የአየር መዛባት ለሚፈጥረው ማነከስ ምርኩዝ

 

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ አቅም ከመጨረሻዎቹ ሃገሮች ተርታ ተሰልፋ ለዘመናት መኖሯ እውነት ነው። የሃገሪቱ መገለጫዎች አስከፊ ድህነት፣ መሃይምነት፣ በሽታ፣ ረሃብና ቸነፈር፣ የእርስ በርስ ጦርነት ወዘተ ሆነው ለዘመናት ኖረዋል። ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ግን ሃገሪቱን ለዘመናት የተጣባትን ድህነት ሰንኮፉን በመንቀል የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና የሃገሪቱን ገጽታ ለመቀየር ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በዚህም እመርታዊ ሊባል የሚችል ለውጥ ተመዝገቧል። ለዚህ ማሳያነት ከአንድ ዓመት በፊት በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራና የተገኘውን ውጤት መለስ ብለን እናስታውስ።

ሃገሪቱን ለዘመናት ተጣብቷት የኖረውን ድህነት መንቀል እና መካከለኛ ገቢ ያላት ሃገር ማድረግን ግቡ አድርጎ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን ከአንድ ዓመት በፊት በ2007 በጀት አመት መዝጊያ ላይ መጠናቀቁ ይታወቃል። የእቅዱ የአምስት ዓመታት አፈፃፃም፣ በአጠቃላይ ተግባራዊ ለማድረግ የተያዙ ዋና ዋና የኢኮኖሚና የልማት ግቦች አብዛኞቹን ማሳካት መቻሉን፣ እመርታዊ ለውጥ ያመጡ ታላላቅ የልማት ውጤቶች መገኘታቸውንም የእቅዱ አፈፃፀም ሪፖርተ በቀረበበት ወቅት መገለጹ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት ፈጣን፣ ዘላቂና መሠረተ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ከማሳካት አንፃር በመንግስት፣ በኅብረተሰቡና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም የእቅዱ አፈፃፀም ሪፖርት ይገልጻል። በዚህም መሰረት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግባራዊ በሆነባቸው ዓመታት፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ 6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ የ20 በመቶ፣ በአገልግሎት ዘርፍ የ10 ነጥብ 7 በመቶ አማካይ ዕድገት ተመዝቧል። ይህ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንፃር፣ እንዲሁም ከሌሎች ፈጣን ዕድገት ከተመዘገበባቸው ሀገራት ኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ የተሳካ ግብ ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል የአፈጻጸም ሪፖርቱ አመልክቷል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በዕቅድ እንደተያዘው ፈጣን፣ ዘላቂ፣ መሠረተ ሰፊና ፍትሐዊ የገቢ ክፍፍልን ያረጋገጠ ዕድገት ብቻ እንዳልነበረ የሚያመለክተው ሪፖርቱ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ያረጋጋጠም ጭምር እንደነበር ይህም በሌሎች ሃገራት ከተመዘገበው እድገት ልዩ እንደሚያደርገው ተመልክቷል። በአጠቃላይ የተመዘገበው ዕድገት በዕቅዱ በመሠረታዊ አማራጭ የተያዘውን የኢኮኖሚ ግብ ያሳካ ነበር።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የተመዘገበው ዕድገት በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር በዕቅዱ ከሚጠበቀው ግብ አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ ባይቻልም፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለው ድርሻ በ2003 ከነበረበት 10 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 3 በመቶ በማደጉ መጠነኛ መሻሻል ማምጣት አስቸሏል። በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት የተለየ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ሪፖርቱ አሳስቦ ነበር።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ወቅት የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረተ ሰፊና በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑ፣ በዚህም በትግበራው  አምስት ዓመታት የዜጎች የገቢ አቅም መሻሻሉ እንዲሁም የድህነት ምጣኔ በጉልህ እንዲቀነስ ማድረግ መቻሉን የእቅዱ አፈጻጻም ሪፖርት አስታውቋል። በተመዘገበው ፈጣን ዕድገት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ (በጊዜው የገበያ ዋጋ) ማደጉን ያመለከተው የአፈጻጸም ሪፖርት፤ በዚህም መሰረት በ2003 ዓ/ም ከነበረበት 396 የአሜሪካን ዶላር ወደ 632 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ማለቱን አመልክቷል። ይህም መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚያስችልም ጠቁሟል።

