጥልቀት አለመታደስ በጥልቀት መቀበርን እንደሚያስከትል ማስታወስ ተገቢ ነው።