ነገረ- አባይ…

 

                                            

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ገንዘብና ጉልበት እየተገነባ የሚገኝ፣ የዘመናት ቁጭታችንን የሻረ፣ ለፀረ -ድህነት ትግሉ ትልቅ ሚና ያለው እንዲሁም የብሔራዊ ጥቅማችን መገለጫ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የግብጽ መንግስታት የአባይ ውሃን ለብቻ የመጠቀሙ ፍላጎታቸው ወልደት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ዕድገቱ ደግሞ ከወደ ዘመነ ቅኝ አገዛዝ ይቀዳል፡፡

ታዲያ ይህ ዕድገት ብቻውን የቆመ አልነበረም— “የአንድ ጠብታ ውሃ…” አባዜን በሰነድ አስደግፎ እንጂ፡፡ ዛቻና ፉከራን አስከትሎም እንደነበር እናስታውሳለን። ለተግባሩ ዋስትናነትም ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ ታዲያ ይህ ሴራ ሁሉንም አማራጮች የመከተል አቅጣጫን በመከተል ዘመናትን ተሻግሮ የእኛው ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልጆች የአይበገሬነት መንደር ላይም ለመገኘት ምንንም የፈራ አይመስልም፡፡

እርግጥ ግብጾች ኢትዮጵያን ለማዳከም ጦር መሰበቅ አንዳማያዋጣቸው ያውቃሉ— ስንቅ ጭነውና ጠመንጃቸውን ወልውለው በኢትዮጵያ ላይ መዝመት ምን ሊያደርስባቸው እንደሚችል ከቅድመ አያቶቻቸው በሚገባ ትምህርት አግኝተዋልና፡፡ እናም ሌላ ደካማ ጎን መፈለግ ነበረባቸው፡፡ ቅጥረኛ መፈለግን አማራጫቸው አደረጉ፡፡ በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ድርጅቶች በማፈላለግ የትጥቅና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ጣሩ፡፡ አማራጫቸውም ከንቱ አልቀረም—  ፍሬ ማፍራት ጀመረ፡፡ እናም ከአንዱ መንግስት ወደ ሌላው መንግስት እየተሸጋገረ ዛሬም የግብጾች ናይልን ለብቻቸው የመጠቀም አባዜ ዋነኛው የማሳኪያ ስልት ሆኖ አገልግሏል፡፡ ግና እንዴት?…ነገሩ እንዲህ ነው።…

…በአንድ ወቅት የግብጽ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጋማል አብዱልናስር ኢትዮጵያን ለማዳከም በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች በራሷ አቅም ምንም መስራት እንዳትችል የማድረግ ስልት ነደፉ፡፡ በዚህም መጀመሪያ የያኔዋ የዚያድባሬዋ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ እንድትሆንና ወደ ጦርነት በማምራት የአደጋ ተጋላጭነቷን ከፍ ለማድረግ ቻሉ፡፡ ይህም ሀገራዊ ትኩረቱ ወደ ልማት ሳይሆን ለልማት ጸር በሆነው ግጭት ላይ እንዲሆን አስገደደ፡፡ ታዲያ በዚህን ጊዜ የአባይ ውሃን የመጠቀሙ ጉዳይ ተዘነጋ ማለት ነው፡፡ ለጥቆም ሌላው የግብጾች ቅጥረኛ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ የቅጥረኝነቱን ሚዛን የደፋው ሻዕቢያ ነበር፡፡ ግብጾች የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሰላም ለማናጋት የሻዕቢያ ዋነኛ የትጥቅና የገንዘብ ምንጭ ሆነው አገልግለዋል፡፡

በእርግጥም ግብጾች ድጋፋቸውን ሲያበረክቱ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት መረጋገጥ ተቆርቋሪዎች እንደሆኑ ከማስመሰል አልቦዘኑም ነበር፡፡ ግና “ውስጡን ለቄስ” እንዲሉ አበው በወቅቱ የኤርትራ ህዝብ ችግር አስጨንቋቸው አልነበረም— የኢትዮጵያ አለመረጋጋት አባይን ለብቻ የመጠቀም ፍላጎታቸው ዋስትና መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንጂ፡፡

ዳሩ ግን የኢፈዴሪ መንግስት ከተቋቋመ ወዲህ የተከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር በሠላም የመኖር አቅጣጫና ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ዛሬ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያለው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ለግብጾች አሳሳቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያን የማተራመሱ ስትራቴጂያቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ለማዞር ተገድደዋል፡፡

እርግጥ የግብጽ መንግት ባለስልጣናት በሀገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሲያድኑ እንዲሁ በዘፈቀደ አልነበረም፡፡ ልክ እንደ ኤርትራ ህዝብ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርም ስላስጨነቃቸው አይደለም— የኢትዮጵያ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ አቅጣጫና ባህሪን በማጥናት አላማቸውን በቅጥረኝነት እንደሚያሳኩላቸው በማወቃቸው እንጂ፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የግብጽ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተስፋ የጣሉባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች በሙሉ ቢሆኑም ብሔራዊ ጥቅማችንን በፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያነት መቀየር ያልፈለጉት በዋናነትም በሀገር ውስጥ  የሚገኙ ፓርቲዎች ድርጊቱን ለመኮነን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከግብጽ ፖለቲከኞች ጎን በመቆም የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ በቴሌቪዠን መስኮት ብቅ ያሉም አልታጡም፡፡ ከሁለቱም ጎራ መሰለፋቸውን በማያሳውቅ ሁኔታ አቋማቸውን ያንጸባረቁም እንዲሁ፡፡ በእኔ እምነት የእነዚህ እሳቤዎች ዙሪያ የተሰለፉ፣ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እንደቆሙ አዘውትረው የሚገልጹ ድርጅቶች ገመናና ማንነት ከምንጊዜውም በላይ እርቃኑን በመውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ገመናቸውንም የሀገራችን ህዝቦች ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ላይ ተገንዝበውታል፡፡ በኤርትራ መንግስት አዝማችነት የሚላላኩት ብሎም በግብፅ ተቋማት የሚላኩትን የሁከት ኃይሎችን አንጥሮ አውቋቸዋል፡፡

እርግጥ በሀገራችን ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳን ባልለየ ሁኔታ የጥላቻ ድባብ ነግሶ እንደነበር የቅርብ ትዝታችን ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ በሚያስማሙ ጉዳዮች የጋራ አቋም ይዞ በሚያለያዩ ጉዳዮች ደግሞ ግልጽ አቋምን አንጸባርቆ መጓዝ እየተለመደ መምጣቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብጽ ተቋማትን መሰሪ ዓላማ ተከትሎ በመንግስትና በአንዳንድ የመንግስት ተቃዋሚ ድርጅቶች የተንጸባረቀው ተመሳሳይ አቋም የአባባሌን እውነትነት ያሚያጠናክር ማስረጃ ነው፡፡ ለነገሩ ሁኔታውን እንደ ኢትዮጵያዊ ሆነን ስናየው በአባይ ጉዳይ ሊኖረን የሚገባው አቋም አንድና አንድ ብቻ ነው—የሀገራችንን የውሃ ሃብት የመጠቀም መብታችን ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን፡፡

በእኔ እምነት በአባይ ወንዝ ሃብታችን የመጠቀም ጉዳይ መንግስትን ለሚደግፍም ሆነ ለሚቃወም ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም፡፡ ምክንያቱም የአባይ የሁላችንም የዘመናት ቁጭት ስለሆነ ነው፡፡ እርግጥ ይህን ለማለት የፈለግኩት እንዲሁ በዘፈቀደ እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ “ለምን?” ቢባል፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የፈጠረውን መነሳሳት ከማንም የተሰወረ ባለመሆኑ ነው፡፡

እርግጥም በዚህ ጉዳይ ላይ የተለየ አቋም ሊኖረው የሚችል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በመሆኑም ነው ዕድሜና ፆታ እንዲሁም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉም ዜጋ በሚችለው አቅም ሁሉ ገንዘቡንና ጉልበቱን በማበርከት ላይ የሚገኘው፡፡ ግድቡ የሁላችንም ስለሆነ ነው 11 ሺህ የሚሆኑ ሰራተኞች ሌት ተቀን ግድቡን ዕውን ለማድረግ እየተሯሯጡ የሚገኙት። እናም የግድቡ ጉዳይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ገመናቸው በጠራራ ፀሃይ ፈጦና ገጦ የወጣው የግብጽ ተላላኪዎች ሌላዎቹ ምልከታዎቼ ናቸው። እነርሱም ራሳቸውን “ግንቦት ሰባት” እና “ኦነግ” እያሉ የሚጠሩ የሽብር ቡድኖች ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ የእነዚህ ሽብር ቡድኖች እሳቤ ከመላላክ በተጨማሪ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ግና እዚህ ላይ ውድ አንባቢያን በእነዚህ እኩይ ሃይሎች ጠላት ተብየው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለቤት የሆነው የሀገራችን ህዝብ መሆኑን ልብ ይሏል!

