ወጣቶች ስራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን የቁጠባ ባህልንም  ማዳበር ይኖርባቸዋል

 

                                                                          

 

የአገራችንን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ ስርዓታችንን ለማጎልበት፣ ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥ ወጣቱን ወሳኝ ሃይል ነው።  ባለፉት 13 ዓመታት በአገራችን በሁሉም ዘርፍ በሚባል መልኩ ለውጦች ተመዝግበዋል። መንግስት ወጣቱ በአገሪቱ ልማት ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን  የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ይችል ዘንድ የወጣቶች ብሄራዊ ፖሊሲ እንዲቀረፅና ተግባራዊ እንዲሆንም አድርጓል።  እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት ባይችሉም የበርካታ ወጣቶችን ህይወት መቀየር ተችሏል። እነዚህ ፖሊሲዋችና ስትራቴጂዎች እስካሁን ባለው  ሁኔታ የብዙዎችን  ህይወት   እንዲቀየር  ምክንያት  ሆነዋል። 

 

ለአብናት ያህል ወጣት እሱባለው በሃዋሳ የሚኖር ወጣት ነው። እሱና ጓደኞቹ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ተሰማርተው ተጨባጭ  ለውጥ ማስመዝገብ ከቻሉ ወጣቶች መካከል ናቸው። በሚሌኒየሙ መባቻ እሱና ጓደኞቹ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተመርቀው  በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጁ። በወቅቱ እሱና አራት ጓደኞቹ በየእንጨትና የብረታብረት ስራ ለመሰማራት ሲንቀሳቀሱ ምንም አይነት ካፒታልም ሆነ ልምድ እንዳልነበራቸው እሱባለው ይናገራል። ይሁንና  በወቅቱ  መንግስት የሚያደርግልንን  የገንዘብም ሆነ  ሌሎች ድጋፎች  በአግባብ ተጠቅመንበታል። ስንጀምር አካባቢ የተሰጠን ብድር ሁለት ሺህ ብር እና የመስሪያ ቦታ እንዲሁም የእንጨትና የብረታ ብረት አሰራርን በተመለከተ የተወሰነ ስልጠና ብቻ ነበር። በየጊዜው ድጋፍና ክትትል ይደረግልናል። የመስሪያ ቦታ ተመቻችቶልናል። የጀመርን አካባቢ የገበያ ትስስር እንዲኖርም እገዛ ተደርጎልናል።  እሱባለው አክም  ገንዘብ አያያዛችን  በጥንቃቄ የተሞላበት  በመሆኑ የብድር አከፋፈላችን በተቀመጠው ጊዜ መሰረት ነበር። በመሆኑም በየጊዜው ብድር የማግኘት ችግር አልገጠመንም።

 

በአሁኑ ወቅት ንብረታችንን ጨምሮ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል መያዝ እንደቻሉ እሱባለው ይናገራል።  እንደየስራችን  ደሞዝም ሆነ ጥቅማጥቅም እናገኛለን። እሱባለው  አያይዞም  የእነርሱ  ድርጅት ከራሳቸው አልፎ ለሶስት ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዛሬ የእነሱባለው ድርጅት እንደማንኛውም ማህበር የግለሰቦችንም ሆነ የማህበራትን እንዲሁም የመንግስትን የብረታብረትና የእንጨት ስራዎች እየተጫረቱ ይሰራል። ለእኛ ማህበር ስኬት ይላል  እሱባለው የገንዘብ አያያዛችን ጥብቅነት አንዱ ነው። በመሆኑም  መህበራት የቱንም ያህል ገቢ ቢኖራቸውም ቁጠባን ልምድ ካላደረጉ ዕድገት ማስመዝገብ አይችሉም። በመሆኑም  የማህበር አባላት የገንዘብ አያያዝንን ጥንቃቄ ማድረግና ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆን መቻል አለበት።

 

