ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ መካከል መተማመን የጠፋባትና የእርስ በርስ ጦርነት የሰፈነባት አገር ነበረች – ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት። ሰው ሰራሹ ችግር ከተፈጥሮ ጋር ተቀናጅቶ አገሪቱ በድህነት ማጥ ከመዘፈቋም ባሻገር ሕዝቦቿ በድህነት አረንቋ እንዲሰምጡና በድህነት እንዲማቅቁ ምክንያት ሆኖ ነበር። አገሪቱ ከዚያ አስከፊ ድህነት ትላቀቃለች፤ ከዚያ ሁከትና ብጥብጥ ወደ ሠላም ጎዳና ትመለሳለች ብሎ ማሰብ አዳጋች ነበር። ዛሬ ግን ትናንት አይደለም—ያ ሁሉ ነገር አልፏል።
ኢትዮጵያ በሕዝቦች ተሳትፎና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የተሰለፈች ሀገር እንድትሆን ራዕይ ተይዞ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦችን ለማምጣት በሚያስችል መልክ እንቅስቃሴው ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሀገራችን ላለፉት 14 ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ተከትሎ እድገቱ ዘላቂና የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ አቅዳ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ቀዳሚው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ2003 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው ቀደም ሲል በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት እንደ መነሻ በመውሰድ ብሎም ድህነትን ታሪክ በማድረግና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ዓላማ አንግቦ ነበር። በዚህ የዕቅድ ዘመን ብዙ ለውጦችን ማጣት ተችሏል።
ይህነዕቅድ ተከትሎ በመንግስት የተነደፈው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም (ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ) ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። የዕቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብም የልማት ውጥኑን ለማሳካት ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ልማታችን ኤክስፖርት መር ሆኖ እንዲመራ በእቅዱ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል። የአገሪቱ ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል። በሌላ መልኩ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ አገራችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን ምርቶች መተካት ነው። ከዚህ አኳያ በሰፊው ሊሰራባቸው የሚገቡ ዘርፎች ተለይተዋል። ከተያዙት ዓበይት የኢንዱስትሪ ግንባታዎች አንዱ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ነው። እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ያላቸውን ማህበረሰባዊ ፋይዳ ለመቃኘት እሞክራለሁ። በቅድሚያ ግን ከነባር ሃቆች ልነሳ።
እንደሚታወቀው ሀገራችን ለስኳር ልማት ተስማሚ የአየር ጠባይ ካላቸው የዓለማቸን አገራት በቀዳሚነት ትመደባለች። ለሸንኮራ አገዳ ምርት የሚውል እስካሁን በሚፈለገው ደረጃ ስራ ላይ ያልዋል ሰፋፊ የእርሻ መሬትም ያላት አገር ነች። በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ያላት እምቅ ሃብት በተገቢው መልክ ሥራ ላይ በማዋል ድህነትን ለመቅረፍ አጋዥ ሳይሆን ለዘመናት ቆይቷል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበሩት ጥቂት ፋብሪካዎችም ቢሆኑ የማስፋፋት ስራዎች አልተደረገላቸውም። የሚጠቀሙበት የቴክኖሎጂ ደረጃም የቆየ ከመሆኑ የተነሳ ምርታማነታቸውን ማረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በዚህ ምክንያት የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም። ሕዝቡ የሚፈልገውን ያህል አቅርቦት ባለማግኘቱ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን መንግሥት በከፍተኛ ወጪ ከተለያዩ አገራት ስኳርን ማስገባት የግድ ሆኖበታል።
መንግስት በአንድ ወቅት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከተለያዩ አገራት ስኳር እየገዛ በማምጣት ያከፋፍል እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ችግሩን ለማቃለል ጊዚያዊ መፍትሄ ተደርጎ ተወስዷል፤ ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አልቻለም፤ ይህን ጉዳይ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት ዘርፉን ለማልማት ቆርጦ ተነስቷል፤ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴም ገብቷል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበሩትን የስኳር ፋብሪካዎች በተገቢው መልክ በማስፋፋትና የያዙትን የምርት ቴክኖሎጂ በዘመናዊ መሣሪያዎች የመቀየር ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል፤ ከእነዚህ ነባር ፋብሪካዎች የሚገኝ ምርትን ማሳደግ የሚቻልበት አቅጣጫም ተቀይሷል። የነባሮቹን ምርታማነት ከማሳደግ ጎን ለጎን አዳዲስ ፋብሪካዎችን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት የህዝቡን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ይገኛል። ምንም እንኳን ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ ቢሆኑም፤ የመጪው ጊዜ ተስፋዎች መሆናቸው ግን የሚያጠያይቅ አይደለም።
