ሰፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች!!  

   
                                                     
መንግሥት አገራችንን  በተደጋጋሚ ሲያጠቃት ከኖረው ድርቅና ረሀብ ለማውጣት ድህነት ግንባር ቀደም ጠላታችን መሆኑን በመግለጽ ታግሎ ለማሸነፍ የሚቻልበትን መንገድና ዘዴ ሁሉ በመተለምና በመጠቀም ሰፊ ትግሎችን አድርጓል፡፡ በማድረግም ላይ ይገኛል፡፡  እጅግ ብዙ ቢቀረንም የተሳኩ የላቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ድርቅና ረሀብ የአገራችን መለያና መታወቂያ እስኪመስሉ ድረስ ከስማችን ተለይተው አይጠሩም ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ስም በጠንካራ ሥራና ውጤት ተለውጧል፡፡
አገሪቷ የነበራትን ከድርቅና ከረሀብ ጋር የተያያዘ ስም ከመሠረቱ የለወጠ ከዓለም መዝገብም እንዲሰረዝ ያስቻለ ሥር ነቀልና ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በማስመዝገብ በግብርናውም በኩል ጥንት ከነበረው ባህላዊ አስተራረስ ወጣ በማለት  የመስኖ ልማትንና ዘመናዊ ግብርናን ለአርሶ አደሩ በማስተማር ትርጉም ያለው ለውጥ በመላው አገሪቱ በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ 
በዓመት የሚመጣውን ዝናብ ብቻ ጠብቆ ከሚታረሰውና ከሚዘራው ሰብል ጎን ለጎን ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን፣ የመስኖ ልማትን፣ የአፈር የውኃ ጥበቃና እንክብካቤን ለአርሶ አደሩ በማስተማር የተጨበጠ ለውጥ ለማየት ተችሏል፡፡ አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነትና ጥገኛነት እንዲወጣ የመስኖ ልማት በመጠቀም ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ሰብሎችን፣ የጓሮ አትክልቶችን እየዘራና እየተጠቀመ የራሱንና የቤተሰቡን ህይወት እንዲለውጥ ማድረግ ተችሏል፡፡
ቀድሞ በነበረው ታሪካችን በየቦታው ወንዞች ያለ ጥቅምና ሥራ እየፈሰሱ ሐይቆች፣ ጅረቶች፣ ባህሮችና ምንጮችም እያሉ እነዚህን ተጠቅሞ ወደ ትልቅ አቅምነት በመለወጥ ድርቅና ረሀብን ለመቋቋም ሳንችል ቀርተን በአደጋው ክፉኛ የተጠቃንበት ከባድ አገራዊ ዋጋም ለመክፈል የተገደድንበትን የትናንት ታሪካችንን በሀዘን እናስታውሰዋለን፡፡ የተፈጥሮ የአየር ንብረታችን ቆላ፣ ደጋና ወይና ደጋ በመሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገን እንጂ የሚጎዳን አልነበረም፡፡
የእውቀትና የባለሙያ አለመኖርና ማነስ ለዚህም ትኩረት ሰጥተው ለችግሩ የሚመጥን መፍትሄ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው አደጋው ከፍቶ የኖረው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የግብርና ባለሙያዎቻችን ስለመስኖ ውኃ ጥቅምና ውጤታማነት ደጋግመው በማስተማር ማሳወቅ ትኩረት ሊሰጡት ቢችሉ ኖሮ ከውኃ እጥረትና ከድርቅ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ብዙዎቹ ችግሮቻችን መፍትሄ ሊያገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ባይበዛም የተሞከሩባቸው አካባቢዎች ሊኖሩም ይችላሉ፡፡
ከፍተኛ በረሀ በሆነ የአየር ንብረት ውስጥ በሚገኙ አገራት የሚኖሩ ህዝቦች በረሀው የሚያስከትለውን የውኃ እጥረት መክተውና ተቋቁመው ባለቻቸው ውኃ (ኩሬም ይሁን ወይም ዝናብ በዘነበበት ወቅት ጉድጓድ ቆፍረው ያጠራቀሙት ውኃ) ይህንኑ በቁጠባ በመጠቀም በውኃ ጠብታ አታክልት አልምተው ወይንም መስኖ ተጠቅመው በማምረት የራሳቸውንና የከብቶቻቸውን ህይወት ጠብቀው ያኖራሉ፡፡ የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ የዳሉል የሲናይ የእኛም የአፋር በረሀዎች ነዋሪዎች ለተባለው ህይወት ምስክሮች ናቸው፡፡
ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች አስቀድመው በተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ ውኃው ሳይባክን እንዲገባ ማድረግ የዝናብ ውኃውን ማከማቸት በቀጣይ ለብዙ ሥራዎች ይጠቅማል፡፡ ውኃውን በማከም ለመጠጥ ውኃ ከመጠቀም ውጪም ለመስኖ ሥራ ለከብቶች መጠጥም ይውላል፡፡ የዝናቡን ውኃ በተቆፈረ መሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲቀር ማድረግ ራሱን ችሎ የመሬት እርጥበት በመፍጠር የአካባቢውን የአየር ሚዛን መለወጥ የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የተለያዩ እጽዋትን በመትከል አካባቢውን አረንጓዴ ለማድረግም ይረዳል፡፡
ለአገራችን አርሶ አደርና አርብቶ አደር የመስኖ ልማትን የመሰለ አዋጪ ዘዴ የለም፡፡ አምና ድርቅ ተከስቶ በነበረባቸው አካባቢዎች ዝናብ ዘንቦ በነበረበት ወቅት በባለሙያ እገዛና ምክር በአግባቡ በመጠቀማቸው የድርቁን አጋጣሚ ዛሬ ላይ መስኖን በመጠቀም ወደ ልማት ለውጠውታል፡፡
ዘንድሮ ደግሞ ድርቁ ካለው ተለዋዋጭ ባህርይ የተነሳ ቀድሞ ባልተከሰተባቸው አንዳንድ የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የተከሰተ ቢሆንም ድርቅን ለመቋቋም ካለን ሰፊ ብሄራዊ ልምድና ተሞክሮ፣ ከገነባነው ጠንካራ ኢኮኖሚና የመከላከል አቅም ዘንድሮ በአጥጋቢ ሁኔታ ከተገኘው ምርትም ጋር አያይዘን ስንመለከተው ተጠቂ ለሆኑት አካባቢዎች ፈጥኖ የመድረስና ለአደጋው እንዳይጋለጡ የማድረግ አቅም አገራችን ገንብታለች፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በስፋት ተጠናክሮ የሚገፋበት ዋናው ሥራ በሁሉም አካባቢዎች የመስኖ ልማት እንዲለመድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጉ ነው፡፡
በሱማሌ ክልል ጎርፍና የወንዝ ውኃን በመገደብ ለመስኖ ልማት ለማዋል የሚያስችሉ ግዙፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን የክልሉ መንግሥት የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት በሰጠው ትኩረት ድርቅን ለመቋቋም የሚረዱ አራት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በካ፣ ጎመርሸኮሽ፣ ኡችዋቺና መራህቶ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡
የበካ ፕሮጀክት በወንዝና ዝናብ የሚፈጠረውን ጎርፍ ተከትሎ ስድስት ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት እንደሚረዳ የፕሮጀክቱ ዋና ኃላፊ ኢንጂነር እስማኤል አውአሕመድ  ጠቅሰዋል። ለፕሮጀክቱ ግንባታ 164 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንና ዋናው የመስኖ ቦይም 17 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም አስረድተዋል፡፡
አማካሪ መሀንዲሱ ኢንጂነር ገብረሚካኤል ከለለ በግድቡ የተሰባሰበውን ውኃ ለማጠራቀም የሚረዱ አምስት ትላልቅ ማጠራቀሚያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ግንባታው 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን ያላለቁት ሥራዎች በሁለት ወራት ይጠናቀቃሉ፡፡ የጎመርሸኮሽ ፕሮጄክት ግንባታ 96 በመቶ መድረሱን ሀላፊው ኢንጂነር ብርሃኑ ለገሰ ገልጸዋል፡፡ዋናው የመስኖ ቦይ 24 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። አምስት የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችም ተዘጋጅተዋል፡፡ 
በግድቡ የሚሰበሰበው ውኃ  6 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው መሆኑን  ኢንጂነሩ ጠቁመው ለግንባታው 100 ሚሊዬን ብር ወጪ ተደርጓል። ሥፍራው አለታማ ስለሆነ ድንጋዩን ለመቦርቦር በተሰሩ ሥራዎች ተጨማሪ 80 ሚሊዮን ብር በጀት ማስፈለጉን ገልፀዋል፡፡ የኡችዋቺ ግድብ ኃላፊ ኢንጂነር ካሊድ መሐመድ የግድቡ 19 ኪሎ ሜትር ዋና የመስኖ ቦይ መስመርና አምስት የውኃ ማጠራቀሚያ ማማ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ግድቡ ስድስት ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ለመረዳት ተችሏል። 
የመራህቶ ፕሮጀክት በ112 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ነው። ዘጠኝ ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል አቅም እንዳለው ኃላፊው ኢንጂነር መሐመድ አብደላ ገልፀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል።  የዋናው መስኖ ቦይ ርዝመት 13 ኪሎ ሜትር መሆኑንና አራት የውኃ ማጠራቀሚያዎችም እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ በየግድቦቹ የተዘጋጁት የውኃ ማጠራቀሚያዎች እያንዳንዳቸው 270 ሺህ ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ ለእያንዳንዱ አባወራም አንድ ሄክታር መሬት ሊያለሙ እንደሚችሉ ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
