ካልታገሉ አቅምን ማወቅ አይቻልም…

 

        
ኢህአዴግ ችግሮች በገጠሙት ጊዜ ሁሉ ሁኔታዎችን ገምግሞ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው በማድረግ ህብረተሰቡ የመፍትሄ አካልም እንዲሆን  የማድረግ አሰራርን ሲተገብር  የቆየ ፓርቲ ነው። ይህ  አሰራሩ ይመስለኛል ፓርቲውን ለስኬትና ህዝባዊ እንዲሆን ያስቻለው። ኢህአዴግ እስካሁን በአገራችን ከታዩ ፓርቲዎች በተለየ መልኩ የሚታወቀው በጠንካራ የግምገማ ባህሉ ነው። በኢህአዴግ ቤት ግምገማ አባላትን እስከ  እብደት ሊዳርግ  የሚችል ሂደት ነው።  ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ የሚሸነቁጠው የግምገማ ባህሉ ፓርቲውን ህዝባዊነት እንዲላበስ አድርጎታል።  
ስለፓርቲው የውስጥ አደረጃጀት ጠለቅ ያለ ዕውቀት አለኝ ባልልም፤  በአራቱም የኢህአዴግ እህትማማች ፓርቲዎች መካከል ጠንካራ  ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትና የመረዳዳት መንፈስ  ያላቸው እንደሆኑ መገንዘብ  ይቻላል። የኢህአዴግ አባላትን ማዋቅራዊ  ሰንሰለት ወይም ግንኙነት   ስንመለከት   የጌታና የሎሌ  እንዳይሆን ተደርጎ የተመሰረተ ፓርቲ በመሆኑ    በድርጅቱ ውስጥ  ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አሰራር  የነገሰበት  ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ  በሁሉም ዘርፍ ማለትም  በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ  ዘርፎች አገራችንን ወደተሻለ ከፍታ ማምጣት ችሏል። ይህን ማለት ያስቻለኝ ፓርቲው  በራሱ ውስጥ ዴሞክራሲን ማስፈን የማይችል ኖሮ  በአገር ደረጃ ዴሞክራሲን ሊያሰፍን ከቶ አይቻለውም።    
ኢህአዴግ እስካሁን የገጠሙትን ተግዳሮቶች ሁሉ ከህዝብ እንዲደበቁ አላደረገም። ይልቁንም ችግሮች በተፈጠሩ ጊዜ ሁሉ ችግሮችን ህዝብ እንዲያውቃቸው በማድረግና ህብረተሰቡ የመፍትሄ አካል እንዲሆን በማድረግ የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ለዚህ እንደአብነት የሚጠቀሰው  የኢትዮ-ኤርትራ  ጦርነት ካበቃ ብኋላ  ፓርቲው የገጠመውን የውስጥ ችግር  በተሃድሶ በመፍታት  አገራችን በአለም እጅግ ፈጣን የተባለ   ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አሃዝ  የኤኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ  ላይ ትገኛለች።  
አሁንም ኢህአዴግ በጥልቀት በመታደስ አሁን የገመውን ችግር በመፍታት ሁኔታውን ወደ መልካም አጋጣሚነት ይቀይረዋል የሚል እምነት አለኝ።   ኢህአዴግ  ያሉበትን ድክመቶችና ችግሮች ከህዝብ እንዲደበቁ አላደረገም። ይልቁንም ችግሮቹን  ራሱ  ነቅሶ ከማውጣት ባሻገር ህብርተሰቡ  እንዲያመላክተው በማድረግ ላይ ነው።  ይህ የሚያሳየው ድርጅቱ  የገጠመውን ችግሮች  በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም እንዳለው ወይም  በራሱ እንደሚተማመን የሚያረጋግጥ ነው። 
አንዳንዶች  ኢህአዴግ የቀድሞው   ጥንካሬው  የለም አመራሮቹ ተከፋፍለዋል ወዘተ  የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ።  ኢህአዴግ የቀድሞው  ጥንካሬው  የከዳው ፓርቲ ቢሆን ኖሮ  ችግሮችን  ራሱ ነቅሶ አውጥቶ  ለህዝብ ይፋ አያደርግም ነበር። ኢህአዴግ በአስርኛው ድርጅታዊ ጉባዔው ላይ የኪራይ ሰብሳቢነትና በስልጣን የመባለግ ችግሮችን ነቅሶ ያወጣው ራሱ ፓርቲው ነው።   ከባለፈው አመት ጀምሮ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን  በመለየት  በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይም ይገኛል። ይሁንና እየተወሰደ ያለው እርምጃ መሰረታዊ ለውጥ አላመጣም በሚለው ሃሳበ  ሁላችንንም ያስማማል።   
