የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና በአገራችን የተጀመረውን የዴሞከራሲ ስርዓትን ለማጎልበት የሚያስችል ጥልቅ ተሃድሶ በየደረጃው ባሉት የተለያዩ አካላት በመካሄድ ላይ ነው። በአገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ ለውጥ ሁሉን አቀፍ ሁሉንም በየደረጃው ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ነው። ይህን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠልና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጎልበት እንዲቻል ሁሉም በየደረጃው ራሱን የሚያይበት መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው።
ኢህአዴግ እንደፓርቲ፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ፣ አባሎቹና ደጋፊዎቹ በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ከርመዋል። ባለፉት 15 ዓመታት ፓረቲው የተገበራቸው አሰራሮች፣ የተገኙ ውጤቶችና የገጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝርና በጥልቀት ታይተዋል። የአመራሮች ጥንካሬና ድክመት በስፋት ተነስተዋል። አሁን ላይ የመንግስት ሰራተኛውም የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት በማካሄድ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ ህብረተሰቡም የተሃድሶ መድረኮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ለአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚኖራቸው ሚና ጉልህ ነው።
በጥልቀት ለመታደስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን መካከል የመጀመርያው በአገሪቱ የተፈጠሩ አዳዲስ እውነታዎች መኖራቸውንና በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የወጣቶችን የልማት ተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጉዳዮችን በተፈለገው መጠን ያለማሳደግ አገራችንን ዋጋ አስከፍሏታል። በመሆኑን ወጣቱን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር መዘርጋት ግድ ሆኗል። ለዚህም የፌዴራል መንግስት ብቻ ሳይሆን የክልል ማንግስታትም ሁኔታውን ገምግመው ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር በመዘርጋት ላይ ይገኛሉ። በቂ ፋይናንስም መድበዋል።
አለማችን በፈጣን ለውጥ ውስጥ ናት። አገራችንም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ልትርቅ አትችልም። የህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፍላጎት እጅጉን አድጓል። የህዝብ በፍጥነት የመልማት ፍላጎት ማደግ መንግስት ከሚያቀርበው የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም። ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን ፊት ለፊት መታገል ጀምሯል። በመሆኑም ህብረተሰቡ የአለም ሁኔታን በሚያይበት መነጽር አገልግሎት ማግኘት ፈለገ። ይሁንና ይህን የሚመጥን አመራር በበቂ ሁኔታ እንደሌለ መገንዘብ ይቻላል።
ይህ የሚያመላክተው የህብረተሰቡ ፍላጎት እጅግ እየተለወጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ባለፈው ጊዜ በአገራችን የታየው ቀውስ በሌላ አንግል ለተመለከተው በአገራችን ጠያቂ ህብረተሰብ (Demanding Society) መፈጠሩን ያረጋግጣል። እንዲህ ያለ ጠያቂ ህብረተሰብ እንዲፈጠር ያደረገው የአገራችን ህዝቦች መብታቸውን እንዲጠይቁ ያደረገው ይህ ስርዓት ነው።
ሌላው ለጥልቅ ተሃድሶ አስፈላጊነት ምክንያት የሆነው ነገር ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን የሚፈታተን እየሆነ የመጣው የመንግሥት ሥልጣን የግል ጥቅም ማስከበሪያና የኑሮ መሠረት የማድረግ ዝንባሌ ነው፡፡ መንግሥት ራሱን ከኪራይ ሰብሳቢ ነፃ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የተፈለገውን ያህል ጠንካራ ያለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት በመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ባሉ ኃይሎች ሲተገበር ታይቷል። መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነባ በመጣው አገራዊ አቅም ሳቢያ መሠረተ ሰፊ የሆኑ ልማት በማከናወን ላይ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች በኮንትራት አስተዳደር፣ በግዥ፣ በግብር አሰባሰብና በመሬት ዕደላና አጠቃቀም ለከፋ ሙስና የሚጋለጥበት ሁኔታ እየሰፉ መጥተዋል። ይህ አጋጣሚ ለመንግሥታዊ ኃላፊነት መብቃት ከፍ ያለ ጥቅም ለማጋበስ እንደሚረዳ በመተማመን ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ሩጫ አባብሶታል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ያጋጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ አንድ በአንድ ሲመረመር፣ እንደገና በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴን የግድ የሚል ሁኔታ ተፈጥሯል። የመንግስት ስልጣን ለህዝብ ማገልገያ መሆኑን ዳግም ለማረጋገጥ ይህ ጥልቅ ተሃድሶ አስፈልጓል። ከዚህ በፊት ይባል እንደነበረው “የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ወደሚባልበት ደረጃ መመለስ ይኖርበታል።