ሆኖም ግድቡ የአሁኑንም ይሁን ቀጣዩን ትውልድ ከድህነት አረንቋ የሚያወጣ እንዲሁም የዘመናት የድህነት ታሪካችንን የሚቀይር መሆኑ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። እናም እሳቤያቸው ፍጹም የተሳሳተ አቅጣጫን የተከተለ ብቻ ሳይሆን በተጠናወታቸው የጠላትነት ስሜት የሀገራችንን ህዝብ ምኞት ማጨለም መሆኑን ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል—ምንም እንኳን ህዝብን በጠላትነት በመፈረጅ የሚገኝ ማናቸውም ጥቅም የትም ሊያደርስ የሚችል ባይሆንም፡፡

እርግጥም በምርጫ 97 ወቅት የቅንጅት አመራር ሆነው ህዝቡን እንመራዋለን ሲሉ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ራሱን “ግንቦት ሰባት” በሚል ስያሜ የሚጠራው የሽብር ቡድን መሪ በሆነው በዶክተር ብርሃኑ ነጋ አማካኝነት የሚከናወንና በተላላኪነት ኮሮጆን የመሙላት አባዜ የትም አያደርስም፡፡ በእኔ ዶክተር ተብዬው ግለሰብ በቀጥታ በሻዕቢያ መንግስት እየተመራ በተዘዋዋሪ ደግሞ የግብፅን ፍርፋሪ የሚቃርም ነው፡፡

ለነገሩ ሻዕቢያ የዶክተሩን የግብረ-ሽበራ ድርጅት አጋሩ ሲያደርግ ተላላኪ እንዲሆንለት እንጂ ስለወደደው አይደለም። ይህን ሃቅ ደግሞ ሁለቱም ያውቁታል— የተቆራኙት “በእከከልኝ ልከክልህ” ገመድ ነውና፡፡ ያም ሆነ ይህ እዚህ ላይ በአንድ ወቅት የሽብር ቡድኑ የሻዕቢያ ቅጥረኛ፣ ሻዕቢያ ደግሞ የግብጽ ቅጥረኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ የተቻለበት ሁነት መፈፀሙን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ እርሱም በአንድ ወቅት አውራምባ ታይምስ ምንጮችን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ በሻዕቢያ አማካኝነት ከግብፅ መንግስት 500 ሺህ ዶላር መቀበሉን ማተቱን ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህ ማረጋገጫም እነ ዶክተር ብርሃኑ እየሰሩ ያሉት ለግብጽ መንግስት መሆኑን ነው፡፡

አሁን ደግሞ ወደ ሌላኛው ተላላኪና በህዳሴው ግድብ ላይ የግብፅ ተቋማት አጋር ስለሆነው “ኦነግ” ስለተሰኘው የኤርትራ መንግስት ተላላኪ የሽብር ቡድን ላምራ። የሽብር ቡድኑ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ካይሮ ከተማ ላይ ባደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ከግብጽ መንግስት ጎን እንደሚቆም ታማኝ ቅጥረኝነቱን ሲያረጋግጥ በቴሌቪዥን መስኮት መታየቱን አስታውሳለሁ፡፡ በቅርቡም ለግብፅ ተቋማት ታማኝ ቅጥረኝነቱን ለማረጋጋጥ ሲማማል በአሳፋሪ ሁኔታ ተመልክተነዋል።

ለነገሩ በኢትዮጵያ ህዝቦች ስቃይ ከሚደሰት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያዊነት ይጠበቃል ብሎ ማሰብ ከዝንብ ማርን የመጠበቅ ያህል በመሆኑ የዚህ ተላላኪ ድርጅት ተግባር እምብዛም የሚገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወትሮም ቢሆን “ኦነግ” የጥፋት እንጂ የልማት ሃይል ሆኖ ስለማያውቅ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሽብር ቡድኑ በየከተሞች እየተዘዋወረ በፊሪ ዱላው የዜጎችን ህይወት በመቅጠፍና መሰረተ ልማትን በማውደም የሚወዳደረው ሃይል አልነበረም፡፡ ዛሬም ይህን እኩይ ሴራውን በግብፅ ተቋማት አማካኝነት በከሃዲነት ለመፈፀም መሞከሩ አይደንቅም—በህዝብ ዘንድ ተጠይነትን ከማትረፍ በስተቀር የሚያስገኝለት አንድም ነገር አይኖርም፡፡

እርግጥ እነዚህ በግብፅ መንግስታትና ተቋማት አማካኝነት ሲከናወኑ የነበሩ ‘የነገረ-አባይ’ ሰንካላ መንገዶች የፈጠሩት ነገር የለም። ሊኖርም አይችልም። በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብትና ላብ የሚገነባ በመሆኑ ለአፍታም አይስተጓጎልም፡፡

የግድቡ ግንባታ የህዝባችንን በራስ ሃብት የመልማትና የማደግ አንዱ ማሳያ በመሆኑም አይቆምም። የግብዕ ተቋማት ዛሬም በእነ ጋማል አብዱልናስር ያልተሳካ ሙከራ ቢጓዙም የግድቡ ባለቤት የሀገራችን ህዝብ በመሆኑ የሚስተጓጎልበት አንዳችም ምክንያት አለመኖሩን ማወቅ የሚኖርባቸው ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በፍትሃዊነት በሀገራቸው ሃብት እንዳይለሙ የሚያግዳቸው ህግም ይሁን አስተሳሰብ ቦታ ሊኖረው እንደማይችል መገንዘብም ያስፈልጋል እላለሁ።