ኢህአዴግ አገሪቱን መምራት ከጀመረበት ባለፉት  22 ዓመታት (በምርጫ አሸንፎ) በአገራችን ተጨባጭ ለውጦችን በየዘርፉ ማስመዝገብ ችሏል።   የፓርቲው መስመር የአገራችንን ዘላቂ ሠላም የሚያስጠብቁ፣ የገጠርና የከተማ ልማትን የሚያፋጥኑ፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታን የሚያሳድጉ፣ በብዝሃነት ላይ የተገነባውን የአገራችንን ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ በመሆናቸው አገራችን  ሰላም እንድትሆን አድርጓታል።  ፓርቲው   ከህዝባች ጋር ተማክሮና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን የተላበሰ  በመሆኑ  የተመዘገቡ ለውጦች ሁሉ የህዝብን ይሁንታ ያገኙ ናቸው። ድርጅቱ ከህዝብ ጋር ተመካክሮና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ያዳበረ በመሆኑ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ የሚያከናውናቸው አንዳችም ነገር የለም።  ኢህአዴግ  ለህዝብ ይጠቅማሉ  ወይም ለአገር ዕድገት የሚያመጡ  ፕሮጀክቶች እንኳን ቢሆኑ  ህብረተሰቡ እስካልፈለጋቸው  ድረስ እንዲሰረዙ አድርጓል። 
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ችግሮች ለማለፍ  የሚያስችሉ ሂደቶችን  “በጥልቀት መታደስ”  በሚል  ንቅናቄ  የድርጅቱ አባላት  በመገምገም ላይ ናቸው።  ይህ  እየተካሄደ ያለው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ  ውጤታማ  የሚሆነው  በህዝብ ተሳትፎ ሲታጀብ  በመሆኑ  ኢህአዴግ  ህብረተሰቡን  ለማሳተፍ  እያደረገ ያለው ጥረት መልካም ነገር ነው። ይህም ሲባል ኢህአዴግ  የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶችን ለመለየት እያደረገ ያለውን ጥረት  በህብረተሰቡ መደገፍ አለበት።  
ኢህአዴግ በቆየ  ጠንካራ የግምገማ ባህሉ ራሱን ማስተካከል የሚችል ድርጅት እንደሆነ በተግባር አሳይቷል።  ባለፉት 28 ዓመታት ፓርቲው የገጠሙትን ተግዳሮቶች በሙሉ በድል መወጣት የቻለ፣ ጠንካራ ድርጅታዊ አሰራር የነገሰበት፣ ህዝባዊነትን የተላበሱ አመራሮችና አባላት ያሉበት  ፓርቲ ነው። ይህ ሲባል ሁሉም የፓርቲው አባላት ለመሰዋዕትነት  የበቁ ናቸው ማለት ግን አይደለም። እንደውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀላል የማይባሉ  አባላቱ  የቡድንተኝነት አሰራርን  ያነገሱ፣  በግል ጥቅም የናወዙ   ሆነው ታይተዋል።  እንደነዚህ ያሉ  አባላቶች ናቸው ኢህአዴግ  የቀድሞ ህዝባዊነቱ ደብዝዟል እንዲባል ያደረጉት። ፓርቲው እነዚህን ጥገኛ ሃይሎች የማጥራት ስራ መስራት አለበት።
በድርጅቱ ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ አባላት እንዲህ ይሁኑ እንጂ ኢህአዴግ አሁንም  ጠንካራ ህዝባዊ መንፈስ የተላበሰ ድርጅት ነው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  ኢህአዴግ ውስጡ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ካላሰፈነ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማምጣት አይቻለውም።  ኢህአዴግ አገሪቱን መምራት ከጀመረ  ሂዜ አንስቶ  ለአገራችን ዘላቂ ሰላም ዋስትና ሊሆን የሚችል የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በአገራችን  እንዲጎለብት፣ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን አውቀው በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ እንዲሁም  የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም አድርጓል። ኢህአዴግ እንዲህ ያለ ስርዓት መከተል በመቻሉ  የአገራችን ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ  ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት  እንዲፈጠር አድርጓል። 
ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙትን ፈተናዎችም ልክ እንደትላንቱ ሁሉ በህዝባዊነትና በጽናት  አልፎ፣ ህዝብን የሚጠቅሙ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አመራር ለመስጠትና የህዝቦችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል  በጥልቀት የመታደስ ድርጅታዊ ንቅናቄ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ተጀምሮ በየደረጃው በመውረድ ላይ ይገኛል። ይህ ሂደት ውጤታማ የሚሆነው ደግሞ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲታከልበት ብቻ ነው። 
እስካሁን ኢህአዴግ ያስመዘገባቸው ድሎች በሙሉ የተመለከትን እንደሆነ  በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየባቸው ናቸው። አሁንም አገራችንን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለመውሰድ ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት ይኖርባቸዋል።  በጥልቀት የመታደስ መነሻም መድረሻም የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የአገራችንን ዕድገት ማፋጠን ነው።  የመንግስት ስልጣን  ህብረተሰብን ለማገልገል እንጂ ስልጣንን መከታ አድርጎ የግል ፍላጎት ለማሳካት መሞከር ተጠያቂነትን ማስከተል መቻል አለበት። 
ኢህአዴግ  የጀመረው በጥልቀት የመታደስ ሂደት ድርጅቱን ለበለጠ ውጤት ሊያተጋው ይገባል። እስካሁን የተመዘገቡ  ስኬቶችን የበለጠ ማጠናከር  እንዲሁም ድክመቶችን ደግሞ በማረምና በማስተካከል የአገራችንን ልማት ማፋጠንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ማጎልበት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን መቻል አለበት።  
የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል   የተሻለ አፈጻጸም ያመጣሉ ያላቸውን  ሃላፊዎችን መንግስት በመመደብ ላይ ይገኛል። ከፌዴራል እስከቀበሌ ድረስ የተሻለ አፈጻጸም ሊያስመዘግቡ ይችላሉ የተባሉ ሃላፊዎችን በመመደብ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንደሚቻል ቢታመንም  በዚህ ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት ግን አይቻልም። መልካም አስተዳደር ማስፈን የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው። ህብርተሰቡም ዋንኛ ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል። ህብረተሰቡ መብቱን ጠያቂ ሲሆን አገልግሎት ሰጪውም ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራል። ከዚህ ባሻገር በኪራይ ሰብሳቢነት የተሰማሩ አመራሮችም ተጨባጭ ማስራጃ እስከተገኘባቸው ድረስ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚዲያዎች ማስታወቃቸው ኢህአዴግ የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ምን ያህል ቁርጠኝነት እንዳለው የሚያመላክት ነው። በትላንት ማንነት አገር ልትመራ አትችልም። በመሆኑም ሁሉም የኢህአዴግ አባላት የህዝብን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማይደግ  ይጠበቅባቸዋል።