በአገራችን ወጣቱን በተመለከተ ያለው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተመቻቸ ነው ባይባልም መልካም ነገሮች እንዳሉት ግን  የሚካድ አይደለም። ወጣቱ አምራች ሃይል እንዲሆን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በመሰራትም ላይ ናቸው። ይሁንና የተፈለገውን ያህል ለውጥ መጥቷል ማለት አይቻልም። የተለያዩ ምክንያቶችን  መጥቀስ ቢቻልም በርካታ ወጣቶች ከስራ ውጭ ናቸው።  በአገራቸው ሰርተው መቀየር እንደሚቻል በተግባር እያሳዩ ወጣቶች መኖራቸውን ያህል አንዳንዶች ደግሞ አሁንም ወደ ውጭ ማማተራቸውን አላቆሙም። በአጭር ጊዜ ሀብትን ማካበት ይቻላል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ  በርካታ ወጣቶች  ህይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ወደተለያዩ አገራት በተለይ ወደመካከለኛው ምስራቅ በህገወጥ መንገድ በመሄድ ላይ ይገኛሉ። በእርግጥ ስደት አለም ዓቀፍ ክስተት ቢሆንም ህገወጥ ስደት እጅግ የከፋ ነው። የቱንም ያህል ቢሰራ ስደት ሙሉ ለሙሉ ይቆማል ማለት አይቻልም። ይሁንና ህገወጥ የሆኑና አጅግ አደገኛ የሚባሉ የስደት መገታት ይኖርበታል። 

 

በአገራችን አንዳንድ ወጣቶች በተሳሳተ ስሌት ለህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ራሳቸውን አጋልጠዋል።  እነዚህ ወጣቶች በአገራቸው ያለውን የስራ አማራጭና እድል  መጠቀም ሲችሉ በአቋራጭ ትከብራላችሁ ለሚሏቸው ህገወጥ ደላሎች ህይወታቸውን በመስጠት    የደላሎች የሀብት ምንጭ ማካበቻ ሆነዋል። በርካታ ወጣቶች  በተጨባጭ ከሚያዩት ይልቅ በደላሎች ለሚነገራቸው አማላይ ቃላቶች ተማርከዋል። በአገር ውስጥ ከነሙሉ ክብር ሰርቶ መለወጥ ይቻላል። በርካቶችም ተቀይረዋል። ከላይ ያነሳሁት የነእሱባለው ድርጅት  ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። እነሱባለው ከምንም ተነስተው አስር አመት ባለሞላው ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ባለቤት ሆነዋል። ከራሳቸው አልፈውም ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

 

አሁን ላይ መንግስት ወጣቱን በተመለከተ ፖሊሲዎቹንና ስትራቴጂዎቹን በማስተካከል ላይ ነው።  መንግስት የፖሊሲ ማስተካከያ እያደረገ እንጂ አዲስ ፖሊሲ ያወጣል ማለት አይደለም። መንግስት ወጣቶች በቡድን በመደራጀት መስራት የሚያስችል  አስር ቢሊዮን ብር  ሪቮልቪንግ ፈንድ  በመመደብ ወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው። ይህ ገንዘብ  ወጣቱ በብድር ወስዶ ራሱን የሚቀይርበትና የሚመልሰው መሆኑን ማወቅ አለበት። ዛሬ የተበደሩ ወጣቶች ውጤታማ ሲሆኑ የሚመልሱት ገንዘብ ለነገ ወጣቶች መነሻ ይሆናል። ተበድረው ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች ለመጪዎች አርዕያ ከመሆናቸው ባሻገር ለሌሎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የስራ እድል መፍጠር ይችላሉ። ይህ ሲሆን ነው አገር ልታድግና ልትለወጥ የምትችለው።

 

በኢትዮጵያ 30 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት ነው። ይህን በአግባብ መጠቀም የሚቻል ከሆነ ጸጋ ነው። ካልሆነ ግን በተቃራኒው መሆኑ አይቀርም።  በባለፉት ስርዓቶች በተለይ በደርግ ወቅት ወጣቱ ከፍላጎቱ ውጪ እየታፈነ በውትድርና እንዲሳተፍ ይደረግ እንደነበርና ማስታወስ አይከብድም። ዛሬ ሁኔታዎች  ተቀይረዋል።  በአሁኑ ወቅት በአገራችን  ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ከሃያ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ። በየዓመቱም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ከከፍተኛና ከቴክኒክና ሙያ  የትምህርት ተቋማትና  ይመረቃሉ።

 

ለእነዚህ ሁሉ ተመራቂዎችና ለሌሎችም ማለትም በየደረጃው በተለያየ ምክንያት ትምህርት መቀጠል ለማይፈልጉ አካላት ስራ መፈጠር የግድ ነው። በአገራችን በየዓመቱ እስከ አንድ ሚሊዮን  የሚሆን የስራ እድል ይፈጠራል። ይሁንና የስራ ፈላጊው ቁጥርና የተፈጠረው የስራ ዕድል ተመጣጣኝ አይደለም። ለዚህም ነው መንግስት ፖሊሲዎቹን ማሻሻል ያስፈለገው። በሰለጠነው አለም እንኳን አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ እድል በየዓመቱ መፍጠር እጅግ ከባድ በሆነበት ሁኔታ አገራችን ለእነዚህን ያህል ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ ነች።  

