“የታገሰ ማር ይበላል!”

 

 

መንግስትና ኢህአዴግ በተለይ ባለፈው ዓመት በመልካም አስተዳዳር መጓደልና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት፤ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት በተፈጠረ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት ሳቢያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መሰረታዊ መንስኤ ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ ወደውስጥ በመመልከት ምክንያቶቹን ለይቷል። በተለያየ ደረጃ በኃላፊነት ላይ በተመደቡ የመንግስት አመራሮች ዘንድ ሕዝብን የማገልገል መንፈስ መዳከምና ከዚህ ይልቅ ስልጣንን የኑሮ መሰረትና የግል መጠቀሚያ ማድረግ በዋነኛ ምክንያትነት ተለይቷል። የአመራር ብቃት ማነስም ሌላው ምክንያት ሆኖ ተቀምጧል። ይህ ነባራዊ ሁኔታ መልካም አሰተዳደርን በማጓደል፤ የልማት ስራዎችን በማጓተት፤ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ተጨማሪ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻል የተፈጠረውን ችግር ለማቃለልና የሕዝብ እርካታ ለመፍጠር በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በመንግስት አመራር ውስጥ በጥልቀት የመታደስ መርሃ ግብር ተጀምሯል።

የዚህ በጥልቀት የመታደስ መርሃ ግብር ቀዳሚ ተግባር በድርጅትና በመንግስት አመራር ውስጥ ሕዝብን የማገልገል ፍላጎትና ተነሳሽነት ለመፍጠር የሚያስችል የአመለካካት ለውጥ ማምጣት ነው። በጥልቀት መታደስ ሕዝብን የማገለገልና ልማቱን የማስቀጠል ብቃትና ፍላጎት ያላቸውን አመራሮች መመደብ፤ አመራር ላይ ያሉ ሰዎችን የተሻለ ሊሰሩ ወደሚችሉበት የኃላፊነት ቦታ ማዛወር፤ ስልጣናቸውን ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ የኑሮ መሰረት ያደረጉና ብቃት የጎደላቸውን አመራሮች ማንሳት፤ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በተጠቀሙና ሕግ በተላለፉት ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድንም ያጠቃልላል።

እስካሁን በፌዴራልና በክልል መንግስታት አዲስ አወቃቀር ተግባራዊ ተደርጓል። በፌዴራልና በክልል ደረጃ የመካከለኛና የመጀመሪያ ደረጃ አመራር ግምገማ ተካሂዷል። የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት መገለጫ፤ የኢህአዴግ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚው በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌን ለማስወገድ ያስቀመጠው በጥልቀት የመታደስ አቅጣጫ በመግባባትና በጥሩ መንፈስ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። በክልሎችና ወደ ታች ባሉ የመንግስት መዋቅሮች በአዲስ መልክ የማደራጀቱ ስራም በተገቢው መንገድ እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል። ስልጣንን ያለአግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል። “እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስልጣናቸውን አላግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፤ በኢህአዴግ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተፈራ ደርበው፤ የአሁኑ በጥልቀት የመታደስ ሂደት በመጀመሪያው የመታደስ ትግበራ ማለትም በ1993 በተካሄደው የመታደስ ትግበራ የታዩ ስኬቶችን መጠበቅና ማስፋት፤ እንዲሁም በትግበራ ወቅት የታዩ ድክመቶችን የማረም ዓላማ የያዘ መሆኑን አስታውቀዋል። መነሻውን ስራ አስፈፃሚ ላይ አድርጎ ወደ ታች እየወረደ ያለው ግምገማም ድርጅቱና በድርጅቱ የሚመራው መንግስት የተጋረጡበትን ችግሮች አንድ በአንድ የለየ መሆኑንም አመልክተዋል።

በግምገማው ችግሮች ተለይተው ለሕዝብ ግልጽ ተደርገዋል። ከዚህ ባሻገር የተለዩ ችግሮችን አመራሩ በባለቤትነት እንዲወስዳቸው ግለ ሂስ ተካሂዷል። እንደአቶ ደርበው ገለጻ፤ በፌዴራል መንግስት የተደረገው የካቢኔ አባላት ሹም ሽርም የፖለቲካ ግምገማው ውጤት እና እርምጃ እንደሆነም ገልጸዋል። ጥልቅ ተሃድሶው በፓርቲ ውስጥ ያለ ኃላፊነት ብቻውን ለመንግስት ሹመት እንዳማያበቃ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ያነሱት አቶ ተፈራ፤ ጥልቅ ተሃድሶው በቀጣይ ወደ ታችኛው መዋቅር እንደሚወርድ አስታውሰው በመላ አገሪቱ ሕዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍበት የውይይት መድረክ ለመፍጠር ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

በጥልቀት መታደስን አሰመልክቶ ከላይ የተገለጸው በመንግስትና በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች የተሰጠው ማብራሪያ፤ በጥልቀት መታደስ ድንኳን እንደመትከል በሆሆታ ታቅዶ በአፍታ የሚጠናቀቅና ውጤት የሚያሳይ ተግባር እንዳልሆነ ያመለክታል። ሂደት ነው፤ በተለይ የሕዝብ አገልጋይነትን መንፈስ የመፍጠሩና በተሃድሶ መልሶ የመገንባቱ ስራ ዓመታትን ማስቆጠሩ አይቀርም።

ይህ ማለት ግን፤ አሁን የተነሱትን አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች የመመለሱ ጉዳይ ዓመታትን ያስቆጥራል ማለት አይደለም። የሕዝብን ጉዳይ ችላ ያሉ፤ ስልጣናቸውን የተደላደለ ኑሮ መፍጠሪያ አድርገው የሚመለከቱና ስልጣናቸውን ተጠቅመው በሕዝብ እጦት ራሳቸውን ያበለጸጉ ኃላፊዎች መነሳት በራሱ በአንድ ዓመትና ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤት ማሳየት ያስችላል። በዚህ እርምጃ በመልካም አስተዳዳር መጓደል ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአመራር ብቃት ማነስና በምዝበራ ችላ ተብለው የተጓተቱ የልማት ስራዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩበት ሁኔታ ይኖራል። ግልጽነትን በማስፈን ሕዝቡ ላነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ያላገኘበትን ምክንያትና ምላሽ የሚያገኘው መቼና በምን ሁኔታ እንደሆነ፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንዲያውቅ ማድረግ የሚቻልበት ሰፊ እድል መኖሩም አይካድም። እነዚህ በራሳቸው በጥልቀት የመታደሱ ውጤቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ በጥልቀት የመታደሱን ጉዳይ አንገብጋቢ ያደረገው የሕዝብ የልማት ጥያቄና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣን የሕዝብ ፍላጎት መሟላት ባለመቻሉ፤ እንዲሁም የመልካም አሰተዳደር ጉድለት እየተባባሰ መምጣት ሕዝብ ተቃውሞውን በይፋ እንዲገልጽ ያስገደደ ምሬት መፍጠሩ ነው። መንግስት ይህ የሕዝብ ምሬት ገንፍሎ ከመውጣቱ ከዓመታት ቀደም ብሎ፤ የመንግስት ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው መበልጸጊያነት የመጠቀም የኪራይ ሰብሳቢነት አካሄድ መልካም አስተዳደርን በማጥፋት፤ ልማትን በማጓተትና በመግታት ሕዝብን እንደሚያማርር፤ ይህም ለሥርዓቱ አደጋ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱ የታወቃል። ይህን ችግር ለማቃለል ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ሞክሯል። ይሁን እንጂ፤ ይህ የመንግስት ዘመቻ ውጤት ከማምጣቱ በፊት ምሬቱ ገንፍሎ  ተቃውሞው የሕዝባዊነት ገጽታ ይዞ ወጥቷል። ይህ እውነት ነው።

ሕዝብን ለተቃውሞ ያነሳሳው ምሬት በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያ ችግር ቢሆንም፤ የሕዝቡ ተቃውሞ የተጠለፈበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ ለህይወት መጥፋትና ለሃብት መውደም ምክንያት የሆነ ሁከት መቀሰቀሱ ይታወሳል። ተገቢው የሕዝብ ቅሬታ ተጠልፎ ወደአውዳሚ ሁከትነት እንዲቀየር በማድረግ ረገድ፤ በተለይ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ግጭት እንድትፈራርስ ስትራቴጂ ቀርጾ የሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግስትና ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በራሷ መጠቀም የሚያስችል አቅም የሌላትና በእርስ በርስ ግጭት የተጠመደች ድሃ አገር እንድትሆን የሚፈልጉ የተፈጠሮ ሃብት ተጋሪ አገራት እጅ እንደነበረበት የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውም ይታወቃል። እነዚህ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች አውዳሚውን ሁከት የመሩት በቀጥታ አልነበረም ። አመቺ አጋጣሚ ሲገኝ ሊጠቀሙባቸው ከለላ የሰጧቸውንና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉላቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ ግንቦት 7ንና ኦነግን የመሳሰሉ ቡድኖችን በመጠቀም ነው ስትራቴጂያቸውን ለማሰፈጸም የሞከሩት፤

እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ ሽብርተኝነትን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ   የሥርዓት ለውጥ በማምጣት ስልጣን ላይ መውጣት የሚፈልጉ ናቸው። ኦነግ ከኦሮሞ ሕዝብ ስምምነት ውጪ ኦሮሚያን ገንጥሎ የሚገዛው አገር የመፍጠር ፍላጎት ያለው ቡድን ነው። በኦሮሚያ ውስጥ ሁከቱ አይሎ የነበረ ጊዜ ጥቂት የኦነግ አባላትና ልሂቃን ተሰብስበው የነጻይቱን ኦሮሚያ ቻርተር ለማርቀቅ በለንደን ያደረጉት ስብሰባ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ግንቦት 7 ብዝሃነትን ጨፍልቆ አሃዳዊ መንግስት የመመስረት ራዕይ ያለው፤ ይህ ካልሆነ ግን የኤርትራን መንግስት ኢትዮጵያን ዳግም አገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ የማጥፋት ስትራቴጂ ለማስፈጸም የቆመ ቡድን ነው።

እነዚህ የሕዝብን ተገቢ ቅሬታ ጠልፈው አውዳሚ ሁከት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ ቡድኖች አሁን ዳግም ሁከት ሊቀሰቀሱ የሚችሉበት እድል እየጠበበ መምጣቱን ተረድተዋል። የኢህአዴግና የመንግስት በጥልቀት የመታደስ እርምጃ በሂደት ለሕዝቡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በሁከት የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ያላቸውን ህልም እንደሚያመክነው ከወዲሁ ተረድተዋል። እናም በጥልቀት የመታደሱን ተግባር ዋጋ ለማሳጣት ውስጥ ውስጡን ዘመቻ ጀመረዋል። የሚያስፈልገው ተሃደሶ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ ነው የሚል ዘመቻ፤

እርግጥ ነው፤ ኢህአዴግ የመንግስትን ስልጣን የያዘው በርስትነት አይደለም። በሕዝብ ውክልና ነው። የሕዝብን ፍላጎት ማሟላትና እርካታ መፍጠር ካልቻለ በስልጣን ላይ አይቆይም። ሕዝብ ውክልናውን አንስቶ ለሌላ የተሻለ ነው ብሎ ላመነበት የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ይሰጣል። አሁን ኢህአዴግ በያዘው በጥልቀት የመታደስ መርሃ ግብሩ፤ የስልጣን ውክልና በተረከበበት ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካልቻለ በህዝብ ድምጽ መሰናበቱ አይቀሬ ነው ።

በአገሪቱ ከዚህ የተለየ ወደስልጣን መምጫና ከስልጣን መሰናበቻ ሕጋዊና ተገቢ መንገድና ሥርዓት የለም። በመሆኑም በጥልቀት የመታደሱ መርሃ ግብር ገና በጅምር ሳለ ይህን ዋጋ በማሳጣት “የሚያስፈልገው የሥርዓት ለውጥ ነው” የሚል ዘመቻ የከፈቱ ቡድኖች በአመዛኙ እነዚያው ባለፈው ዓመት ሁከት አዝለው ሲያተራምሱን የከረሙ ቡድኖችና ከጀርባቸው ያሉ የአገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች መሆናቸውን መጠርጠር ተገቢ ነው። እርግጥ፤ ኢህአዴግ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማጥፋት ሲፎክር ቆይቶ እዚህ ግባ የሚባል ወጤት ማስመዝገብ ባለመቻሉ ተሰፋ የቆረጡ ዜጎች በጥልቀት መታደሱ ላይ እምነት ያጡበት ሁኔታ አለ። ይህም ቢሆን ግን መፍትሄው ሕገወጥ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ በሆነው የምርጫ ሥርዓት የተሻለ ብለው ላመኑበት ተፎካካሪ ድምጻቸውን መስጠትና አብላጫ የሕዝብ ድምጽ ያገኘው የስልጣን ውክልና እንዲረከብ ማድረግ ብቻ ነው። ተገቢውም የሚያዛልቀውም መንገድ ይህ ብቻ ነው።

በአጠቃላይ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግስት የጀመሩት በጥልቀት የመታደስ መርሃ ግብር ገና ጅምር ነው። ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ከመቅጽበት ሳይሆን በሂደት ነው። በየወቅቱ ተጨባጭ መሻሻል ማሳየት ያለበት መሆኑ ሳይዘነጋ፤ እናም ኦሮሞዎች “obsaatu damma gnaataa/ኦብሳቱ ዳማ ኛታ ወይም ማር የሚበላው ታጋሽ ነው” እንዲሉ የተሃድሶውን ውጤት በትእግስትና በመረጋጋት መጠበቅ ብልህነት ይመስለኛል።