የወጣቱ ተጠቃሚነት የልማትና የሰላም መሰረት ነው

 

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንድስታወቁት ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 70 በመቶ ያህሉ እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው። ማለትም 100 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ከሚገመተው የአገሪቱ ሕዝብ 70 ሚሊዮን ያህሉ ወጣት ነው። ይህ አገሪቱ የወጣቶች አገር መሆኗን ያመለክታል። ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ብቻ አይደለችም። የተማረና ወላጆቹ ይኖሩ ከነበሩት የተሻለ ህይወት የመኖር ፍላጎት ያለው ወጣት አገር ነች። በመሆኑም ያለማቋረጥ ወጣቱን ማስተናገድ የሚያስችል የስራ እድል መፈጠር አለበት። ይህን ማድረግ ካልተቻለ የመኖር ትርጉም የጠፋው ተስፋ የቆረጠ ወጣት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በየወቅቱ የአዋቂዎችን ጎራ ለሚቀላቀለው ወጣት የስራ እድል መፍጠር የበጎ አድራጎት ጉዳይ አይደለም። መንግስት ይህን የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት።

የስራ እድል ፈጠራ የኢኮኖሚ እድገት ጥያቄ ነው። የኢኮኖሚ እድገት ደግሞ ከምንም በላይ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ይሻል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰላምና መረጋጋት ውስጥ በቆየችባቸውና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ባስመዘገበችባቸው ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ሰፊ የስራ እድል ፈጥራለች። በተለይ ከመሰረተ ልማት መዘርጋትና ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ እድገት ያሳየው የኮንስትራክሽን ዘርፍ፤ እንዲሁም የአገልገሎት ዘርፍ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች፤ በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር አስችሏል። ከ1998 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ የተረደገው የመጀመሪያው የወጣቶች ተጠቃሚነት ፓኬጅ ወጣቶችን ለስራ ፈጠራ በማነሳሳት በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ በሚሊዮን ለሚቆጠሩት የስራ እድል ተፈጥሯል።

ከ2003 እሰከ 2007 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ዓመታት ብቻ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ገደማ ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የስራ እድል እንዲያገኙ ተደርጓል። በእቅድ ዘመኑ በአጠቃላይ ለ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከ2008 እስከ 2012 ተግባራዊ በሚደረገው የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን ደግሞ ለ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመጀመሪያው ዓመት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፤ በ2009 በጀት ዓመትም ለ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን አስታውቋል። በ2009 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 200 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንና ከእነዚህም ውስጥ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተመራቂዎች እንደሚገኙበት ኤጀንሲው አስታውቋል። 31 ሺህ 235 ኢንተርፕራይዞችንም ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገበያ ዕድል መፈጠሩንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

እነዚህ እውነታዎች የኢኮኖሚ እድገት በተመዘገበባቸው ያለፉት ዓመታት በአገሪቱ ከፍተኛ የስራ እድል መፈጠሩን ያመለክታሉ። ምናልባት በአገሪቱ ታሪክ ይህን ያህል የስራ እድል የተፈጠረበት ዘመን እንሌለ በድፍረት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ይሁን እንጂ፤ አሁንም የስራ ፈላጊዎችን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገሪቱ በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ስራ ፈላጊዎች እንደሚኖሩና ከእነዚህ መካከል የስራ እድል ሊፈጠርላቸው የሚችሉት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እናም በቂ የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህም መሰረት በእርሻ፤ በእንስሳት እርባታና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ መስኮችን መለየት መጀመራቸውን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ለወጣቱ የቀጥታ ብድር አገልግሎት ከማመቻቸት በተጨማሪ እንደእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስቴር፤ የአሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴርና የኢንዱስትሪ ተቋማት ወጣቶች የሚሳተፉባቸውንና ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን ቦታዎች እየለዩ መሆኑን፤ ወጣቶችም ተቋማቱ በሚለዩዋቸው ቦታዎች እየገቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሚኒስቴሩ አመልክቷል። በቀጣይ የወጣቶችን ፍላጎት ያማከሉ ስራዎችን በመስራት በገጠር ግብርና፤ በመሰረተ ልማት፤ እንዲሁም በከተሞች በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፎች ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቋል።

አሁን ሁለተኛው የወጣቶቸ ተጠቃሚነት ፓኬጅ እየተዘጋጀ ነው። ወቅታዊውን ሁኔታ ባገናዘበ አኳኋን የሚዘጋጀው የወጣቶች ፓኬጅ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀውን የወጣቶች ፓኬጅ ማስፈጸሚያ መሪ እቅድ ክልሎች በራሳቸው እንዲያዘጋጁ አቅጣጫ ተቀምጧል። ፓኬጁ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከተዘጋጀለት ስትራቴጂክ እቅድ ጋር ጸድቆ ወደ ተግባር እንደሚገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል። የተሻሻለው ፓኬጅ የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማስቀጠልና የተሻለ ስራን ይዞ የሚመጣ ነው ተብሏል።