 

አሁን ላይ መንግስት  የስራ ፈላጊውን ቁጥርና የሚፈጠረውን የስራ ዕድል ለማመጣጠን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማሻሻል ላይ ይገኛል። ወጣቱም ስለስራ ያለውን አመለካከት መቀየር መቻል አለበት።  እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለመውሰድ አሁንም ለስራ ያለን አመለካከት ሊቀየር ይገባል።  በእርግጥ  ከባለፈው ጊዜ  አሁን ላይ  የተለወጡ ነገሮች አሉ። አንድ  ከአሜሪካ የተመለሰ ወዳጄ እንደነገረኝ አሜሪካ ስራ አገኘህ፣ ስራ አለህ ወይ ይባላል እንጂ ስራው ምንድን ነው ተብሎ አይጠየቅም። እኛ አገር ግን ስራ የማማረጥ አባዜ ክፉኛ ተጠናውቶናል። በመሆኑም  የስራ ባህላችን ለድህነት ከዳረጉን ምክንያቶች አንዱ ይመስለኛክ።

 

በአገራችን እጅግ በርካታ ልንሰራቸው የሚገቡ ፤ ነገር ግን ያልሰራናቸው ዕድሎች ለበርካቶቻችን የቢሮ ስራ ካልሆነ ሌላው ስራ ስራ መስሎ አይታየንም። በተለይ ተማርን የምንል ወገኖች። ለመለወጥ  መጀመሪያ  እያንዳንዳችን  ለስራ ያለን አመለካከት ሊቀየር ይገባል። ወጣቱ ስራ ሳያማርጥ መስራት መቻል አለበት። ከለይ የጠቀስኩት ከአሜሪካ የመጣው ወዳጄ አክሎ እንዳወገኝ  አገር ቤት የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እኛ አሜሪካ የምንኖር ኢትዮያዊያኖች የምንሰራውን ስራ ብታውቋቸው ኖሮ የስደት ኑሮ ምን ማለት እንደሆነ ትረዱት ነበር።  አገራችን እንኳን ልንሰራቸው ይቅርና ልናስባቸው የማንፈልጋቸውን ስራዎች ለመስራት እንሽቀዳድማለን።  ማንም የፈለገውንና የመረጠውን መስራት እስኪችል ያገኘውን በአግባብ መስራት ይኖርበታል ሲል ወዳጄ አጫውቶኛል።

 

ወጣቶች የለውጥ መሰረት ናቸው። በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሊጠናከር የሚችለውም ሆነ ልማታችን ዘለቄታዊነት የሚኖረው  የወጣቶች ቀጥተኛ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ከወጣቶች ጋር ባረደጉት ውይይት ላይ እንዳሉት "የወጣቶች ንቁና የተደራጀ ተሳትፎ የፈጣን ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ መሰረት  በመሆኑ ለወጣቱ ልዩ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው"።  በመሆኑም በአገራችን እስካሁን ለተመዘገቡት ስኬቶች ወጣቱ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ ቀጣይነት ለማረጋገገጥ  አሁንም ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል። ወጣቱ  የስራ ፈጣሪ ባቻ ሳይሆን ስራ አክባሪም መሆን መቻል አለበት። ስራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ስራ ማክበርም  ለመለወጥ ተገቢ ነው። 

    

መንግስት የነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስኬታማ የሚሆኑት በአስተግባሪዎች ጥረት ጭምር መሆኑንም ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው። በመሆኑም የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በየአካባቢው ያሉ የታችኛው የመንግስት አመራር አካላት ከወጣቱ ጋር ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል።  ለወጣቶች  ብድርና የስራ ቦታ ማመቻቸት፣ ስልጠና መስጠት፣ የገበያ ትስስር መፍጠር ወዘተ ማድረግ ብቻ ሳይሆን  ወጣቱ የጀመረው ስራ መስመር እስኪይዙ ድረስ  የቅርብ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው።  ከሁሉም በላይ ወጣቱ ከሚያገኘው ገቢ ላይ  የቁጠባ  ባህሉን ማዳበር  ይኖርበታል። የመለወጥ መሰረት ቁጠባ ነው። ቁጠባ ባህል ካልተደረገ ምንም ያህል ገቢ ቢያድግ መለወጥ አይቻልም። በመሆኑም ወጣቶች  የዕድገት መሰረት የሆነውን ቁጠባ  መልመድ መቻል ይኖርባቸዋል።