የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን

ኢትዮጵያ በታላቅ ኢኮኖሚያዊ ሥር ነቀል ለውጥና የመሠረተ ልማት ግንባታ ውስጥ የምትገኝ አገር ስትሆን ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የገነባችና በመገንባትም ላይ ትገኛለች፡፡ ለዘመናት ገኖና ተንሰራፍቶ የኖረውን ድህነትና ኋላ ቀርነት ከሥሩ መንግሎ ለመጣል ይህ ቀረው የማይባል ትግል በብሄራዊ ደረጃ በሁሉም መስክ በህዝቦቿ ሙሉ ተሳትፎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የአገርንና የህዝብን ክብር የሚያዋርደው ድህነት እንደ መሆኑ መጠን ይህን የከፋ ጠላት ታግሎ ድል ማድረግ የሚቻለው ልማትና እድገት እንዲሰፍን ጠንክሮና ተግቶ በመሥራት ብቻ ነው፡፡ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንዳሉት መለመን ስናቆም መከበር እንጀምራለን፡፡ ይህ ዘመን የማይሽረው እውነታ ነው፡፡
ዛሬ በብዙ መስኮች በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ መከበር ጀምራለች፡፡ የቀጣናው ልዕለ ኃያል ተሰሚና ተደማጭ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ዛሬም ድህነትን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ለማንበርከክ ትግሉና ትንቅንቁ የቀጠለ ቢሆንም በአገር ደረጃ ብዙ እንደሚቀረን ብዙ መሥራትም እንደሚጠበቅ ይታወቃል ፡፡
የታላላቅ ግድቦችና የዘመናዊ የኃይል ማመንጫ ባለቤት፣ ከራሷም አልፎ ለጎረቤት አገራት ለመሸጥ የምትችልበት ደረጃ የተቃረበች፣ የንፋስና የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ባለቤት መሆን የጀመረች፣ የዘመናዊ የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር አገልግሎት በሰብ ሰሀራ አፍሪካ አገራት በቀዳሚነት የገነባች፣ አገር አቋራጭ ከባድ የባቡር መስመር መገንባት የቻለች አገር ነች፡፡
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ አውሮፕላኖች ድሪም ላይነርና ኤየር ባስ ባለቤትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአየር ማረፊያ አስፋፍታ የሰራች፣ አየር መንገዷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራት አገልግሎት ሰጪነቱና እንግዳ ተቀባይነቱ በተደጋጋሚ ዘመን የተሸለመና የተመሰገነ፣ ከራሷ ብሄራዊ የስኳር ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ አገራት ለመላክ የተዘጋጀች አገርም ነች – ኢትዮጵያ፡፡
አሁንም ብዙ ግድቦችን፣ ፋብሪካዎችን፣ መንገዶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ኮሌጆችን፣ ዩኒቨርስቲዎችን፣ ጤና ጣቢያዎችን በመሥራት ላይ ስትሆን ድሮ በሚያጠቃት ድርቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ ስሟ በተረጂነትና በተመጽዋችነት ትታወቅ የነበረችው  ኢትዮጵያ አምና የተከሰተውን ድርቅ ብዙም የውጭ እርዳታና ድጋፍ ሳያስፈልጋት በራሷ አቅም ለመቋቋም መቻሏን ለዓለም አሳይታለች፡፡ ይህንንም በማድነቅ የውጭ ለጋሾች ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ስሟ ተለውጦ በዓለማችን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት አገራት ተርታ በመጠራት ላይ ይገኛል፡፡ "የአፍሪካ አምበሣ" ሲሉ እነሲኤን ኤን በቅርቡ አወድሰዋታል፡፡ ይገባታልም፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው መንግሥት በነደፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዋጪ ትክክለኛ አቅጣጫ አገሪቱ ለመራመድ በመቻሏ ነው፡፡
ይህንን ታላቅ አገራዊ የልማትና የእድገት ጉዞ ለማሰናከል ዳግም አገራችን የኋሊት ጉዞ ውስጥ ወድቃ እንድትንሸራተትና ከድህነት ቀንብር እንዳትወጣ በመመኘት የሚራወጡ የውጭ ኃይሎችንና የውስጥ ተላላኪዎቻቸውን ታግሎ የማሳፈሩ አንገት የማስደፋቱ ድርሻ የህዝብ ነው፡፡ 
ከድህነትና ከተረጂነት የሚገኘው ትርፍ ብሄራዊ ክብርን ማጣትና አንገት መድፋት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ እየወጣን ቢሆንም አሁንም የተጀመሩትን ታላላቅ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከዳር ለማድረስ ህዝቡ ለአገር ጠላቶች ቀዳዳ ሳይከፍት አንድነቱን አፅንቶ ትግሉን በላቀ ደረጃ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በታላቅ የህዳሴ ጉዞ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗ በመደጋገም የሚነሳው፡፡
