ጊቤ ሶስት ወይም ወይም በእኔ አጠራር ‘ሳልሳዊ ጊቤ’ በታዳሽ አቅም ፖሊሲያችን ከተገነቡት የሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች አንዱ ነው። ማመንጫው በሙሉ ኃይሉ ስራ ሲጀምር፤ 187 ሜጋ ዋት በሚያመነጩት 10 ተርባይኖቹ አማካኝነት 1870 ሜጋ ዋት የኤሌክሪትሪክ ኃይል ያመነጫል። ይህም አሁን ያለውን የሀገራችንን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም በእጥፍ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ኢትዮጵያ ከ4ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ይኖራታል። ይህም ኢትዮጵያ እየተከተለች ላለችውና እ.ኤ.አ በ2025 ምንም ዓይነት በካይ ጋዝ ላለመልቀቅ በዕቅድ ለያዘችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዓይነተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። ይህም ሀገራችን እያዝመዘገበችው ላለው ፈጣን ልማት ሳቢያ ለሚፈጠረው የኢንዱስትሪ ልማት በችግር ፈቺነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አይቀሬ ይሆናል።
ይሁንና ይህ የሀገራችን የልማት ትልም በአንዳንድ ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች በጎ ምልከታ አልነበረውም። በተለይም እንደ ጊቤ ሶስት ዓይነት ወሳኝ የልማት ትልሞች የተለያዩ “የዳቦ ስም” እየተሰጣቸው በጎውንና ሀገራችንን ብሎም ቀጣናውን የሚጠቅመውን ፕሮጀክት ያልተባለ ነገር የለም ቢባል ከእውነታው መራቅ አይመስለኝም። ራሳቸውን ኢንተርናሽናል ሰርቫይቫል ግሩፕ፣ ኢንተርናሽናል ሪቨርስ፣ ፍሬንድስ ኦፍ ሌክ ቱርካና፣ ሂዮማን ራይትስ ዎች…ወዘተ. እያሉ የሚጠሩ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች በዘመቻ መልክ ሲያሰራጩት የነበረው የተሳሳተ ምልከታና ውትወታ ለዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል።
ለነገሩ ራሳቸውን “በአካባቢ ደህንነት ተቆርቋሪና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት” ካባ ውስጥ ሸሽገው፣ በተግባር ግን በአክራሪ ኒዮ ሊበራል ኃይልነት በመንቀሳቀስ ከራሳቸው ስውር የርዕዩተ ዓለም ፍላጎት አኳያ በመነሳት በየጊዜው በኢፌዴሪ መንግስት የተሰሩትንና በመሰራት ላይ የሚገኙትን የልማት ፕሮጀክቶች በመኮነን ከሀገራዊና ቀጣናዊ ተጠቃሚነታችን ለማናጠብ የሚያደርጉት ጥረት ግልፅ ነው። ይኸውም በራስ አቅም የሚገነባና ህዝቦችን “የነገ ሰው” የሚያደርግ ልማታዊ ክንዋነኔዎችን በመቃወም ከእኛ ዕውቅና እና ድጋፍ ውጭ ማደግ አትችሉም በማለት ራስ በቀል የሆነን አዲስ የልማት ስልትን መቃወም ነው። በታዳጊ ሀገራት የተፈጥሮ ሃብት እነርሱ አዛዥና ናዛዥ በመሆን በምንም ዓይነት መንገድ ከእነርሱ ዕውቅና ውጭ እንዳናድግ የሚያካሂዱት ዘመቻም ነው።
እነዚህ ኃይሎች አፍሪካዊያን እንዳያድጉና የምንጊዜም ተመፅዋች ሆነው እንዲኖሩ የሚሹ ናቸው። በዚህም ምክንያት አፍሪካ ውስጥ ያሉ አርብቶ አደሮች በተፈጥሮ ፀጋዎቻቸው እንዳይለሙ ከማድረግ ባሻገር፣ የተለያዩ የፈጠራም ምክንያቶችን በመደርደር ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት መለወጥ በፅናት ይቃወማሉ። ለዚህም ይመስለኛል— የጊቤ ሶስት ፕሮጀክት በእነዚህ ሃይሎች አንድም ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ህብረተሰብ ምንም ዓይነት እርባና እንደሌለው፣ ሁለትም የቱርካናን ሃይቅ እንደሚያደርቅ እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ አደጋ እንደሆነ አድርገው በማቅረብ የፈጠራ ወሬዎችን ሲያናፍሱ እንደነበር አይዘነጋም።
ይሁንና ቀደም ሲል በኢፌዴሪ መንግስት ሲገለፅ እንደነበረውና አሁን ፕሮጀክቱ በፍፃሜ ዋዜማው ላይ ሆኖ የወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሃይል ማመንጫው አክራሪ ኒዮ ሊበራሎቹ ሲገልፁት ከነበረው የፈጠራ ድርሰት ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው። አዎ! ግንባታው በኢትዮጵያ መንግስት 40 በመቶ እንዲሁም በቻይና መንግስት 60 በመቶ ድጋፍ በተገኘ የገንዘብ ፍፃሜውን ያገኘውና ግድቡ ውሃ ሲሞላ ሁሉም ተርባይኖቹ ወደ ስራ የሚገቡት ሳልሳዊ ጎቤ፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሃይቅ አካባቢ ለሚኖሩ የኢትዮጰያና የኬንያ ዜጎች ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።
እንደሚታወቀው በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በኬንያ መንግስታት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተደረሰ ሙሉ ስምምነት የተገነባ ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊያኑ ሙርሲዎችና ኛንጋቶሞች የሚገኙበት ኦሞ ወንዝ ለኬንያው የቱርካና ሐይቅ ገባር ቢሆንም ቅሉ፣ በወንዙ ላይ የሚገነባው ጊቤ ሶሰት በሐይቁም ይሁን በአካባቢው በሚኖሩ ቱርካናዎች ላይ የሚያስከትለው አንዳችም ተፅዕኖ አለመኖሩ ተረጋግጧል። እንዲያውም በአካባቢው ለሚገኙ ህዝቦችና ለቱርካና ሐይቅ የጎላ ጠቀሜታ ያለውና ቀደም ሲል የነበረውን የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክረው መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች የወጡ ጥናቶች ማረጋገጣቸው አይዘነጋም። ይህን ዕውነታ ተመርኩዞም የኢትዮጵያ መንግስት ኮንትራቱን ለሳሊኒ ኮንስትራክሽን በመስጠት ስራውን አከናውኗል።
በዚህ ክንዋኔም በኦሞ ወንዝ አካባቢ የሚገኙት የሀገራችን ህዝቦች ቀደም ሲል ከነበሩበት የጨለማ ብርሃን ወጥተው ዛሬ ወደ ዘመናዊ አኗኗር ለመሸጋገር ችለዋል። በዚህ መሰረትም የግድቡ መገንባትየፕሮጀክቱ እውን መሆን የአካባቢው ህዝብ ከከብት እርባታ በተጨማሪ በአሳ ማስገርና በመስኖ ልማት እንዲጠቀም የሚያስችል ነው።
እጅግ ኋላ ቀር በሆነው በዚያ አካባቢ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድና ኢንቨስትመንትን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማትና የንግድ ስራዎች እንዲካሄዱ ዕድል ይፈጥራል። እንዲሁም ለዘመናት የብርሃን ጭላንጭል አይቶ የማያውቀው የአካባቢው ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሰለሚያገኝ በአኗኗር ዘይቤው ላይ ለውጥ ያመጣል። ቀደም ሲል በውኃ ሙላት ይጥለቀለቁ የነበሩት ህዝቦችን ህይወት ለመታደግም የኤሌክትሪክ ሃይል ግንባታው ዕውን መሆን ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል። በግንባታው መጠናቀቂያ ዋዜማ ላይ እንደተገለፀው፤ ፕሮጀክቱ ፍፃሜ ማግኘቱ የአካባቢው ማህበረሰብ በትምህርት፣ በጤና በመሰረተ ልማትና በሌሎች የልማት ዘርፎች ተጠቃሚ አድርጓል።
እርግጥ የጥቅሞቹ ተቋዳሾች በወንዙ አካባቢ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያኑ ኛንጋቶሞችና ሙርሲዎች ብቻ አይደሉም። ኬንያዊያኑ ቱርካናዎችም ቢሆኑ ከግድቡ መገንባት ተጠቃሚዎች ናቸው። ይህም የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን በአካባቢው የሚገኙትን ሁሉንም ህዝቦች ወደ ተሻለ ህይወትና የልማት አቅጣጫ የሚወስድ መሆኑን ያመላክታል።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የጊቤ ሶስት ዓይነት የልማት ፕሮጀክቶች በታዳጊ ሀገራት ውስጥ መገንባት የሚጎዳው አክራሪ ኒዮ ሊበራሎችን ነው። ‘ለምን?’ ከተባለ ነገሩ ወዲህ ነው።…ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች በሀገራቱ ውስጥ መገንባታቻው የማህበራዊና የመሰረተ ልማት ትሩፋቶችን የአካባቢው ማህበረሰብ ያገኛል።
ይህ አዲስ ሁኔታም የአካባቢው ህዝቦች በመሰረተ ልማትና በሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ሳቢያ ዓይናቸውን በመክፈት የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዲቀይሩ ያደርጋቸዋል። እነዚያ ህዝቦች ህይወትን ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታም መምራት መጀመራቸውም የሰብዓዊ መብት ጥቅምን ይገነዘባሉ። ቀደም ሲል በግጦሽና በውሃ ምክንያት ከሚጋጯቸው ህዝቦች ጋርም በሰላም ተከባብረው ይኖራሉ።
ታዲያ አንድ ህዝብ ከዕድገት ጋር ተያይዞ በሚፈጥረው ሚዛናዊ እሳቤ ስለ ሰብዓዊ መብትም ይሁን ስለ ግጭት አፈታት በቂ ግንዛቤ ከያዘ፣ ለሰብዓዊ መብት እሟገታለሁ የሚል ድርጅትም ሆነ ግጭት ፈቺ ተቋማት ሊያስፈልጉ አይችሉም። ከልማቱ ጋር አብሮ በሚዳብር ንቃተ ህሊና የተመቻቸ አካባቢና የቅርስ ጥበቃ አስተሳሰብ መጎልበቱ ስለማይቀርም የአካባቢ ተንከባካቢ ድርጅትም እንዲሁ ሊፈለግ አይችልም። በዚህም ሳቢያ የጊቤ ሶስት መገንባቱ አደጋው ከአካባቢው ህዝቦችና ስነ-ምህዳር ይልቅ ለአክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች መሆኑ አይቀሬ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— እነዚህ ሃይሎች እንደ ጊቤ ሶስት ዓይነት ጠቃሚ የልማት መነቃቃትና ቀጣናዊ ትስስር ፈጣሪ ፕሮጀክቶችን በዘመቻ መልክ እያወገዙ ዛሬ ላይ የደረሱት።
ምን ይህ ብቻ። የግድቡ መገንባት በየጊዜው በመዋዥቅ የሚታወቀውን የቱርካና ሐይቅ ፍሰት ወጥነት እንዲኖረው እንዲሁም ትነቱ እንዲቀነስና የውኃው መጠንም እንዲጨምር የማድረግ አቅም አለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጎረቤት ኬንያ ከግንባታው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆኗ አይቀርም። ይህም የቀጣናውን የልማት ትስስር የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፤ ዜጎቻቸው በድህነትና በድርቅ ለሚማቅቁት የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች የምስራችና እጅ ለእጅ ተያይዞ የማደግ ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።
ያም ሆነ ይህ ግን በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፈውና በእኔ እምነት የማድረግ አቅማችን ማሳያ የሆነውና በራስ የልማት ትልም ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያሳየው ይህ የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፤ ሀገራችን የተያያዛቸውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በማንም ውትወታ ለአፍታም የማይቆምና ሁልጊዜም የሀገራችንንና የቀጣናውን ህዝቦች ጥቅሞች በማስከበር ላይ ብቻ የሚያጠነጥን የዕድገት ምሳሌ ሆኗል ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ የጊቤ ሶስት ግንባታ ዕውን መሆን ሀገራችን ለጀመረቻቸው ማናቸውም የልማት ፕሮጀክት ምን ያህል በጽናትና በታጋሽነት እንደምትሰራና ለውጤትም እንድትበቃ ሁነኛ ማሳያ ነው። ይህ አቋሟም በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ውሃ የሚይዙ ግድቦች በመድረቃቸው ሳቢያ ጊቤ ሶስት 900 ሜጋ ዋት በማመንጨት ሀገር ውስጥ የነበረውን የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ሊታደግላት ችሏል። እርግጥ ሁሌም በጋራ የማደግ ቀጣናዊ ራዕይ ያለው የኢፌዴሪ መንግስት እንደ ህዳሴው ግድብ ዓይነት ባሉ የልማት ትልሞችም ላይ የጊቤ ሶስት ልምዱን አጠናክሮ መቀጠሉ የሚቀር አይመስለኝም። በጊቤ ሶስት ፕሮጀክት የሀገራችንን የማድረግ አቅም ያሳየ በመሆኑም፤ ይህ የማድረግ አቅማችን በማናቸውም የልማት ትልሞቻችን ውስጥ ሊጎለብትና የሀገራችን መገለጫም መሆን ይኖርበታል እላለሁ።