ሃገራችን ከማንኛውም ሃገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ፣ ከጠላትነት ፍረጃ የተላቀቀና ግንኙነቱ የመልካም ጉርብት እንዲሆን፤ በተለይ በህዳሴው ማግስት በወጣው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በግልጽ የተመለከተ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ፖሊሲ በድርቅና በእርስ በእርስ ጦርነት የደቀቀው የአገራችን ኢኮኖሚና ሰብአዊ ሃብት ውድመት አገራችንን በአለም አደባባይ አንገት የሚያስደፋ ስም ያሰጣትና ለብሄራዊ ውርደት የዳረገ መሆኑን መነሻ ያደረገና የችግሩን ምንጮች ለይቶ በማቅረብ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህም በአገር ውስጥ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት መሄድ የሚያስችለን ጥንት አባቶቻችን ያነጿቸው ታላላቅ ሃውልቶችና ምኩራቦች ሳይሆኑ በወሳኝ መልኩ አሁን ባለንበት ዘመን በምንሰራው ተጨባጭ ስራ እንደሆነ ታምኖበት ልማት፣ ዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው የነፍስ አድን ስራ ተደርጎ መወሰዱና በተግባርም ወደስራ መገባቱም ይታወቃል ።
ይህ ተረክ አሁንም ከሟርት ያልቦዘኑ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ከውጭ ኢንቨስትመንታችን ጋራ ተያይዞ የበሬ ወለደ ዘገባዎች ማሽጎድጎዳቸውን ያልተዉ መሆኑን መነሻ በማድረግ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሃገራችን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻና የሰላም ሃዋርያ የሆነችበትን እና የምትሆንበትን ምክንያቶች ያወሳል።
ከሃገሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በእኩል ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ፣ የውጭ ሃይሎችን ሳይሆን ውስጣዊ ሃገራዊ ሁኔታው ዋነኛ የደህንነት ምንጭ እንደሆነ በመተነተን ድህነትና ኋላቀርነትን በማስወገድ፣ ዘላቂና ህዝቡ በየደራጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማት፣ ዴሞከራሲና መልካም አስተዳደርን እውን በማድረግ ለሃገራችን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና እድገት የሚተጋ ሰላም ወዳድ መንግስት ስለመገንባታችን ብዙዎች እየመሰከሩ የሚገኙት እንደው ዝም ብለው ሳይሆን ፖሊሲው የሚገለጽባቸው ተግባራትና ውጤቶችን በተጨባጭ ስላዩ ነው።
ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት ውጤታማ የአደጋ ተጋላጭነት መከላከያ ስትራቴጂ ነድፈን ውጤት አስመዝገበናል። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን መነሻና መድረሻ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም ማስጠበቅና የሀገራችንን ሉአላዊነት ማክበር እንደሆነ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በግልፅ ተደንግጓል። ከማነኛውም ሀገር ጋር የምናካሂዳቸው ግንኙነቶችም የሀገራቱን መንግስታት ሉአላዊነትና እኩልነት በማክበርና በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት ላይ የተመሰረተ ነው። ሃገራችን በምትከተለው ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት ከጎረቤቶች ህዝቦችና መንግስታት ጋር ለዘመናት የነበረን ያለመተማመን ግንኙነት በመሰረቱ ተቀይሮ በወዳጅነትና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት ሆኗል። ከታላላቅ የአለም መንግስታትና አገሮች ጋር ለረዢም ዘመን በሰጪና ተቀባይ፣ በእርዳታ እና ብድር ላይ የተመሰረተው ግንኙነት በህዳሴው ማግስት ግንኙነቱ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የንግድና ኢንቨስትመንት አጀንዳ እየሆነ መጥቷል። ሀገራችን ከአፍሪካ ታላላቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ፣ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ በዘርፉ ቀዳሚ መዳረሻ ለመሆን ችላለች።
በአሁኑ ወቅት ሃገራችን የአለምን ቀልብ በበጎ መሳብ በመቻሏ ያደጉትና በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉት ሃገራት መሪዎች ወደ ሃገራችን በመምጣት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ፍላጎታቸውን መግለፃቸውና የተለያዩ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። የሩቁን ትተን ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ እንኳን ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ . . . ወዘተ የመጡ የሃገራቱ መሪዎችና የባለሃብቶች ልዑካን ጋር የተደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች ሃገራችን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻና የሰላም ሃዋርያ ስለመሆኗ ማረጋገጫ ነው።
ጥቅል የሆኑትን እና በሁለት አመታት ውስጥ የነበሩ አስረጂዎች በቂ ሆነው ለማያገኟቸው እና እንዳረጀ አስረጅ ለሚቆጥሩት ደግሞ፤ ይልቁንም ባለፈው አመት ገጥሞን ከነበረው ቀውስ ጋር በማያያዝ የውጭ ኢንቨስትመንታችንና የቱሪዝም ፍሰታችን ማሽቆልቆሉን ለሚሰብኩት የቀረቡ እና ሰሞንኛ የነበሩ አስረጂዎች መጥቀስ ተገቢ ይሆናል።
ጣሊያን እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚያከናውኗው ተግባራት የሚውል 2.8 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ በኩል እንዲደረግ ጣልያን መወሰኗን የተመለከተው አለምአቀፍ ዘገባ የመጀመሪያው እና የመልካም ግንኙነታችን ማሳያ የሚሆን ሰሞንኛ ዘገባ ነው።
