አንድ ሀገር የሚከተለው የፖለቲካል-ኢኮኖሚ መስመር ከራሱ ነባራዊ ዕውነታ ጋር የተቆራኘ መሆን ይኖርበታል። የሚከተለው መስመር ምንም ይሁን ምን፣ የሀገሩን ተጨባጭ ሁኔታዎች ያገናዘበና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር በአስተማማኝ ደረጃ መፍታት የሚችል መሆን ይኖርበታል። ያ ሳይሆን ቀርቶ ሌሎች የተከተሉትን ርዕዩተ ዓለም እንዳለ በመገልበጥ በሀገሩ ውስጥ ገቢራዊ እንዲሆን የሚደረግ ከሆነ ከህዝቡ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄድ ብሎም ሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ሊፈታ አይችልም። ይህ ሁኔታም ሁሉም ሀገሮች አንድ ዓይነት ርዕዩተ-ዓለማዊ መስመርን እንዳይከተሉ አርድጓቸዋል።
ይህን ዕውነታ በመመርኮዝም ሀገራችንን ላለፉት 25 ዓመታት በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለውን ርዕዩተ-ዓለማዊ መስመር ለይቷል—ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መሆኑን በማወጅ። ለመሆኑ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ሲባል ምን ማለት ነው?፣ ከሊበራሊዝምና እርሱን ተከትሎ ከመጣው አዲሱ ሊበራሊዝም (Neo-Liberalism) በምን ይለያል?…ከንባብ ካገኘሁት ጥቅል ዕውነታ በመነሳት በዚህ አጭር መጣጥፍ ላይ የበኩሌን ለማለት ብዕሬን አንስቻለሁ። በቅድሚያ ግን ብዙውን ጊዜ በንፅፅር ከሚቀርበው ሊበራሊዝም (ኒዮ ሊበራሊዝም) ምንነት ለመነሳት ወሰንኩ። መልካም ንባብ።
ሊበራሊዝም ወይም የኒዮ-ሊበራሊዝም ርዕዩተ ዓለም ዋነኛ መሰረት ‘ሁሉም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት መተው አለበት፤ መንግስት ህግና ሥርዓትን ከማስፈን ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚል አመለካከት ነው፡፡ ርዕዩቱ መንግስት ኃይል የሌለውና ቀጫጫ እንዲሆን ይሻል።
መንግስት ከልማታዊ ስራዎች ርቆ ጥቂት ባለሃብቶች በሀገር ምጣኔ ሃብት ላይ እንዳሻቸው እንዲያዙ፣ ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል የእነርሱ አዳማቂ እንዲሆን የሚሻ ርዕዩት ነው። ርዕዩቱ መንግስት በገዛ ሀገሩ ምጣኔ ሃብት ውስጥ የዘበኝነትና የተቆጣጣሪነት ተግባር ብቻ እንዲኖረው ይሻል። ይህን ዕውን እንዲሆንም ትላልቅ ሀገራዊ ተቋማት ለግል ባለሃብቶች እንዲሸጡ ያደርጋል።
ሊበራሊዝም በግል መብቶች ላይ እንጂ በጋራ መብቶች ላይ አያተኩርም ። እርሱን ተከትሎ የመጣው አዲሱ ኒዮ-ሊበራሊዝም (ኒዮ ሊበራሊዝም) የግል መብትን ትርክት ጫፍ ላይ አድርሶታል። ይህም ርዕዩቱና አራማጆቹ በየአደባባዮ የሚያንፀባረቁት ምልከታ የግል መብት ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዲሆን አድርጎታል። ይህን አባባሌን በማስረጃ ለማስደገፍም የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር በአንድ ወቅት “ህዝብ ብሎ ነገር የለም፣ ሁሉም ነገር በግለሰቦች ላይ የተመሰረተና የታጠረ ነው” በማለት የተናገሩትን መጥቀስ እችላለሁ። ይህም ዕውነታም ኒዮ-ሊበራሊዝም በግልና በቡድን መብቶች መካከል ያሉትንና የማይለያዮትን መስተጋብሮች እንደማይቀበል የሚያመላክት ይመስለኛል።
ኒዮ ሊበራሊዝም በጥቂቶች እጅ የሚገኝ የዳበረ ኢኮኖሚ ባለቤት ነው። የርዕዩቱ መሰረታውያን እነዚሁ ጥቂት ቱጃሮች በመሆናቸው በሀገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጉዳዩች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በእነርሱ የሚዘወር ነው። እነዚህ ሃይሎች እጃቸውም ረጅም ነው። ከሀገራቸው አልፈው በሌሎች ሀገራት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ፖለቲካል ኢኮኖሚያቸውን በኃይል ለመዘወር ይሞክራሉ። በተለይም አፍሪካውያንን ከአመለካከታቸው፣ ከባህላቸውና ከተፈጥሮአዊ ማንነታቸው ያፈነገጡ እሴቶችን ላያቸው ላይ በመጫን ሲያስገድዳቸው ይስተዋላል። በዚህም ድሃ ሀገራት ትላልቅ ተቋሞቻቸውን እንዲሸጡ በማድረግ ባለ ሃብቶቻቸውን ወደ ሀገራቱ በማሰማራት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይዋትታሉ።
ስለ ሊበራሊዝም (ኒዮ ሊበራሊዝም) ጥቅል ዕውነታ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትስ ከዚህ ርዕዩት በምን ይለያል? የሚለውን ሃቅ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲባል፤ ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሁለት ፈርጆችን ያቀፈ ነው—ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን አብሮ መሳ ለመሳ የሚያስኬድ። ሆኖም ልማቱም ይሁን ዴሞክራሲው አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚመረኮዝ መስመር ነው። በዚህም ጥቂቶችን ሳይሆን ብዙሃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት አቅጣጫን ይከተላል።
