በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ላይ የተቀመጡትንና በምግብ ራስን ከመቻል ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች አለማቀፉ ድርጅት በምጣኔ ሃብታዊ ቀመሮች ለክቶ በምግብ ራሳችንን ስለመቻላችን የሁለተኛውን ዙር የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በጀመርንበት ሰአት ላይ ማረጋገጡ ይታወሳል። ምዘናው በወቅቱ በግብርናው ዘርፍ ያለውን የሥራሥርና ፍራፍሬ ምርቶች ወደጎን የተወና በሰብል ምርት ብቻ የነበረውን የመኸር ወቅት ያሰላ መሆኑም በተመሳሳይ ይታወሳል። 300 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለአጠቃላይ የህዝብ ቁጥራችን አካፍለን አለማቀፉ ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት ስንመዝነው ውጤቱ በመስፈርቱ ከተቀመጠው በላይ የሆነ በመሆኑ በምግብ ራሳችንን ስለመቻላችን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ማለት ግን እንያንዳንዱ ቤተሰብ ሁሉንም አይነት የምግብ ንጥረ ነገር (nutration) እያገኘ ነው ማለት እንዳልሆነ እዚህ ጋር ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አጀንዳም ይህን ውጤትና ውጤቱን ተከትሎ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ መቋቋም የቻልንባቸውን እና የግብርናችንን ደረጃ የተመለከቱ ጉዳዮችን በማንሳት ቀጣዩን ለመተንበይ የሚያስችል መረጃ መስጠት ነው።
በድርቁ ሳቢያ ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ለማካካስ ከተሰሩትና በመሰራት ላይ ከሚገኙት ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዘውና የግብርናችንን እና የአርሶአደሮቻችንን ደረጃ የሚያሳይልን መስኖ ልማት ነው። ሰፋፊ የሆኑትን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴዎች ትተን በአነስተኛ መስኖ ፈጥነው የሚደርሱ ሠብሎችን ስንመለከት ድርቁን ለመቋቋም ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሆነው እናገኛቸዋለን። በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋርና ሐረሪ ክልሎች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የተመለከተው የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚንስቴር መረጃም የሚያጠይቀው ይህንኑ ነው።
በሚኒስቴሩ የአነስተኛ ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ይገዙ እንዳሉት ድርቅ የሚያስከትለውን የምርት እጥረት በመስኖ ለማካካስ ጥረት እየተደረገ ነው። የመስኖ ልማቱን ለማጠናከር ቀደም ብሎ የዝግጅት ስራ የተከናወነ ሲሆን አብዛኞቹ ክልሎችም ቀደም ብለው ወደ ልማቱ ገብተዋል። እስካሁን ከዘርፉ ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ አርሶአደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።
ቀደም ብለው ወደ መስኖ ልማቱ የገቡት የአማራ፣ የደቡብ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች 184 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ፣ 80 ሺህ ቶን ብስባሽና ከ168 ሺህ በላይ ምርጥ ዘር በመጠቀም 485 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ሸፍነዋል። ከዚህ ውስጥ 362 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በአዝርዕት፣ በስራስርና በሌሎችም ሲሸፈን ቀሪው የእርሻ መሬት በዝግጅት ላይ ነው። ወደ መስኖ ልማቱ ቀድመው ከገቡ ክልሎች በተለይ የደቡብና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። በዘንድሮ አጠቃላይ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ለማምረት እየተሰራ ሲሆን አርሶአደሩ መስኖ አስፈላጊ መሆኑን በአግባቡ ተረድቶ እንዲያከናውን የተሰጠው የግንዛቤ ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም የሚያረጋግጥ ውጤት ነው።
ሌላውና የግብርናችንን ደረጃና መዘመን የሚያመላክትልን ጉዳይ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም እና ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር የተያያዘው እንቅስቃሴ ነው።
አርሶአደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ በመጠቀም የሰብል ምርታማነቱን ስለማሳደጉ በርከት ያሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። እያንዳንዱ አርሶአደር በነፍስ ወከፍ ከ20 እስከ 25 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በየአመቱ አዘጋጅቶ በመጠቀም በየዓመቱ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግዥ ከሚያወጣው ገንዘብ ውስጥ እስከ ሁለት ሺህ 500 ብር መቆጠብ እየቻለ መሆኑንም ነው እነዚህ መረጃዎች የሚያመለክቱት ።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም የማሳን ለምነት ጠብቆ እንዲቆይ ከማድረጉ በተጨማሪ ምርታማነት አንዲጨምር በማድረግ በድንገት በሚከሰት የአየር መዛባት የሚደርስን የድርቅ አደጋ ለመቋቋምም ያስችላል።
በሶስተኛ ደረጃ ድርቅን ለመቋቋም ካስቻሉንና ወደፊትም ከሚያስችሉን ምክንያቶች መካከል የምርጥ ዘር አጠቃቀማችን እና የምርምር ውጤቶቻችን ናቸው። ይህን በተመለከተ ሁነኛ አስረጅ የሚሆነን ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ነው። ባለፉት 10 ዓመታት 132 የአየር ንብረት ለውጥና በሽታን የሚቋቋሙ የጥራጥሬ ዝርያዎች በማውጣት ምርታማነት እንዲያድግ ማስቻሉን ኢንስቲቲዩት ይፋ አድርጓል ።
ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በሄክታር በአማካይ ከ10 ኩንታል ያልበጠ ምርት ይገኝ የነበረው በተሰሩ የምርምር ውጤቶች አሁን ላይ ምርታማነቱን በሄክታር ከ16 ኩንታል በላይ ማድረስ መቻላቸው ድርቅን መቋቋም የሚያስችል የምርት ባለቤት እንድንሆን አድርጎናል ። ከ10 ዓመት በፊት በዓመት 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የጥራጥሬ ምርት የተገኘ ሲሆን በ2007/2008 ምርት ዘመን 27 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የሚያሳዩት መረጃዎች የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው።
ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ የጥራጥሬ ሰብሎችን በማምረት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ያላትን ሃብት አሟጦ የመጠቀምና እሴት ጨምሮ የማዘጋጀት ክፍተቶች አሉባት። በተለይ በአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ምርት የሚገኝበትን የጥራጥሬ ምርት በአግባቡ ባለመጠቀም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንዳልቻለች ነው መረጃዎቹ የሚያመላክቱት። ለጥራጥሬ ምርት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በአግባቡ ወደ አርሶአደሩ አለማድረስ፣ የዘር ስርዓቱ ላይ አለመስራትና ሌሎችም በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች አምስተኛ ደረጃን የሚይዘው ደግሞ የጥራጥሬ ምርት ነው። ከዘርፉ በዓመት እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ ቢሆንም የበለጠ ቢሰራ በየዓመቱም በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የማግኘት አቅም እንዳለ ነው በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች የሚገልጹት። የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥና በሽታዎችን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎች የማባዛትና ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል በተደጋጋሚ ማስታወሱም ስለዚህ ነው፡፡
ስለሆነም ምርጥ ዘሮችን በማባዛት፣ በሰብል አያያዝ፣ በተባይ መከላከል፣ የዘር ሥርዓቱን በማስተካከልና ከገበያ ጋር በማገናኘት የተሻሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑ ተገቢ ነው፤ በየዓመቱም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በጥራጥሬ ምርት እንደሚሸፈን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ለዘንድሮው ዓመት የእርሻ ስራ የሚውል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርም ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ ነው።
የሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓት ግብይት ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ለዘንድሮው የመኸር፣ የበልግና የመስኖ እርሻ የሚውሉ ማዳበሪያዎች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው። በ2007/2008 የምርት ዘመን የጀመረው የአፈር ለምነት ካርታን መሰረት ያደረጉ ማዳበሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ የማዳረስ አሰራርም ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ቀደም ሲል ሁለት ብቻ የነበሩትን የማዳበሪያ አይነቶች ወደ ስድስት በማሳደግ የአፈር አይነትን መሰረት በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። አርሶ አደሩ ኤን.ፒ.ኤስ፣ ኤን.ፒ.ኤስ ቦሮን፣ ኤን.ፒ.ኤስ ዚንክ፣ ኤን.ፒ.ኤስ ዚንክ ቦሮን፣ ዩሪያና ኮፐር የተሰኙትን ማዳበሪያዎች የሚያርሰውን አፈር አይነት መነሻ በማድረግ እንዲጠቀም በማድረግ ምርታማነትን የማሳደግና ድርቅን የመቋቋም ተግባሮች ተጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚንስቴር ገልፇል።
ለ2008/2009 የምርት ዘመን ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ዝግጅት እየተገባደደ መሆኑን የሚገልጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው። ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር የሚወጡ ቅድመ መስራች፣ መስራችና የመነሻ ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ እያደረገ ነው። ከ24 በላይ የሰብል አይነቶችን እንዲሁም ከ100 በላይ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን በማባዛት እያሰራጨም ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም የክልል የምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞችን የአቅም ክፍተት በመለየት ድጋፍ እየሰጠ ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ ውጤቶችም ሆኑ ቀጣይ እንቅስቃሴዎች የሚያመላክቱት አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ግብርናችን እና አርሶአደሮቻችን ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችል ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸውና መዘመናቸውን ነው።