የሰብል ዋጋ መውረድ አርሶ አደሩን እንዳይጎዳው!

 

የዛሬ ሃያ ዓመት በ1989 ዓ.ም ጥሩ የሰብል ምርት የተገኘበት ዘመን ነበር። የኢትዮጵያ ግብርና በለስ ቀንቶት ነበር። በድንገት የአርሶ አደሩን ምርታማነት በዚያ ደረጃ እንዲያድግና የሰብል ምርት እንዲትረፈረፍ ያደረገውን ምክንያት አሁን በውል አላስታውሰውም። ብቻ ያኔ ከዚያ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እህል “አሸዋ” ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። ልብ በሉ ሁሉም የኢትዮጵያ አርሶ አደር በጎተራው በቂ ምርት ነበረው እያልኩ አይደለም። በተለያየ ምክንያት ከምርት ውጭ የሆኑ፤ ምናልባትም ዳተኛ አርሶ አደሮች እንዲሁም በአገሪቱ ደረቃማ አካባቢ የሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮች እህል አለሞላቸውም ነበር። ያም ሆነ ይህ፤ በ1989 ዓ.ም ሰብል በገፍ ነበር የተመረተው።

ይሁን እንጂ፤ የሰብሉ መትረፍረፍ አርሶ አደሩን አልጠቀመውም። እንዳይጠቀም ያደረገው ደግሞ የሰብል ምርት ዋጋ ከሚጠበቀው በታች በማሽቆልቆሉ ነበር። አርሶ አደሩ የሰበሰበውን ምርት ሸጦ ገና እየተለማመደው ለነበረው የተሻለ የምርት ግብአት (ማዳበሪያና ምርጥ ዘር) ያወጣውን ወጪ መሸፈን፤ የማዳበሪያ ብድሩን መክፈል አልቻለም። በወቅቱ በቆሎ አምራች በሆኑ ራቅ ያሉ የአገሪቱ አካባቢዎች የአንድ ኩንታል በቆሎ ዋጋ ወደ 5 ብር ወርዶ እንደነበር ይታወሳል። አንድ ኩንታል ስንዴና ገብስ ወደ 50 እና 60 ብር ወርዶ ነበር። አጃ፣ ስንዴና ገብስ በገፍ በሚመረትበት ባሌ ዞን የእነዚህ ምርቶች ዋጋ እስከ 40 ብር ድረስ ወርዶ እንደነበረ አስታውሳለሁ።

በአንዳንድ አካባቢዎች እህሉን ገበያ አውጥቶ ከመሸጥ፣ ለከብት መኖነት ተጠቅሞ የደለበውን ከብት ገበያ ማውጣት የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ የሆነበት ሁኔታ ነበር። እስካሁንም ያልተፈታልኝ ጉዳይ ግን፤ በወቅቱ ከዱቄት ፋብሪካዎች የሚወጣው ለከብቶች መኖ የሚሆነው የፉሩሽካ ተረፈ ምርት ከእህል ዋጋ እጅግ ጋር የተቀራረበ ዋጋ የነበረው መሆኑ ነው። ባሌ ሮቤ የነበሩ ሰዎች ይህን ያስታውሳሉ።

በዚህ ሁኔታ አርሶ አደሩ ትርፉ ልፋቱ ብቻ ሆኖ ነበር። የእህል ዋጋ መውደቅ ከዚህም ያለፈ መዘዝ ነበረው። አርሶ አደሩ በቀጣይ ዓመት ምርታማነቱን የማሳደግ ተነሳሽነት አጥቷል። ተነሳሽነቱ ቢኖረውም በቀደመው ዓመት ስለከሰረ የካፒታል አቅም አልነበረውም። መበደርም ፈራ። የእህል ዋጋ ወርዶ ባለእዳ ሆኖ የመጠየቅ ስጋት ከፊቱ እየተደቀነ፤

በዚያ ዓመት የነበረው የእህል ዋጋ ማሽቆልቆል አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጎድቶ ነበር። ከአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው የግብርና ውጤት የሆነው የሰብል ምርት ዋጋ ማሽቆልቆል፣ በአርሶ አደሩ ላይ ያስከተለው ኪሳራ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ መቀዛቀዝ አስከትሎ ነበር።

