የሻዕቢያ “አዲሱ ገፅታ”—በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ጠጅ?!

                                                     
አንድ ዛሬም ድረስ በስፋት የሚነገርለት አባባል አለ—“ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም” የሚል። አባባሉ የነብርን ዥንጉርጉርነት እንዲሁ በለሆሳሱ ለመግለፅ ሲባል በእማሬያዊ (ግልፅ) ንግግር የተባለ አይመስለኝም። ይልቁንም ውስጣዊ ባህሪን ወይም ማንነትን ለማመላከት ሲባል በፍካሬያዊ (ድብቅ) ትርጉም የተነገረ ይመስለኛል። ይኸውም ‘ሰውን ጨምሮ ነብርም ይሁን ሌላ እንስሳ እሱነቱን ወይም ድብቅ ማንነቱን ሊተው አይችልም’ የሚል አንድምታ ያለው ይመስለኛል።
ይህን የነብርን መዥጎርጎር ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም— ከሰሞኑ ፈገግ የሚያሰኝ አንድ ሻዕቢያዊ “አክሮባት” ትውስ ብሎኝ እንጂ። ከመሰንበቻው ኤርትራን የሚመራው የአቶ ኢሳያስ መንግስት አዲሱን የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጅ እየጠና መሆኑ እየተነገረ ነው። ይህ የአቶ ኢሳያስ “አዲስ ገፅታ” ምክንያት አልቦ አይመስለኝም፤ ሻዕቢያ ‘ቀጣናውን የማተራመስ አመሌን በጉያዬ ውስጥ ከትቻለሁ’ ብሎም አይደለም— በሌለ ማንነቱና ውሳጣዊ ባህሪው ሰላማዊ መስሎ በመቅረብ ትናንት ሲያልም የነበረውን ‘የምስራቅ አፍሪካ አውራ’ የመሆን የቀን ቅዠቱን በጭላጭልም ቢሆን አጮልቆ ለማየት እየሞከረ እንጂ።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ግን የኤርትራ መንግስት የአተራማሽነት ባህሪውን ሊተው አይችልም—ልክ እንደ ነብር ዥንጉርጉርነት። ለዚህ የሻዕቢያ የማይቀየር ማንነት ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ አብነቶችን ማንሳት ቢቻልም፤ በዚህ ፅሑፌ ላይ ከአል ሸባብ ጋር የነበረውን ግንኙነት ማንሳት በቂ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው አል ሸባብ በምስራቅ አፍሪካ የአሸባሪው አል ቃዒዳ ወኪል ነው። በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤትም በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን ነው። የሽብር ቡድኑ በተለያዩ የቀጣናው ሀገራት ላይ፣ በተለይም በዑጋንዳና በኬንያ ላይ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ሲያደርስ የነበረና የበርካታ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ መሆኑን ዓለም ጠንቅቆ ያውቀዋል። 
በዚህም ሳቢያ የኤርትራ መንግስት ለአል ሸባብ የሚያደርገውን ድጋፍ ዓለም አቀፉ ማህረሰብ በማውገዝ ማዕቀብ ጥሎበታል። ካንዴም ሁለቴ። ሻዕቢያ ከአስመራ አንስቶ እስከ ሶማሊያ ድረስ የሽብር መረብ ዘርግቶ እንደነበር ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ይህ  የትርምስ መረብ በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንና በሀገራችን ህዝቦች ንቁ ተጋድሎና ተሳትፎ ሲበጣጠስበት፣ ፊቱን ወደ ሶማሊያ ግንባር በማዞር በዓለም መንግሥታት ዕውቅና የተሰጠውን የሀገሪቱን ፌዴራላዊ የሽግግር መንግስት ለመጣል በይፋ አውጆ መንቀሳቀሱ የትናንት ትውስታችነ ነው። 
ሰላማዊ ኑሮና የልማት እንቅስቃሴ ምንጊዜም የሚያስደነግጠው የኤርትራ መንግስት መንግሥት፤ “ጭር ሲል አልወድም” የሚለው ፖሊሲውን ገቢራዊ ለማድረግ ከፅንፈኛው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትና አል ሸባብ እያለ ራሱን በሚጠራው የአሸባሪዎች ስብስብ መጠለያ በመስጠትና በመደገፍ በሶማሊያ ልሳነ ምድር ያላስተኮሰው ጥይትና ሮኬት፣ ያላስወረወረው ቦምብና ያላስቀበረው የፈንጂ ዓይነት ያለ አይመስለኝም። 
የኤርትራ መንግስት ላለፉት 10 ዓመታት ያህል “የሶማሊያውያንን ችግር መፍታት ያለበት በሶማሊያውያን ነው፤ ሶማሊያ ውስጥ ያለው አሸባሪ ሳይሆን ነፃ አውጪ ኃይል ነው” እያለ የበግ ለምድ ለብሶ የሰላምን አስፈላጊነት እያስወራ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አል ሸባብን ለመሳሰሉ አሸባሪና ፅንፈኛ ቡድኖች የሎጀስቲክስና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠትና በማስታጠቅ በሀገሪቱ እየጐለበተ ያለውን አንፃራዊ የሰላም ጭላንጭል ለማዳፈን መሯሯጡ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቀት የተሰወረ አይደለም። 
ለዚህም በየጊዜው ሶማሊያ ውስጥ በተለያዩ የአውሮኘላን በረራዎችና በትላልቅ ጀልባዎች ለአሸባሪዎች በገፍ የሚያቀርባቸው የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች፣ ሮኬቶች፣ ፈንጂዎችና ቦምቦች የመንግስቱን ፀረ ጐረቤት ሀገር ራዕይና ፀረ ህዝብ አመለካከት ቁልጭ አድርገው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳይቷል፡፡ 
በያኔዋ ሶማሊያ ውስጥ የሽብር መረቡን በመዘርጋት ራሱን የቀጣናው አድራጊ ፈጣሪ አድርጎ በመሾም ‘ዘራፍ እኔ የአሸባሪዎች አለቃ’ እያለ ራሱ በፈጠረው ግጥምና ዜማ ዳንኪራ ተውረግርጓል፡፡ ዜማዊ ዳንኪራው ግን ስልተ ምቱን የሳተ ስለነበር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓይን ሊያርፍበት ችሏል። 
እናም እነዚህን እኩይ የትርምስ ተግባሮቹን በራሱ የቅኝት መንገድ አጣሪ ቡድን መድቦ በጥብቅ ሲከታተለው የነበረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በፀጥታ ምክር ቤቱ አማካኝነት የሻዕቢያውያን አስተዳደር “ለአከባቢው ሰላምና መረጋጋት አደገኛ ነው” በማለት የመሳሪያና የባለስልጣናት ዝውውር ዕገዳን ያካተተ የመጀመሪያው ማዕቀብ እንደጣለበት ከአሜሪካም ይሁን ከሌሎች ሰላም ወዳድ ሀገራት የተሰወረ አይደለም፡፡ 
ይህ የመጀመሪያው ማዕቀብ አልበቃ ያለው ይመስል፤ ከሚያካሂደው የትርምስ ተግባር አልተቆጠበም። ሻዕቢያ ራሱን ከግብረ-ሽበራ ተግባር ቆጥቦና ከቀጣናው ሀገራት ጋር ተስማምቶ መኖር ሲገባው፤ እርሱ ግን ብሶበት ተገኝቷል። በወቅቱ የመንግስታቱ ድርጅት የመደበው አጣሪ ቡድን ከድርጅቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከባቢ ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ሲያጠና ቆይቶ ከ400 የሚልቅ ገፅ ሪፖርት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ 
ሪፖርቱ ከዚህ በፊት ለመንግስታቱ ድርጅት ከቀረቡት መረጃዎች ተመሳሳይነት ባለው መልኩ የአቶ ኢሳያስ መንግስት የፀጥታው ምክር ቤትን የመሳሪያ ዕገዳ ማዕቀብን በመጣስ የሽብር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድቶ ነበር፡፡ በገለልተኝነትና በጥንቃቄ የተጠናቀረው ይህ ሪፖርት፤ የአስመራው አስተዳደር እንደ ሃሺሽ በቦምብና በፈንጂ ጪስ “ሳይጀነጀን” የማያድርበት ቀን የሌለ መሆኑንም ማጋለጡ አይዘነጋም፡፡ 
በሶማሊያ የተለያዩ ቦታዎች ውስጥ በአል ሸባብ አማካኝነት የተፈፀመው የቦምብ ጥቃት፣ በአዲስ አበባው የአፍሪካ ህብረት 16ኛው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ሊቃጣ የነበረው የፈንጂ ናዳ እንዲሁም በተለያዩ የመዲናችን ከባቢዎች ሊከናወኑ የነበሩ የቦምብ ፍንዳታዎች ተቀናብረው የነበሩት ጄኔራል ጠዓመ ጐይትኦም የተባሉ ግለሰብ በሚመሩት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቢሮ መሆኑንም የቡድኑ ሪፖርት ይፋ ማድረጉም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚዘነጋው ዕውነታ አይደለም፡፡ 
ሻዕቢያ ለሶማሊያው የሸብር ቡድን ወታደራዊ ስልጠና ኤርትራ ውስጥ ከመስጠትና መሳሪያ ከማስታጠቅ ባሻገር አንድ አስገራሚ ድርጊትም መፈፀሙ ተደርሶበታል፡፡ ይኸውም ለአል ሸባብን በየወሩ ሰማንያ ሺህ ዶላር ኬንያ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ሲሰጠው እንደነበር በሪፖርቱ ላይ ተጋልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጂቡቲን ድንበር ጥሶ በመግባት ወረራ መፈፀሙም ተመልክቷል። በተለይም አል ሸባብ ዑጋንዳ- ካምፓላ ውስጥ ከ76 በላይ ንፁሃን ዜጎችን የገደለበት ‘ሲ-4’ የተሰኘ ተቀጣጣይ ፈንጂ፤ አቶ ኢሳያስ በ16ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በአሸባሪው “ኦነግ” ሰዎች አማኝነት ለማፈንዳት ልከውት ከነበሩትና ከተያዙት ፈንጂዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑ በአጣሪ ቡድኑ መገለፁ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። 