ፓኬጁ የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ያለው ሚኒስቴሩ አሁን ካለው የኢኮኖሚ እድገት ጋር መጣጣም በሚቻልበት ደረጃ የተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቋል። ፓኬጁ ለዚሁ ተግባር የወጣቶች የልማት ፈንድና መሰል ተቋማትም እስከማቋቋም የሚዘልቅ አወቃቀርን ይይዛልም ተብሎለታል። በልዩ ተጠቃሚነት የሚታዩ ወጣቶች ጉዳይም በፓኬጁ እንዲካተት ተደርጓል ተብሏል።

ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ የተያዘው 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት ማስፈጸሚያ ረቂቅ መመሪያም ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ መመሪያ የታሰበውን የለውጥ ምዕራፍ ለማሳለጥ የሚያስችል እንደሆነ ተነግሮለታል። መመሪያው ወጣቱ ስራ ፈጥሮ በዚህ ስራ ላይ ለመሰማራት በሚመጣበት ወቅት ያጋጥመው የነበረውን ከቅድመ ቁጠባ ገንዘብ ጋር ለተያያዘ ችግር ምላሽ ይሰጣል። በረቂቅ መመሪያው ላይ ሶስትና ከዚያ በላይ ሆነው የሚደራጁ ወጣቶች ምንም አይነት ቅድመ ቁጠባ ማዘጋጀት ሳይጠበቅባቸው ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ብቻ ብድሩን ማግኘት እንደሚችሉ አመልክቷል። ከዋስትና ጋር ተያይዞም ከግልና ከቡድን የኢንተርፕራይዝ ውል ውጭ ሌላ ዋስ እንዲያቀርቡ አያስገድድም። ወጣቱ አካባቢያዊና ወቅታዊ ሁኔታን መሰረት ያደረገ ማንኛውንም የስራ ፕሮጀክት ነድፎ ሲመጣ ተገምግሞ ወደ ስራ እንዲገባ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ተነግሯል።

የ10 ቢሊዮን ብሩን ፈንድ ከማስተዳደር ጀምሮ የብድር አሰጣጡንና አመላለሱን  በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፤ በወለድ መጠን ላይ ለውጥ በማድረግ እስከ 15 በመቶ ዝቅ ብሎ አንድ ኢንተርፕራይዝ የብድሩን 6 በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍል እንደሚደረግ ተገልጿል። አጠቃላይ የብድር መመለሻ ጊዜም ጣሪያው አምስት ዓመት ሆኖ እንደፕሮጀክቱ ዓይነትና መጠን ከ5 አመት በፊት ተመላሽ የሚሆንበት አሰራርም ተቀምጧል። የእፎይታ ጊዜን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ደግሞ እስከ አንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ተመቻችቶላቸዋል። በመመሪያው መሰረት አንድ ኢንተርፕራይዝ የቀረጸውን ፕሮጀክት ሕጋዊነት አረጋግጦና የአባላቱን የስራ ኃላፊነት፤ እንዲሁም የሚሰሩበትን ቦታና ማመልከቻ አካቶ ሲያቀርብ ባንኩ በአምስት ቀናት ውስጥ ምላሽ ይሰጣል።

የገንዘብ አወሳሰዱና አመላለሱም ተጠያቂነትን ያገናዘበና ከታለመለት ዓላማ ውጭ እንዳይውል የሚያደርግ አሰራርም ተዘርግቶለታል። በትግበራው ምዕራፉ ወቅት ከመነሻው ጀምሮ በልዩ ትኩረት የሚከታተልና የሚቆጣጠር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሯል። ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም ጉዳዮች ያካተተው ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ የተያዘው 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት ማስፈጸሚያ ረቂቅ መመሪያ በቅርቡ ጸድቆ ስራ ላይ ይውላል።

እነዚህ ከላይ የተመለከቱ የስራ አጥነትን ችግር በተለይ ወጣት ስራ አጦችን ችግር ለማቃለል የተዘጋጁ መርሃ ግብሮች ወጣቱን የልማት ኃይል በማድረግ ከኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላሉ። ወጣቱን የልማት ኃይል በማድረግ  ከልማቱ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት ሥርዓት መዘርጋቱ በአጠቃላይ በወጣቱ ማህበረሰብ ላይ ብሩህ ተሰፋ ይፈነጥቃል። ይህም የአገሪቱ ዘላቂ እድገትና ልማት መሰረት የሆነውን ሰላምና መረጋጋት ዋስትና ያለው እንዲሆን ያደርገዋል። በመሆኑም፤ ከላይ የተመለከትነው በመርሃ ግብር ደረጃ ያለው የወጣቶች ተጠቃሚነት ፓኬጅ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል።