የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማነታችን …

 

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ ለማስጀመር መሠረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ወራት ቢቀሩት ነው። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 60 በመቶ ያህል ሊደርስ የቻለው ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በማስተባበር ላቅ ያለ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ነው።

 

ከግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ በፊት የነበሩት የአገሪቱ ፖለቲከኞች ከእንዲህ ያለ ጋብቻ የሚገኝን ጥቅምን ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በጋራ ሀብታችን ላይ በውይይት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር ከመከተል ይልቅ ሕዝብን ማደናገርና የጥላቻ ዘር መዝራትን ሥራዬ አድርገው ይዘውት ነበር። ፍትኃዊ የውኃ ተጠቃሚነትንም መተግበር አይፈልጉም ነበር። ይባስ ብለው ኢትዮጵያ አባይን ገድባ የግብጽን ህዝብ ለረሃብና ለስደት ልትዳርግ እየጣረች ነው በማለት ሕዝቡን ያደናግሩት ነበር። ኢትዮጵያ የአባይን ውኃ መጠቀም እንዳትችል ለማድረግም እነዚሁ የቀድሞ አመራሮች ሲከተሏቸው ከነበሩት የተለያዩ ዘዴዎች መካከል በኢትዮጵያ ሠላም እንዳይኖር ማድረግን ነበር።

 

በአገር ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠርም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ የድንበር ጉርብትና ካለው የኤርትራ መንግሥት ጋር ሴራ በመሸረብ ግጭት መፍጠር ነበር። በዚህ መልክ አገሪቱ ሠላም ማረጋገጥን ቅድሚያ ሰጥታ ከልማት ግስጋሴዋ እንድትገታ የማድረግ አቅጣጫ ነው።  

 

በተለይ ደግሞ የኤርትራ መንግሥት የሚከተለው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአገራችን ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ የተለያዩ የሽብር ተግባራት እንዲፈፀሙ የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ ሲሳተፍ የግብጽ መንግሥታትም በተለያየ መልክ ያግዙ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህን ደግሞ የግብጽ ፖለቲከኞች በአንደበታቸው በዘመነ ሙርሲ ጊዜም ተናግረውታል።

 

የኤርትራ መንግሥት ካለፉት የግብጽ አመራሮችና ከሌሎች የሽብር ቡድኖች  ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ሠላም ለማደፍረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል። የግብፅ መንግሥታት የእነዚህን ሁለት አገሮች ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ማለት ነው ግንኙነታቸው እንዲጠናከር፣ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር ያደረጉት አንዳችም ነገር አልነበረም። በኢኮኖሚ የተጠናከረች ኢትዮጵያ ከተፈጠረች አባይን ትገድባለች፤ የግብጽ ህዝብ በውኃ እጦት ያልቃል የሚል የተሳሳተ እምነት ይዘው የአገሪቱን ልማት ሲቃወሙና የልማት አጋሮችም ፋይናንስ እንዳያደርጉ ሲማጠኑ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው።

 

ይሁንና ይህ እምነት በእጅጉ የተሳሳተ እንደነበር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይልቁንም ጠንካራ ኢኮኖሚ በተፈጠረ ቁጥር በአገራት መካከል የሚኖረው ትብብር መተሳሰብና መደጋገፍ እየጨመረ እንደሚሄድ ነው። ግብጽና ኢትዮጵያ ያላቸው የኢኮኖሚ ግንኙነት በተጠናከረ ቁጥር ሁለቱ አገራት ተደጋግፈው አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ ለመኖር በር ይከፍታል።

 

አገራቱ በተናጠል ያልተሻገሯቸውን ችግሮች በጋራ ድል ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ዳር በማድረስ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ለግብጽ ህዝብ  ብታቀርብና ግብጽ በፊናዋ ከሌሎች አገራት በየዓመቱ ወደአገሯ የምታስገባውን የምግብ ፍጆታ ከኢትዮጵያ መግዛት ብትችል ሁለቱ አገራትና ህዝቦች እርስ በርስ ተደጋግፈው ማደጋቸው አይቀሬ ይሆናል።

 

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን ውኃ የምታመነጭ ሆና እያለች ተጠቃሚነቷ ግን ከሁለት በመቶ በታች እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ እስካሁን ባለው ጥናት መሠረት 95 ከመቶ በላይ የሚሆነው የአባይ ተፋሰስ ሀብት ገና ጥቅም ላይ አልዋለም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸው የ1929 እና የ1959 ስምምነቶች ከ85 በመቶ በላይ የውኃ ድርሻ ያላትን አገር ምንም ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጉ ስምምነቶች ናቸው።

 

ቀደምት የግብፅ መንግሥታት የተሳሳተ የግብጽ ኢኮኖሚን ለማሳደግ አባይን  ከምንጩ መቆጣጠርና እንዳለ አግበስብሶ ለብቻ መጠቀም የሚል የተሳሰተ መንገድ ይከተሉ ነበር። አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነትም አባይን ብቻ አድርገው የማየትና ሌሎች ፈርጀ ብዙ የትብብር ዘርፎች መኖራቸውን አለመገንዘብ ነበር።

 

የአባይ ውኃ ወሣኝ ቢሆንም ሁለቱ አገራት ግን ከዚህም ባለፈ በርካታ ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የትብብር ፕሮግራሞች እንዳሉ መገንዘብ የግድ ይላል። አባይ አንዱና ዋነኛው የትብብር መስክ ነው። ከአባይ ባሻገር በርካታ የግንኙነትና የትብብር ዘርፎች አሉ።

 

ኢትዮጵያና ግብጽ ከአባይ በተጨማሪ በርካታ የሚያስተሳስሯችው የሁለትዮሽ ግንኙነት መስኮችን ሊያዩና እነዚህንም ሊያጠናክሩ እንደሚገባ በርካታ ምሁራን ይጠቁማሉ። የአባይን ውኃ አጠቃቀምም ቢሆን ግብጻዊያንን ሊጎዳ የሚችል ምንም ዓይነት ግንባታ ኢትዮጵያ እንደማታካሂድ ከአገሪቱ ታሪክ ለመገንዘብ አያዳግትም። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለግብጽና ለሱዳን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ምሁራን ይናገራሉ።

 

ይሁንና ግብጽ ቀደም ሲል የነበሩ ለግብጽ ውኃውን የመጠቀም ሙሉ መብት የሚሰጡና የውኃ ባለቤትና አመንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን የበይ ተመልካች አድርገው የተው ስምምነቶች ነበሩ።

 

በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ቅኝ ባትገዛም ጎረቤቶቿና የአካባቢው አገራት ቅኝ ስለተገዙ ቅኝ ገዢዎች አካባቢ የራሳቸውን ልማት ሲያከናውኑ ኢትዮጵያን ሳያሳውቁ፣ ሳያማክሩና ሳይጠይቁ ብዙ ስምምነቶችን አድርገዋል። እነዚህን ስምምነቶች ሲያደርጉ በሚያስገርም ሁኔታ የውኃዎቹ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን አይጠቅሱም። ኢትዮጵያ ውኃውን ተጠቅማ ወደፊት ለልማት ሥራ መጠቀም እንደምትችልም አያመላክቱም። በመሆኑም ወንዞቹን በተመለከተ እነዚህ ቅኝ ገዢዎች በመጨረሻ ያወረሱን ጭቅጭቅ ብቻ እንደነበር የዘርፉ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ።

 

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የሁለትዮሽ ግንኙነትን እያስፋፋች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የግብጽ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሬ እሰራለሁ፣ ውይይቱን እቀጥላለሁ፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመጓዝ ተከታታይ ምክክሮችን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አደርጋለሁ ማለቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው። በዚህ መሠረትም እስካሁን ተከታታይነት ያለው የሦስትዮሽ ምክክር ተካሂዷል፤ በጎ ውጤትም ተገኝቶበታል።  

 

ይህም በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሦስትዮሽ ድርድሩን ግብጽ ባቋረጠችበት ወቅትም ሁለቱ ሕዝቦችና አገራት ተጠቃሚ የሚሆኑት ከውይይትና ችግሮችን በመነጋገር በመፍታት እንጂ በሌሎች አማራጮች እንዳልሆነ አስመሮበት ነበር።

 

ያም ሆነ ይህ ግን ኢትዮጵያና ግብጽ ከአባይ ባሻገር በርካታ የግንኙነት ዘርፎች አሏቸው። እነዚህን አማራጮች ለመጠቀም የሚያስችል የጋራ መርሃ ግብርን መንደፍና በቁርጠኝነት መተግበር የግድ ይላል።

 

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጁ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ  የአባይን ውኃ በፍትኃዊነት ለመጠቀም እንጂ የግብጽን ሕዝብ የሚጎዳ ልማት ለማድረግ ፍላጎት የለውም። የአገሪቱ የውጭ ፖሊሲም ቢሆን የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ ነው።

 

ከዚህ አንጻር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለግብጽም ሆነ ለሱዳን ህዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ በመሆኑ የሚያወዛግብ ሊሆን አይገባም። በዚህ ልማት በጋራ ከመጠቀም ባሻገር ሁለቱ አገራት የትብብር መርህ ግብራቸውን የማስፋትና በኢኮኖሚ ተሳስረው የማደግ አቅጣጫን ሊከተሉ ይገባል።

ቀደም ሲል የነበረው የግብጽ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ከመሥራት ይልቅ ሁለቱ አገራት ወደ ውዝግብ እንዲገቡ የሚያደርግ አካሄድን ነበር ሲከተሉ የነበሩት። በተለይ በመሣሪያነትና እንደመከላከለያ ሲጠቀሙባቸው የነበሩት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ከግብጽ ፈቃድ ውጭ ማንም አገር በውኃው መጠቀም እንደማይችል ነው። ይህ ካልሆነ ግን ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ በሚል አልፎ አልፎ ዛቻ በመሰንዘር የሌሎችን ቀልብ ለመሳብ ጭምር ይጠቀሙበት ነበር።

 

እንደዚያ ዓይነቱ አካሄድ ባለንበት ዘመን የሚያመጣው ውጤት እንደሌለው አዲሱ የግብጽ መንግሥት የተገነዘበ ይመስላል። የሚያዋጣው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትብብር ማድረግ እንደሆነም ግንዛቤ በመፍጠር አባይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማ መሆኑን መገንዘብ  የሚያስችል ነው።