‹‹ናይል ውሃ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን የሚደግፍ ሥርዓት ነው››ዶ/ር ሞሐመድ ሞሄይድን

 

 

 

በአባይ ተፋሰስ አገራት መካከል ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ በመደረግ ላይም ናቸው። በቀደሙት ሥርዓታት በታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም በግብጽና አጋሮቿ በነበረው ጫናና በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ በነበሩ መንግሥታት ሕዝባዊነት መጓደል ምክንያት የላይኛው ተፋሰስ አገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘመናት አልፈዋል።

በርካታ ግብጻዊያን አባይ ከየት እንደመጣ መገንዘብ የጀመሩት ከኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አፍሪካን ሦሳይቲ በሚባል በሚታወቀው የግብጽ ተቋም ዳይሬክተር በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ግብፅን ለጎበኘው የአፍካ ጋዜጠኞች ቡድን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ዐረብ ነን ብሎ ያምን ነበር፤ 40 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አቋም አልነበረውም ብለዋል።  
 

“አባይ ሥሩ ኢትዮጵያ ፍሬው ግብጽ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ ግብጽ አጠቃላይ ህይወቷ የተመሠረተው አፍሪካ ላይ መሆኑን እስከ መርሳት ደርሳ ነበር። ግብጻዊያን የቻሉትን ያህል ፍሬ እየለቀሙ ሲመገቡና የተረፋቸውን እንዳሻቸው እያባክኑ ዘመናት ተለዋውጠዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የተፋሰስ አገራት ደግሞ መነሻ  ሆነው ያለምንም ተጠቃሚነት ዘልቀዋል። አስተሳሰቡም በአባይ ተፋሰስ አገራት ለዘመናት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ዘልቋል። በተለይም ለአባይ ውኃ የአንበሣውን ድርሻ የያዘችው ኢትዮጵያ በዚህ አባባልና ተግባር ለዘመናት ተጎጂ ሆና መኖሯ ይታወቃል። በየጊዜው በአገሪቱ የነበሩ መንግሥታትም ቢሆኑ የውስጥ መረጋጋት ስላልነበራቸውና የልማት የሁልጊዜ ስራቸው የውጭ ጠላት ማፈላለግ ስለነበር ግብጽ ውኃውን እንዳሻት ስትጠቀምበትና ሌሎች አገራት የብድርም ሆነ ሌላ ድጋፍ አግኝተው በአባይ ውኃ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ስታከላክል ኖራለች። ባለሙያዎቹ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂነቱን ለሚዲያው እየሰጡት መሆናቸው የዚህ ጽሁፍ አጀንዳ ነው።

በተፋሰሱ ሃገራት የሚገኙ ሚዲያዎችን ጨምሮ አለም አቀፍ የሆኑቱ የሚዲያ ተቋማት  ናይልን በተመለከተ የሚያደርጉት  የሐሳብ ልውውጥ በፖለቲካው መደብ ላይ ያተኮረ መሆኑ በትብብር ስለመልማት የመጀመሪያውን አሉታዊ ተጽእኖ ያሳረፈ ጉዳይ ነው። የምሥራቃዊ ናይል ቀጣና የቴክኒክ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ልማትና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዶ/ ውባለም ፈቃደ፣ ‹‹የእኛ ጥረት በናይል ላይ የሚደረገውን የሐሳብ ልውው በዋነኝነት ወይም በብቸኝነት የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ችግር አድርጎ ከማየት የተፈጥሮ ሀብት ማኔጅመንት ችግር አድርጎ ወደማየት ማሻገር ነው፡፡ ጉዳዩ ከመጠን በላይ የፖለቲካ ገጽታ ሲላበስ ትክክለኛ መረጃ መጣመሙ አይቀርም፡፡ የፖለቲከኞችን መረጃ መሞገት ሲሆን ማስተካከል የብልህ ጋዜጠኛ ግዴታ ነው፤›› ሲሉ መናገራቸውም ለዚሁና ፖለቲካን መሰረት ያደረገው የሚዲያ ጨዋታ አዋጭነት እንደሌለው በመገንዘብ ነው፡፡

የናይልን ጉዳይ የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ጉዳይ አድርጎ ማየት ለጉዳዩ ተገቢ የሆኑ አካላትን ከውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ያገላል፡፡ የናይልን ጉዳይ የተመለከተው እና ሌላኛው የሆነው የሚዲያ ችግር በተፋሰሱ ሃገራት መካከል በሚኖሩ ግጭቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መስራቱና በመስራት ላይ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ዓለም አቀፍ ሚዲያው የተለየ አጀንዳ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምናልባትም እንደ ክልላዊ አልያም ብሔራዊ ሚዲያ ኃላፊነት ላይሰማቸው ይችላል፡፡ አሳዛኙ ነገር ክልላዊና ብሔራዊ ሚዲያውም ግጭት ላይ ሲያተኩር መስተዋሉ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያው ተፅዕኖ ወደ በተፋሰስ ሃገራቱ ወደሚገኙ ሚዲያዎች መተላለፉ ነው፡፡ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ ሚዲያው የናይል ጉዳይን ስሜት ቀስቃሽ ጉዳይ አድርጎ የሚያቀርበው ሲሆን፣ ውስብስቡን የናይል ጉዳይ ከግጭትና ከቀውስ ጋር ብቻ አስተሳስሮ መሳሉን ተከትለን በዚያው መንገድ መፍሰሳችን የናይል ጉዳይ መቋጫ እንዳያገኝ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል።  

