የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 እንዲከበር የተወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው ሦስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትም ገና ከመግቢያው ጀምሮ በሕዝቦች መካከል መቻቻል፣ አብሮ መኖርና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር የሚያመላክት ሃሳብን አስፍሯል። የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ዓላማም በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ የተሰባሰቡት ሕዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጥሩ፣ በህዝቦች መካከልም መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት የህዝቦችን ነጻነት በማረጋገጥ ረገድ ከማንኛውም አገር ህገመንግሥት በተሻለ ሁኔታ የሚጠቀስ ነው። በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስከመገንጠል የሚፈቅደውን አንቀጽ አንዳንዶች አገሪቱን ወደመበታተን የሚወስድ ነው በማለት ከህገ-መንግሥቱ ላይ እንዲነሳ ሲወተውቱ ይታያሉ። ይሁንና በተግባር ይህ አንቀጽ በህገ መንግሥቱ ላይ መካተቱ በተግበር የተመለከትነው በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲነግስ ያደረገ መሆኑን ነው። ይህ አንቀጽ በአገራችን ዳግም ጭቆና እንዳያንሰራራ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዋስትና የሚሰጥ አንቀጽ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። አንቀጽ 39 ጭቆና ሊያመጣ የሚፈልግ አካልን እጁን እንዲሰበስብ ያደረገ አንቀጽም ነው።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዋነኛ ዓላማም ህገመንግሥቱ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያስገኘላቸውን ጥቅሞች እንዲያስቧቸውና ባህላቸውን እንዲተዋወቁ ለማድረግና በቀጣይ ማከናወን የሚገባቸውን ተግባሮች ላይም መምከር እንዲችሉ ነው። የህገ መንግሥታችን ውጤት ከሆኑት አንዱ የሆነው የፌዴራል ሥርዓታችን የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶቻችንን ከማጎልበት ባሻገር ህዝቦች በአገራችው ጉዳይ በያገባኛል እንዲወስኑ አስችሏቸዋል።
የዘንድሮው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በተከበረበት ወቅት የአገራችንን ዘላቂ ሠላም ለማጠናከር፣ ፈጣን የልማታችንንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንን አጠናክረን ለማስቀጠል፣ አገራችን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን ቃል የገባንበት ወቅት ነው።
የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የሚያሳየው የፌዴራል ሥርዓቱ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተገነባ መሆኑን የሚያስመሰክሩበት አንዱ መድረክ ነው። እንዲሁም ይህ በዓል በአገራችን የብሔር ጭቆና፣ አፈናና አድልዎ ዳግም ላይመለስ መቀበሩን በድጋሚ ያረጋገጡበት እንዲሁም የድህነትና ኋላ ቀርነት ዘመን እንዳይመለስ ለማድረግ ጠንክረው ለመሥራት ቃል የገቡበትም ወቅት ጭምር ነው። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሚከበርበት ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዚህ ሁሉ ድልና ስኬት መሠረት የጣለው ህገ መንግሥታችንን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለብን ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ወደፊትም ቃላችንን የምናድስበት ይሆናል።
የፌዴራል መንግሥቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላቸውን እንዲያለሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ዕድገት የተመጣጠነ እንዲሆን አስችሎታል። ለዚህም ጥሩ ማሣያ የሚሆነው ከስምንተኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ጀምሮ እስካሁን የሚከበርባቸው ክልሎች የአርብቶ አደር አካባቢዎች በመሆናቸው ባለፉት ሥርዓቶች የተረሱ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ያልነበራቸው ነበሩ። ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገራችን በተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሣቢያ በየትኛውም አቅጣጫ ያሉ የአገራችን ከተሞች የተመጣጠኑ እንዲሆን ተደርጓል።
እነዚህ አርብቶ አደር አካባቢዎች እንዲህ ያሉ ትላልቅ ሁነቶችን ማስተናገድ መቻላቸው የአገራችን ዕድገት በማዕከል ብቻ ላለመከማቸቱ ጥሩ ማረጋጋጫ ይመስለኛል። በአገራችን እየተመዘገበ ካለው ዕድገት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መኖሩን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል የተመጣጠነ የከተሞች ዕድገት መታየቱ ነው።
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የአገራችን ህዝቦች በህገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጡ መብቶቻቸውን ተጠቅመው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስቀመጡትን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ ተረባርበዋል። በአገራችን ዘለቄታዊ ሠላም ማስፈን በመቻሉም ዓለምን ያስደመመ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። አገራችን እያስመዘገባች ያለችው ባለሁለት አኃዝ ዕድገት የህገ መንግሥታችን ውጤት መሆኑን መገንዘብ የሚያስቸግር አይመስለኝም። በእርስ በርስ ጦርነትና ረሃብ ትታወቅ የየነበረች አገር ከአፍሪካ አልፋ በዓለም በዕድገት መታወቅ የቻለችው በዚህ ህገ መንግሥት ሣቢያ በተገኘ ዘላቂ ሠላም ነው።
ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ "ህገ መንግሥታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል የተከበረው በምሥራቅ የአገራችን ክፍል በሐረሪ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በሐረር ከተማ ነው። ከተማዋም የአካባቢውን ነዋሪዎችና እንግዶቿን ተቀብላ በጥሩ መስተንግዶ ሸኝታለች። በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ብዝሃነት እንዲጎለብት ሲደረግ በሥርዓቱ ውስጥ በተሻለ ደረጃ ግልጽነትን ስለሚፈጥር ለኪራይ ሰብሳቢነት፣ ለጥበትና ትምክህት እንዲሁም ለፀረ ሠላም ኃይሎች የመደበቂያ ዋሻን ለመናድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ዕድሉ ትልቅ ነው፡፡ እንዲሁም ብዝሃነት ለኃይማኖትና ለብሄር ማክረርም ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በጣም ዘመናዊ ከሚባሉ ህገ መንግሥቶች የሚመደብ ነው። ህገ መንግሥቱ የዜጎችን ሰብዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በግልጽ የሚደነግጉ አንቀጾችን አካቷል። ሕገ መንግሥቱ የአገራችን ዜጎች ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሠረት ጥሏል። ዛሬ በአገራችን በፖለቲካዊ አስተሳሰብ መደራጀት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ። ሃሳብን የመግለፅ መብት በመረጋገጡም የግል ሚዲያ እየተስፋፋ ይገኛል። የተለያዩ ሃሳቦችም በነፃነት ይንሸራሸራሉ።
በኃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ኃይማኖቶች በእኩልነት እየተስተናገዱ ይገኛሉ። ዛሬ በአገራችን መንግሥታዊ ኃይማኖትም ሆነ ኃይማኖታዊ መንግሥት የለም። ይህ በመሆኑም ኃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስሥረት ተችሏል። በዜጎች የንብረት መብት ላይ የተጣለው ገደብ ተነስቶ ዜጎች ያልተገደበ ሃብት የማፍራትና የመጠቀም መብታቸውን በተግባር ላይ አውለዋል። የአገራችን ሠራተኞች ተደራጅተው ለመብታቸው የመታገልና ጥቅማቸውን የማስከበር መብታቸውን አረጋግጠዋል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የህገ መንግስሥታችን ትሩፋቶች ናቸው።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በአገራችን የታየው ልማትና ዕድገትም ቢሆን የህገ መንግሥታችን ውጤት ነው። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አገራችን በታሪኳ አከናውናው የማታውቃቸውን እጅግ ግዙፍ የሆኑ ባለ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መገንባት ጀምራለች። ለአብነት ያህል ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎችና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም በመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታ ወዘተ…አገልግሎት የታዩት ዕድገቶች እጅግ ከፍተኛ ከመሆናቸውም ባሻገር የአገራችንን ዕድገት ወደፊት በማራመድ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው።
መንግሥት የከተማ ነዋሪዎችን ህይወት ለመለወጥ እንዲቻል የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተንቀሳቅሷል። በዚህም በርካታ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሆኑበትን የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መስፋፋት ሣቢያ በርካታ ዜጎች ሥራ የተፈጠሩላቸው በመሆኑና ገቢያቸው እንዲጨምር በመደረጉ የከተማ ነዋሪዎች ህይወት መለወጥ ችሏል። በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ በከፍተኛ ድጎማ የመኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በዕጣ እያከፋፈለ ይገኛል። ይህም በርካታ የከተማ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች የቤት ባለቤት የሆኑበት ሁኔታን ማየት ይቻላል።
በትምህርትና በጤናው ዘርፍ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት በበርካታ አንፀባራቂ ድሎች የተሞሉ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተዋል። የአገራችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ብቻ ከ35 በላይ ለማድረስ ተችሏል። በአገራችን የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ እንዲሁም የተማሪዎች ቁጥርም ወደ 30 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው። ዛሬ በአገራችን ከሦስት ሰዎች አንዱ ተማሪ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህ የሚያሳየው አገራችን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል የተማረ የሰው ሃይል ሊኖራት እንደሚችል መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም። በጤናው ዘርፍም አገራችን ከፍተኛ ስኬት ያሳየችበት ነው። በአንዳምንዶቹ ዘርፎች አገራችን የሚሌኒየም ዴቨሎፕመንት ጎሉን ቀድማ በማሳካት እንደ አብነት የምትጠቀስ አገር መሆን ችላለች። ይህ ሁሉ ስኬቶች የአገራችን ህገ መንግሥት ውጤቶች ናቸው።
በህገ መንግሥታችን የፀደቀው የፌዴራል ሥርዓታችን ውጤታማ የሆነው በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን በመደረጉ ነው። የሕግ የበላይነትም ሆነ የተቋማት አደረጃጀት እና አሠራር መረጋጋት ሊረጋገጥባቸው ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥቱ በፌዴራሉ ሥርዓት ውስጥ ሕዝቦች በመካከላቸው ስለሚኖር ዝምድና እና የጋራ መስተጋብር መሠረታዊ መርሆዎችን ያስቀምጣል።
የፌዴራሉን ሥርዓት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችሉ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል መርሆዎችንም ያስቀምጣል። እነዚህ መርሆዎች በህገ መንግሥቱ የሰፈሩ ቢሆንም በአተገባበር ረገድ እጥረት ይታያል። የሕግ የበላይነት በተከበረበት ሁሉም ወገኖች ድምፃቸው የሚሰማበትና ውሣኔ በማሳለፍ ሂደት ላይም ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ መቻቻል ሊጎብት ይችላል።
የዘንድሮው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ሕገ መንግሥታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን በበዓሉ ወቅት በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን የተመዘገቡትን ድሎች መለስ ብለን የምንዳስስበትና ስኬቶቻችንን የምናሰፋበት ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናፈላልግበት እንዲሁም ለተጨማሪ ድሎች ማስመዝገብ ጠንክረን ለመሥራት ቃል የምንገባበት ይሆናል።