አመታዊው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዋናነት የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት የተረጋገጠበትን ህገ-መንግስት መሰረት በማድረግ ህገ-መንገስቱ በጸደቀበት ህዳር 29 ቀን በየአመቱ የሚከበር ታላቅ ህዝባዊና ሀገራዊ በዓል ነው፡፡ ታላቅነቱ የሚለካው ደግሞ ሃገራችን ባለፉት 25 ዓመትት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ዘርፍ ላስመዘገበችው ውጤት መሰረቱ የመላው ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ መገለጫ የሆነው ህገ-መንግስት በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ልማታዊ ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥር እየሰደደ እንዲሄድና ፈጣን ወደ ሆነ የልማት ጎዳና እንድትገባ ያደረገው መላው ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ገዢያችን ነው ሲሉ ያጸደቁት ህገ መንግስት ህዝቡን በውስጡ በያዛቸው ድንጋጌዎች በመምራቱ መሆኑም አያጠራጥርም፡፡
ስለሆነም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁ ተሞክሮ እንዲለዋወጡና የለውጣቸውም መሠረት የሆነውን ህገ መንግስት ከማናቸውም አደጋ ለመጠበቅ በጋራ ቃል ኪዳናቸውን ያድሱ ዘንድ የበዓሉ መከበር ዋነኛ ፋይዳ ነው፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በሃረሪ ብሄራዊ ክልል ህገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እና ለህዳሴያችን በሚል መሪ ቃል የሚከበረው በአል የሚኖረውን ፋይዳ ከህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች አኳያ መቃኘት የዚህ ፅሁፍ መሰረታዊ መነሻ ነው።
መንግስት ዛሬ ላይ ባሳለፍናቸው 25 ዓመታት አስመዝገብኩ የሚላቸውና እስከነ ችግሮቹም በተግባር ለምናያቸው የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጤቶች ሁሉ ባለቤቶቹ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ናቸው፡፡ ስለሆነም ብሄሮች ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የዘነጋ ልማት የለም። ሊኖርም አይችልም፡፡ ብሄረሰቦችን የዘነጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለም። ሊታሰብም አይችልም፡፡ የልማትም ሆነ የዲሞክራሲ መናሻውም ሆነ ግቡ ሃገሬው ነውና፡፡ ሃገሬው ደግሞ የተለያየ ባህል ቋንቋና ኃይማኖት ያለው በመሆኑ የሁሉንም እኩልነት መሰረት ያደረገ አንድነት ግድ የሚለን መሆኑ አያከራክርም፡፡
የትኛውም አይነት የሃገሪቱ ፖሊሲ መነሻ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሆናቸው እና እነዚህም የሚገለጹትና መልካቸውም ሆነ ልካቸው በደማቁ የሰፈረው በህገመንግስቱ ላይ በመሆኑ እለተ ቀኑን ማክበር የተያያዝነውን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ፤ይልቁንም ብሄርተኝነትን ሌላ መልክ በመስጠት ሊያደናብሩ የሚሹ ሃይሎችን ስለዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የሚኖረው ሚና አይናቅም።
የኢትዮጵያ ህብረብሄራዊ የፌደራል ስርዓት የተመሰረተበት እና የብሄረሰቦች ቀን የሚከበርበት አንዱና መሰረታዊ የሆነው መነሻ ያለፉት ስርዓቶች የፈጠሯቸውን የተዛቡ ግንኙነቶች ስለዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ግንዛቤ በማስጨበጥ ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እና ህዳሴያችን የምናውልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው።
