በየክልሉ፣ በየከተማ አስተዳደሩ፤ በዞንና የወረዳ ደረጃ በተለያየ የሃላፊነት እርከን ላይ ሊመደቡ የተዘጋጁ እጩ ተሿሚዎች ህዝብ ፊት ቀርበው የህዝቡን ይሁንታ ሲያገኙ ብቻ ሹመታቸው እንዲጸና እየተደረገ ነው። ይህ በጥልቀት የመታደሱን እንቅስቃሴ ወደህዝቡ በማውረድ ውጤት እንዲያገኝ ማድረግ ስለሚችል መልካም ተግባር ነው። ይሁን እንጂ፤ በጎ የሆነውን ያህል ችግርም እንዳለው ነው የሚነገረው።
ለምሳሌ፤- ከአንድ ወር በፊት በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስልጤ ዞን፣ ለዞን የመመሪያ ሃላፊነት ከቀረቡ እጩዎች መካከል አንዱን ህዝቡ “ሙሰኛ ስለሆነ አንፈልገውም” ቢልም እጩውን ያቀረበው አካል፣ የህዝቡን አስተያያት ችላ ብሎ ራሱ ያቀረበውን እጩ ሹመቱ እንዲጸና ያደረገበትን ሁኔታ ታዝበናል። ይህ ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር ተዛምቶ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል። ህዝብ አልፈልገውም ያለውን በአውቅልሃለሁ ባይነት አልቀበል ማለት ተሿሚዎቹን ያቀረበው አካል ራሱ በጥልቀት የመታደስን ጉዳይ የግድ ያለውን ምክንያት ያልተገነዘበ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ሊሆን ይችል ይሆናል። እናም ጉዳዩ ሊጤን ይገባል።
በሌላ በኩል፤ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኢሉአባቦር ዞን የዞን የመመሪያ ሃላፊዎች እጩ ተሿሚዎች ህዝብ ፊት ቀርበው ነበር። እጩ ተሿሚዎቹ የቀረቡለት ህዝብ በተለይ የወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ እጩ ሆኖ የቀረበውን ግለሰብ፤ “ከዚህ ቀደም በሃላፊነት ቦታ ላይ ተቀመጦ ምንም አለሰራም፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት የሚታወቅ ነው፣ ስለዚህ አንፈልገውም” የሚል አሰተያየት ሰጥቶ የግለሰቡ ሹመት በይፋ ውድቅ ተደርጓል። ህዝቡ ከዚህም አልፎ “የሰውየውን ማንነት እያወቃችሁ እንዴት በእጩነት ታቀርባላችሁ?” እስከማለት ደርሷል። ይህ በየኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን የታየው ደግሞ የህዝብን የበላይነት ያከበረ በመሆኑ በበጎ ተሞክሮነት ሊጠቀስ የሚገባው ነው።
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግስት በጥልቀት መታደስ ያስፈለጋቸው በዋናነት በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎች በስልጣናቸው ህዝብን ከማገለገል ይልቅ፣ ስልጣናቸውን የግል መጠቀሚያ፣ የተሻለ ህይወት ማደላደያ በማድረጋቸው ነው። ይህንን ኢህአዴግም መንግስትም በይፋ የተናገሩት ነው። በጥልቀት የመታደሱ ዓላማ ችግር ያለባቸውን ሃላፊዎች አስወግዶ፣ ስልጣናቸውን ህዝብን ለማገልገል፣ ህዝቡ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለማድረግ ዓላማ ብቻ የሚጠቀሙ ሃላፊዎችን ለመመደብ ነው። በጥልቀት መታደሱን የግድ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማቃለል ይህ አማራጭ የሌለው ርምጃ ነው። ማን እንደሚበጅ ደግሞ ከህዝብ በላይ የሚያውቅ የለም። በመሆኑም፤ እጩዎችን ህዝብ ፊት አቅርቦ በማስገምገም፣ የህዝብን ይሁንታ ያገኙትን ብቻ የመመደቡ አካሄድ ተሃድሶውን ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል። ታዲያ እዚህ ላይ፤ ህዝብ በእጩዎች ላይ የሚያቀርበውን አስተያያት ማጣጣል አደጋ ያለው መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።
ይህ ዓይነቱ ህዝቡ አስተዳዳሪዎቹን እንዲተች የማድረግና ይሁንታ የሰጣቸው ብቻ ሃላፊነት እንዲረከቡ የማድረግ ተግባር በጥልቀት የመታደሱ ንቅናቄ ወደህዝብ መውረዱን ያመለክታል። ወደህዝቡ መውረዱ ደግሞ የተሃድሶውን ንቅናቄ እንደሚያሳካ አይጠረጠርም።
ከዚሀ በተጨማሪ፤ በየክልሉና በፌዴራል መንግስት ስር ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በጥልቅ የመታደስ ግምገማ በማካሄድ ላይ ናቸው። ተሃድሶው በየተቋሙ ከሰራተኞችና ከአጠቃላይ አሰራር ጋር በተገናኘ ያለውን፤ ሰራተኛውን ያማረረና ያሳዘነ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት ከማጋለጥ የሚጀምር ነው። ህዝብን ያማረረ የመልካም አስተዳደር ችግር በመንግስት ሰራተኛውና በተገልጋይ ህዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በአስተዳደሩና በሰራተኛው መካከልም መኖሩ ይታወቃል። በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ በደል ይፈጸማል። የመንግስት ንብረትና ገንዘብ ይመዘበራል። በመሆኑም፤ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ህዝብን ለማገልገል ከመነሳቱ በፊት በውስጡ ከመልካም አስተዳደርና ከኪራይ ሰብሳቢነት የጠራ ስርአት ሊኖረው ይገባል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለህዝብ አገልግሎት ሰጪ ናቸው። ህዝብን ያማረረና በተለይ ባለፈው ዓመት ህዝብ ተቆጥቶ በመንግስት ላይ ተቃውሞው እንዲያሰማ ያስገደደ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት የተፈጸመው ህዝብን ለማገልገል በተቋቋሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡት በሰራተኞቻቸው አማካኝነት በመሆኑ የመልካም አስተዳደር መጓደል የሚፈጸመው ከሃላፊዎችና ከሰራተኞች ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም፤ የመንግስት ሰራተኛው የሚያካሂደው ጥልቅ ተሀድሶ በቀጥታ ከህዝብ ጋር የሚገናኘው አካል ጋር እንደሚፈጸም መታደስ የሚታይ ነው።
የመንግስት ሰራተኛው በጥልቀት ወደተሀድሶ እንዲገባ መወሰኑን ተከትሎ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ፣ የመንግስት ሰራተኛው የሚጠበቀውን ያህል የህዝብ አገልጋይነትን መንፈስ ተላብሶ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን ጠቁሟል። ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት፣ የህዝብ አገልጋይነትን መንፈስ አለመላበስ፤ እንዲሁም ኃላፊነትን ለግል ጥቅም ማዋል በመንግሥት ሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውንም አመልክቷል።
ከዚህ በመነሳት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በአገሪቱ ብቁ እና ውጤታማ የመንግስት ሰራተኛ በመፍጠር የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሚረዳ የተሃድሶ ስልጠና መስጠት የሚያስችል ሁለት የስልጠና ሰነዶችን አዘጋጅቷል። የሰነዱ የመጀመሪያ ክፍል ባለፉት ሃያአምስት አመታት መንግስት በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት በተከተላቸው መስመሮች ባህሪያትና ተልዕኮዎች ላይ ግልፅነት የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው። የሰነዱ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የተመዘገቡትን ለውጦችና በመንግስት ሰራተኞች በኩል የሚታዩ ጉድለቶችን የሚመለከት ነው። የስልጠና ሰነዶቹ እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛና መስሪያ ቤቶች ራሳቸውን እንደሚለከቱ የሚያስችሉ ነጥቦችን የያዙ ናቸው። በእነዚህ ሰነዶች ላይ በመመስረት በየመስሪያ ቤቱ በመካሄድ ላይ ያለው የተሃድሶ ስልጠና በየተቋማቱ የሚታዩ ጉድለቶች በጥልቀት እንዲነሱ ማድረግ፣ እያንዳንዱ ሰራተኛም የራሱን ጉድለቶች እንዲያይ ማድረግ የሚያስችል እድል ፈጥሯል።
እንግዲህ፤ ህዝብን ያማረረ የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ያዛባ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት በአገሪቱ መኖሩን መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አምነው መቀበላቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ነው። ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁከት እንዲቀሰቀስ መነሻ የሆነውም ይሄው የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊትና አመለካከት ገዢ ሆኖ መውጣት እንደሆነ አምነዋል። ለሁከቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት ውጪያዊ ከማድረግ ይልቅ ወደውስጥ በመመልከት ተጠያቂው መንግስትና ገዢው ፓርቲ መሆናቸውም በይፋ ተገልጿል።
እንግዲህ፤ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በጥልቀት ወደመታደስ እንዲገቡ ያደረጋቸው መሰረታዊ ምክንያት ይህ ነው። በዚህ መሰረት፤ ተሃድሶው ከስድስት ወራት በፊት የጀመረው በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በአባል ድርጅቶቹ (ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን) ስራ አስፈጻሚና ምክር ቤት ደረጃ በመካሄድ ነበር። በመቀጠል ኢህአዴግ በሚያስተዳደራቸው ክልላዊ መንግስታት፤ ትግራይ፤ አማራ፤ ኦሮሚያና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ አመራር ደረጃ ተከናውኗል። በዚህም በሁሉም ክልሎች የካቢኔ አባላት ሹም ሽርና ሽግሽግ ተካሂዷል። የፌደራል መንግስት ካቢኔ ለውጥና ሽግሽግም ተደርጓል። ይህ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተካሄደ የተሃደሶ እርምጃ ነው። በጥልቀት የመታደሱን ንቅናቄ አገራዊ ለማድረግ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ወደሚያስተዳድሯቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ህዝቦችም ይዘልቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንዳነሳሁት፤ በጥልቀት የመታደሱ እንቅስቃሴ ከድርጅቱና ከከፍተኛ የመንግስት መዋቅር ወጥቶ ወደህዝቡ እየወረደ ነው። ተሃድሶው ወደ ህዝቡ የወረደው በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳድሮች የመንግስት መዋቅር ሃላፊዎች ሹመት ላይ ህዝብ እንዲሳተፍ በማድረግ፤ እንዲሁም ለህዝቡ ቀጥተኛ አገልግሎት የሚሰጠው የመንግስት ሰራተኛ በሚሰራበት ተቋምና በራሱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በተጨባጭ ተገንዝቦ ተቋሙን እንዲያቃና ራሱንም እንዲያርም ማድረግ የሚያስችሉ መድረኮች በማዘጋጀት ነው። የመንግስትና የገዢው ፓርቲ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ውጤታማ የሚሆነው ወደህዝብ ሲወርድና ህዝቡ በባለቤትነት ሲይዘው ብቻ በመሆኑ ርምጃው የሚደገፍ ነው። ይሁን እንጂ፤ ተሃድሶውን ወደህዝብ የማውረዱ ተግባር ለይስሙላ መሆን የለበትም። የብልጣብልጥ አድርባይ ካድሬዎችና የስልጣን ጥመኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን፤ አስመሳዩ ከእውነተኛው ተበጥሮ መለየት አለበት። ህዝብ የሚለውን ማዳመጥና ውሳኔውን መቀበልም የግድ ነው። በጥልቀት የመታደሱ ተግባር በህዝብ ባለቤትነት ስር የሚሆነውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው።