አንድ የምወዳትን የታላቁን መሪ አባባል በማስታወስ ጽሁፌን ልጀምር። “…ዋንኛ ጠላታችን ድህነት ነው፤ ድህነትን ማሸነፍ ከቻልን ሁሉም ነገር መፍትሄ ያገኛል”። እጅግ ድንቅ አባባል ነው። እንደኔ ይህ ትውልድ ውጤታማ ትውልድ ነው። ምክንያቱም ለአገራችን የኋልዮሽ ጉዞ ዋንኛ መንስዔ የሆነው ድህነት መሆኑ ስለታወቀ ዘመቻ ተከፍቶበታል። በዚህም በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የህዳሴውን ግድብ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት “ይህች ድንጋይ ለእኔ፤ የውርደት ካባን ማራገፍ የጀምርንባት ድንጋይ ነች›› ሲሉ ተናግረው ነበር። አዎ ያቺ ድንጋይ የአንድ የታሪክ ምዕራፍ መዝጊያና የአዲስና የይቻላል መንፈስ በህዝቦች መስረጽ የጀመረበት ታሪካዊ ድንጋይ ነች፡፡ ከዚያች ድንጋይ በይፋ መቀመጥ በፊት እና በኋላ ነገሮች በእጅጉ ተቀያይረዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ሁለት ትላልቅ ነገሮችን በአገራችን ላይ ፈጥሯል። የመከመሪያው እኛ በራሳችን “እንችላለን” የሚል ስሜት እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዓለም ህብረተሰብ ስለእኛ የነበረው ግምት መቀየር የጀመረበት ወቅት ነው።
ይህ ትውልድ የመሰዋዓትነት ትውልድ ነው። ምክንያቱም ለአገራችን ዕድገት መሰረት የሆኑት በርካታ ለውጦች መመዝገብ የጀመሩት በዚህ ትውልድ ነው። ለአብነት አገራችን በህዝቦች ይሁንታ እውን የሆነ ህገመንግስት ባለቤት መሆን ችላለች። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት ክልሎች መመስረት እንዲሁም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ጠንካራ ፌዴራላዊ ኢትዮጵያን መገንባት ችለዋል። ከዚህም ባሻገር በአለም ቀጣይነት ያለውና ፈጣን የሚባል የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የተጀመረው በዚሁ ትውልድ ነው።
ትላልቅ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ በርካታ ፕሮጀክቶች ለአብነት አገር አቋራጭ አውራ መንገዶች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የሃይል ማመንጫጨዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ ኤርፖርቶች፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ ወዘተ፣ መገንባት ጀምረዋል። እነዚህ ለውጦች ለአገራችን ቀጣይ ትውልድ መሰረቶች ናቸው። ይህ ትውልድ እነዚህን ሁሉ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ የቻለው እዚህ ግባ የሚባል እርሾ ሳይኖረው ነው። ከቁልቁለት ጉዞ የተነሳችን አገር ወደ ከፍታ ለማውጣት ሁሉም ዜጎች የበኩላቸውን በማበርከት ላይ ናቸው።
ይህ ትውልድ ወገብ የሚያጎብጡ እቅዶችን በማቀድና በመተግበር ለቀጣዩ ትውልድ መደላድል ለመሆን የቆረጠ ትውልድ ነው። የዘመናት ቁጭት የሆነውን ታላቁ ወንዛችንን ማልማት የጀመረው ይህ ትውልድ ነው። ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው እኩልነትና ፍትህ ተነፍጎት በኖረና ነጻነቱን በሃይል ባስከበረው በዚህ በኛው ትውልድ መሆኑ ትልቅ ኩራት ሊሰማን ይገባል፡፡ ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ይህ ትውልድ የመሰዋዓትነት ትውልድ ነው። ምክንያቱም በአገራችን እነዚህን ሁሉ በርካታ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው ይህ ትውልድ ተደላድሎ መኖር ሳያምረው ያገኘውን ነገር ሁሉ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ማፍሰስ በመቻሉ ነው።
ኢትዮጵያ በስፋት ያላት ሐብት በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ሃይል፣ መሬትና ውሃ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ለማልማት ያለው አማራጭ እነዚህን ማቀናጀት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ እጅግ ፈታኝ ስራ ነው። በርካታ ታዳጊ አገራት የመልማት እድላቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይሁንና ይህ ትውልድ ኢትዮጵያ አሏት የሚባሉትን የተፈጥሮ ሃብቶች ብቻ በማቀናጀት ለውጥ እያመጣ ነው። በርካታ የአለም አገራት ፈጣን እድገት ማስመዝገብ የቻሉት በተፈጥሮ ሃብት በተለይ በነዳጅ ላይ በመመስረት ነው። የአገራችን እድገት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። አገራችን ፈጣን እድገት ማስመዝገብ የቻለችው ኢህአዴግ በቀረጻቸው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነው። እውነታው ይህ ነው።
ኢትዮጵያ የውሃ ሃበቷን ለዘመናት ሳትጠቀምባቸው ቆይታለች። ለረጅም ዓመታት ትልቁን የውሃ ሃበቷ የሆነውን አባይን ለማልማት የተለያዩ ጥረቶች ስታደርግ ብትቆይም ሊሳካላት አልቻለም፡፡ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም በዋንኝነት የሚነሳው ግን አባይን ለማልማት የሚያስችል ካፒታል በሐገር ውስጥ መፍጠር አለመቻሏ ነው፡፡ አዎ አባይን ለማልማት ሁለት አማራጮች ብቻ ነው ያሉት አንድ የውጭ ዕርዳታ ማግኘት አሊያም በራስ ሃይል መስራት ናቸው። ይሁንና ሁለቱም አማራጮች የማይታሰቡ በመሆናቸው አባይ ለዘመናት ከዜማ በዘለለ የፈየደልን አንዳችም ነገር አልነበረም።
ይሁንና አገራችን ባለፉት ጥቂት አመታት ማስመዝገብ በቻለችው ፈጣን ዕድገት የዘመናት ህልሟን ማሳካት ችላለች። ኢትዮጵያ በራስ አቅም እንዲህ ያለ ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለመስራት መነሳቷ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት የሚኖረው ትርጉም ትልቅ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ የመሰረት ድንጋገይ በተጣለበት ወቅት “… እኛው የፋይናንስ ምንጭ፣ እኛው አናጢ፣ እኛው ግንበኛ፣ እኛው መሃንዲስ ሆነን….ግድቡን እንገነባዋለን” ሲሉ ነበር ታላቁ መሪ የምስራቹን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበሰሩት። አዎ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ከዚህ የሚልቅ የምስራች የለም።
አገራችን የህዳሴውን ግድብ እቅድ ይፋ ባደረገችበት በዚያን ወቅት ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ወዳጆችና የልማት አጋሮች ጭምር እንዲህ ያለ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በታዳጊ አገር የፋይናንስ ምንጭና የግንባታ ልምድ የማይታሰብ በማለት ተሳልቀውብን ነበር። እንደእኔ ያን አስተያየት ቢሰጥ የሚገርም አልነበረም። ምክንያቱም ለዘመናት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የኖረች አገር ያን አይነት እቅድ ታሳካለች ብሎ ማሰብ የሚከብድ ነበር። ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፕሮጀክቱን ከ60 በመቶ በላይ ማድረስ ችለዋል። ማንም ሊቀለብሰው እንደማይችልም ዓለም እንዲረዳው አድርገዋል።
የሕዳሴው ግድብ በአባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች ውስጥ ትልቁ ግድብ እንጂ ሌሎች ግድቦችም አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በአባይ ተፋሰስ ሊሰሩ የሚችሉ እና በዕቅድ የተያዙ ሌሎች ግድቦች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በለሙያዎች እንደሚናነገሩት የህዳሴው ግድብ ለመጪዎቹ መቶዎች ዓመታት ሊያገለግል እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ያለ ግድብ ከመሆኑ ባሻገር በሁሉም መስፈርት አዋጪ የሆነ ፕሮጀክት ነው። ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ተጠልቆ የማያልቅ የነዳጅ ሃብት በመሆኑ የእኛ ትውልድ ለቀጣይ ትውልዶች ከሚያስረክባቸው ቅርሶች መካከል አንዱ የታሪክ አሻራ ነው።
አባቶቻችን የጥቁር ህዝቦች መመኪያ የሆነውን የአድዋ ድልን ትተውልን ሄደዋል። እኛ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እናስረክባቸዋለን። ሁላችንም በየፈርጁ እንዘከራለን። በአድዋ ድል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ታሪካዊ ክስተት ነበር። በተመሳሳይ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ነው። የእኛ ትውልድ ለዘመናት የቁልቁለት ጉዞ ስትንደረደር የነበረችን አገር በሁለት እግሯ እንድትቆም ማድረግ የቻለ ትውልድ ነው፡፡ እንደእኔ እንደኔ ይህ ትውልድ በአገራችን የአይቻልም መንፈስን መስበር የቻለ ጀግና ትውልድ ነው፡፡
ይህ የእኛ ትውልድ ከቀዳሚው ትውልድ ድህነትና የቁልቁለት ጉዞን የተረከበ ቢሆንም ለቀጠቀዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ እየጣረ ያለ ጠንካራ ትውልድ ነው፡፡ እንደእኔ እንደኔ ይህን ትውልድ ከቀዳሚዎቹ ትውልዶች ስኬታማ እንዲሆን ያደረገው ለውድቀት የዳረጉ ምክንያቶችን ለይቶ ማወቁ ይመስለኛል። በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ ዋንኛ ጠላታችን ድህነት ነው፤ ድህነትን ማሸነፍ ከቻልን ሁሉም ነገር ተወጣነው ማለት ነው ብለው ነበር። አዎ ሌሎች ጠላቶቻችን ሁሉ በአንድ ላይ ቢደመሩ በእርግጥ ከድህነት የሚበልጡ አይደሉም። እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ድህነትን ለማሸነፍ ጦርነት ገጥመናል፤ በርካታም ተጨባጭ ለውጮችን በማስመዝገግብ ላይ ነን። አሁንም እኛ ስራ ላይ ነን። በራችንን ዘግተን ስራችንን ማፋጠን አለብን።
የጥንት አባቶቻችን በአድዋ ያስመዘገቡት ዘመን ተሻጋሪ ድል አገራችን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ኩራት ለመሆን አብቅቷታል። ለምዕራባዊያኖችም ጥሩ ትምህርት ሰጥታቸዋለች። የእኛ ትውልድ ደግሞ ለአፍሪካውያንና ለሌሎች መሰል አገራት ኢትዮጵያችን በራሷ የልማት መንገድ ተጉዛ ያለምንም የውጭ እርዳታና ብድር ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን መስራትና መለወጥ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል። ኢትዮጵያችን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ብቻ ሳትሆን የልማት አብነትም እየሆነች ነው።