በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክርስትናና በእስልምና ኃይማኖትቶች ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አልፎ…አልፎ እንደሚታዩና የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ማጠንጠኛቸውም ፀረ ሠላም አስተሳሰብና ግለኝነት እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ይህ እንቅስቃሴ ከኃይማኖት አክራሪነትና ከሽብርተኝነት ተግባራት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ከዚህ ቀደም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብዙ…ብዙ ተብሏል፤ በበኩሌ መነሻ ነጥቦችን ጠቃቅሼም አስተያየቴን አስፍሬያለሁ። በመሠረታዊ ትርጓሜው ላይ ብዥታ ያላቸው እና የሚደናገሩ ሰዎች ዛሬም ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ጉዳዩን የበለጠ ማጥራት ተገቢነት አለውና ትንሽ ማብራራትን ፈለግሁ። በቅድሚያ ብዙዎች የሚስማሙበትን ትርጓሜ መነሻ ሀሳብን በመጋራት ጽሁፌን ልጀምር።
አክራሪነት ማለት አጥባቂነት ማለት አይደለም። አጥባቂነት ለአንድ ኃይማኖት ተከታይ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው የያዘውን እምነት ማጥበቅ ይችላል። ይህ ማለት ኃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚያዘውን ነገር በሙሉ ያለምንም ማመንታት መፈፀም ማለት ነው። አንድ የእስልምና ወይም የክርስት ኃይማኖት ተከታይ ኃይማኖቱን አጥብቆ ሊይዝ ይችላል። ኃይማኖቱን አጥብቆ በመያዙ ተቃውሞ አይቀርብበትም። የሚቃወመውም ሰው አይኖርም። መንግሥትም ቢሆን ኃይማኖትህን ለምን አጥብቀህ ያዝክ የሚል ነገር አያመጣበትም – ይህ ህገ መንግሥቱ የሰጠው መብት ነውና።
አጥባቂነት ማለት ድንጋጌን ሳያዛንፉና በሌላ ጥቅም ሳይታወሩ አሳምሮ መያዝና መፈፀም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት የሚጎዳ ሌላ አካል አይኖርም። አጥባቂነት የሌላን ወገን እምነትም ሆነ ሌላ ተግባር የሚነካ አይደለም። የሌላውን መብት የሚተላለፍና እኔ ያልኩት ብቻ የሚል አይደለም። ስለዚህ አጥባቂነት በመሠረቱ የማንም ሥጋት አይደለም። የሠላም ፀርም አይደለም። አክራሪነት ማለት ግን ከላይ ከተዘረዘረው የተለየ ነው። አክራሪነት እኔ ከያዝኩት እምነት ሌላ እምነት የለም የሚል ነው። እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ስለሆነ ሁሉም ሰው እኔ የያዝኩትን ይያዝ የሚል አካሄድ አለው። በዚህ ምክንያትም የሌሎች ወገኖች ፍላጎትንና መብትን የሚተላለፍ ይሆናል። ይህ ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። የሌሎች መብት ይታፈን፤ የእኔ ብቻ ይከበር የሚል እይታ ለሠላምም የሚበጅ አለመሆኑ አያጠራጥርም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ኃይማኖት አማኞች ባሉባቸው አገራት አክራሪነት ተቀባይነት ስለማይኖረው ወደ አሸባሪነት ይቀየራል። አሸባሪነት ደግሞ እያደፈጡ በሠላማዊ ዜጎችና በህዝብ ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀምን ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ኃይል ነው። ይህ ኃይል በመሠረቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ነው። ፀረ ሠላምና መረጋጋት ኃይልም ነው። ዜጎች በሠላም ውለው እንዳይገቡ የሚያደርግ የሁከት እና የሥጋት ኃይል ነው።
በዓለማችን በተለያዩ አገራት እየታየ ያለው የአሸባሪዎች ድርጊትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ በመሠረቱ ፀረ ሕዝብ የሆነ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ተግባር ከኃይማኖት ጋር አስተሳስሮ በኃይማኖት ሽፋን ለመፈፀም የሚደረገው ጥረት ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ገጽታው ነው። አክራሪነትን በጽንሰ ሃሳብ ብቻ ለመረዳት መሞከር ትንሽ ያስቸግር ይሆናል። በተለይ ከአጥባቂነት ጋር ያለውን ልዩነት ለመገንዘብም ሳያስቸግር ይቀራል የሚል እምነት የለኝም። የአክራሪነትና የአጥባቂነት ተግባራትን ማየቱ ግን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ያሳየናል። አጥባቂነት ሠላማዊ ተግባር ነው። አክራሪነት ግን ፀረ ሠላም ተግባር ነው። አጥባቂነት በራስ ዙሪያ የታጠረ ነው። አክራሪነት ግን የሌሎች ህይወትና መብት የሚነካ እንቅስቃሴ ነው።
አክራሪነትን ይበልጥ ለመገንዘብ ደግሞ በተለያዩ አገራት የተፈፀሙና የበርካታ ንጹኃንን ህይወት የቀጩ ድርጊቶችን ማየት ጠቃሚ ይሆናል። በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በሶማሊያና በናይጄሪያ የተፈፀሙ የአሸባሪዎች እኩይ ተግባራትን በመመርመር አክራሪነትና ሽብርተኝነት ምን ያህል አስከፊ ገጽታ እንዳላቸው ለመገንዘብ አያዳግትም። እነዚህን ተግባራት የሚያራምዱ ወገኖች ደግሞ ፀረ ሠላምና ፀረ ህዝብ ኃይሎች መሆናቸውን ለመረዳት የሚያጠራጥር ነገር አይኖረውም። አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነት ከአንድ ኃይማኖት ወይም ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር የሚያያዝ እሴት እንዳልሆነ በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች የሚያካሂዱ ምሁራን ይገልጻሉ። የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ምንጩ የተለያየ የተዛባ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ባህሪ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ብዝኃነትንና ልዩነትን የማይቀብል ስብዕና ባላቸው ሰዎች ዘንድ የሚከወን እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ። ሌሎችን በማንነታቸው ለመቀበል ያልተዘጋጁና ማንነታቸውን ጥለው እነሱን እንዲመስሉ የሚሹ ሰዎች ናቸው አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉት። መቻቻል የሚባል ነገር የማይዋጥላቸውና በእነሱ አስተሳሰብ የበላይነት መረጋገጥ ብቻ የሚያመልኩ ሌላውንም በዚህ ደረጃ የሚለኩ ሰዎችና እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያዘለና ከእኔ ሌላ ላሳር የሚል እምነት የያዙ ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚያራምዱት ተግባር ነው – አክራሪነት። ይህ ደግሞ ሠላምን ለማረጋገጥና የህዝቦችን እኩልነት ለማስፈን የማያስችል ጉዳይ ነው። ወደ አገራችን ተመልሰን ያለውን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን ስናይም ከላይ ከተተነተነው የተለየ ነገር አይኖረውም። የኢትዮጵያን ሠላም የማይመኙና የያዘችውን የልማት ጎዳና ማደናቀፍ ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ለሚተጉ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነት የተደፈቀው አስከፊ ሥርዓት ናፋቂና፣ የከሰረ ፖለቲካቸውን ለማራመድ ሲሉ ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በኃይማኖት ሽፋን በአክራሪነትና በፅንፈኝነት ጎዳና ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴያቸውም በማናቸውም መስፈርት ቢለካ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንደሆነ ለማየት አያስቸግርም።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 11 መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ኃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በማለት በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል፡፡ አክራሪዎች ግን ይህንን መብት ለመሸርሸር የማያደርጉት ነገር የለም። መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለት መንግሥት የህዝቦችን ሠላም አይጠብቅም፣ ህግንና ደንብን አያስከብርም ማለት አይደለም። የኃይማኖት ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ግን ይህንን ይጠቀማሉ።
ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ እያደረጉና ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጩ መንግሥት በዝምታ እንዲመለከታቸው ይፈልጋሉ። የአገሪቱን ሠላም ሲያደፈርሱ መንግሥት በታዛቢነት እንዲያይ መፈለጋቸው የመንግሥት ተግባርና ኃላፊነት ጠፍቷቸው ሳይሆን ኅብተሰቡን ለማደናገር ነው። ስለሆነም በየትኛውም መንገድ መንግሥታዊ ኃይማኖት ለመመሥረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ህገ መንግሥታችንን ለመናድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ማናችንም ብንሆን ብዥታ የለንም፡፡ መንግሥታዊ ኃይማኖት በመደንገግ ወይም ኃይማኖታዊ መንግሥት በመፍጠር ሌሎች ኃይማኖቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመደፍጠጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም – ኢ ህገ መንግሥታዊ የሆነ አፍራሽ አስተሳሰብ /ተግባር ነውና። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን ከሆነ ሁለት አሥርት ዓመታት አልፎታል። የአገሪቱ ሕገ መንግሥት መጽደቅን ተከትሎ የብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ተረጋግጧል፤ የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እውን ሆኗል፤ የፕሬስ ነጻነት ተከብሯል፤ የኃይማኖት ነጻነት ተረጋግጧል። ይህ ደግሞ ላለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ የኃይማኖት ነጻነት በመረጋገጡ ዜጎች የመረጡትን ኃይማኖት የማምለክና ኃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ያለምንም መሸማቀቅ መፈፀም የሚያስችላቸው ሥርዓት ተፈጥሯል። ዛሬ ይህ ነጻነት ሥር ሰዷል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የኃይማኖት ነጻነት ጥያቄ የሚነሳበት መሠረት የለም። ያለንበት ዘመን የኃይማኖት ነጻነት እንበለ ገደብ የተረጋገጠበት ሥርዓት በመሆኑ መንግሥት በኃይማኖት የማይገባበት ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ የማይገባበት ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ ከሆነ ይኸው ከሃያ ዓመት በላይ ተቆጥሯል።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የከሰሩ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በመሣሪያነት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት በጣም ከፍተኛ ነው። ከደርግ ውድቀት ማግሥት አንዳንድ የሥርዓቱ ርዝራዦች የወሰዱት አማራጭም ከዚህ የተለየ አልነበረም። አገሪቱን ባስተዳደሩበት 17 ዓመታት ኃይማኖትን ለማጥፋት በወሰዱት እርምጃ ኃይማኖት ህልውናውን አጥቶ ነበር። የኃይማኖት ነጻነት የሚታሰብበት አልነበረም። ቤተክርስቲያናትና መስጂዶች ወታደራዊ ካምፖች ሆነው ነበር፡፡ የሥርዓቱ አቀንቃኞች ወደ እምነት ሥፍራዎች መሄድም ሆነ ማመን የተወገዘ ነበር። አማኞችም ለኃይማኖታዊ ተልዕኮ ሲሰባሰቡ ፀረ ህዝብ እየተባሉ ለግርፋት፣ ለእሥርና ለግድያ ይዳረጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው።
ከደርግ ውድቀት ማግሥት የተረጋገጠው የኃይማኖት ነጻነትን በመጠቀም አንዳንዶች ህቡዕ አጀንዳቸውን በኃይማኖት ሽፋን ለማራመድ በሁሉም የኃይማኖት አማኞች መካከል መሰግሰግን መርጠው ነበር። የኢሕአዴግ መንግሥት የክርስትና እምነት ሊያጠፋ ለሌሎች ኃይማኖቶች ነጻነትን ሰጥቷል የሚል ማደናገሪያ ይዘው በክርስትና ኃይማኖት ሽፋን የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማናጋት ቀላል የማይባል ጥረት አድርገዋል። በእምነት በዓላት ህዝበ ክርስቲያኑ ለፀሎትና ኃይማኖታዊ ተልዕኮ በሚሰበሰብበት ወቅት ብጥብጥና ሁከትን በማንሳት ሠላምን ለማደፍረስ ሙከራ ቢያደርጉም ምዕመናን የፖለቲከኞቹ ድብቅ ሴራ እየተገነዘቡ በመምጣታቸው ዓላማቸው ሊከሽፍ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ ሳይቆርጡ ሥልታቸውን እየቀያየሩ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ምዕመኑ የከሰሩ ፖለቲከኞች በእምነት ተቋማት እየተገኙ ከእምነቱ አስተምህሮ የተለየ ነገር በሚያቀርቡበት ወቅት እንደ ወረደ ከመቀበል ይልቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመረ፡፡ መንግሥት ኃይማኖት ላይ የሚያደርገው ምንም ዓይነት ጫና እንደሌለ የሚያየው የእምነቱ ተከታይ ህዝብ ለምን? ማለት ጀመረ። ኃይማኖታዊ ተልዕኳችንን በነጻነት እያራመድን እስከሆነ ድረስ ለምን በእምነት ቦታዎቻችንና በኃይማኖታችን ስም የፖለቲካ ስብከት ይሰበካል? በእምነት ሥፍራዎቻችን ለምን ኃይማኖታዊ ተግባራትን ብቻ አንፈጽምም? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አማኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የታቀደው ሴራ ሳይሳከ ቀረ። ፖለቲከኞቹ ግን ሥልታቸውን እየቀያየሩ በኃይማኖት ሽፋን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ቀጠሉ።