ኢህአዴግ የህዝበችን ፍላጎት ለማሟላት ያስችላሉ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ በመተግበር ላይ ነው። በቅርቡ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች እንዳሳወቁት ዕውቅና ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመከራከርና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል። ቀደም ሲልም የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጎልበት በርካታ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መስርተው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ደግሞ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ካገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በአገር ጉዳይ ለመነጋገር የሚያስችል አካሄድን ኢህአዴግ ተከትሏል። ይህን አይነት አካሄድ መተግበር መጀመሩ ለአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊ ነው።
በሰላማዊ መንገድ የሚንሸራሸሩ የሃሳብ ልዩነቶች ለአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ጠቃሚ ናቸው። በቀጣይ መሆን ያለበት አካሄድ ፓርቲዎች በሚያቀራርቧቸው በጋራ መስራት ይችላሉ፣ በሚለያዩባቸው ጉዳዮች ደግሞ ሃሰብን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ መቻል አንዱ የዴሞክራሲ ባህል መጎልበት መገለጫ ጤናማ አካሄድ መሆኑን መቀበል ተገቢ ነው። የፓርቲዎች የንግግር ወይም የድርድር የመጨረሻ ግብ የሕዝብ ተጠቃሚነት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሁሉም የአገርና የህዝብ ጉዳይ ሊገደው ይገባል። የፓርቲዎችም ሆነ ሌላው አካላት የመነጋገሪያ አጀንዳ ሊያተኩር የሚገባው ሕዝብንና አገርን ያማከለ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። የሃሳብ ልዕልና ማስፈን የሚቻለው በግትርነት ሳይሆን በምክንያታዊነት መሆን መቻል አለበት። የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዋነኛ መገለጫ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መደራደር መቻል አለባቸው።
ልዩነቶችን እያጦዙ አላስፈላጊ ውዝግቦች ውስጥ ከመግባት ይልቅ በድርድር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ማግኘት እየተቻለ፣ ጭፍን ጥላቻ በመፍጠር ለክፉ መፈላለግ የአገራችን ፖለቲከኞች መውጣት ይኖርባቸዋል። ሕዝባችን ውስጥ ግን የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከት፣ ወዘተ. ልዩነቶች ቢኖሩም አንዱ ወገን የሌላውን አክብሮ በሰላም መኖሩና ከዚያም አልፎ ተርፎ የተዋለደው በአርቆ አሳቢነት ላይ የተመሠረተ የጋራ መግባባት መፍጠር በመቻሉ ነው፡፡ ይህ በቃላት ባይገለጽም የምርጥ ድርድር ማሳያ ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እባካችሁ ከህብረተሰቡ ተነማሩ። ህብረተሰባችን ውስጥ ያለው በርካታ ልዩነቶች ህብረተሰቡን ለመጥፎ ነገር አጋልጠውት አያውቁም።
የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ ወቅት ከይስሙላና ከታይታ አቀራረቦች በመታቀብ ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ በማትኮር የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ማጎልበት ይኖርባቸዋል። ሁሉም አካላት ለሕግ የበላይነት ተገዢ መሆን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተገዢ እንዲሆኑ መስራት ይኖርባቸዋል።
በአገራችን አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲፈጠር፣ ፍትሐዊ የሃብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር እንዲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሻለ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ መንግስት ብቻ ሳየሆን ሁሉም ፓርቲዎች የየድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ በእውነተኛ መንፈስ እንዲጎለብት ከተፈለገ፣ ገዢው ፓርቲ ግማሽ መንገድ ድረስ በመሄድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር ወይም መደራደርን እንደመረጠ ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለኢህአዴግ መስታወት ልትሆኑት ይገባል። የሚሰሩ እጆች ይቆሽሻሉ እንደሚባለው ድክመቶችን እየመረጡ ማጎኑ አስተማሪ አይሆንም።
እንደኔ እንደኔ ይህ ውይይት ከዚህ በፊት በምርጫ ወቅት እንደምናያቸው ክርክሮች አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ወይም እያንኳሰሰ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት እንዳይሆኑ እፈልጋለሁ፡፡ አገራችን በርካታ መልካም ጅምር ነገሮች ያሏት በመሆኑ የሚካሄዱት መድረኮች እነዚህ መልካም ጅምሮች የሚጎለብቱበት መሆን ይኖርበታል። ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ህልውና ሲባል በሠለጠነና በዘመናዊ አስተሳሰብ መደራደር ያለፈውን አስከፊ ምዕራፍ ለመዝጋት ይረዳል፡፡ የሁሉም ትኩረት መሆን ያለበት የተሻለች የነገዋ ኢትዮጵያ መሆን መቻል አለበት።