ከግጭት ተጋላጭነት ወደ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት

                                                             
ይህን ፅሑፍ ለማሰናዳት ምክንያት የሆነኝ “አፍሪካ ቢዝነስ ኮሚዩኒቲ ዳት ኮም” “africabusinesscommunities.com” የተሰኘ ድረ ገፅ ሰሞኑን ያስነበበን ዘገባ ነው። ዘገባው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መዲና በሆነችው ጂግጂጋ የተገነባው ዘመናዊ ቄራ ወደ ተባበሩት ዐረብ ኢሚሬትስ የስጋ ውጤቶችን መላክ ስለመጀመሩ ያትታል። ይህ ሃተታም በውስጤ አንድ ስሜት ጫረ። ይኸውም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ትናንት ከሚታወቅበት የድርቅ ተጠቂነትና የግጭት አውድነት ተላቅቆ፣ ዛሬ ወደ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት መቀየሩ ነው። ይህ ዕውነታም ህዝብና መንግስት በአንድነት ተናብበው ከሰሩ የማይለወጥ ነገር አለመኖሩን በጥሩ ማሳያነት ሊቀርብ የሚችል ይመስለኛል።
እርግጥ የትናንቱ የትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሁኔታ የተለየ ነበር። ምንም እንኳን የክልሉ ህዝብ ለሰብዓዊና ዴሞክራሰያዊ መብቶች መከበር በተካሄደውና የደርግ አገዛዝን ለመገርሰስ በተካሄደው ትግል ከመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ትግሉን ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ 
ትግሉ በድል ከተቋጨ በኋላም ቢሆን በሀገራዊው ልማትና ሰላም ተጠቃሚነቱን ማጣጣም ቢጀምርም፤ እንዳሰበው ሊቀጥልና ሊዘልቅ ግን አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት ጉዳዮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ አንደኛው የክልሉ ሠላም መስፈንና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማየት የማይሹ የውጭና የውስጥ  ፀረ-ሠላም ኃይሎችና አሸባሪዎች የፈጠሩት እኩይ ሴራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ሲል በክልሉ በነበሩ አንዳንድ ጨለምተኛ አመራሮች ሳቢያ ሲደርስ የነበረው ፀረ- ዴሞክራሲያዊነትና የኪራይ ሰብሳቢነት ባህሪ ነው። 
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የጦር አበጋዞች የሁከትና የብጥብጥ ስፍራ ከነበረችው ሀገረ-ሶማሊያ ጋር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የሀገራችን ሰላምና ዕድገት የሚያንገበግባቸው የውጭ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚስማሩበት እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አል-ኢትሃድን የመሳሰሉ አክራሪዎችችና በኢፌዴሪ መንግስት በአሸባሪነት የተሰየሙትን እንደ ኦብነግና ኦነግ የመሳሰሉ አሸባሪዎችን በመቅጠር እኩይ ምግባራቸው ሲፈጽሙ መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ 
በክልሉ የተጀመረውን የሠላምና የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ ብሎም የክልሉ ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዳይሆን ያልቆፈሩት የጥፋት ጉድጓድ አልነበረም—ምንም እንኳን ይህ ቀቢፀ-ተስፋቸው በሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብና በፀጥታ ሃይሎች የጋራ ጥረት መክኖ ዛሬ ላይ ክልሉ በአስተማማኝ ሰላምና የልማት ጎዳና ላይ የሚገኝ ቢሆንም። 
ከዚህ ጎን ለጎንም የክልሉ ህዝብ በማንነቱ ኮርቶ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማጣጣም የመምረጥና የመመረጥ ህገ – መንግስታዊ መብቱ ተጠቅሞ ለስልጣን የሚያበቃቸው አመራሮች የመረጣቸውን ህዝብ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ጨለምተኛ አስተሳሰብ ይዘው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ሲመርጡ ተስተውለዋል—ህዝቡ የጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በማለት። 