ሥልታቸውንም በመቀየር የክርስትና ኃይማኖት አማኞችን ከእስልምና ኃይማኖት አማኞች ጋር ማጋጨት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈው ተንቀሳቀሱ፡፡ የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ፖለቲከኞችን ወደ እስልምና እምነት አማኞች እንዲሰገሰጉ እንዲሁም የክርስትና ኃይማኖት አማኝ አባሎቻቸውን ከክርስትና ኃይማኖት አማኞች ጋር እንዲሰገሰጉ በማድረግ በሁለቱ አማኞች መካከል መቋጫ የሌለው ግጭት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ቀላል አልነበረም፡፡ ፖለቲከኞቹ የእስልምና አልባሣትን በመልበስና የእስልምና ኃይማኖት አማኞች የሚጠቀሙባቸውን የእምነት ቃላት አዘውትረው በመጠቀም በቤተክርስቲያኖች እየገቡ በመጮህና ህዝበ ክርስቲያኑን ለማበሳጨትና ለግጭት እንዲነሳሳ በማድረግ ሠላምን ለማደፍረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል። በዚህ መልክ ያደረጉት ጥረትም ለዘመናት የዘለቀውን የህዝበ ሙስሊሙና የህዝበ ክርስቲያኑን የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል ሰብሮ ዓላማቸውን ሊያሳካላቸው አልቻለም። ከዚህ አንጻር እቅዳቸው መክኖ ቀርቷል። ከ1997ቱ አገራዊ ምርጫ ማግሥትም በፖለቲካው ሜዳ ሮጠው መቅደም ያልቻሉና ድል ያልቀናቸው ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በመሣሪያነት ለመጠቀም ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። በኃይማኖት ሽፋን ወጣቱን ለሥውር የፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈፀሚያ በማሰማራት ሰፊ ዘመቻ አድርገዋል። ህዝበ ክርስቲያኑ ኃይማኖታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት በሚሰባሰብባቸው የእምነት ቦታዎች በመገኘት ብጥብጥና ሁከትን ለማንገስ ያልበጠሱት ቅጠል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በአገሪቱ ባለፉት 25 ዓመታት በተለያየ ሥልትና በተለያየ ኃይማኖት ሽፋን የተደረጉ ጥረቶች ተጽዕኖ አላሳደሩም ማለት ባይቻልም ኃይማኖታዊ ተልዕኮ እንዳልነበራቸው እርቃናቸውን እየወጡ በመምጣታቸው ዛሬ…ዛሬ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም።
የኢትዮጵያ እድገት እንደ እሣት የሚያንገበግባቸው አካላት ተስፋ ሳይቆርጡ ሥልታቸውን እየቀያየሩ ሠላም የማደፍረስ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል። የከሰሩ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን ለድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ በመሣሪያነት መጠቀምን ለምን መረጡ? ተግባራቸው በተደጋጋሚ እየተጋለጠ ለምን መቋጫ አላገኘም? አማኞች እምነቱ ከሚያዘው ውጭ የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው ለምን አፋጣኝ እርምጃ አይወስዱም? የሚሉትንና ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ ተገቢነት ይኖረዋል። እነዚህ የከሰሩ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በመሣሪያነት መጠቀም የፈለጉበት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ለኃይማኖቱ ቀናኢ ለእምነቱ ሟች መሆኑን ስለሚያውቁ ነው። የእስልምናም ሆነ የክርስትና ኃይማኖት አማኞች ለኃይማኖታቸው ህወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት እንደማያመነቱ በመገንዘብ ነው። ከዚህ አንጻር ኃይማኖታዊ የመሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አማኞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት በመርዝ የተለወሰ ማር ለማጉረስ ጥረት ማድረግ ያዋጣል የሚል እምነት በማሳደራቸው ነው። ሌላው ደግሞ በኃይማኖት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች መቋጫ አይኖራቸውም የሚል እምነት በማሳደራቸውና ህዝቡን መቋጫ ወደሌለው ግጭትና ሁከት ለማስገባት በማቀድ ነው። ለዚህም ነው አንድ ጊዜ በእስልምና ኃይማኖት በሌላ ጊዜ ደግሞ በክርስትና ኃይማኖት ሽፋን እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት። ሁኔታው በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም እነዚህ ፖለቲከኞች የሚያነሷቸው ኃይማኖት አዘል ጥያቄዎችና የሚያደርጓቸው ኃይማኖት ለበስ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ የተቃኙ በመሆናቸው መቋጫ አልተገኘላቸውም። ትክክለኛ የኃይማኖት ጉዳይ መስለው እንዲታዩ በየወቅቱ ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር እያቆራኙ ከማቅረባቸው በላይ በእያንዳንዱ እምነት ውስጥ ለተሰገሰጉ አባሎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አንዳንድ ፈሪሃ ፈጣሪ የራቃቸውን አማኞች በገንዘብ ኃይል በማታለል የእነሱን ፍላጎት እንዲያራምዱ ስለሚያደርጉ ነው። ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ ያነሷቸው ጥያቄዎች ኃይማኖታዊ ተልዕኮ እንደሌላቸው እርቃናቸው የወጡበት ሁኔታ ቢኖርም ከውጭ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍና ሥልታቸውን በመቀያየር አፍራሽ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ጥረት ስለሚያደርጉ መቋጫ የለሽ ሆኗል። በየወቅቱ ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር ነገሮችን በማዛመድ የተለያየ ኃይማኖት ለበስ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ አማኙ ኅብረተሰብ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የተዛመደውን ነገር እውነት መስሎ ስለሚታየው እውነታው እስኪወጣ ድረስ በቀናኢነት ስለሚቀበል ነው። ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ህዝበ ክርስቲያኑ ማንኛውም ነገር ከፈጣሪ መሆኑን ያምናል። ክፉ የሚሰራ ዋጋውን ከፈጣሪ ያገኛል የሚል እምነት ስላለው ይታገሳል። የሚነሳው ነገር ኃይማኖታዊ ሽፋን የለበሰ ፖለቲካ በመሆኑ ግን አንድ ጊዜ ተነስቶ የሚቆም አይሆንም። በተደጋገመ ቁጥር ኃይማኖታዊ ሥርዓቱንና አስተምህሮ እየሳተ ወደዋና ዓላማው መግባት ይጀምራል። ውሎ ሲያድርም ኃይማኖታዊ ተልዕኮ እንደሌለው ፈጦ ይወጣል።
በተለያየ ጊዜ በኃይማኖት ሽፋን የተደረጉ ሙከራዎች ውጤት የሚያሳየውም ከዚህ የተለየ አይደለም። የክርስትናም ሆነ የእስልምና ኃይማኖቶች አስተምህሮ እንደሚያስቀምጠው አንድ ሰው ለሁለት አለቆች ወይም ጌቶች መገዛት አይቻልም። ገንዘብንና ፈጣሪን አጣምሮ መውደድ አይቻልም። ለገንዘብ ያደረ አምላክን ትቷል፤ ገንዘብን የናቀ አምላክን ወዷል ይላል አስተምህሮው። አንዳንድ አማኞች ለገንዘብ በመገዛት ሌላውን አማኝ ለማሳመን ጥረት ስለሚያደርጉ የኃይማኖቱ ተከታዮች የጉዳዩን ውስጠ ምስጢር ለማወቅ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ለጊዘውም ቢሆን በፈጣሪ ስም የሚመጣ በመሆኑ ይቀበሉታል። ተስፋ የቆረጡ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በሁለት መልክ ይፈልጉታል። አንደኛው በኃጥያትና በክፋት የተጨማለቀ ህሊናቸው ትንሽ ለማሳረፍ ያስችለናል ከሚል እምነት ነው።
ሌላው ደግሞ በዚያ ለኃይማኖቱ ቀናኢ የሆነ ህዝብ በሚሰበሰብበት የተቀደሰ ሥፍራ ኃይማኖት ለበስ ህቡዕ አጀንዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዘናል ብለው ስለሚያምኑ ነው። በኃይማኖት ሽፋን የአገራችንን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶች ቁጥር የት የለሌ ነው። በሁሉም የኃይማኖት እምነቶች እየተከሰተ ያለ ጉዳይ ነው። በተለያዩ የኃይማኖት እምነቶች ይከሰት እንጂ ዓላማው አንድ እና አንድ ነው። ዓላማው የአገሪቱን ሠላም በማደፍረስ በግርግር ለመጠቀም መሞከር ነው። የከሰሩ ፖለቲከኞች ከኃይማኖትና ከጽንፈኝነት የሚቆራኙትም ከዚህ አንጻር ነው። ተስፋ የቆረጠ አጥፍቶ መጥፋትን ይመርጣል። ሌላውንም ይዞ መሞትን ይመኛል። የሚታየው ህይወትም ሆነ ብሩህ ነገር አይኖርም። ሁሉም ነገር ጨለማ ነው። ጨለማውን ግን ብቻውን ለመጋፈጥ አቅምና ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ አይኖረውም። ይህ በውስጥ ከሰነቀው ህቡዕ አጀንዳ ጋር ሲጣመር የጥፋት መንገድን መከተል ዓይነተኛ ስትራቴጂ አድርጎ ይጠቀማል። ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” አይደል ተረቱ። የከሰሩ ፖለቲከኞች፤ ኃይማኖትና ጽንፈኝነት ያላቸው ቁርኝትም ከዚሁ የመነጨ ነው።