በዕቅዱ የትግበራ ዘመናት ተግባራዊ የተደረጉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለኅብረተሰቡ በርካታ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ማስቻሉን፣ የኅብረተሰቡንም የገቢ አቅም ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል። በዚህም መሠረት በ1997 የድህነት ምጣኔው 38 ነጥብ 7 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በ2003 ዓ/ም ወደ 29 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማለቱን በቤተሰብ ገቢና የፍጆታ ወጪ መረጃ ላይ ተመሥርቶ የተካሄደው የድህነት ዳሰሳ ጥናት ማመልከቱን አስታውቋል። ከ2004 ዓ/ም ወዲህም በተከታታይ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የድህነት ምጣኔው እንዲቀንስ ያስቻለ እንደነበረ፣ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ በተጠናቀቀበት በ2007 ዓ/ም ከድህነት ወለል በላይ የሚሸጋገሩ ዜጎች ቁጥር ግምት ውስጥ ሲገባ ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘውን የህዝብ ቁጥር ምጣኔ በግማሽ ለመቀነስ ወይም 22 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት መቻሉን አመልክቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተመዘገበው ዕድገት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን፣ በተለይም በከተሞች ውስጥ የነበረው ሥራ አጥነት ምጣኔ መቀነሱን አመልክቷል። ሆኖም የነበረው ድህነትና ሥራ አጥነት ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማፋጠን የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻልና የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ አሁንም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክቷል።

በ2008 በጀት ዓመት 2ኛው የእደገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ተጀመሯል። አሁን እቅዱ የመጀመሪያውን የትግበራ ዓመት አጠናቆ ሁለተኛውን ወደማጋመሱ ነው። ታዲያ ሰሞኑን የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን የ2008 በጀት ዓመት አጠቃላይ እድገትና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከት መረጃ ይፋ አድርጓል።

በዚህ መረጃ መሰረት የ2ዐዐ8 አጠቃላይ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት 8 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ እድገት ከ7 በመቶ በላይ በመሆኑ ሃገሪቱ አሁንም በፈጣን እድገት ላይ መሆኗን የሚያመለክት ቢሆንም፣ ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ከተመዘገበው ባለሁለት አሃዝ እድገት ጋር ሲተያይ ዝቅ ብሏል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም  የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜን ዕቅድ ትግበራ ዘመን  በየዓመቱ በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡ ይታወሳል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ሰሞኑን የፋ ባደረገው መግለጫ በ2007 ዓ/ም  በኤሊኖ ሳቢያ በሃገሪቱ የተከሰተው ድርቅ የግብርና ምርት ላይ ያስከተለው መቀነስ ለአጠቃላይ አመታዊ እድገቱ ዝቅ ማለት ምክንያት መሆኑን አስታውቋል። ድርቁ በአገሪቱ የመኸር ግብርና ምርት ላይ የ1 ነጥብ 3 በመቶ ቅናሽ እንዲኖር አድርጓል። ከድርቁ በተጨማሪ የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና የሸቀጦች ዋጋ መቀነስም ለእድገቱ መቀነሰ አስተዋጽኦ እንደነበረው ኮሚሽኑ አመልክቷል። የተመዘገበው እድገት ከተያዘው እቅድ አኳያ ቅናሽ ቢያሳይም ሀአገሪቱ ገጥሟት ከነበረው ችግር አንፃር ሲታይ ግን መልካም የሚባል መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

አገሪቱ ላለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት፣ መሰናክሎች ተቋቁማ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላት ኮሚሽኑ አስታውቋል። በ2008 በጀት ዓመት ግብርና በ2 ነጥብ 3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ20 ነጥብ 6 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ በ8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ማሳየቱን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 44 ነጥብ 4 በመቶ በ2008 በጀት ዓመት ወደ 36 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል። በአንፃሩ የኢንዱስትሪ ድርሻ በተጠቀሰው ጊዜ ከ10 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 16 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል። የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ከነበረበት 45 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 47 በመቶ ከፍ ብሏል፤ የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው።

በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ የትግበራ ዓመት አፈጻጻም በኢንደስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ አበረታች ውጤት ቢታይም የግብርናው ዘርፍ ላይ የታየው የእድገት ማሽቆልቆል አጠቃላይ እድገቱን ቁልቁል ስቦታል። የግብርናው እድገት ያሽቆለቆለው በተፈጥሮ መሰናክል ነው። የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶችና የተሻለ ቴክኖሎጂ ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ የ2007 ድርቅ ግብአቶቹንና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንዳይቻል መሰናክል ሆኗል።

የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ዘንድሮ በመሰብሰብ ላይ ከሚገኘው የመኸር ሰብል  በአጠቃላይ 320 ሚሊዮን ኩንታል ያህል ምርት ይሰበሳባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቋል። የታረሰው መሬት መጠነ 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል። በመኸር ወቅት በሃገሪቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ለግብርና ተስማሚ የሆነ የዝናብ ሥርጭት መኖሩ ለአርሶ አደሩ ከተሰጠው ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ተግባር ተኮር ሥልጠና ጋር ተዳምሮ ለምርታማነቱ ማደግ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልከቷል።

የዘንድሮ የመኸር ምርጥ ቀደም ሲል ከነበሩት አመታት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ነው፤ በአግባቡ ተሰብስቦ ለገበያ መቅረብ ከቻለ። ይሁን እንጂ የሃገሪቱ የግብርና ምርት አሁንም በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው። ዘንድሮ 320 ሚሊየን ኩንታል (ከመኸር ብቻ) መሰብሰቡ፣ በቀጣይ ዓመታት የተሻለ ወይም ተመሳሳይ መጠን ያለው ምርት ማምረት ለመቻሉ ዋስትና አይሰጥም። እስካሁን የሰው ልጅ ሊቆጣጣረው ያልቻለው የአየር ንብረት መዛባት  ካጋጠመ አርሶ አደሩ ራሱን መመገብ እንዳይችል በሚያደርግ ደረጃ ማሽቆልቆሉ አይቀሬ ነው። ይህ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሄ ይሻል። ቀዳሚው መፍትሄ ሃገሪቱ ያላትን ከፍተኛ የገጸ መድርና የከርሰ ምድር ውሃ የአጠቃቀም ዘላቂነቱን በሚያረጋግጥ አኳኋን ለመስኖ ልማት መጠቀም ነው።

እርግጥ ባለፉት አመታት በመስኖ ልማት ረገድ ከፍተኛ ተግባራት ተከናውነዋል። በቀጣይነትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል። ለዚህም የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ተነድፎ ተግባራዊ ተደርጓል። ላለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያ ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 116 አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተዋል። በዚህም 12 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት እንደተቻና ከ64 ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠማቂ መሆን እንደቻሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሰሞኑን ደግሞ ሁለተኛው ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ተደርጓል። ፕሮጀክቱ 108 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገልጿል። በቀጣይ 7 ዓመታት ስራ ላይ የሚውለው የሁለተኛው ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 145 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል። በዚህ ምእራፍ 150 የአነስተኛ መስኖ ልማት አውታሮችን ለመገንባት ታቅዷል። አውታሮቹ የምድር ቁፋሮ በማካሄድ፣ አነስተኛ ግድቦችን በመገንባት፣ የውሃ ቅየሳ፣ ምንጭ በማጎልበት እንዲሁም የጎርፍ ውሃን በማጠራቀም የሚከናወን እንደሚሆን መርሃ ግብሩ ይፋ በተደረገበት ስነስርአት ላይ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አሰታውቋል። ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 110 ወረዳዎች እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በአጠቃላይ የሃገሪቱን ግብርና አስተማማኝ ለማድረግ ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ቀዳሚው ተግባር ነው። በዚህ ረገድ ከላይ የተመለከቱት መረጃዎች ጥሩ ጅምር መኖሩን ያመለክታሉ። በአየረ ንብረት መዛባት ሊያጋጥም የሚችል የምርት መጓደል በመጠኑም ቢሆን ይሞላል። ይህን አጠናክሮ መቀጠል ደግሞ ችላ ሊባል የማይችል ጉዳይ ነው። የመስኖ እርሻ ተፈጥሮ በምታስከትለው የአየር መዛባት የሚፈጠረውን ማነከስ የሚደግፍ ምርኩዝ ነው።