መቻቻልንና መከባበርን የሚያንፀባርቅ በዓል

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን ይከበራል። ይህ በዓል የሀገራችን ህዝቦች የዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው መገለጫ የሆነው ህገ መንግስት የፀደቀበትን ቀን የሚዘክር ነው። ታዲያ በዓሉ የዘንድሮውን ጨምሮ ለ11 ጊዜያት በተለያዩ ከተማዎች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በሁሉም አካባቢዎች የነበሩት ድባቦች ህብረ-ብሔራዊነትን፣ አንድነትንና መፈቃቀድን የሚያበስሩ ነበሩ፣ ናቸውም።

በዓሎቹ ስለ ተለያዩ ባህሎች ይበልጥ ለመገንዘብ መልካም አጋጣሚንም ፈጥረዋል። በተለይም በየበዓሉ ሀገራችን የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ከግብ ለማድረስ መላው ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ቃል ኪዳናቸውን የሚያደሱባቸው መድረኮች ናቸው። በዓሉ የተለያዩ ባህላዊ ትእይንቶችን ከመመልከት ባለፈ፣ የህዝብ ለህዝብ ትውውቅንና ትስስርን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው።

በየጊዜው በተከበሩ በዓላት እነዚህን የመሳሰሉ ድንቅ የበዓሉን ትሩፋቶች ብንመለከትም ቅሉ፤ በዚህ ፅሑፌ ግን የበዓሉ አከባበር ስለ ተፈፀሙት ክንዋኔዎች ለመቃኘት አልሻም። ይልቁንም ከበዓሉ አከባበር ባሻገር፤ ዕለቱ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ዕውን ከማድረግ ባሻገር ከመቻቻልና ከመከባበር አኳያም ያለውን ፋይዳ ለመመልከት እሞክራለሁ።

እንደሚታወቀው ለበዓሉ መከበር ዋነኛው አነሳሽ ምክንያት የህገ መንግስቱ መፅደቅ ቢሆንም፤ በህገ መንግስቱ መፅደቅ ሳቢያ በህዝቦች መካካል ለዘመናት የነበረው የተዛበ ግንኙነት ከመሻሩም በላይ፤ በምትኩ መቻቻል፣ መከባበበርና አብሮ መኖር የሰፈነበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች መገለጫ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የቃል ኪዳን ማሰሪያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች። የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች።

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ፤ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ በመዳበር ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ወደሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የህዳር 29 ድል የመቻቻልና የመከባበር ተጨባጭ ፍሬ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ የመንግስት ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ ተረጋግጧል። ስርዓቱ በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያስገኘ ነው።

በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ህገ መንግስታዊ ስርዓት በህዝቦች መካከል መቻቻልንና መከባበርን ሊፈጥር ችሏል። ይህም ህዝቦች ያሰቡት የጋራ የኢኮኖሚ ስርዓትን የመመስረት ራዕያቸውን ዕውን የሚያደርግ ነው። በህዳር 29 በየዓመቱ የሚከበሩ በዓላትን ስናስብ በህዝቦች መካከል ያለውን የጠነከረ የመከባበርና በጋራ አብሮ የመኖር ትውፊታቸውንም እያሰብን ነው። በየበዓላቱ ላይ የምንመለከታቸው የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌቶች የመቻቻላችንና አንዳችን በሌላችን የመድመቃችን ሁነኛ አስረጅ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው የመላው ህዝባችንን ጥያቄዎች የፈታውና ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዋስትና የሰጠው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የፀደቀበት ዕለት በታላቅ ድምቀትና በልዩ ሁኔታ በየዓመቱ እየተከበረ የሚገኘው።

ይህ በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በታላቅ ድምቀት የሚከበረው ህዳር 29 ቀን የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ውበት ነው። ይህም ሊሆን የቻለው የሆነው ህዝባችን ከህገ መንግስቱ ጋር በብዙ መልኩ እጅግ የጠበቀ ቁርኝት ስላለው ነው። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ መንግስቱ ባለቤቶች ናቸው። ህዝቡም ህገ መንግስቱን ያቋቋመና የመንግስትን አወቃቀር የነደፈ ነው። ይህም በህገ መንግስቱ በግልጽ ሰፍሯል። ህዝቡ ባቋቋመውና የመንግስት መዋቅር እንዲሆን በወሰነው ስርዓት ውስጥ የተገነባው የመቻቻልና የአብሮነት ጉዞውም በአስተማማኝ ሁኔታ ዘልቆ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው።

ህዳር 29 ጸድቆ በሥራ የዋለው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለፈውን መጥፎ ታሪክ የሻረ ከመሆኑም በላይ፤ መጻዒ ዕድላቸውን ብሩህ ያደረገ መሆኑ አይካድም። ይህ ሃቅም ባለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት በገሃድ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም በሀገራችን ህዝቦች መካከል የተፈጠረው መቻቻልና መከባበር ብሎም በጋራ አብሮ የመኖር ትውፊት በሀገራችን ታሪክ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ማድረግ መየመቻሉን እውነት የምንመሰክርበት ነው።

በመሆኑም ይህን ታሪክዊ ድል የተቀዳጀንበትን ዕለት በልዩ ድምቀት ስናከብር ከመቻቻልና ከመከባበር ጋር የተፈጠረውን አብሮ በጋራ የመኖር ትውፊትንም በማሰብ ይሆናል። ዘንድሮም የሚከበረውን የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ቀን ስናስብ በዓሉን ከማክበር በዘለለ ሀገራችን ውስጥ እየተፈጠረ የሚገኘውን ጠንካራ የመቻቻልና አንደኛው ህዝብ ለሌላኛው የኩራቱ ምንጭ መሆኑን በማሰብ ጭምርም ነው።

እርግጥ ከዚህ በፊት በነበረው ታሪካችን ልዩነታችን ውበታችንና የኩራታችን ምንጭ ሆኖ አያውቅም። በታሪካችን ልዩነታችን የብዝሃነታችን መገለጫ ሳይሆን በህብረ- ብሔራዊነታችን ተሸማቅቀን በአሃዳዊ ሥርዓት እንድንማቅቅ መደረጋችን የትናንት ማንነታችን ሁመኛ መገለጫ ነው። ሆኖም ይህ መገለጫችን በህገ መንግስቱ ተሽሯል። ዳግም ላይመለስም የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መሰረት በሆኑት መቻቻላችንና መከባበራችን ተሽሯል። ያም ሆኖ ዛሬ አንዳንድ ወገኖች መቻቻላችንና መከባበራችን ብሎም በጋራ አብሮ መኖራችነ አደጋ ላይ እንደወደቀ በማስመሰል ሊያስረዱን ይችላሉ። ይህ ግን ፈፅሞ ሃሰት ነው። መቻቻላችንና መከባበራችን ይበልጥ እያደገና እየጎለበተ እንጂ የግንኙነታችን ችግር የሚሆንበት ምክንያት የለም።

እርግጥ እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ በህዝቦች ታሪካዊ ግንኙነቶች ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ሆኖም የዚህ ችግር መነሻም ይሁን መድረሻ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ ሊሆን አይችልም። በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የተዛቡ ግንኙነቶች በአንዳንድ የህዝቦችን መቻቻልና መከባባር ሊሸረሽሩ በሚችሉ ሃይሎች አማካኝነት የሚፈጠሩ ቢሆኑም፤ በመሰረታዊነት የስርዓቱ መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱ አይደሉም። ምክንያቱም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስርዓቱን በህገ መንግስቱ አማካኝነት ዕውን ሲያደርጉ ቀደም ሲሉ የነበሩ የተዛቡ ግንኙነታቸውን በማረምና ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድ የጋራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ለመመስረት ቃል በመግባታቸው ነው። ይህ ቃል ኪዳናቸውም አብሮነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክር እንጂ የሚያላላ አይደለም። እናም ይህ የአብሮነት ቃል ኪዳን የማይሸረሸር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። በየዓመቱ በሚከበረው የኢትዮጵያ ሀዝቦች የልደት ቀን በዓል ላይ የምንመለከተውም ይህንኑ ዕውነታ ነውና።

በአጠቃላይ በሀገራችን የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ስናከብር በበዓሉ ላይ ከምንመለከታቸው በርካታ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና አንዱ የሌላውን ወግና ባህል ከማወቅ አኳያ ካላው ፋይዳ ባሻገር፤ በህዝቦች መካከል ያለውን መቻቻልና በመከባበር አብሮ የመኖር ትሩፋትንም የምንዘክርበት ዕለት ነው።

ይህ ጠንካራ የግንኙነት መስተጋብርም በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸው ወደውና ፈቅደው ባፀደቁት ህገ መንግስት አማካኝነት ስለሆነ በዓሉን  ስናከብር፤ እነዚህን ነባራዊ ሀገራዊ ሃቆችንም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን ይኖርበታል። የመቻቻላችንና የመከባበራችን መሰረት ህገ መንግስቱ ነውና ህገ መንግስቱን ለማምጣት ዳግም የማይገኝ ህይወታቸውን ቤዛ ያደረጉ፣ አካላቸውን ያጎደሉና ንብረታቸውን ያጡ ውድ የህዝብ ልጆችን ሁሌም ልናስባቸውና ልንዘክራቸው ይገባል—የዛሬው መቻቻላችንና አብሮነታችን ፋና ወጊዎች ናቸውና።