ሰሞኑን ኢህአዴግ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ተፊካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይትና ድርድር ማድረግ የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ ላይ ተወያይታል። እርግጥ ነው ኢህአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ድርድር ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በ2001 ዓ/ም ማገባደጃ ላይ በተለይ የምርጫ ስነምግባር ደንብ ለማዘጋጀት ሁሉንም በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋብዞ ወራት የፈጀ ድርድር ማደረጉ የታወሳል። በወቅቱ “ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአንድ ላይ ከኢህአዴግ ጋር መወያያት አልፈልግም፣ ለብቻ መወያያት አለብኝ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የሚገኘበት ስብሰባ ላይ አልሳተፍም” በሚል ውይይቱ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ረግጦ ከወጣው መድረክ ውጭ የተቀሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ማጽደቃቸው ይታወሳል።
የምርጫ ስነምግባር ደንቡ ላይ ኢህአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካሄዱት ውይይት ደንቡን ከማጽደቅ ያለፈም ፋይዳ ነበረው። በውይይትና በድርድሩ ላይ ተሳተፈው በስምምነት ደንቡን ያጸደቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ያለውን ፋይዳ ተረድተው በቀጣይነት በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሰይ ውይይቶችን ለማካሄድ የሚያስችል መዋቅር እንዲኖር ተስማምተው ይህ ደንቡ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል። ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ህግ እንዲሆን በተስማሙበት የምርጫ ስነምግባር ደንብ ላይ ያካተቱት የውይይትና የድርድር መዋቅር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ማቃቋም ነው።
የደንቡን መጽደቅ ተከትሎ ወራት በፈጀ ውይይት የምርጫ ስነምግባር ደንቡ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ የተስማሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በደንቡ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋቁመዋል። በተመሳሳይ በክልል ደረጃም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በደንቡ መሰረት በየክልላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋቁመዋል። በተለይ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰረቱት የጋራ ምክር ቤት ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል። የምርጫ ሰነምግባር ደንቡን ያጸደቁት ፓርቲዎች በዚህ ምክር ቤት አማካኝነት በተለያዩ ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲመከሩና ውሳኔ ሲያሳልፉ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ4ኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ ላይ ኢህአዴግ በተወዳደረባቸው አራት ክለሎች በ50 + 1 አብላጫ ድምጽ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን በተለይ በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ መቀመጫ በሰተቀር ሁሉንም ጠቅለሎ ማሸነፉን ተከትሎ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በመስቀል አደባባይ ኢህአዴግን ለመረጠው ህዝብ ባደረጉት ንግግር፣ “በምርጫው ተወዳድረው በአብላጫ ድመጽ የተሸነፉት ፓርቲዎች፣ አነሰም በዛ የሚወክሉት ህዝብ ሰላላ በሃገራዊ ጉዳይ ላይ አብረን እንሰራለን” በሚል ቃል የገቡትን ለማስፈጸም አገልግሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች ማንኛውንም ኢህአዴግን ጨምሮ በሌሎች ፓርቲዎች ምላሽ ሊሰጠበት ይገባል፣ ሊጣራ የገባል ብለው ያመኑበትን አጀንዳ ለዚህ ምክር ቤት አቅረበው ውይይት ያደርጋሉ፣ አጣሪ ከሚቴ አዋቅረው ችግሮችን መርምረው ለጋራ ምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባሉ፣ በምርመራው ሪፖርት መሰረት የእርምት እርምጃ የወስዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋሉ፣ ክትትል ያደርጋሉ። ለምሳሌ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት አባል ናቸው። የግድቡን የግንባታ ሂደት ይከታተላሉ። ባለፈው አመት በተከሰተው ድርቅ ከ10 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለአሰቸኳይ ግዜ የምግብ እርዳታ ጠባቂነት በተጋለጡ ወቅት የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ድርቁ ባጠቃቸው አካባቢዎች ያለውን የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ አሰጣጥ ቦታዎቹ ድረስ በመሄድ ተከታትለው በጋራና በየፓርቲያቸው መግለጫ ሰጥተዋል። በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት በወቀታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል።
የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ5ኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት የአመቱን የመንግስት ክንውኖች ያመላከተ ንግግር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአመለካከት ብዝሃነትን ማስተናገድ እንዲችል የምርጫ ሀጉን ማሻሸል እንደሚያስፈልግና ይህ አንደሚከናወን መግለጻቸው ይታወሳል። የዚህ የመንግስት ውሳኔ መነሻ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ የጋራ ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃየለማረያም ጋር ያደረገው ውይይት ነው። ምክር ቤቱ ከጠቅላይ ሚነስትሩ ጋር ተወያይቶ በነበረበት ወቅት ይህ ጉዳይ ተነስቶ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበረ ይታወሳል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግባበት ተነሰቶ የህግ ማእቀፍ እንዲበጅለት መንግስት አቋም የያዘበትን ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊነት አስመልክተው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ባደረጉት ንግግር የሚከተለውን ነበረ ያሉት፤
ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከማበልፀግ አኳያ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ በአገራችን የፍላጐት ብዙህነት እንዳለ ተገንዝቦ፣ እነዚህን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የምክር ቤቶቻችንን ተዋፅኦ የማጐልበት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት በድምሩ ለአስር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ በአገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል። በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል።
ሰሞኑን በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሊያካሂዱት የተስማሙበትና በቅድመ ሁኔታ ላይ መግባበት ላይ የደረሱበት ውይይት ከፖለቲካ ፓርቲዎቸ የጋራ ምክር ቤት የመነጨና በመንግስት ተቀባይነት አግኝቶ በፕሬዝዳንተ ሙላቱ ንግግር የተገለጸ የአመለካከት ብዝሃነትን ማስተናገድ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
ከላይ ያለው እውነታ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት፣ ድርድርና በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራት አዲስ እንዳልሆነ ያመለክታል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰሞኑን የውይይትና የድርድር ጥሪውን ባስተላለፉበት ወቅት፣ “ድርጅቱ እንደ ገዢ ፓርቲ በጋራ ከመስራት አኳያ የነበረበትን ውስጣዊ ክፍተት በመለየት በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ተዘጋጅቷል” ብለዋል። ቀደም ሲልም አብሮ ለመስራት ፍላጎቱ ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት መስርቶ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል። ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ማናቸውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። እንደ አቶ ሺፈራው ገለጻ፣ ኢህአዴግ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ውይይትና ድርድር ያደርጋል፤ በሚለያዩባቸው ጉዳዮች ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ክርክር ያካሂል። በዚህም “ፓርቲዎቹ ለሕዝቡ ‘አለን’ የሚሉትን ሀሳብ አቅርበው ህዝቡ አጀንዳቸውን በግልጽ እንዲያይና እንዲወስን የሚያስችለውን ግንዛቤ ይይዛል” ብለዋል። ኢህአዴግም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የድርድር ሥርዓቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የየራሳቸውን ሃሳብ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ኢህአዴግ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ኢህአዴግን ጨምሮ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥር 10፣ 2009 ዓ/ም በመንግስት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰብስበው ውይይት እና ድርድር ለመጀመር በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ መክረዋል።
የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት የህዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንደገለጹት፣ በዚህ ውይይት መጀመሪያ በሀገር ጉዳይ ላይ መወያየት፣ “መከራከርና መደራደር አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም? ኢህአዴግ በተነሳሽነት የጠራው ውይይት አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም?” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በአጠቃላይ የውይይትና ድርድር አስፈላጊነት ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመቀጠል በአራት ነጥቦች ላይ መነጋራቸውን ያመለከቱት አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ እነዚህም 1ኛ የስብሰባ ስነ ስርዓቱ ምን መሆን አለበት፣ 2ኛ የመድረክ መሪነት እንዴት መካሄድ አለበት፣ 3ኛ የፕሬስ መግለጫ አሰጣጥ እንዴት መከናወን ይገባዋል፣ 4ኛ የውይይት ታዛቢዎች ሁኔታን የሚመለከቱ መሆናቸውን አስታወቀዋል። በመጨረሻም እስከ ጥር 25 ባለው ጊዜ ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡና በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አቋም በሚያስቀጥሉበት ጉዳይ ዙሪያ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ ተደርሷል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡዋቸው ሃሳቦች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እንዲያስተባብረው መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
እንግዲህ ዋናው ድርድር ከዚህ በኋላ የሚካሄድ ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየት ያስፈለገው ባለፉ ሃያ አምስት አመታት በሃገሪቱ የሰፈነውን ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ማስፋትና ማጥለቅ ነው።