በክልሉ በዝናብ ወቅት በጎርፍ አለአግባብ የሚፈሰውን ውኃና በጋ ሲሆን የሚደርቀውን የወንዝ ውኃ ግድብ በመገንባት ውኃውን አሰባስቦ በማጠራቀም ለመስኖ ለማዋል የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ  ይገኛሉ፡፡ 
ከዚሁ ከመስኖ ሥራ ልማትና ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል 1 ነጥብ 97 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነውን  መሬት በመስኖ ለማልማት እየሰራ ነው። የኦሮሚያ የመስኖ ልማት ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን መሐዲ በተያዘው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 97 ሚሊዮን ሄክታር አዲስ መሬት በመስኖ በማልማት 2 ነጥብ 45  ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። 

አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው የመስኖ ውኃ አማራጮችን እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ በክልሉ አንድ የአርሶ አደር ቤተሰብ ቢያንስ የተቆፈሩ ጉድጓዶችንም ሆነ አነስተኛ የመስኖ ውኃን በመጠቀም በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርት እየተሰራ ነው። 

125 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች በ470 ሚሊዮን ብር ወጪ በመሰራት ላይ ይገኛል። የአገሪቱ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ለክልሉ የመስኖ ልማት ሥራ የሚውለውን ግማሽ በጀት ሸፍኗልል፡፡ በመገንባት ላይ ያሉት አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦች  የግንባታ አፈጻፀማቸው ከ50 በመቶ በላይ ደርሷል። አብዛኞቹ  ከየካቲት በኋላ ተጠናቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል። 
ባለሥልጣኑ በክልሉ የመስኖ ተጠቃሚዎች ማህበር እንዲቋቋም የሚያስችል አዋጅን በማጽደቅ ኅብረተሰሰቡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እንዲሁም በአግባቡ ተረክቦ ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ  በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
የኦሮሚያ የመስኖ ልማት ባለሥልጣን  ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ  ትላልቅ፣ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ  ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ  የክልሉን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።  
የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያ ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 116 አነስተኛ የመስኖ አውታሮች በመገንባት በዚህም 12 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቶ ከ64 ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ ለመሆን መብቃታቸውን  ገልጿል፡፡
በቅርቡም ቀጣዩ ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ወደ ሥራ የገባ ሲሆን 108 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። በመጪዎቹ ሰባት ዓመታት ሥራ ላይ የሚውለው የሁለተኛው ምዕራፍ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት 145 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል። በዚህ ምዕራፍ 150 የአነስተኛ መስኖ ልማት አውታሮችን ለመገንባት መታቀዱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ 
ሥራዎቹ የምድር ቁፋሮ በማካሄድ፣ አነስተኛ ግድቦችን በመገንባት፣ የውኃ ቅየሳ፣ ምንጭ በማጎልበት፣ የጎርፍ ውኃን በማጠራቀም የሚከናወኑ ይሆናሉ። ፕሮጀክቱ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 110 ወረዳዎች የሚካሄድ መሆኑን ከእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