በቱርክ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኒሃት ዜይቤኪች አማካኝነት የሚመራው የቱርክ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ መሆኑን የተመለከተው እና ህዋዌ የተሰኘው የቻይናው ቴሌኮም ኩባንያ እና የቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኪዩፕመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ የተሰኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን የሀይል ቋት የተሻለ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የተመለከተው ሰሞንኛ ወሬም ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ስለተሰራና ይልቁንም የአህጉሪቱ የሰላም ሃዋርያ ሆነን በመገኘታችን ነው።
የታንዛኒያ መንግሥት ከ2019 ጀምሮ ከኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገባት ስራ ይጀምራል ሲሉ የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ጠቅሶ ብሉምበርግ በድረ ገጹ ላይ ያሰፈረው ሰሞንኛ ዘገባም ሃገራችን ከአውሮፓ እስከ አሜሪካና ኤዢያ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት ሃገራትም ሳይቀር ተፈላጊ የምትሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች ያሏት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን ለማስፋፋት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር የአራት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት መፈራረሟም ስለተረፋት እንዳልሆነ እና ተመራጭ ያደረጋት ምክንያት ስላለ መሆኑ መቼም አያከራክርም።
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅ ብትመታም፣ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደነቅ ነው ሲል የዓለም ባንክ በባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በኩል ይፋ ያደረገውን ሪፖርት እና የዩናይትድ ስቴትስ ንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈቱን እና ይህም ተግባር አሜሪካውያን ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ያላቸውን የሥራ ግንኙነት ለማጠናከር መሆኑን የተመለከተው የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘገባም መቼም የሰላም ሃዋርያ መሆናችን ያስገኘልን ትሩፋት ለመሆኑ ከበቂም በላይ አስረጂዎች ሆነው ሊወሰዱ መገባታቸው ላይ ልዩነት ይኖራል ብሎ ማሰብ የሚከብድ ይሆናል።
ሃገራችን ካለፉት 25 አመታት ወዲህም ቢሆን የድርቅ አደጋ ተለይቷት የማያውቅ መሆኑ ይታወቃል። በ1995/6 ከ14 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ ለድርቅ ተጋልጦ የነበረ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። በ2008 ከ10.2 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በውቅያኖስ ሙቀት መጨመር የተነሳ አብዛኛውን የበልግ አብቃይ አካባቢዎችንና ሌሎችንም አካባቢዎች ያዳረሰ ድርቅ መከሰቱም በተመሳሳይ። ይሁን እንጂ ካለፉት አመታት የባሰ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለከባድ የድርቅ አደጋ የተጋለጠ ቢሆንም ወደ ሃገራችን የሚገባው የውስጥ ኢንቨስትመንት ከመቆም ወይም ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መምጣቱም ከተለገሰን የተፈጥሮ ሀብት ውጪ የሰላም ሃዋርያ ስለመሆናችን ማረጋገጫ ነው። አህጉራዊና አለማቀፍ ኮንፈረንሶችና ስብሰባዎች በመጠንም በይዘትም አልቀነሱም፤ የማይዳሰሱ ቅርሶችን የተመለከተው የዩኔስኮ አለም አቀፍ ሰሞንኛ ኮንፍረንስንም ከዚሁ ጋረ አያይዞ መረዳት ጠቃሚ ነው።
የዚህ ሁሉ ምንጭ የሕዳሴው መስመር ሃያልነት የፈጠረው ተፅእኖ ነው። ተከታታይና ፈጣን እድገት ያስመዘገበች አገር ለመፍጠር መቻላችን ነው። በውስጣችን የፈጠርነው ሰላምና መረጋጋት የአለምን ቀልብ ገዝቶልናል። ግዙፍ የድርቅ አደጋ ቢደቀንብንም ችግሩን የራሳችንን የእህል ክምችት አቅም በመገንባት እና ፈጣን የሎጂስቲክ ስርአት ተግባራዊ በማድረግ ተቋቁመነዋል። የማስተባበር አቅማችን ምን ያህል እንደጎለበተም እግረ መንገዱን አሳይቶን አልፏል።
የአለም ህብረተሰብ ካለፉት አመታት ወዲህ በአዲስ መልክ ለሃገራችን የሰጠው በጎ ገጽታ አሁንም ቢሆን ተለውጦ ሊታይ አይቻልም። በውስጧ በፈጠረችው የመቋቋም አቅም እና ከሁሉም ሃገሮች ጋር በገነባችው የወዳጅነት ግንኙነት ችግሩን ለመቋቋም ስሟ በድርቅና ረኃብ ብሎም በእርስ በርስና የጎረቤት ጦርነት የሚትታወቀው ሃገራችን አሁን ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ስማችን በበጎ ከሚነሳባቸው መስኮች መካከል ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገታችን፣ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ መሆናችን፣ ግዙፍና ስኬታማ የአየር መንገድ ባለቤት መሆናችንን፣ በአለም ከትላልቆቹ ሀገራት ተርታ የሚሰለፍ የሃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባን መሆናችን፣ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹና ተመራጭ መሆናችን፣ አለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕከል የሆነች ርዕሰ ከተማ ያለን መሆናችን . . . ጥቂቶቹ እና ሊጠቀሱ የሚገባቸው ምክንያቶች ናቸው ።