አባይ ከልማት ተጠቃሚነት ባሻገር…

 

 

የአባይ ውኃ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ህዝቦች ከድህነት ለመውጣት ለሚያደርጉት ጥረት ወሣኝ ሚና የሚኖረው የተፈጥሮ ሀብት ነው። ሆኖም ላለፉት ዘመናት ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘልቀዋል። ይልቁን አባይ የዘመናት የህዝብ ቁጭትና እንጉርጉሮ ሆኖ ቀርቶ ቆይቷል። በአባይ ውኃ ልማት የማይታሰብ ተደርጎ መደምደሙም የማይረሳ ጉዳይ ነው።  

 

የኢትዮጵያን ህዝብ አባይን ከሚያህል ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቃሚ ባለመሆኑ የተነሳ ለዘመናት በእያንዳንዱ ዜጋ ሲብሰለሰል የኖረው ቁጭት ብቻ ነበር። ያ ቁጭት ዛሬ መቋጫውን አግኝቷል። አባይ ከዚህ በኋላ የቁጭት እንጉርጉሮ የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል – አባይ ዳቦ መሆን ጀምሯልና። 

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ተስፋ ላይ ይገኛል። ለዘመናት ሲንጠው የኖረውን  ድህነት ለማራገፍ በአንድነት ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል። ከድሀነት የመውጣት ተስፋው ለምልሟል። ለዚህ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።  አባይ የአገር ሲሳይ፤  ዘላቂ የልማት መሠረት መሆኑ የግድ ሆኗል።

 

ይህንን የተፈጥሮ ሃሀብት በተለይ በኤሌክትሪክ ማመንጫነት መጠቀም የጎላ ጠቀሜታ አለው። እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ አገር ዕድገት መሠረት ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እያስመዘገበች የመጣችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከኃይል ማመንጫ ውጭ የሚታሰብ አልነበረም። መሠረታዊ የዕድገት ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በቂ የኃይል ምንጭ ካለ ብቻ ነው።

 

አገሪቱ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ አካሂዳለች። በነገው እለት (ታህሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም) የሚመረቀውና  1870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨውን የግልገል ጊቤ ሦስትን ጨምሮ የተከዜ፣ የፊንጫ፣ የግልገል ጊቤ ሁለት፣ የጣና በለስና ሌሎች ከፍተኛ ወጪን የጠየቁ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ተገንብተዋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱም የነበራትን ዝቅተኛ የኃይል መጠን ማሳደግ በመቻሏ ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ መጥቷል። የኢንዱስትሪ ልማቱም በዚያው ልክ እያደገ ሄዷል።

 

ይህ አገሪቱ ለተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር ጎን ለጎን አጣጥማ መሥራት በመቻሏ ምክንያት የመጣ ውጤት ነው። ከውኃ ከሚገነቡት የኤሌክትሪክ ግድቦች በተጨማሪ አገሪቱ የንፋስና የሦላር የኤሌክትሪክ ምንጮችን በማምረት ላይም ትገኛለች።  

 

በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የኃይል ምንጭ ግድቦቹን የበለጠ በማጠናከር ላይ ይገኛል። አዳዲስ ግድቦችን የመገንባት ሥራው በመጀመሪያው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ልዩ ትኩረት ካገኘው አንዱ ዐቢይ የልማት ዘርፍ  ነው። በዘርፉ በዕቅድ ተይዘው እየተሰሩ ካሉ ግድቦች መካከል የአንበሣውን ድርሻ የያዘው ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።

 

ታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሩህ ተስፋ ነው። አገሪቱ በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት ከምትችላቸው ልማቶች ሁሉ በግዙፍነቱም ሆነ በጠቀሜታው የጎላ ድርሻ ያለው ግድብ ነው – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ። የህዳሴው ግድብ አገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ጉዞ ለማሳካት የሚኖረው አስተዋጽኦ ተኪ አይኖረውም።

 

ይሁንና አባይ ወንዝን በተመለከተ የታችኛውና የላይኛው የተፋሰሱ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቀደሙት ሥርዓታት ማለት ነው በጥርጣሬና በሥጋት የተሞላ እንደነበር የታሪክ ማህደራት ያሳያሉ። በተለይ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የልማት ፕሮጀክት እንዳትገነባ ስትከላከል የኖረችው ግብጽ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለውን አማራጭ መቀበል የግድ ሆኖባታል።

 

ይህንን ለግብጽ ህዝብ በግልጽ የማቅረብና እውነታውን የማሳመን ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት በሰፊው አንቀሳቅሷል። ይህ ደግሞ በአገራቱ ቀደም ሲል የነበረውን ግንኙነት በመቀየር ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር የግድ የሚል ሆኗል። በተለይ የኢትዮጵያ ፕብሊክ ዲፕሎማሲ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለውን ግንኙነት ከሥጋትና ከጥርጣሬ የራቀ እንዲሆንም የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ማለት ይቻላል።

 

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።  ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጠናዊ ትስስርን የሚፈጥርና ሁሉንም አገራት ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል በኢትዮጵያ በኩል ፍትኃዊ የውኃ አጠቃቀም ላይ የተያዘው አቋም ጠንካራና የማይቀለበስ መሆኑ አንዱ ሊጠቀስ የሚገባው ቁም ነገር ነው።

 

ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት ሆነ ከሌሎች የዓለማችን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ የድንበር ወሰን ካላቸው እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኤርትራ የመሳሰሉ አገራት በሠላም አብሮ የመኖርና የጋራ ተጠቃሚ የመሆን ስትራቴጂ እንደምትከተል ይታወቃል።   

 

ባለፉት ሥርዓታት ኢትዮጵያ ድንበር ከምትጋራቸው አገሮች ጋር የነበራት ግንኙነት  መልካም እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ግንኙነቱ በጥላቻና በጦርነት ላይ የተመሠረተ ነበር። ግብጽን ጨምሮ በሌሎቹ አገራት የነበሩ መንግሥታትም ቢሆኑ ለሠላምና  ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ ባለመስጠታቸው የተነሳ በቀጠናው ሠላም አልነበረም።

 

ይሁንና ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ  ዲፕሎማሲን መሠረት ያደረገው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በመተግበር አገሪቱ ዛሬ ላይ ከኤርትራ መንግሥት በቀር ከሌሎቹ አጎራባች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

 

ይህ ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም ማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሲዋን ተግባራዊ በማድረጓ የተነሳም ተጠቃሚ የሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በአካባቢዋ ያሉት አገራት ጭምር ናቸው። ለዚህ አንዱ ማሣያ ደግሞ ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ያላት ሠላምን የማረጋገጥ ተሳትፎ በዋናነት በተለይ ደግሞ በደቡብ ሱዳንም ሆነ በሱዳን መንግሥት አመኔታን አግኝታ በሁለቱ አገራት አጨቃጫቂ በሆነው የጋራ ድንበራቸው አብዬ ሠላም አስከባሪ እንድታሰማራ መመረጧ የአገሪቱ ፖሊሲና የህዝቦቿ ታማኝነት ምን ያህል የተጠናከረ መሆኑን ያመላክታል።

 

ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሠረት የሚያደርገው የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና አገራዊ ህልውናን በማረጋገጥ እንዲሁም በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና ለአካባቢው ህዝቦች ጥቅም በጋራ በመሥራት ላይ ነው።

 

ይህ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ለሁሉም አገራት የሚሰራ በመሆኑ ግብጽ ላይ የተለየ አቋም ሊኖራት አይችልም። የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን ነው ከግብጽ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት እየተጠቀመችበት ያለው።

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይነት በፈጣን ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ ከቀጠናው አገራት ጋር ያላት የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር እየሰፋ መጥቷል። በኢትዮጵያና በጅቡቲ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ተፈጥሯል።

 

ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በመጠቀም ወደአገር ውስጥ ለምታስገባው ማንኛውም ዓይነት ምርት ለጅቡቲ ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ ታስገኝላታለች። ጅቡቲም ብትሆን ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ከመስጠቷ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ለኢትዮጵያ ገቢ ማደግ ድርሻ አላት።

 

በዚህ መልክ እጅግ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠራቸው ዛሬ ላይ አንዱ አገር ለሌላኛዋ ህልውና ወሣኝ ሆነዋል። በዚህም የህዝቦች የጋራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር ተችሏል። ከአጎራባቾቿ ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች የመጣችው ኢትዮጵያ ይህንን ትስስር የሚያጠናክሩ የተለያዩ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንደ መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የአውሮፕላን የበረራ መስመሮች፣ የኃይል አቅርቦት፣ የፀጥታ ትብብርና የመረጃ ልውውጥ ግንኙነቶችን በማጠናከር ሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

 

ይህንን ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ከምትጠቀምባቸው ዘርፎች አንዱ ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው። አገራቱ በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በሰፊው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እያመቻቸች ትገኛለች።

 

ይህ የኢኮኖሚ ትስስር ግብጽንና ሕዝቦቿንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው። ለግብጽ የተለየ አሠራር ስለማትከተል ግብጽ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች። ይህንን ኃይል በመጠቀምም የኢንዱስትሪ ልማቷን ማስፋፋት የሚያስችላት ዕድሏ ይሰፋል።

 

በሁለቱ አገራት ያለው ግንኙነት እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራና ጅቡቲ የጋራ ድንበር ወሰን ባይኖራቸውም የአባይ ውኃ ያስተሳስራቸዋል። የአባይ ውኃ ለግብጾች ህይወታቸው እንደሆነው ሁሉ ለኢትዮጵያዊያንም ሕይወታቸው እንደሆነ መረዳት የግድ ይላል። ግብጻዊያኑ የእርሻ ልማታቸውም ሆነ የሚጠጡት ውኃ አባይን ነው፤ ኢትዮጵያዊያኑ ደግሞ ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን የውኃ ሀብት ለመጠቀም  ያላቸው ዋናው አማራጭ የአባይ ወንዝ ነው።

 

ኢትዮጵያዊያን ጠላታችን ድህነት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። ከድህነት የከፋ ጠላት አለን ብለውም አይወስዱም። ድህነትን ድል ለማድረግ ደግሞ አባይን ጨምሮ ያላቸውን ሀብት መጠቀም የግድ ይላቸዋል።

 

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ለግብጽ ሚዲያ በሰጡት ቃለ ምልልስ  ላይ የተናገሩትን በመጥቀስ ጽሁፌን ማጠናቀቅ ፈለግሁ። እንዲህ ነበር ያሉት። "የኢትዮጵያ እና የግብጽ አገራት ግንኙነት ‘ፍቺ ሊፈፀምበት የማይቻል ጠንካራ ጋብቻ’ ነው" ሲሉ የገለጹትን።