በተጀመረው ሁል አቀፍ የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ መነሻ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ ናቸው፡፡ በያዝነው ሣምንት ከተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ ብዙ ይብቃል፡፡ የፖለቲካ አቋም ልዩነት፤ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መወያየትን እንደማይከለክል መማር የሚገባው የሐገራችን ዴሞክራሲ ከዚህ ውይይት አትራፊ ነው፡፡ የጥቅም ግጭቶችን እና የአቋም ልዩነቶችን በኃይል የማስተናገድ የቆየ ልምድ ያለው ህዝብ፤ ቀስ በቀስ ከኋላ ቀር ልማዶች የሚላቀቀው እንዲህ ያሉ ፈዋሽ እርምጃዎችን በመውሰድ ነው፡፡
የፖለቲካ አቋም ልዩነት ለግጭት መንስዔ ሊሆን አይገባም፡፡ ሆኖም የረጅም ዘመን ታሪካች ይህን ሐሳብ የሚደግፍ አብነት የለውም፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች በርዕዮተ ዓለም ጎራ ከወዲያ እና ከወዲህ ለመቆም እና ለመወጋገዝ ሲዳርገን አይተናል፡፡ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ደም ሲያፋስስ ተመልክተናል፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ የልዩነት ጎራ ፈጥሮ፤ የርዕዮተ ዓለም ባንዲራ አስይዞ፤ ይህ ‹‹ወገን›› – ያኛው ‹‹ጠላት›› ነው በሚል አስፈርጆ፤ በባላንጣነት ሲያሰላልፈን ቆይቷል፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች ለግጭት ምክንያት ሲሆኑ አይተናል፡፡ ይሁንና የሐሳብ ልዩነት፤ የግድ – ሁልጊዜ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ በአንድ መድረክ ተቀምጦ ከመወያየት አያግድም፡፡ ሰዎች የተለየ ሐሳብን ይጠሉ ይሆናል እንጂ ሐሳቦች ሰዎችን አይጠሉም፡፡ ሐሳቦች ሐሳብን አይጠሉም፡፡ እንዲያውም ሐሳቦች ጥራት እና ብቃት የሚያገኙት፤ የህግ እና የቋሚ እውነት ማዕረግ የሚቀዳጁት በተቃራኒ ድጋፍ ሐሳብ ነው፡፡ የሐሳብ ከተማ ውይይት ነው፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በዚህ ረገድ ብዙ መሻሻሎችን ያሳየን ቢሆንም፤ የሚገባውን ያህል ግን አልተጓዝንም፡፡ የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴው በዚህ ረገድ ያለብንን ችግር ለመፍታት እንዲያግዝ ተደርጎ መመራቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ታዲያ ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ወገን የበኩሉን ድርሻ መጫወት ይኖርበታል፡፡ ከተለመደው የነገር አያያዝ ወጣ ብሎ ነገሮች መመልከት እና ጀማሪ ዲሞክራሲያችን የተደላደለ መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ውይይቱ እንደተለመደው ‹‹ነጥብ በማስቆጠር›› መንፈስ መቃኘት አይኖርበትም፡፡ ይልቅስ የነጻ መንፈስ ልዕልና የሚታይበት እና ከድሁር መንፈስ የሚያላቅቅ ውይይት መሆን ይኖርበታል፡፡ ችግርን በመፍታት ፍላጎት የሚመሩ የተጻራሪ ሐሳቦች ጉባዔ መሆን አለበት፡፡ ከልዩነቶታችን እሣት ሳይሆን ሳይሆን ለሐገር እና ለህዝብ የሚበጅ እውነት እንዲፈልቅ ማድግ ይኖብናል፡፡
ሁልጊዜም፤ ውይይት እንደ ጽጌረዳ አበባ ነው፡፡ የጽጌረዳ አበባ፤ እሾህ እና በቀለም የተዋቡ ቅጠሎች አሉት፡፡ አበባው ጽጌረዳ ከሆነ፤ እሾህ ብቻ ሳይሆን ውብ ቀለም ያላቸው ቅጠሎች ይኖሩታል፡፡ ውብ ቅጠሎች ወይም እሾህ ብቻ የምናይ ከሆነ፤ የምናየው ጽጌረዳ አበባ አይደለም፡፡ በውይይቱ እሾህን ብቻ ሳይሆን ውብ ቅጠሎችን ለማየት መሞከር ይኖርብናል፡፡
ተወያዮቹ እሾሁን የሚያነሱት፤ የተቀናቃኛቸውን ስሜት ለመጉዳት ሊሆን አይገባም፡፡ አበባውን ሲጠቅሱም ለመሸንገል መሆን የለበትም፡፡ እሾሁ በመጎዳዳት ስሌት ሳይሆን በመተራረም ስሌት መነሳት ይኖርበታል፡፡ ባለ ቀለሙ ውብ ቅጠልም በአድርባይነት ወይም በግብዝነት መንፈስ መያዝ የለበትም፡፡ አስቀያሚ እውነቶችን በውብ ቅጠሎች ጉዝጓዝ ለመሸፈን ሙከራ የሚደረግበት መድረክም መሆን አይገባውም፡፡
የተናጋሪ ሰው መልዕክት፤ በሚናገረው ነገር ብቻ አይወሰንም፡፡ መልዕክት በአነጋገር ዘይቤም ይወሰናል፡፡ ተወያዮቹ ከሚናገሩት ነገር እኩል፤ ለአነጋገራቸው (ለአቀራረባቸው) ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም በየራሳቸው የአመለካከት፣ የትንታኔ ወይም የእይታ ዛቢያ እየተሸከረከሩ፤ ዓላማቸው በአንድ የሐሳብ ፀሐይ ዙሪያ እንዲዞር ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ በራሳቸው የሐሳብ ዛቢያ እየተሸከረከሩ፤ ዑደታቸው ሐገራችን የገጠማትን ችግር በመፍታት ዓላማ ዙሪያ የሚመላለስ ሊሆን ይገባል፡፡ በአንድ ጸሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ የተለያዩ (ተቃራኒ) ሐሳቦችም በመልክ ቢለያዩም በዜማ አንድ ይሆናሉ፡፡