የስኳር ልማት ፕሮጄክት የኢንዱስትሪና የግብርና ዘርፎች ከፍተኛ ተመጋጋቢነት እንዲኖራቸው በማገዝ ረገድ ቀላል የማይባል ድርሻ ይኖረዋል። ከስኳር ምርቱ ጎን ለጎን ለግብርናው ዘርፍ መጠናከር የሚያግዙ ተግባራት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል። በተያያዥነት ሊሰሩ ከሚችሉት ተግባራት አንዱ የኢታኖል ምርት ነው። ኢታኖልን ከስኳር ፋብሪካዎቹ ተረፈ ምርት በሰፊው በማምረት ሀገራችን ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ ያግዛል። የነዳጅ ሃብትን አፈላልጎ የማውጣት ተግባር በተገቢው መንገድ እያስኬዱ፤ ከስኳር ምርቱ ጎን ለጎን ደግሞ የኢታኖል ምርትን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የሀገሪቱን ወጪ በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ ፍቱን መድሃኒት ይመስለኛል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኢታኖል ምርቷን በማሳደግ ከቤንዚን ጋር በመቀላቀል ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ አስችሏል። ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑት ተግባሮችም ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ኢታኖል መጠን ባደገ ቁጥር ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የነዳጅ መጠን ለመቀነስ ስለሚያስችላት በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከዚህ አኳያ የሚሰጠው ጠቀሜታም የጎላ ይሆናል። ከኢታኖል ምርት ጎን ለጎን የስኳር ፋብሪካዎቹ በመቋቋማቸው ምክንያት የሚገኘው ሌላው ጥቅም የዓሣ ምርት ነው። በእነዚህ ትላልቅ የስኳር ፋብሪካዎች በሚገነቡ ሰው ሰራሽ ሐይቆች ዓሣን በሰፊው ማምረት የሚያስችል ነው።
ይህ ሁኔታም ፋብሪካዎቹ የሚገኙባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በሁለት መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል። አንደኛው ዓሣን እያራባ ለምግብነት መጠቀም ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዓሣን በሰፊው እያመረቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል። የተፈጥሮ ሐይቆች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የዓሣ ምርትን ከራሳቸው ምግብ አልፎ ለገቢ ማስገኛም የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህንን ተሞክሮ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች በማስረፅ ሰው ሰራሽ ሐይቆቹን የዓሣ ምርት በማስፋፋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።
እንስሳትን ማድለብ ሌላኛው የፋብሪካዎቹ ጠቀሜታ ነው። በእነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች አካባቢ የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደሮች የፋብሪካዎቹን ተረፈ ምርቶች እየተጠቀሙ እንስሳትን እንዲያረቡና እንዲያደልቡ ይደረጋል። እናም አርብቶ አደሩ ከዚህ ተግባር ተጠቃሚነቱ ይጨምራል። ከዚህ ጎን ለጎንም አካባቢው ወደ ከተማነት ስለሚቀየርና እንደ መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ስለሚስፋፉ የሚያደልቧቸው እንስሳት ለገበያ የማቅረብ ችግር አያጋጥማቸውም። ይህም ቀደም ሲል በመሠረተ ልማት ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ አቅርበው በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግርም የሚፈታ ይሆናል።
አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ በእነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች መከፈት ምክንያት የሚያገኘው ሌላው ጥቅም ደግሞ መስኖ ገብ እርሻ ልማትን ማከናወን ነው። መስኖ ገብ ማሳዎችን በማስፋፋት በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያመርቱ ይደረጋል። በዚህ መልክ አርሶ አደሩ የግብርና ምርቱን ለማሳደግ የሚያስችለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረግለታል። የስኳር ልማት ፕሮጀክቶቹ የሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት በማሟላት የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት በተጨማሪ በሚቋቋሙበት አካባቢ የሚኖረውን ኅብረተሰብ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። በዚህ የተቀናጀ እንቅስቃሴም ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናል።
ከእነዚህ መካከል ፋብሪካዎቹ በሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ይጠቀሳሉ። ለኅብረተሰቡ በቂ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የመንገድ፣ የጤና፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንደሮችና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እየተሟሉ ነው። ከፋብሪካዎቹ በቀጥታ የተያያዙ እንደ ግድብና ውኃን ለመጥለፍ የሚያስችሉ ሥራዎችም ሳይቆራረጡ በመከናወን ላይ ናቸው።
ያም ሆነ ይህ ግን በመንግስት ደረጃ ተይዘው በመከናወን ላይ የሚገኙት የስኳር ልማት ፋብሪካዎች ከስኳር ልማት ባሻገር ማህበራዊ ፋይዳው የትየለሌ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ፋብሪካዎቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ይዘውት የሚመጡት ማህበራዊ ትሩፋቶች የየአካባቢውን ህብረተሰብ የዘመናት የመልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል።