ትኩረት የሚሻው የኃይል ምንጭ

 

 

አገራችን ኢትዮጵያ የተጓዘችባቸው ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እንደሌሎች መስኮች ሁሉ የጸረ ድህነት ዘመቻው ልዩ ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል የመሰረተ ልማት ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ መንግስት ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በማልማት የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ታሻሽል ዘንድ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ሊስፋፉባት ይገባል ብሎ በማመን ገና ከጠዋቱ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ሥራ ላይ መጠመዱም ይታወቃል፡፡ የደረስንበትን ደረጃ ስናሰላ መንግስት መሰረተ ልማት ማስፋፋት የጀመረው በዝቅተኛ የፋይናንስና የመፈፀም አቅም ላይ እያለም ጭምር የነበረ ስለመሆኑና ይህንንም “የመንግስት ሚና ዝቅ ማለት አለበት” ከሚለው የኒዮ ሊበራል አስተሳሰብ ጋር በመፋለም ጭምር የነበረ መሆኑን እዚህ ጋር ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ በልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ የተመራ ነበር ባይባልም በየመስኩ ግን እጅግ ቁልፍ የሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታ  ስራዎች  ተከናውነዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በተለይ ለሁሉም እንቅስቃሴያችን ቁልፍ በሆነው የሃይል ልማት ዘርፍ ያኔም መትጋቱ የማይተባበል ነው። በጣና ሃይቅ ላይ የተሰራው የጫራ ጫራ ግድብና በርካታ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታዎች፣ መንግስት ገና ከጠዋቱ ለኢነርጂ ልማት ልዩ ትኩረት እንደሰጠ ከሚያመላክቱ ማሳያዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡   

ካሳለፍናቸው 15 ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በዚህ ረገድ የተከናወኑት ስራዎች እጅግ አመርቂና ሁሉ አቀፍ ለሆነው እድገታችን መሰረቶች ናቸው። በዚሁ መሰረት ይህ ትርክትም በሃይል ዘርፍ እየሄድን ያለንበትን ደረጃ በተለይ የቅርቦቹን ዋቢ እያደረገ የሚመዝን ይሆናል።

ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በተለይ ከተቀጣጠለው የተሃድሶ እንቅስቃሴና በዚህም አማካይነት ተነድፈው ተግባር ላይ ከዋሉት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በኋላ የሃገራችን የመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በዋነኛነት በልማታዊ አስተሳሰብና አመክንዮ ላይ ተመስርቶ እጅጉን እንዲስፋፋ ስለመደረጉ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ አገራችንን ከማሳደግ አኳያ ሀብት ፈጣሪ የሆኑት ዋነኛ ዘርፎች ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ እንደሆኑ ታምኖበት እነዚህን ለመደገፍ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ በተለይም የሃይል ዘርፍ የመንግስት ዋነኛ የርብርብ ማዕከል መሆኑንም ጭምር፤ ይህ ዘመቻ ደግሞ   ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጀምሮ በሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ እቅድ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እስከ ባቡር ልማት ድረስ የተጀማመሩት ፕሮጀክቶች አገራችን የዛሬና የትላንት የመሰረተ ልማት ጉጉት ከማቃለል አልፋ የነገን እድገት የሚሸከም የመሰረተ ልማት አውታር ወደማስፋፋት እየተሸጋገረች እንደሆነ የሚያሳዩ ስለመሆናቸውም እየተነገረ ነውና የመነገሩን እውነታነት በቅርብ አስረጂዎች አስደግፈን እንመልከት፡፡ ከፍተኛ ሃይል የሚያመነጩትና ህዝቡ ራሱ ባለቤት የሆነባቸው ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አይነቶቹ ለጊዜው አጀንዳችን አይሆኑም ። ወጋችን ብዙ ስለማናውቃቸው የሃይል ሃብቶቻችን ነው።

በምዕራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ ከአዲስ አበባ በ270 ኪ.ሜ ርቀት፤ ከዞኑ መዲና ከሻሸመኔ  በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኮርቢቲ ቀበሌ ዙሪያውን በተራራ የተከበበና ዕምቅ የጂኦተርማል ሀብት ከሚገኝባቸው የስምጥ ሸለቆ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ ተራራው ከስሩ የሚንቀለቀለው እሳተ ጎመራ ሲያንገበግበው የውስጥ ቃጠሎና ንዳዱን ለመተንፈስ ፈልጎ ኡፍ እያለ ድምጽ አውጥቶ የእንፋሎት ትንፋሹን ይረጫል፡፡

በእንፋሎት ጉም ተጋርዶ በዚንክና ሰልፈር በታጠነው በዚያ ስፍራ በአገራችን የወደፊት ጉዞ ላይ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን የሚነገርለት ከባድ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ስፍራ በከርሱ አምቆ የያዘው እሳተ ጎመራ የሚፈጥረው እንፋሎት እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ የጂኦተርማል ሀብት አለው፡፡

ይህን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው 150 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ከዳሎል እስከ ኬንያ ድንበር ባለው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ለጂኦተርማል ኃይል መዋል የሚችሉ ከ22 በላይ አካባቢዎች ተለይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የጂኦተርማል እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥታ በመረባረብ ላይ ከምትገኝባቸው አካባቢዎችና ዘርፎች መካከልም የኮርቢቲ ቀበሌ አንደኛው ነው፡፡

ከወንዞች ኃይል ለማመንጨት እየተከናወነ ካለው ተግባር ጎን ለጎን ለጂኦተርማል ኃይል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተንዳሆ 100 ሜጋ ዋት፤ ኮርቤቲ 75 ፤ አባያ 100፤ ቱሉ ሞዬ 40 ሜጋ ዋትና ዶፋን ፈንታሌ 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል ዕቅድ ወጥቶ ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም፤ የኮርቤቲና የቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ስለአጀንዳችን በወካይነት ተመርጧል ፡፡

ከሶስት አመት በፊት ይፋ የተደረገው የኮርቤቲና ቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ስራ የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል ሲሆን፤ 1000 ሜጋ ዋት /በኮርቤቲ 500 በቱሉ ሞዬ 500/ ኃይል ለማመንጨት ለእያንዳንዱ 2 ቢሊዮን በአጠቃላይ 4 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦ ስምምነቱን የተፈራረመው ሬይኪያቪክ ጂኦተርማል የተሰኘ የአይስላንድ ኩባንያ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 500 ሜጋ ዋት የሚሆነውን የጂኦተርማል ኃይል ለማመንጨት የሚያስችለውን ስራ ለመጀመር በርክሌይ ኢነርጂና አይስላንድ ድሪሊንግ የተሰኙ ሁለት ኩባንያዎች በኮርቤቲ የመንገድ የውሀና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወኑ ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞች ባለቤት በመሆኗ የተለያዩ ግድቦችን በመገደብ ለሀይል ማመንጫነት እያዋለች ቢሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ወንዞች መጠናቸው ሊቀንስ ብሎም ሊደርቅ ስለሚችል በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ሊደርስበት የማይችለውን የጂኦተርማል ሀብት መጠቀም የግድ መሆኑን በማስላት የንፋስ፤ የጸሀይና የጂኦተርማል አማራጮችን ለመጠቀም እየሰራች መሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛና ይልቁንም ልማታዊ ነኝ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ስለሆነም በጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ መሰረት በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በተከናወነው ጥናት 22 አካባቢዎች የተለዩ መሆኑ ተመልክቷልና እነዚህን አካባቢዎችም ጨምሮ በማልማት መጠቀም የግድ ይሆናል ማለት ነው ።  

የግድ የሚሆነው ደግሞ ከላይ ከተመለከተው የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን፤ ከጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ስራ ውስብስብ ያልሆነና ቀላል ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ አቅሙን በቀላሉ እያሳደጉ መቀጠል የሚያስችል ዘርፍ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ ምን ይህ ብቻ! የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በአፍሪካ ለጂኦተርማል የሀይል ምንጭ መዋል ከሚችለው ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑና የበይ ተመልካች ሆነን የመቆየታችን እውነታም ነው የሚያስገድደን፤

የዘርፉን ቀላልነትና አዋጭነት በተመለከተም ባለሙያዎቹ ኬኒያን አብነት አድርገው ሲገልጹ ፦ ኬንያ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት ስትጀምር ከአንድ ጉድጓድ ከ2 ሜጋ ዋት ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰው፤ አቅሙን በማጎልበትና ቴክኖሎጂውን በመቀየር ብቻ ከሰላሳ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት እንደቻለችና አሁን 700 ሜጋዋት መድረስ መቿሏን በማስታወስ ነው፡፡

በእርግጥ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለውን የጂኦተርማል ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የአሉቶ ላንጋኖ የጂኦተርማል ፕሮጀክትን ማስፋፋት፤ የተንዳሆ ፕሮጀክትን ወደ ኃይል ማመንጨት ስራ ማስገባትና በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለውን የአቅም ጥናት ማጠናቀቅም እየተከናወኑ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ ጂኦተርማል የአየር ንብረት ለውጥ ቢከሰት የማይጠፋ፤ ዘለቄታዊ፤ ታዳሽ፤ በዋጋ ደረጃ ርካሽ የሆነ ቴክኖሎጂን የሚጠቀምና ለማልማት የማያስቸግር የሀይል ምንጭ ነው፡፡ በተጨማሪም ከብክለት ነጻ በመሆኑ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያደርስ፤ በግንባታ ወቅት ከአደጋ ነጻ የሆነና የሚጠቀመው ቴክኖሎጂም ያልተወሳሰበ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ በቀላሉ አቅሙን ለማሳደግ አመቺ ነው፡፡ ስለሆነም፤ መንግስት የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት አገራት በመሸጥ ኢኮኖሚውን ለመደጎም በማቀድ ባለፉት አስር ዓመታት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን ቀርፋፋ ይመስላል ፡፡

ወንዞችን መሰረት አድርገው ኢኮኖሚያችንን ከውድቀት የታደጉልንን የጊቤ አንድ፤ ሁለትና ሶስት፤ የተከዜ፤ የጣና በለስና ሌሎች የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎችን፤ይልቁንም በአገራችን እና በዜጎቿ ዘንድ ከሃይል ያለፈ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለውን እና በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዘንግተን እንዳልሆነ እዚህ ላይ ልብ ይሏል።

ጉዳያችን እና አንክሯችን ውሀን መሰረት ያደረጉ የሀይል ማመንጨት ስራዎች በአየር ንብረት ተጽእኖ ስር በመሆናቸው ዘለቄታዊ ሊሆኑ የማይችሉ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሀይል አጠቃቀም ዙሪያ ከአመታት በፊት በተደረገ ጥናት የውሃ ኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ 1 በመቶ፤ በነዳጅ ከሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል 4 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የኃይል ምንጭ የሚገኘው ከደን፤ ከእንስሳትና ከሰብል ተረፈ ምርት ነው፡፡ አብዛኛው ነዳጅ ለተሽከርካሪ ጥቅም ይውላል፡፡በዓመት 40 ሚሊዮን ቶን ማገዶ እንጨትና 8 ሚሊዮን ቶን የሰብል ተረፈ ምርት በኃይል ምንጭነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

ስለሆነም ይህን የተፈጥሮ ሀብት መንጥሮ ለማገዶነት በማዋል በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ከውሃ በተሻለ ታዳሽ ኃይል ምንጭ በሆነው የጂኦተርማል ሃይል ልማት ላይ ማተኮር የግድና ወቅቱ የሚጠይቀን ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ረገድ ምንም የለም ማለታችን  አይደለም። ይልቁንም ይጠናከር ማለታችን እንጂ!