ወጣቱና የነገ ተስፋዎቹ

                                                   

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንደ ሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ፤ ወጣቱም ከሀገሪቱ ልማት ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም ባለፉት 25 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት ወጣቱ እንደ ሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። ሆኖም ብዙ የሚቀሩ ጉዳዩች እንዳሉ ባለፉት ጊዜያት ታይተዋል። በተለይም የሀገራችንን ሰላምና ብልፅግና የማይሹ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች በቅርቡ በሀገራችን ውስጥ እንዲፈጠር ባደረጉት ሁከትና ብጥብጥ ተዋናይ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

ምንም እንኳን ወጣቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በተለያዩ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ታቅፎ በልማት ስራ ላይ ተሰማርቷል። ከድህነት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ የነገ ማንነቱን ብሩህ ለማድረግም እየተጋ ነው። ይህም የወጣቱ ተጠቃሚነት ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ገቢራዊ እየሆነ የመጣ እንጂ ዛሬ የታሰበ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው።

እርግጥ የሀገራችን ወጣት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተኮትኩቶ የበቀለና የዴሞክራሲን ምንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ እንዲሁም ነገሮችን በጥሞና የሚመለከት ከመሆን ባለፈ፤ የሥርዓቱ የነገ ተረካቢ በመሆኑም የሚበጀውንና የሚጠቅመውን መለየት የሚችል ኃይል ነው። ያም ሆኖ ግን ግማሽ ለሚሆነው ለዚህ የህብረተሰብ ክፍል የሚፈለገውን ያህል ስራ ማቅረብ ባለመቻሉ ለፅንፈኛ ዲያስፖራዎች መጠቀሚያ ሊሆን ችሏል። ያም ሆኖ ይህን ክፍተት መሙላት የሚገባ ይመስለኛል።

እነወ እስከሚገባኝ ድረስ ወጣቱ ከመንግስት የሚሻው ነገር ተጠቃሚነትን ነው። ይህን ለመከወንም መንግስት ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ሊውል የሚችል የ10 ቢሊዮን ብር መድቧል። ገንዘቡ የወጣቱን የስራ ፍላጎት ለማሟላት የተበጀተ ሲሆን፤ ከመሰንበቻው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባና ወጣቱም ተጠቃሚ እንደሚሆን ማዘዛቸው ይታወቃል። እርግጥ ይህ ሁኔታ ወጣቱ ከስራ ፈጠራ አኳያ የሚጠብቀው ብሩህ ተስፋ መኖሩን የሚያመላክት ይመስለኛል። ዳሩ ግን ይህን የወጣቱን ብሩህ ተስፋ ለማጣጣል የሚሞክሩ አንዳንድ የውጭ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎችን አሉባለታዎችን መስማት አይኖርበትም። ወጣቱ ያለበት ችግር በሀገሩ መንግስትና ህዝብ እንጂ በፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ምላሽ የማያገኝ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል።

እርግጥ ወጣቱ ክፍል በዕድሜ ለጋ ቢሆንም ይህን ዕውነታ ይዘነጋዋል እያልኩ አይደለም።  የሀገራችንን ብሩህ ተስፋ ለማጨለም ለሚሯሯጡ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን የሚሰሩ የከሰሩ ፖለቲከኞችንም ዓላማና ግብ አይገነዘብም እያልኩም አይደለም። በግልፅ ለመናገር ወጣቱ ተስፋውና መፃዒ ዕድሉ የተያያዘው ሀገረሪቱን ከሚመራው መንግስት እንጂ በቅጥረኝነት ተሰልፈው የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከሚጥሩ ኃይሎች አለመሆኑን ነው። እናም መጪው ጊዜ ከሀገሩ መንግስትና ህዝብ ጋር እንጂ ለአንድም ሰኮንድ ቢሆን ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የሚያስገኝለት ምንም ነገር አለመኖሩን ሁሌም ሊዘነጋው የሚገባ አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባሮች ተግባራዊ ሆነዋል። ለአብነት ያህልም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም በግብርና የሥራ መስኮች 2 ነጥብ 21 ሚሊዮን እንዲሁም ከግብርና ውጭ በሆኑ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች 2 ነጥብ 43 ሚሊዮን ወጣቶች ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል። እንዲሁም በ553 ወረዳዎች 1 ሺህ 684 የወጣት ማዕከላት በማስፋፋት በአሁኑ ወቅት ነባሮችን ጨምሮ የማዕከላቱ ቁጥር ወደ 2 ሺህ 284 እንዲደርስ ማድረግ ተችሏል። በእነዚህ ማዕከላትም ከ6 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህ ዕውነታም ወጣቱ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ወቅት ምን ያህል ተጠቃሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እርግጥ የወጣቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በልማቱ ልክ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን ዛሬም ከትናንቱ በተሻለ ሁኔታ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋዎች ተወጥነዋል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ለመስራት ታቅዷል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

የሀገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የሀገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ በኢንዱስትሪዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የሀገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እርግጥ እነዚህን ተግባራት ዕውን ለማድረግም ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የሚውልና ቀደም ሲል የጠቀስኩት የ10 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ በአፋጣኝ ወደ ስራ ለመግባትም ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም የወጣቱን የነገ ተስፋ የሚያለመልምና ከሀገሩ ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚ የሚሆነው በመንግስት ብቻ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ያም ሆነ ይህ ወጣቱ ይህን ብሩህ ተስፋ በሚገባ መመልከት ያለበት ይመስለኛል። ትናንት የነበረው ተጠቃሚነቱ ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚቋረጥ አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል ባይ ነኝ።

ወጣቱ በመንግስት ስትራቴጀዎችና ፓኬጆች እየተመራ የነገ ሰው ነው። የነገ ኢንጂነር፣ ሐኪም፣ ስራ ፈጣሪና ባለሃብት ነው። ይህ ህልሙ በፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የሚደናቀፍ አይደለም። ዛሬም እንደ ትናንቱ የነገ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሁከት ሃይሎችን ቀረርቶ መስማት አይኖርበትም። እርግጥ የሀገራችንን ዕድገት የማይሹ ሃይሎች ላለፉት ጊዜያት ልማታችንን ለማደናቀፍ ያልጣሩት ነገር አልነበረም። ግና በእነዚያ ዓመታት ወጣቱ የእነዚህን ሃይሎች የቁራ ጩኸት አልሰማም ነበር።

እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቱ የእነዚህን የሁከት ሃይሎች የአመጽ ጥሪንና ፀረ ልማት ዲስኩሩን ያልሰማው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግሮች መፍታት የሚችል ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያለው መሆኑን በመገንዘቡ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የወጣቱ አስተሳሰብ ከሁከት ሃይሎቹ የላቀ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ፅንፈኛው የሁከት ኃይል በየትኛውም ሀገር ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችንና ነባራዊ እውነቶችን በማጋነንና ብሶትን በማራገብ አመጽ ለመቀስቀስ  ብሎም ፀረ ልማት ተግባር ለመከወን አስቦ፤ በወጣቱ ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊና አስተዋይ ማንነት ሳቢያ ጨንግፎበታል፡፡ ይህ ሁኔታም ወጣቱ ላለፉት ዓመታት በእነዚህ ሃይሎች ዲስኩር የማይመራ እንደነበር የሚያሳይ ነው።

ሆኖም በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ወጣቱን ከተጠቃሚነት ጎራ ያፈናቀለውና በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ አላደረገውም። ይህ ሁኔታም ወጣቱ ለፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የተሳሳተ ተልዕኮ እንዲጋለጥ አድርጎታል።

ታዲያ ወጣቱ የነገ ተስፋው የለመለመና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በማወቅ ወደ ትናንቱ አመዛዛኝና ለሁከት ሃይሎች ፊት የማይሰጥ ማንነቱ መመለስ ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም የወጣቱ ችግር የሚፈታው ልማትንና ዴሞክራሲን በማሳለጥ ላይ በሚገኘው ህዝባዊ መንግስት እንጂ፤ ለውጭ ሃይሎች ባደሩ ፅንፈኛ የሁከት ኃይሎች ባለመሆኑ ነው።