የዚህ ጽሁፍ ትኩረት በ1989 ዓ.ም አጋጥሞ የነበረው የሰብል ምርት ዋጋ መውረድና አስከትሎት የነበረውን ውጤት ማስታወስ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፤ ዘንድሮ በአገሪቱ ከታየው ከእስካሁኑ ሁሉ የላቀ የሰብል ምርት መገኘት ሳቢያ፤ በተለይ በአርሶ አደሩ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግርና መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮችን ማመላከት ነው።

በዘንድሮ መኸር 320 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ነው የሚመረተው። ይህ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ12 በመቶ እድገት አሳይቷል። አሁን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቦ ገብቷል። አርሶ አደሩ ምርቱን ገበያ ማውጣት የጀመረበት ሁኔታም አለ። ታዲያ ሰሞኑን እንደምንሰማው የሰብል ምርት ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻጻር እስከ 25 በመቶ የወረደበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ፤- ባለፈው ዓመት 1 ሺህ ብር ያወጣ የነበረው አንድ ኩንታል ስንዴ እስከ 6 መቶ ብር የወረደበት ሁኔታ አለ።

ይህ አርሶ አደሩን ስጋት ላይ ጥሎታል። አርሶ አደሩ አሁን ያለው የሰብል ምርት የመሸጫ ዋጋ ምርታማነቱን ለመጨመር ለተሻሻሉ የምርት ግብአቶች (ማዳበሪያና ምርጥ ዘር) ያዋለውን ወጪ፣ በአንዳንደ ቦታዎች ደግሞ በኮምባይነር አሳጭዶ ለመውቃት እና ለሌሎችም ከማምርት ጋር ለተያያዙ ስራዎች ያወጣውን ወጪ በወጉ አይሸፍንለትም። በዚህም አርሶ አደሩ ኪሳራ ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት ገብቶታል። ይህ ሁኔታ በአርሶ አደሩ ቀጣይ የማምረት አቅምም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። የሰብል ምርት ዋጋ ማሽቆልቆል በግብርናው ዘርፍ የተገኘውን መልካም ስኬት መድገም የማይቻልበትን ሁኔታ ሊያስከትልም ይችላል። ይህ የሰብል ምርት ዋጋ መውረድ አርሶ አደሩን ጎድቶ በተለይ በቂ ካፒታል ያላቸውና ምርቱን ገዝተው ከገበያ ዝውውር ውጭ አድርገው አከማችተው ጥሩ ዋጋ ያለበትን ቀን ቆጥረው ምርቱን ለሚያወጡ ነጋዴዎች ሲሳይ እንዳይሆን ጥንቃቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

በእርግጥ፤ የአሁን ሁኔታዎች 1989 ዓ.ም ላይ ከነበረው ይለያሉ። በቅድሚያ ባለፉት አስር ዓመታት በተመዘገበው የግብርና ምርት እድገት የአርሶ አደሩ ገቢ በማደጉ በርካታ አርሶ አደሮች ለእለት ኑሮ የሚሆን ጥሪት ቋጥረዋል። በዚህ ምክንያት ምርት እንደሰበሰቡ ወዲያውኑ ምርታቸውን በገፍ ለገበያ እንዲያወጡ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ የለም። ይህ ግን የሁሉንም አርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ አይወክልም። አሁንም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ላይ የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች አሉ። በመሆኑም የሰብል ምርት ዋጋ መውረድ ተጽእኖ መቋቋም የሚያስችል የመፍትሄ እርምጃ መወሰድ አለበት።

ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ የመስጠት አቅም ያላቸው በስትራቴጂክ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ አርሶ አደሩ ያቋቋማቸው የህብረት ስራ ዩኒየኖች ናቸው። እነዚህ ተቋማት የሰብል ምርት ገበያ ሲያዘቀዝቅ በተመጣጣኝ ዋጋ ከአርሶ አደሩ ገዝቶ በማከማቸት አርሶ አደሩን ከኪሳራ ጉዳት የመከላከል፣ ዋጋ ሲያሻቅብ ደግሞ ምርቱን ወደገበያ በማውጣት አቅርቦቱን በመጨመር ሸማቹን ከጉዳት የመከላከል ድርሻ አላቸው።

በተለይ በስትራቴጂክ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ የሚያከናውነው ግዢ የአገሪቱን የመጠባበቂያ የእህል ክምችት በማጠናከር በድርቅና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሊያጋጥም የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እጥረት፤ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መከላከል የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። በመሆኑም ትርፍ የሰብል ምርት ሲኖር በብዛት ግዢ ያከናውናል። ይህም በገበያ ውስጥ ያለውን ተጨማሪ አቅርቦት በመሰብሰብ ገበያውን ከማረጋጋትና አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ከመፍጠሩ በተጨማሪ የአገሪቱን የአደጋ ስጋት የመቋቋም አቅም ያጠናክራል።

በዚህ ረገድ መንግስት በስትራቴጂክ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ አማካኝነት በቀጣይ አራት ዓመታት የአገሪቱን የምግብ ክምችት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ለማድረስ እየሰራ ይገኛል። እስካሁን የአገሪቱ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ከ450 ሺህ ሜትሪክ ቶን አልፎ አያውቅም። የመጠባበቂያ የመግብ ክምችቱን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ አሁን በስራ ላይ ካሉ ሰባት የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ማከማቻ መጋዘኖች በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ስድስት የማከማቻ መጋዘኖች ይገነባሉ። ማከማቻ መጋዘኖቹ፣ ትርፍ አምራች በሆኑ ፍናተ ሰላም፣ ባሌ፣ ሆሳዕና፣ ምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች ይገኛሉ። ሁለቱ መጋዘኖች ደግሞ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑት በሶማሌ ቀብሪድሃርና በጉጂ ቦርና የሚገነቡ ናቸው። ይህም ሊከስት ለሚችል የድርቅ አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስችላል። የስትራቴጂክ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ እንዳስታወቀው  መጋዝኖችን ለመገንባት 40 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ይህ የመጠባበቂያ የእህል ምርት ግዢ፣ ትርፍ የሰብል ምርት ሲኖር ምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ የሚያስችል ስርአት ነው። ይህ ዘንደሮ በተገኘው ትርፍ የሰብል ምርት ሊያጋጥም የሚችለውን የዋጋ ማሽቆልቆል ተጽእኖ ለመቋቋም ተግባራዊ ይደረጋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ዘንድሮ በተገኘው ከፍተኛ ምርት ምክንያት የዋጋ መዋዠቅ እንዳይከሰትና አርሶ አደሩ ተጎጂ እንዳይሆን ለማድረግ መንግሥት ተመን በማውጣት የእህል ግዥ እየፈጸመ መሆኑን አስታውቀዋል። በአገሪቱ የግብርና ምርት በሚፈለገው መልኩ ዕድገት ማሳየቱን ከቀጠለ፣ ከውጭ አገራት የሚፈጸመው የስንዴ ግዥ እንደቋረጥ የማድረግ እርምጃም በመፍትሄነት መቀመጡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። የአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎት እንዳይጓድልና በቀጣይ ዓመት የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር ለማድረግ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አርሶ አደሮች አባል ሆነው ያቋቋሟቸው የህብረት ስራ ዩኒየኖች የአርሶ አደሩን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ ይገኛሉ። ከዚህ ባሻገር፤ ዩኒየኖቹ ከአርሶ አደሩ የገዙትን ምርት በተሻለ ዋጋ በሚሸጡበት ጊዜ አርሶ አደሩ ያጣውን ተጨማሪ ዋጋ በማካካሻነት የሚሰጡበት አሰራርም አላቸው። ይህ አርሶ አደሩ ገንዘብ ሲያስፈልገው ምርቱን ያለስጋት በወቅቱ ዋጋ ለዩኒየኖች ማቅረብ ያስችለዋል።

በአጠቃላይ በዘንደሮው መኸር ከፍተኛ ምርት በመመረቱ በቀጣይ በበልግ ከሚመረተውና ከመስኖ ምርት ጋር ተዳምሮ በቀጣይ ሊኖር በሚችለው ትርፍ ምርት ሳቢያ የሰብል አቅርቦት ጨምሮ አርሶ አደሩን ሊጎዳ የሚችል የዋጋ ማሽቆልቆል እንዲፈጠር የሚያደርግ ሁኔታ አለ። ይሁን እንጂ፤ ከላይ የተጠቀሱት ዋጋን የሚያረጋጉ ስርአቶች በመዘርጋታቸው አርሶ አደሩን ከጉዳት መታደግ ይቻላል። እናም የተዘረጉት የዋጋ ማረጋጊያ ስርአቶች ግን በወቅቱ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ከተደረጉ፤ አርሶ አደሩ በሰብል ምርት ዋጋ ማሽቆልቆል የተነሳ ይጎዳል የሚለው ስጋት አይኖርም። አለበለዚያ አርሶ አደሩ ስጋት ላይ ነው።