በሌላ በኩል የናይል ጉዳይን የሚሸፍኑ የሚዲያ ተቋማት በብሔራዊ ጥቅም ስም ገለልተኝነታቸውን እያጡ እንደሆነ የሚያስጠነቅቁም አሉ፡፡ በግብፅ ሚኑፊያ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሞሐመድ ሞሄይድን፣ ‹‹ሚዲያውን በንቃት ነው የምከታተለው፡፡ ከልምድ እንዳየነው የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚዲያ ተቋማት ለሕዝቡ የሚሰጡት መንግሥት ሕዝቡ እንዲያውቅ የሚፈልገውን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ዋና ዓላማቸውም ሕዝቡን ወደ አንድ የተወሰነ አቅጣጫ እንዲያስብ ማድረግ ነው፡፡ ተመራጩ መንገድ ግን የሚዲያ ሚና የመንግሥት ይፋዊ መረጃን እንዲሞግትና እንዲጠይቅ ይጠብቃል፤›› ማለታቸው ስለዚህ ነው ፡፡  

ብሔራዊና ክልላዊ ሚዲያ ሕዝቡን የማስተማር የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከናይል ዓውድ አንፃር ገንቢ ጋዜጠኝነት ማለት ጥያቄ የማይቀርብባቸውንና በሳይንስ የተረጋገጡ የናይል አደጋዎችን ለሕዝቡ ማስተማር ማለት ነው፡፡ የናይል ጉዳይን ከውኃ ጉዳይ ጋር ብቻ አቆራኝቶ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ናይል ውኃ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ሕይወት የሚደግፍ ሥርዓት ነው፡፡ ናይል ማለት ምግብ፣ ኢነርጂ፣ ኃይል፣ የውኃ ትራንስፖርት፣ ጂኦፖሊቲክስ፣ የዱር እንስሳት፣ ባህልና ሌላ ሌላም ነገር ማለት ነው፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎች ያልዳሰሷቸውና ያልደረሱባቸው በርካታ የናይል ጉዳዮች እንዳሉም ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ፣ ጂኦስትራቴጂካዊ፣ ከሕግ ጋር የተያያዙ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና መሰል የናይል ጉዳዮችን ሌሎች ወገኖችን ሳያስቀይም ሚዲያው ሊጽፍና ሊያስተምር ይገባል፡፡

የማንኛውም ሚዲያ ዋና ሥራ ትክክለኛ፣ እውነተኛና ተጨባጭ መረጃ መስጠት ነው፡፡ በናይል ጉዳይ ላይ የሚሠራ ሚዲያም ከዚህ አንፃር የተለየ ሚና አይኖረውም፡፡ በናይል ጉዳይ ተገቢ የሆነ ድርሻ ያላቸው አካላት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚዲያውን አገልግሎት አጥብቀው መሻታቸው አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ብሔራዊ ሚዲያው ስለናይል በቋሚነት ለሕዝቡ መረጃ የመስጠት፣ የማስተማር፣ የማነሳሳትና የማንቀሳቀስ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት አይገባም፡፡ 

ሚዲያው የሕዝብ ድጋፍን በማንቀሳቀስ፣ የሕዝቡን አመለካከትና አስተያየት በመቅረጽ አዋቂ፣ ብሩህና ደፋር መሪዎችን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ያም ሆኖ ግን ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተፋሰሱ አገሮች አንፃራዊ ተጠቃሚነትን በማጉላት ትብብር የመፍጠር ሚናውን ለጫወት አልቻለም፡፡ የተለያዩ የናይል ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ድልድይ ሆኖ የመስራት ሚናውንም አጥቷል።

ቁጥራቸው እያደገ ያለና አሳማኝ ማስረጃዎችን የያዙ በርካታ የጥናት ውጤቶች ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለመቀልበስ አስቸኳይ የተቀናጀ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ ይደመድማሉ፡፡ በዚህም ሚዲያ ተፋሰሱ በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊገጥም ስለሚችለው አደጋ ለሕዝቡ የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡ ሚዲያው በዚህ ኃላፊነት ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ፍላጎት ጭምር መቆም እንዳለበትም በጥናቶቹ ተመልክቷል፡፡ በርካታ ጥናቶች ናይልን እየገጠሙት ያሉት በርካታ ችግሮች እየተባባሱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡  