ተወያዮቹ የሚናገሩትን ነገር በደንብ የሚያውቁ እና የሚያውቁትን ነገርም በደንብ መናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ የተረዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ንግግራቸው ለመወቃቀስ እና ለመጎዳዳት ሳይሆን፤ ዓይን ለዓይን ለመተያየት መሆን ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ያለ የውይይት መንፈስ ካለ፤ ውይይታቸው ፍሬአማ ይሆናል፡፡ ተወያዮቹ ራሳቸውን ማየት ያለባቸው፤ የሐገርን ችግር ለመፍታት በመተጋገዝ የሚሰሩ እና በአንድነት መንፈስ ጥረት የሚያደርጉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች እንጂ ለመሸናነፍ የሚጫወቱ ተቀናቃኞች አድርገው አይደለም፡፡
በገዢው ፓርቲ ራሱን በደንብ አይቶ ወደ መድረኩ እንደመጣ፤ አነሱም ራሳቸውን በደንብ ፈትሸው ወደ መድረኩ መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ራሱን መርምሮ ነቅሶ ያወጣቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሰራ፤ እነሱም ችግሮቻቸውን አንጥረው አውጥተው ከችግራቸው ለመላቀቅ የሚሰሩ ከሆነ ውይይቱ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በዚህ መንፈስ ለውይይት የታደሙ ቡድኖች ችግሮቻቸው ሲጠቀሱ ቁጣ አይፈጠርባቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ የውይይቱ ድባብ አይደፈርስም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የአንድ ቡድን ተጫዋጮች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ልዩነት ቢኖር በችግሮች አፈታት እንጂ በችግሮች ላይ አይሆንም፡፡ ይህም ሁኔታ ለውይይቱ ልዩ ጥንካሬ ይሰጠዋል፡፡ ሐገር እና ህዝብን ተጠቃሚያደርጋል፡፡
በርግጥ፤ ሐገሪቱ ለገጠማት ችግር የመፍትሔ ሐሳብ ሆነው በሚቀርቡ ጉዳዮች ወይም በችግሮቹ ምንጮች ዙሪያ ልዩነት ይኖራል፡፡ መፍትሔ ተደርገው በሚቀርቡ ነገሮችም ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ ያለ ልዩነት፤ ከውይይቱ ሊገኝ በታሰበው፤ ወይም ሐገር እና ህዝብን ተጠቃሚ በማድረግ ፍላጎት በተቀረጸው ግብ ላይ ልዩነት ከሌለ መፍትሔ ከሌለ፤ ልዩነቱን በአንድ የሚያስር ነገር እናገኛለን፡፡ ይህም ለድርድ እና ሰጥቶ ለመቀበል መሰረት የሚሆን ልብ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡
ከተነሱት ችግሮች መገንዘብ እንደሚቻለው፤ ለችግሮቻችን የሚሆን መፍትሔ የሚገኘው ለዴሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ በትኩረት በመስራት ነው፡፡ ችግሮቻችን በተቋማት ጥንካሬ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ በሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ወዘተ ለተጠቀሱ ችግሮችን መፍትሔው፤ በትክክለኛ መርህ እና እውነተኛ እምነት የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን በመፍጠር ወይም በማጠናከር ነው፡፡
በዓለም ሐገራት መካከል በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና በሐብት ረገድ የሚታየው ልዩነት መነሻው፤ የህገ መንግስት አንቀጾች መለያየት፤ የቴክኖሎጂ፣ የካፒታል፣ የሰው ኃይል፣ የመሬት፣ የተፈጥሮ ሐብት ወይም የማዐድናት ወዘተ ልዩነት አይደለም፡፡ ሐገራት የኢኮኖሚ ልማት ሊቀዳጁ የሚችሉት ትክክለኛ የሆነ ወይም ዕድገት አሳላጭ (Pro-growth) ፖለቲካዊ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ዕድገት መለያየት ሊኖር ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ተቋማት የሚፈጠሩትም፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ (ተቋማት) ሲኖሩ ነው፡፡ በአጭሩ፤ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕ፣ የማህበራዊ ወዘተ ተቋማቱ ዕድግት አሳላጭ በሆነ መንገድ ሊፈጠሩ የሚችሉት፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡
ዕድገት አሳላጭ ፖለቲካዊ ተቋማት ሲፈጠሩ እና ሲጠናከሩ ሐገራት የዕድገት ጎዳናን ተከትለው ብድግ ይላሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ ተቋማት ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እያስተካከሉ እና እየቃኙ መጓዝ አቅቷቸው ሲቸከሉ ወይም አቅማቸው በተለያየ ምክንያት ሲዳከም ወይም ጨርሶ ሲወድቅ፤ ሐገራት የገነቡት ስርዓት ተርገድግዶ ይፈራርሳል፡፡ ሐገራቱም አይወድቁ አወዳደቅ ይወድቃሉ፡፡
ከዚህ ጋር አያይዤ ማንሳት የምፈልገው መንግስት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚለውን ችግር ነው፡፡ ይህም ችግር ጠንካራ ተቋማትን በመፍጠር ሊወገድ የሚችል ነው፡፡ በርግጥ፤ በማናቸውም ዘመን እና በየትኛውም ሐገር፤ የመንግስትን ስልጣን ለመቆጣጠር እና በራሳቸው ፍላጎት ልጓም የተለጎመ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ መኖራቸው አይቀርም፡፡ መንግስትን የጠባብ ቡድናዊ ወይም ግላዊ ፍላጎታቸው መሣሪያ ሊያደርጉት የሚፈልጉ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የእነሱን መሻት ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ቅይድ መንግስት እንዲኖር የሚጥሩ ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወዘተ ኃይል በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሰፊ ማህበራዊ ልማትን የሚያደናቅፍ ፍላጎት ይዘው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነሱ ፍላጎት ይሳካ እንጂ የሚሊዮኖችን ዕድል የሚያሰናክል ወይም ሐገርን የሚያፈርስ ነገር መያዛቸው ጨርሶ አያሳስባቸውም፡፡ ስለዚህ የፈለጉት እንዲፈጸምላቸው ከመጣጣር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሐገር የሚያጠፋ ተግባር ቢሆንም ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አያመነቱም፡፡ እናም እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡
ታዲያ እነዚህን የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣን ያላቸው ኃያል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አደብ እንዲገዙ ማድረግ የሚቻለው፤ እነሱን ፍላጎት ተረድቶ አንቅስቃሴአቸውን መቆጣጠር የሚችል ህይወት ያለው እና ብቁ እና ንቁ የዴሞክራሲ ስርዓት በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው አማራጭ ሁለት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንዳሻቸው የማድረግ ዕድል እንዳያገኙ በሩን ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት ወይም ሐገር ሲፈራርስ ቁጭ ብሎ መመልከት ብቻ ነው፡፡
ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት በመፍጠር እነዚህ ወገኖች ከሚጎትቱብን አደጋ መጠበቅ እንችላለን፡፡ ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት ሳይመሰረቱ ዕድገት ወይም ብልጽግና የሚታሰብ አይደለም፡፡ የዕድገት ምስጢር ነጻነት ነው፡፡ ያለ ነጻነት (በሁሉም ገጽታ) ዕድገት እና ልማት የህልም እንጀራ ነው፡፡
የዓለምን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪክ መፈተሽ ይቻላል፡፡ ሁልጊዜም ሐገራትን ሐብታም ወይም ድሃ የሚያደርጋቸው፤ የፖለቲካ መዋቅራቸው ልዩነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የዓለም ሐገራት ባለጸጋ ለመሆን የቻሉት፤ ሁሉን አካታች፣ ሳይዛነፍ የሚሰራ፣ የስልጣን ክፍፍልን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ተቋማትን መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት ለውጥ ሳንፈጥር፤ ጥሩ የኢኮኖሚ ሐሳቦችን መያዝ እና ምርጥ ፖሊሲዎችን መንደፍ ለውጥ አያመጣም፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማቱ ተደጋግፈው እና ተሳስረው ካልሰሩ ልማት አይገኝም፡፡ ስለሆነም፤ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ልማትን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር መትጋት ይኖርብናል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ለዚህ የሚያግዝ ውሳኔ እንጠብቃለን፡፡