በሀገሩ ውስጥ የሚያከናውነውን ልማት ዕውን ለማድረግ፣የግሉ ባለሃብት ልማታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በተመረጡ የልማት አውታሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ልማቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ይጥራል። በዚህም በልማቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ትላልቅ የልማት አውታሮችን ያስተዳድራል። ታዲያ ይህን ጥቅል ዕውነታ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ልንመለከተው የምንችል ይመስለኛል።
እንደ እኛ ያለ በማደግ ላይ የሚገኝ ህዝብ በዋነኛነት ምጣኔ ሃብቱን አሳድጎ የነገ ሰውነቱን ዕውን ለማድረግ በዋነኛነት መጠቀም ያለበት የራሱን ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት መሆኑ አያጠያይቅም። ኢኮኖሚውም ሙሉ ለሙሉ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ጥገኛ መሆን የለበትም— ሀገር በቀል መሆን አለበት። ዕውነታውን የሀገራችን ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ሁኔታ አኳያ ስናየው ምጣኔ ሃብታችን ታዲጊና ለጋ ሆኖ እናገኘዋለን። ምንም እንኳን የግሉ ባለሃብት ለኢኮኖሚያችን ማደግ ተገቢውን ሚና እየተወጣ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ያለው አቅም ግን ይህን ያህል ዳብሯል ሊባል የሚችል አይመስለኝም።
የታዳጊ ሀገር ባለሃብት በመሆኑም አቅሙ ወደፊት እያደገና እየጎለበተ የሚሄድ ነው። እናም ይህ ባለሃብት በግሉ ዘርፍ ማከናወን ያልቻላቸውን ጉዳዮች የገበያ ክፍተት እንዳይፈጠር ልማታዊው መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ እንዲገባ ያደርገዋል። ይህም የገበያውን ጉድለት በመሙላት ረገድ እጅግ የላቀ ሚና ይጫወታል። እናም በልማት ሂደቱ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት በገበያ ጉድለቱ የተከሰቱ ክፍተቶችን በማስወገድ ልማትን ለማፋጠን እንዲቻል መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ባለንበት ሁኔታ አንድ የሀገራችን ባለሃብት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውና የኢኮኖሚያችን ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው አርሶ አደር በሚገኝበት ገጠር ወስጥ ገብቶ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን፣ መሰረተ-ልማቶችን…ወዘተ. ገንብቶ ለህዝቡ ሊሰጥ አይችልም—የተለያዩ ግላዊና ስነ-ልቦናዊ ምክንያቶች። እናም የእነዚህ ተግባራት አለመከወን ለመንግስት ከገበያ ጉድለት ባለፈ የህልውና ጉዳዮች ናቸው—ልማት የሀገራችን ህዝብና መንግስት የሞት ሽረት ጉዳይ ነውና።
ታዲያ እነዚህን ልማታዊ ተግባራት ለመከወን መንግሰት ገንዘብ ያስፈልገዋል። በመሆኑም የሀገሩን ታላላቅ ተቋማት በገንዘብ ምንጭነት መያዝ የግድ ይለዋል። እናም እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ ባንክ፣…ወዘተ. የመሳሰሉ ተቋማት በመንግስትና በህዝብ እጅ መኖር አለባቸው። ከእነርሱ የሚገኘው ገንዘብም አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ ወደ አዲስ የልማት ጎዳና እንዲያመራ የበኩሉን ድርሻ መጫወተ አይቀሬ ነው።
በመሆኑም ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስትም እንደ ኒዮ-ሊበራሎቹ የገበያ ክፍተቱን በሙሉ በግሉ ባለ ሃብት እንዲሸፈን ማድረግ አይችልም። ይልቁንም የሀገሪቱ ሃብት ይበልጥ እስኪጎለብት ድረስ ተቋማቱ የግድ በመንግስትና በህዝብ እጅ እንዲቆዩ ያደርጋል። ይህ አካሄድ ደግሞ ልማታዊውና ዴሚክራሲያዊው መንግሰት በነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትትራቴጂዎች እየተመራ ላለፉት 15 ዓመታት ህዝቡን በነቂስ በማሳተፍ ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ሊያረጋግጥ መቻሉን ልብ ይሏል።