በዚህም ህዝቡ ተማርሮ ወደ ሌላ ተግባር እንዲሰማራ አድርገዋል፡፡ በዚህም በክልሉ የተጀመረው የሰላምና የልማት ጉዞ እንዲደናቀፍ የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ታዲያ እነዚህን ተግዳሮች ብልሃት በተሞላበት በህዝቡ ቁርጠኛ ትግል ያለፈው ክልሉ፤ ዛሬ በተረጋጋ ሰላም ላይ በመሆኑ ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚያደርግ የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት ለመሆን በቅቷል። 
ነገሩ “ሾላ በድፍን” እንዲሉት ዓይነት እንዳይሆንብኝ ጥቂት አብነቶችን እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። ትናንት ከጅጅጋ—ጎዴ ለመድረስ በርካታ ቀናትን ይፈጅ የነበረው ጉዞ፤ በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ወደ አንድ ቀን ተቀይሯል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የጥይት ጩኸትን ሲያስተናግዱ የቆዩት የክልሉ ከተሞች የመሰረተ ልማት ግንባታ ድምፆችን ማጣጣም ችለዋል፡፡ 
ዜጎች እንደወጡ ይቀሩበት የነበረው የያኔው የሶማሌ ክልል፤ ዛሬ ላይ ነዋሪዎቹ ካሰቡት ውለው፣ ያሰቡትን ፈጽመውና አሳክተው በሰላም ቤታቸው የሚገቡበት አስተማማኝ ቦታ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ በመሆናቸውም በክልሉ እንደ ሰላሙ ሁሉ ልማቱም በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ 
ያኔ አንድም ባለሃብት ዝር የማይልበት ይህ ክልል፤ ዛሬ ላይ የበርካታ ኢንቨስተሮችን ቀልብ እየሳበ የትናንት አሻራውን እየቀየረ ነው፡፡ ሰሞነኛው የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ምርቱን ወደ ውጭ መላኩ የዚህ አባባሌ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው ብል ከእውነታው የራቅኩ አይመስለኝም። ይህ ደግሞ የክልሉ ህዝብ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት፣ በልማት ላይ የሚያደርገው ርብርብና የጠንካራ መንግስታዊ አመራር ውጤት መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለስራ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ተጉዣለሁ። ትናንትና ዛሬ። እናም የህዝቡን ስሜት በሚገባ አውቀዋለሁ። አዎ! የክልሉ ህዝብ ትናንትን በመጥፎ፣ ዛሬን በተስፋ የነገን ደግሞ ብሩህነት አውርቶ አይጠግብም፡፡ በእርግጥም የጥሩም ሆነ የመጥፎ ትዝታዎች በሰዎች ህሊና ውስጥ ተቀርጸው መቀመጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ ጉዳዩ የሚያስደስት ቢሆንም እንኳን ቁጭቱ ግን ቀላል አይሆንም፡፡ 
ከዓመታት በፊት እንደ እነ ቀብሪ ደሃር፣ ደገሃቡርና ጎዴ በመሳሰሉ ከተሞች አመሻሹ ሌላ ክስተት ይዞ የሚመጣ በመሆኑ በጊዜ ወደ ቤት መግባት የግድ ስለሚል የሁሉም ሰው የዕለት ተዕለት ተግባሩ ራሱን መጠበቅ ነበር፡፡ ምሽቱ የጭንቀት ድባብ የሚሰፍንበት መሆኑም እንዲሁ፡፡ ከመሸ ከቤት መውጣት የሚመክር አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ጨለማን ተገን በማድረግ የሚንቀሳቀሱት ፀረ-ሰላም ሃይሎች በመሳሪያ ተኩስ ህዝቡን የሚያሳድዱበት ጊዜ ነበር፡፡ 
ዛሬ በክልሉ ከተሞች የሙዚቃ እንጂ የተኩስ ድምጽን መስማት ፈጽሞ አይታሰብም፣ በጊዜ ወደ ቤት መግባትም እንዲሁ፡፡ ምሽቱ የደስታ ድባብን እንጂ የሞት ጥላ አያጠላበትም፡፡ የክልሉ ነዋሪዎች ወይኔ ከምኔው መሸ እንጂ፤ ‘ኤዲያ ደግሞ መሸ!’ የሚል ብስጭትና ጭንቀት አይሰማቸውም፡፡ ስለ ኑሯቸው መሻሻል እንጂ ስለሚገጥማቸው አደጋ አያስቡም፡፡ የትናንቱ ሰቆቃ በዛሬው አስተማማኝ ሰላም ተተክቷል፣ የነገን ብርሁነትንም ማመላከት ጀምሯል፡፡ በእኔ እምነት የሰላም ፍሬን ጣፍጭነት የክልሉ ህዝብ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለዛሬው ልማት መሰረት ሆኗል።
ክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጥሮ የአየር ለውጥ ምክንያት በድርቅ የሚጠቃ ቢሆንም፤ እየተካሄደ ባለው ልማት ወደ ረሃብነት ሊቀየር እንዳይችል አድርጎታል። ለዚህም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁሉ፤ ከድህነትና ከኃላቀርነት ለመላቀቅ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም፣ ለተጀመረው ልማት ቀጣይነትም ቁርጠኝነቱን በተግባር በማስመስከር ላይ ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ተሰማርተው ፀረ ሰላም ተግባራቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት ኃይሎች ምንም ትርጉም ወደ ሌለው ደረጃ በመድረሳቸው በሁሉን አቀፍ የልማት ጎዞ ላይ እየተረባረበ ነው፡፡ 
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ባከናወነው ቅንጅታዊ ስራ ለሰላምና ለልማት የሚሆን ጥርጊያ ጎዳና እንጂ፤ ለፀረ ሰላም ሃይሎች መደበቂያነትና ከለላነነት የሚሆን ነባራዊ ሁኔታ እንደሌለም በግልፅ እያስመሰከረ ነው፡፡ ይህ የህዝቡ ቁርጠኛ አቋምም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በፀረ ሰላምና በፀረ ልማት ተግባር ላይ ተሰማርተው የህዝቡን ኑሮ “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሸጋገር በከንቱ ምኞት ሲኳትኑ የነበሩ ሃይሎች እጃቸውን በመስጠት ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲገፉ ያደረገ መሆኑን ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ 
በተለይም ቀደም ሲል ራሳቸውን “የምዕራብ ጎዴ ነፃ አውጪ ግንባር” በማለት ሲጠሩ ለነበሩትና በተሳሳተ ጎዳና ሲጓዙ የነበሩ ኃይሎችን በክልሉ ውስጥ ሰርቶ መክበር እንደሚቻል፣ በጥረት ማደግ መቻልን እንዲያውቁና ከስህተታቸው እንዲማሩም ማድረጉን መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዩች በህገ-መንግስቱ መሰረት መፈታት የሚችሉ መሆናቸውን ማስተማሩንም እንዲሁ። 
ይህ የህዝቡ ቁርጠኛ አቋምም በተሳሳተ መንገድ ሲጓዙ የነበሩትን ሃይሎች ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰው በጎዴ አካባቢ በመስኖ እርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው የልማት ሃይል በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲለውጡ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች የሚያመርቱት የአትክልት ውጤት ከአካባቢው ህብረተሰብ ባሻገር፤ የክልሉ መዲና የሆነችው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪም ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በጥቅሉ በህዝብና በመንግስት ጥረት በሰፈነው ሰላም ክልሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነ መጥቷል።  
እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው የክልሉ ህዝብ ለሰላም ያለው ቀናዒነትና ከሰላም የሚገኘውን ውጤት በሚገባ ስለሚገነዘብ ይመስለኛል። ዛሬ የክልሉ ህዝብ ክልሉ ባለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ልክ ሰሞኑን ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ላይ እንደሚገኘው የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሁሉ፣ ሌሎች ባለሃብቶችም የክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት በመረዳት መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ ይገባል—በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አስተማማኝ ሰላም ተዘርግቷልና።