ያለፉት ሥርዓቶች የፈጠሯቸውን ግንኙነቶች ማስተካከል ማለት የብሄሮች ብሄረሰቦችና የሃይማኖት እኩልነትን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ማንነቶች ቋንቋዎቻቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና ሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ማለት ነው፡፡ ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች መካከል የፈጠሩትን ጥርጣሬና መራራቅ በማስወገድ ኢትዮጵያ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገድባት የብሄር ብረሰቦችና ህዝቦች ቤት እንድትሆን በማድረግ በአይነቱ የተለየ እና አስፈላጊነቱ ጥርጣሬ ላይ የማይወድቅ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በመገንባት የኢትዮጵያን ህዳሴ ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝቦች ከታሪካቸው የወረሱትን በጎ ትስስር በማጎልበት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት ቃል ኪዳናቸውን የሚያድሱበትና የሚማማሩበት መድረክ ነው የብሄረሰቦች ቀን ክብረ በአል ።
የኢትዮጵያ ህዝቦች ባሳለፏቸው የዘውድና የደርጉ ስርዓቶች በሃገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠሩበት ፍፁም ፀረዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችን ማሳለፋቸው እሙን ነው፡፡ የወቅቱ ገዢዎችና አገልጋዮቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ዕድል ለመወሰን የተቀመጡ አምባገነኖች እንጂ ህዝብን ሊያገልግሉ የተቀመጡ እንዳልነበረም ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚጠበቀው አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ የጥቂቶቹን ልዕልና ያሰፈነውን ያለፈውን ስርዓትና ለውርሱ የሚተጉ ሃይሎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስወገድ የህዝቦችን ልዕልና ማረጋገጥ የሚችለውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት በመገንባት የኢትዮጵያ ህዳሴን ማፋጠን ነው።
የዚህን የህዝብ ልዕልና መሰረት ያደረገው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 8 ድንጋጌ ግልጽ ትርጉምም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት እንጂ በዚህና በዚያ ቢሉ ያልሰመረላቸው የግዴታ ኢትዮጵያዊነትን አቀንቃኞች የሆኑት የትምክህት ሃይሎች የሚሰብኩት የመገነጣጠል ስምምነት አይደለም፡፡
ስለአዲሱ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማሄስ ቀድሞ ስለነበረው የኢትዮጵያ ሁኔታ መጠነኛ ምልከታ ማድረግ ተገቢና ምክንያታዊም ያደርገናል። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶችን ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር መሆኑ የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በመገንባት የኢትዮጵያን ህዳሴ ማረጋገጥ ካስፈለገ ይህን ጭቆና በትግል በማስወገድ የራስ አስተዳደር መብትን ማረጋገጥ ብቻ በቂ እንደማይሆን አያከራክርም፡፡ ለዚህ ደግሞ ህገ መንግስቱን በማፅደቅ ሂደት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችና ክርክሮች ሁነኛ አስረጂዎች ይሆናሉ፡፡ እንደሚታወሰው የአንዳንድ ብሄሮች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ከጅምሩ የመገንጠል ጥያቄ አንስተዋል። አንዳንዶች ደግሞ ነባሩ የተዛባ ግንኙነት በፈጠረባቸው ስነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አመራረጥ ሳይቀር በስፋት መከራከራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ከመገንጠል በመለስ ያለውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማረጋገጥ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእርግጥ የሚያረካ እንዳልነበረ ነው፡፡ ካለፉት 25 ዓመታት ተጨባጭ ተሞክሮ የምንረዳው ጉዳይ የመገንጠል መብት የብሄርና ተጓዳኝ ጭቆናዎችን ለማስወገድ ዋስትና ተደርጎ እንደታየ፣ እንዲሁም ይህ መብት በህገ መንግስት ከተደነገገ በኋላ ጥያቄውን ሲያነሱ የነበሩ ሃይሎች በህብረቱ መቀጠል መቻላቸውን ነው፡፡
በዚህ አግባብ እና መሰረታዊ መነሻ 11ኛውን እና ህገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እና ህዳሴያችን በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ከመሪ ቃሉ አኳያ ለማሄስ ከህገ መንግስቱ ዓላማዎች የተወሰኑትን እና ይልቁንም የትምክህት ሃይሎች ስለ በዓሉ አከባበር የሚቆምሩባቸውን ነጥቦች በተለየ እና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመገንባት አንጻር በወሳኝነታቸው የተመለከቱትን እና የሚታወቁትን ድንጋጌዎች ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡
መንግስት ሁሉም ዜጎች የሃገሪቱን የተጠራቀመ እውቀትና ሃብት በፍትሃዊነት ይጠቀሙ ዘንዳ እንዲሰራ የተሰጠው ሃላፊነት መነሻው የብሄር ብሄረሰቦች ኢኮኖሚያዊ እኩልነት መሆኑ የመጀመሪያውና ስለዴሞክራሲያዊ አንድነት እና የኢትዮጵያ ህዳሴ ሊጤን የሚገባው መሰረታዊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቀድሞዋ የላሸቀች ኢትዮጵያ ሁነኛ ምክንያት የነበረ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ነው። ስለሆነም ይህንን የተዛባ ግንኙነት ለማስወገድ የሃገሪቱ ባለቤት የሆኑት ብሄር ብሄረሰቦችን ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ማረጋገጥ የግድ መሆኑ ስለታመነበት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 89 በግልጽ ተደንግጎ ዋስትና አግኝቷል ።
ህገ-መንገስቱ እጅግ ተራማጅ የሆኑ የህዝቡን እኩል ተጠቃሚነት የሚደንግጉ ማህበራዊ አለማዎችን ያስቀመጠውም ያለምክንያት ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በመገንባት የኢትዮጵያ ህዳሴን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁሉንም ዜጎች ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መገንባት እንዲቻል ለልማት መሰረት የሆኑትን የትምህርት የጤና አገልግሎት የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብ እና መሰል ማህበራዊ ዋስትናዎችን የማግኘት መብት በህገ መንግስቱ ተረጋግጦ ወደተግባር በመውረዱም ለህዳሴው ጉዞ መደላድል ፈጥሮልናል፡፡
ዴሞክራሲያዊ አንድነት መለያዋ የሆነውን አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመገንባት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በፕሮጀክቱ ባለቤትነትና መስራችነት እንዲሰለፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም አያከራክርም፡፡ ይልቁንም ቅድመ ሁኔታ ነው። በኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ እንደማንኛውም ጥሩ የጋራ ፕሮጀክት ሁሉ ሁሉም ህዝቦች እኩል የመሳተፍ እድል ተሰጥቷቸው እንደአቅማቸው ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በመደረጉ ነው የእኩል ተጠቃሚነት መብታቸውም የተረጋገጠው፡፡
ያለፈው ሂደት ተሸሮ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በአዲስ መሰረት ላይ ስትጀመር የዞሩ እዳዎችን ሁሉ አራግፋ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ካለፈው ታሪክ በመነሳት ባዕድና ቤተኛ የሚባሉ ህዝቦች የሉም፡፡በዚህ ምክንያት ካለፈው ውርድትም ሆነ የገናናነት ታሪክ በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዳሴ የሁሉም ህዝቦች ህዳሴ እና የሁሉም ህዝቦች የጋራ ፕሮጀከት ለመሆን በቅቷል፡፡
የኢትዮጵያን ህዳሴ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂና ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን ከማረጋገጥ አኳያ የተከተለው አቅጣጫና እስካሁን የተመዘገበው ውጤት ከላይ በተጠቀሰው መልክ እሰየው የሚያስብል ቢሆንም በዚህ ረገድ ያለው የህዝቡ ግንዛቤ ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑ ግን ሊዘነጋ የማይገባውና ይልቁንም የብሄረሰቦች ቀን ክብረ በአል ፋይዳዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደም የሆነውም ይህ መሆኑ ስለዚሁ ክፍተት ነው፡፡
ስለሆነም የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ስናከብር የኢትዮጵያ ህዳሴ የተመሰረተባቸውን መርሆዎች ይዘትና ውጤት በሰፊው በማስተጋባትና ብዝሃነታችን በብቃት የሚሰተናገድበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በማስመዝገብ መሆኑም ከበአሉ ፋይዳዎች እንደአንድና ወሳኝ ሁነት ሊወሰድ ይገባል።