በናይል ጉዳይ ተቀዳሚው የሚዲያ ኃላፊነት የአገሮቹን የጋራ ተጠቃሚነት በማውጣት ትብብርን ማስፋፋት ነው። የናይል ውኃ ሁሉንም አባል አገሮች ተጠቃሚ በሚያደርግበት መንገድና አገሮቹ እርስ በርስ መተማመንና መግባባት እንዲኖራቸው ማድረግን ግቡ ያደረገ ዘገባና ትንታኔም ከሚዲያው ይጠበቃል። የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና አሠራሮችንም ፈትሾ መተንተን ያስፈልጋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሚዲያ ሚና ቁልፍ እንደሆነም መዘንጋት አይገባም፡፡ ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ትኩረት የሚደረግባቸው አካላትን ተደራሽ ለማድረግና የሕዝቡን አስተያየት ለመቅረጽ ከሚዲያ የተሻለ ሌላ አካል ለማግኘት ስለማይቻል፡፡

ያለሚዲያ እገዛ የናይል ትብብር ግቡን አይታም። ሚዲያው ትብብርን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት በራሱ ወይም ለሌሎች መድረክ የመፍጠር ሰፊ እድል አለው፡፡ ከዚህ ባሻገር ያለውና ጉዳያቸው ያልሆኑትን የውጭ ሚዲያዎች ተከትሎ መፍሰስ የተፋሰስ ሃገራቱን ዋጋ ያስከፍላል፤ በተለይም እኛን።

ይህ አደገኛና የሚያሳዝን የሚዲያዎቻችን አካሄድ፤ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ እንደእንቅፋት መታየት ያለበት ነው። ሚዲያዎቻችን ከስህተታቸው ተምረው የአቅጣጫ ለውጥ እንዲያደርጉና ብሄራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መደረግ አለበት። በጉባ በረሃ ከሚማስነው የልማት ሰራዊት እኩል መስዋእትነት የሚከፍል የሚዲያ የልማት ሰራዊት መፈጠር አለበት።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችን የማንቃትና የማስተባበር ስራ በመንግስት በኩል መሰራት አለበት። ሚዲያዎቻችን ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና የልማት አጋር አንዲሆኑ ተፅእኖ ማሳደር የሚችል ተቋምም መገንባት ይጠበቅብናል። በጥቅሉ ከፍተኛ የሚዲያ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋል።

ፕሮጀክቱን እንደ ፓለቲካዊ መሳሪያ ለሚመለከቱ የሀገር ውስጥና የውጪ ፅንፈኛ ሀይሎች የተደራጀ ቴክኒካዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንጂ አባይን ስለጎበኙ ባለስልጣናት ሰርክ የሚያወራልን ሚዲያ አያስፈልገንም። በሌሎች ታላላቅ ሀገራት የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን እና ልምዶችን በማጋራት የዕውቀት፣ የእሴትና የስነልቡና ሽግግር መፍጠር የሚያስችል ሚዲያ ነው አሁን የምንፈልገው። ለሀገር ውሰጥ ሙያተኞች ልፋትና ድካም ክብር የሚሰጡ የሚዲያ ተቋማትን እንሻለን። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በታላቅ ተጋድሎና ርብርብ እንዲጠናቀቅ ማገዝ ማለት ለነዙሁ ሙያተኞች ክብር መስጠት ስለሆነ።

ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ እና ስለሌሎች የሀገር ውስጥ የልማት ፕሮጀክቶች የተጠናና ሚዛናዊ መረጃ የሚሰጡ ሚዲያዎች ያሹናል – የአለማችንን ታላላቅ ግድቦች በጥልቀት የሚዳስሱ፤ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስላሉት ብቻ ሳይሆን በጅምር ላይ ስላሉትና ገና በእቅድ ደረጃ ስለሚገኙ ግድቦች በስፋት የሚያነሱ። የምህንድስና ጥበባቸውን፣ ሀገራዊ እሴትነታቸውን፣ ሲገነቡ የታየውን የመንግስታት ቁርጠኝነትና የህዝብ ተሳትፎ አብራርተው በመረጃ የሚያስታጥቁን፤ ስለጋራ ተጠቃሚነት፣ በሰላምና በፍትሀዊ መንገድ የተፈጥሮ ሀብቶችን ስለመጋራት የሚያስተምሩ የውሃ ሀይል ማመንጫ ግድቦችን ግለ—ታሪክ በጥልቀት የሚቃኙ ሚዲያዎች እንጂ የታላቁን ግድብ ልደት ብቻ ዘወትር የሚያቀነቅኑትን አንሻም ።

በጥቅሉ ስለ ታላቁ ግድባችን ቁመት፣ ርዝመት፣ ስፋት ወዘተ እያሉ በተለምዷዊ መግለጫዎች ጊዜ የሚያባክኑትን አሁን አንፈልግም። ማህበራዊ መስተጋብራቸውን፤ ፖለቲካዊ ትርጓሜያቸውን በጥልቀት የሚቃኙት ናቸው አሁን  ለኛ የሚያስፈልጉን ።