ከዴሞክራሲ አኳያም ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት ከሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ይከተላል። እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ መንግስት በህገ መንግስታዊ ስርዓት የሚመራ መድብለ ፓርቲና የምርጫ ስርዓት ይኖሩታል። በዴሞክራሲው ረገድ ኒዮ-ሊበራል ስርዓት እንደሚከተለው የግል መብት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም—ለግልም ይሁን ለቡድን መብቶች ዕውቅና ይሰጣል።
አዎ! ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዮ ማህበራዊ ክፍሎች የቡድን መብቶቻቸው ካልተከበረ በግልም ነፃ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ ያምናል። ይህን አባባሌን ይበልጥ ለማስረዳት ያህል የሴቶችን የፆታ ነፃነትና እኩልነትን ትግል ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ሴቶች የግል መብቶቻቸው ተከብረውላቸው የሚደርስባቸው ፆታዊ አድልኦ በእኩልነት ካልተተካላቸው መቼም ቢሆን በግላቸው ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። እናም የፆታ እኩልነት መብቶቻቸውን ማስከበር የሚችሉት በግል ሳይሆን፣ በቡድን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
በተለይም ይህን ዕውነታ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ስንመለከተው፤ ከ75 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባሉበትና የዘመናት የመብት ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ የታገሉ ህዝቦች ባሉበት በእኛ ሀገር ውስጥ መብቶች በግልና በተናጠል ሊከበሩ አይችሉም—በጋራና በቡድን እንጂ። እርግጥ እዚህ ላይ ‘በልማታዊ መንግስት ውስጥ የግል መብት አይከበርም’ እያልኩ እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል። ምክንያቱም ለማለት የፈለግኩት የቡድንና የግል መብቶች የየራሳቸው ነፃ ህልውና ያላቸው እንዲሁም አንዱ ያለ ሌላው ሊፈፀም የማይችል መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታም ኒዮ ሊበራሊዝም ከሚከተለውና ሁሉንም ነገር ለገበያውና ለግሉ ባለሃብት ከሚተወው የገበያ አክራሪነት (market fundamentalism) አስተሳሰቡ በተደማሪነት የሚታይ ልዩነት ነው።
በጥቅሉ ልማታዊና ዴክራሲያዊ መንግስት ፈጣን ልማትን ያረጋገጠና ለወደፊቱም ይበልጥ ሊያረጋግጥ የሚችል የፖለቲካል ኢኮኖሞ ስርዓት ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና በቀጣይም በተጠናከረ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል አቅጣጫን ይከተላል። ይህ ዕውነታ ሀገራችንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ዕውን ሆኗል። ሌላውን ትተን በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት የምትመራውን ሀገራችንን ብንመለከት እንኳን፣ በዚህ መስመር በየዓመቱ በአማካይ የ11 በመቶ ዕድገት ባለቤት መሆን ችለናል።
በኒዮ ሊበራሊዝም ቀኖና የሚመሩት ትላልቅ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሳይቀሩ እንደመሰከሩት፤ ልማታዊው መንግስት በቀየሰው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማህበራዊ ዘርፎች መስክ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል። ለዚህም ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገቡት ሁሉን አቀፍ ዕድገቶች ዋቢ ናቸው። ምንም እንኳን በልማታዊ መንግሰት አማካኝነት የሚካሄዱ ተግባራት ተግዳሮቶች ቢኖርባቸውም፣ ችግሮቹ በሂደት የሚፈቱ ናቸው።
ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩ ራሱን በራሱ የሚያርምበት አሰራር ያለው በመሆኑ ችግሮችን እንደ አመጣጣቸው የመፍታት አቅምና ችሎታ ያለው ነው። እናም መንግስት በቀጣይነትም ልማትንና ዴሞክራሲን እንደ ህልውናው በማየት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ከግሉ ባለ ሃብት በተነፃፃሪ ነፃ በመሆን እንዲሁም በሂደት የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነትን በመፍጠር ዕድገቱን እንደሚያፋጥን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል—እየተከተለ ያለው መስመር ከነባራዊ ሁኔታችን ጋር የሚጣጣምና ትክክለኛነቱን በተግባር ማረጋገጥ የቻለ ነውና።