አሁን በዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ላይ ተመስርቶ እየተገነባ በሚገኘው ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሁሉም ህቦች የጋራ የታደሰችዋ ሃገር መስራቾች ሆነዋል፡፡ ሁሉም ህዝቦች የጋራ ለሆነው የህዳሴ ጉዞ እኩል አስተዋጽኦ የማድረግ እድል ተሰጥቷቸው የአቅማቸውን ያህል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ነባራዊ ሐቆች ደግሞ ደጋግሞ (የብሄረሰብ ቀን የመሰሉ በአላትን በማስታከክ) ማስገንዘብና ለአስተሳሰብ ትግሉ መነሻ ማድረግ ብዝሃነትን በብቃት ለሚያስተናግደው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላውና ህገ መንግስታችን ከዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እና ህዳሴያችን አንጻር የሚገለጽበት ጉዳይ ከኃይማኖት ብዝሃነት ጋር የተያያዘውን የተዛባ ግንኙነት መመለሱን ከተመለከቱ መሰረታዊ ነጥቦች ጋር ነው። የተዛባው የሃይማኖት ብዝሃነት በህገ መንግስቱ አማካኝነት ከጅምሩ በሶስት አቅጣጫዎች ላይ ተመስርቶ ተመሳሳይ ስር ነቀል ለውጥ አንዲካሄድበት አስችሏል ፡፡
አንደኛው አቅጣጫ ማንኛውም ዜጋ የእምነት ነጻነቱ የተጠበቀ እንዲሆን መደረጉና ሁሉም እምነቶች እኩል መሆናቸው መረጋገጡን የሚያመለክተው ውሳኔ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግስትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውና አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ እንደማይገባ በጥብቅና በዝርዝር የሚያስቀምጠው የአለማዊ (የሴኩላሪዝም) መርሆ ነው፡፡ ሶስተኛው በኃይማኖቶች መካከል እኩልነት ብቻ ሳይሆን መቻቻልና መከባበር እንዲኖር የሚያዘው የህገ መንግስቱ መርህ ነው፡፡ እነዚህ በምንም መልኩ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በመገንባት የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ የመፍትሔው አካላት ናቸው፡፡ በብሔር ጥያቄ ላይ እንደታየው ሁሉ ብዝሃነታችንን ለማስተናገድ የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ቢቀመጥም ይኸው አቅጣጫ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ካልተጠነከረና ካለተተገበረ ታጥቦ ጭቃ ከመሆን የሚድን አይሆንም፡፡ የኃይማት ጉዳይም እንደ ብሔር ጉዳይ ሁሉ የኪራይ ሰብሳቢዎችና የትምክህት ሃይሎች የሚደበቁበት ዋሻ ነበርና ይህንን ዋሻ ለመደርመስ የሚያስችል አስተማማኝ መሰረት ባልተጣለበት ሁኔታ ስር ነቀል ለውጡ በጅምር ብቻ ተወስኖ የሚቀለበስበት ክስተት አይቀሬ ስለሆነ እንደ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ያሉ በአላትን በመጠቀም መስመሩን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
በዚህ መሰረት በብሄረሰቦች ቀን በመጀመሪያ ዜጎች በሚከተሉት እምነት ሳቢያ ባለቤት እና ባይተዋር የነበሩበት ያሉፉት ስርዓቶች የተዛባ አሰራር የእምነት ነጻነትን የኃይማኖት እኩለነትና መቻቻልን እንዲሁም የመንግስትና ኃይማኖት መለያየትን መሰረት በማድረግ በተጀመረው አዲስ የህዳሴ ጉዞ መናዱን የምንመሰክርበት እና የምንዘክርበት ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ባህልና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ከልማት ሂደቱ ጋር ተያይዘው እንዲስፋፉ በማደረግ ለአክራሪዎችና ለውጭ የጥፋት ሃይሎች የማይመች ሁኔታን ለመፍጠርም እድል የሚሰጠን ቀን ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው አኳኋን እና መሰል የበዙ ምክንያቶች ለ11ኛ ጊዜ የምናከብረውም የብሄረሰቦች ቀን ብዝሃነታችንን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት የመገንባት ትግሉ የህዳሴው ጉዞ አካልና በህዳሴው ጉዞ አጠቃላይ ስኬታማናት በይበልጥ ስኬታማ እየሆነ በሚሄድበት ሰላምን ለማረጋገጥ ብሎም የህዳሴው ጉዞ ሳይቆራረጥ ከዳር የሚደርስበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችለን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