በመላው አገሪቱ በሁሉም ክልሎች ታሪክንና ትውልድን የሚቀይሩ በእጅጉም የሚያኮሩ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ብሄራዊ ሀብት የፈሰሰባቸው ታላላቅ መሠረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸው የአገሪቱን ፈጣን ልማትና ግስጋሴ በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህ ስኬትና ድል የአገሪቱን ልማትና እድገት ለማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ከፍተኛ የራስ ህመም እንደሆነባቸው ይታወቃል፡፡ አርፈው የማይተኙትም ለዚህ ነው፡፡
ለዚህም ነው ቀዳዳ እየፈለጉ በህዝቡ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዲጠፋ የተጀመሩት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲስተጓጎሉ ለማድረግ ሲራወጡ የሚታዩት፡፡ እንደማይሆንላቸው ያውቃሉ፡፡ መፍጨርጨራቸው ተፈጥሯዊ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡
ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና እድገት ወሣኝ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከውኃ፣ ከንፋስና ከእንፋሎት በመጠቀም አቅም የማሳደግና የማጎልበቱን ሥራ አገራችን በሰፊው ተያይዛዋለች፡፡ በቅርቡ የተመረቀው ጊቤ ሦስት ወደፊትም ሥራው ተገባዶ የሚመረቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቅርቡም የሚጀመሩት አዳዲስ ግድብ ግንባታዎች ከንፋስና ከእንፋሎት ኃይል የማመንጨቱ ሥራ ፈርጀ ብዙ ጥቅም ያለው ከመሆኑም በላይ የአገሪቱን አቅም አስተማማኝና የጎለበተ ያደርገዋል፡፡
በቅርቡ በተደጋጋሚ የውጭ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የአፍሪካ ፓወር ሀውስ የኃይል ማመንጫ ዋነኛዋ ቤት ትሆናለች ማለት ነው፡፡ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለውኃ እና ለመንገድ ግንባታዎች በቢሊዮኖች ዶላር እየወጣ ሥራው ለሊትና ቀን በመቀላጠፍ ላይ ይገኛል፡፡
በአገራችን ባላሰለሰ ሁኔታ የቴሌኮም መሠረተ ልማት፣ የስኳር፣ የማዳበሪያ፣ የሲሚንቶና ሌሎችም ከባድ ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሥራ ከፍጻሜ ለማድረስ በትጋት ሥራቸው ቀጥሏል፡፡ ሲጠናቀቁም ወደ ምርት ተግባራቸው ይገባሉ፡፡ 
ለመላው የአገራችን ህዝብ የስኳር ፍጆታውን መሸፈን የሚችሉ ግዙፍ ፋብሪካዎችን በመገንባት ወደ ሥራ መግባት አምራችና ውጤታማ ማድረግ መቻል ራሱን የቻለ ብሄራዊ   ስኬት ነው፡፡ በተመዘገቡ ተጨባጭ አገራዊ የሥራ ውጤቶች በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ሥራቸው መዳረሻቸው ኢትዮጵያን አድርገው መምረጥ ከጀመሩ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዛሬም ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር ነች፡፡
የተጀመረውና ውጤት እያስመዘገበ በመትመም ላይ ያለው አገራዊ የልማትና የእድገት ጉዞ የዛሬው ትውልድ ታላቅ አሻራ ሲሆን ለመጪው ትውልድ ደግሞ የክብሩና የአገራዊ ኩራቱ መለያ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ይህን ዘመን በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ብሎ መጥራት ይቻላል፡፡ ግዙፍ ከባድ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በብዛት እየተገነቡ ወደማምረት ሥራ እየገቡ ያሉበት የተለየ ዘመን ነው፡፡
ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድሎች የሚፈጥሩ፣ ሥራ አጥነትን የሚቀንሱ፣ የዘመኑን የቴክኖሎጂ እውቀት ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ እውቀትና ልምድ የሚያስጨብጡ በመሆናቸውም አገራዊ እድገቱን የላቀ ያደርጉታል፡፡
ከተጀመሩት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተጠናቀቁት ወደ ሥራ ሲገቡ ሥራቸው ያላለቀው ደግሞ በመንግሥትና ህዝብ ርብርብ ተገባደው ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናሉ፡፡ ሊገታቸውም  ሆነ ሊያሰናክላቸውም የሚችል ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት  ነውና፡፡