እነዚህን የአጣሪ ቡድኑን ዕውነታዎች የተገነዘበው እንዲሁም ከኢጋድና ከአፍሪካ ህብረት ተጨማሪ መረጃ ያገኘው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በአስመራው መንግስት ላይ ቀደም ሲል ከተጣለበት ማዕቀብ በተጨማሪ የባለስልጣናትና የገንዘብ ዝውውር ዕገዳን ብሎም ሻዕቢያ ለመሳሪያ ግዥ የሚጠቀምበትንና ውጭ ካሉት ዜጎቹ የሚሰበስበውን የሁለት በመቶ ቀረጥ ሀገራት እንዲከለክሉ የሚያካትተውን ሁለተኛውን ማዕቀብ እንደጣለበት ይታወቃል። ይህን ዕውነታ አሜሪካም ይሁን የትኛውም የመንግስታቱ ድርጅት ሀገር ይገነዘባል።
ሻዕቢያ ግን ከሁለተኛው ማዕቀብ በኋላም ቢሆን ራሱን ሊያቅብ አልቻለም። ለዚህም የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ አጣሪ ቡድኑ አዲስ ሪፖርት ይዞ ብቅ ማለቱን አስታውሳለሁ። ሪፖርቱ ባለ 80 ገፅ ነው—ኤርትራን ብቻ የሚመለከት። የኤርትራው መንግስት በአስመራ ከሚንቀሳቀሰውና “ኤአርኤስ-አስመራ” በመባል ከሚታወቀው የሶማሊያ አክራሪ ቡድን መሪ ዘካርያ መሐመድ ሒጂ አብዲ ጋር በስውር ይሠራል ተብሎ የሚታመነው አብዲ ዋል በመባል የሚጠራው በሞቃዶሾ የሚኖር አክራሪ ግለሰብ ሙሉ ድጋፍ የሚያገኘው ከአቶ ኢሳያስ አስተዳደር እንደነበር ሪፖርቱ በወቅቱ አጋልጧል። 
ምን ይህ ብቻ! ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችም ከኤርትራ ድጋፍ እንደሚያገኙ እንዲሁ ተብራርቶ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል። በተለይም የአሸባሪው አል-ሸባብ የፖለቲካ ክንፍ አስተባባሪ ሼክ አህመድ ኑር የአስመራው መንግስት ዕርዳታ ተቀባይ እንደነበሩ በስፋት ተገልፀዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግለሰቡ በዋነኛነት በሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ከነበሩት መሐመድ ማንታይ ጋር ያደረጉት ድብቅ ምክክርና ውይይት በማስረጃነት በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡ ይህም ሻዕቢያ ሁሌም ከትርምስ ጋር የሚኖር የአሸባሪዎች አጋፋሪ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቅ ያደረገው ነው። 
እነዚህ ሁሉ ዕውነታዎች በአሜሪካ የፕሬዚዳንት ለውጥ ስለተደረገ ይሻራሉ ማለት የሚቻል አይመስለኝም። እናም የኤርትራ መንግስት “በአዲስ ገፅታ” ከአሜሪካ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጋር እያደረገ ነው የሚባለው ግንኙነት የትናንት ማንነቱን የሚሰርዝለት አይመስለኝም። የኤርትራ መንግስት ከሽብርተኞች ጋር ያለው የቁርኝት ቋጠሮ እንዲሁ በቀላሉ የሚፈታ አለመሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ ይገነዘባል። ለአሜሪካም አልሸባብ በአሸባሪነት የተመዘገበ ድርጅት ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አሜሪካ ከአሸባሪዎችም ይሁን ከእነርሱ አጋፋሪዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት የላትም።
ያም ሆኖ ምናልባት ሻዕቢያ እንዲህ ዓይነቱ “አዲስ ገፅታ” ያዋጣኛል ብሎ ካሰበ፤ ሃሳቡ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ጠጅ እንደ መገልበጥ የሚቆጠር መሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። የወይን ጠጂ መያዣ አቁማዳው እስካልተቀየረ ድረስ ወይኑን በመቀያየር ብቻ በመጠጡ ላይ የተለየ ባህሪያዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ሻዕቢያም ማንነቱን እስካልቀየረ ድረስ “በአዲስ ገፅታ” ለማምታታት የሚያደርገው ጥረትም የሚታወቅበትን ባህሪያዊ ማንነት ስለማይቀይረው ሊሰምርለት የሚችል አይመስለኝም።